ፈር ቀዳጇ የአፋን ኦሮሞ የሕጻናት መጽሔት – ናኦታ

በርከት ያሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በዕለተ ቅዳሜ በአዳማ ኃይሌ ሪዞርት ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የመልካ አዳማ እና ሌተናል ኮሎኔል ደጀኔ ስሜ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ በሪዞርቱ የመገኘታቸው ምስጢር ደግሞ ናኦታ የተሰኘች የልጆች መጽሔት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የምረቃ መርሐ ግብርን ለመሳተፍ ምክንያት በማድረግ ነው፡፡

በመልካ አዳማ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ኩኩ ሰለሞን እና ማርታ ፈቃዱ እንደሚሉት፤ ናኦታ መጽሔት በአፋን ኦሮሞ ለንባብ መብቃቷ አስደስቷቸዋል፡፡ በሚማሩበት ትምህርት ቤት በቅርብ ርቀት ማግኘት እንደሚፈልጓትም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ሕጻናትን አስመልክቶ የተዘጋጀ መጽሔት አንብቤ አላውቅም የምትለው ተማሪ ኩኩ፣ የማውቀው ነገር ቢኖር የተረት መጽሐፍ ማንበቤ ነው ትላለች፡፡ ይህ የሕጻናት መጽሔት ግን በአሁኑ ጊዜ ለኅትመት በመብቃቱ ደስ ያለኝ ሲሆን፣ በትምህርት ቤታችንም ተገኝቶ የማንበብ ዕድሌ ቢሰፋ ዕድለኛ ነኝ ስትል ትገልጻለች፡፡

ተማሪ ማርታም፣ መጽሔቷ በታሪክም ሆነ በባህል በኩል ያለውን እውቀት የምታስጨበጥ እንደመሆኗ በማንበብ ግንዛቤ መጨበጥ እንችላለን ትላለች፡፡ ነገር ግን ይህን ዕድል ማግኘት የምንችለው በትምህርት ቤታችን ውስጥ ማግኘት ስንችል ነው ብላለች፡፡

ለናኦታ መጽሔት ምረቃ ከቤተሰቡ ጋር ከአዲስ አበባ አዳማ የተገኘው የሒልሳይድ ትምህርት ቤት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ቤካ አሳየ እንደሚናገረው፤ በመጽሔቷ መመረቅ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል። ይህቺን መጽሔት ደግሞ በትምህርት ቤቴ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ባገኛት በምፈልገው ሰዓት ማንበብ እችላለሁ ብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ከመማሪያ መጽሐፍት ውጭ የምናነበው የተረት መጽሐፎችን ነው ያለው ተማሪ ቤካ፣ አሁን ግን በየወሩ ታትማ የምትወጣዋን ናኦታን ለማንበብ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልኛል ሲል ተናግሯል፡፡

በአዳማ ከተማ የሌተናል ኮሎኔል ደጀኔ ስሜ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆኑት ተማሪ ፍራኦል ታደለ፣ ናኦል መኮንን እና ናኦል ፈይሳ በየበኩላቸው፤ የናኦታ መጽሔት መጀመር ከመማሪያ መጽሐፍት ጎን ለጎን ትልቅ አቅም የሚፈጥርልን ነው ብለዋል፡፡ ተማሪዎቹ ለልጆች ተብሎ የተዘጋጀ መጽሔት ከዚህ በፊት በትምህርት ቤታቸው እንዳላዩ ጠቅሰው፤ ናኦታ በትምህርት ቤታቸው ብትገኝ ብዙ የሚማሩባት መርጃ መጽሔት እንደምትሆን ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡

የዕለቱ እንግዳ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አዝመራ እንደሞ፣ ትናንት ሳናማርጥና ሳንመርጥ የዘራነው ዘር ዛሬ ላይ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል ብለዋል። ክፉውን የዘር ሰንኮፍ ለመንቀል ዛሬ ላይ ጥሩውን ዘር መዝራት የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መልካሙን ጎዳና ተያይዟል፡፡

ይህች በአፋን ኦሮሞ በየወሩ እየተዘጋጀች ለንባብ የምትበቃው የሕጻናት መጽሔት፣ ድርጅቱ ብዝኃነትን ያካተተ ሥራ መሥራቱን የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸው፤ ይህ ደግሞ የወል ትርክትን ለመገንባት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

የአዳማ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ በበኩላቸው፤ እውቀት ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ነው፤ አንጋፋው የኅትመት ሚዲያው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መረጃን ለሕዝብ በማድረስ በኩል ቀደምት ነው ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል በሪሳን ለኅትመት ያበቃው ይህ አንጋፋ የኅትመት ሚዲያ፣ ዛሬም በአፋን ኦሮሞ የሕጻናት መጽሔት በማዘጋጀቱ ሊመሰገን የሚገባው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው፣ እኛም በዚህች ናኦታ መጽሔት ልጆቻችን እንዲጠቀሙ እንሻለን ሲሉ ተናግረው፤ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትውልድ ታሪኩን፣ ባህሉንና የሀገር ፍቅርን እንዲያውቅ በማድረጉ በኩል የራሱን ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከድርጅቱ ጎን እንደሚቆሙም ቃል ገብተዋል፡፡

ሙሉ ለሙሉ ሕጻናት ላይ ትኩረቷን ያደረገችው “ናኦታ መጽሔት” በ40 ገጾች የተቀነበበች ናት፡፡ መጽሔቷ ርዕሰ አንቀጽን ጨምሮ 20 ዋና ዋና ርዕሶችን ይዛለች፡፡ ከይዘት አኳያ ስትመዘን በእውቀትም ሆነ በሥነ ምግባር ልጆችን የምታስተምር እና ደግሞም የምታዝናና መጽሔት ነች፡፡

ይህች በየወሩ በመታተም ለንባብ የምትበቃ መጽሔት ልጆችን የታሪክ እውቀት እንዲኖራቸው ከማድረግ በዘለለ የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና አዳዲስ ነገሮችን እንዲቀስሙ በማድረግ ረገድ ሚናዋ የጎላ ነው። መጽሔቷ ያካተተቻቸው ዓምዶች፤ አባ መላ፣ ኩንስ ቢየ ኮት፣ ዋልትነ፣ አፎለ፣ ካሜቱማ፣ ፋነ ጎቶታ በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

መጽሔቷ በአጠቃላይ ሕጻናት የሚማሩበት፣ ልምድ የሚቀስሙበትና ስለሀገራቸው የሚያውቁበት ዓምዶችን ያካተተች ነች፡፡

መጽሔቷ በትምህርት ቤቶች፣ በሕጻናት ማሳደጊዎች እና ሕጻናት ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች፣ ጨምሮ በድርጅቱ የመሸጫ ሱቆች ላይ ማዕከል ተደርጎ በመሰራጨት ላይ ትገኛለች፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You