
1822 ዓ.ም ላይ በጅማው ንጉሥ አባ ጅፋር እንደተቆረቆረች ይነገራል። ጣሊያኖች “ፒኮሎ ሮማ” ወይም ትንሿ ሮም ሲሉ በጊዜው ይጠሯት ነበር። ከኢትዮጵያ ቀደምት ታሪካዊ የንግድ ማዕከል ከሆኑ ከተሞች አንዷ የሆነችው ጅማ በቡና፣ በጨርቃጨርቅ፣ ብረታ ብረት፣ የእንጨት ዕደ ጥበብ ሥራዎችም ይበልጥ ታዋቂ ነች።
ዙሪያዋን ከከበባት ውብና ጥቅጥቅ ደን በተጨማሪ ከከተማዋ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የሰቃ ፏፏቴ እና በከተማዋ እምብርት የሚፈሰው የአዌቱ ወንዝ ልዩ ተፈጥሯዊ ስጦታዎቿ ናቸው። ይህም ከንግድ ማዕከልነት ባሻገር ለቱሪዝምም ተመራጭ ያደርጋታል።
ከአዲስ አበባ በ365 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ጅማ ውብና አረንጓዴ ገፅታን የተላበሰች ለመኖር ምቹ የሆነች ከተማ መሆኗን እግር ጥሎት የሄደ ሁሉ ይመሰክራል። ጣሊያኖች፣ አርመኖች፣ ዓረቦችና ሕንዶች ዛሬም በከተማዋ እንደሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ብዙዎች በስሟ የተቀኙላትና ያቀነቀኑላት ጅማ ወርቃማው የንግድ ማዕከልነቷ የዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በደርግ ከተተካ ወዲህ እየተዳከመ ሄዷል። ይባስ ብሎም በኢሕአዴግ የመንግሥት ሥርዓት ከሠላሳ ዓመታት በላይ “ሞቷል” በሚባል ደረጃ ላይ እንደደረሰ የከተማው ነዋሪዎች በቁጭት ይናገራሉ። ይህም ቀድማ
የከተማነትን ወግ በማየቷ የት ትደርሳለች የተባለችው ጅማ “አሮጌ ከተማ” አሰኝቷት ቆይቷል።
አሁን ላይ ጅማ ካንቀላፋችበት እየነቃች ነው። ስሟንና ታሪኳን የምትመጥን ከተማ ለመሆን መንገድ ጀምራለች። ገናናው የንግድ እንቅስቃሴዋም “ሞቷል” የተባለውን ታሪክ ለመቀየር በትንሳዔ ላይ ይገኛል። ለዚህም ታሪካዊቷንና እድሜ ጠገቧን ከተማ ውብ ለኑሮ የተመቸችና የቱሪስት መስኅብ ለማድረግ እየተሠራ የሚገኘው ጅማን የማስዋብ ሥራ እያነቃቃት ይገኛል።
የጅማ ከተማ የንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጉተማ ጊዲ፣ ጅማ በኢትዮጵያ ረጅም እድሜ ካስቆጠሩ ታሪካዊ ከተሞች አንዷ እንደሆነች በማስታወስ በተለይም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በንግድ እንቅስቃሴ ትልቅ ዐሻራ ማሳረፏን ይናገራሉ። እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ ከተማዋ ከጅማው ንጉሥ አባ ጅፋር አንስቶ በተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶች ውስጥ አልፋለች። በደርግና በኢሕአዴግ ሥርዓቶች ግን ቀድሞ የነበራት የንግድ እንቅስቃሴ ደብዝዞ ያላትን እምቅ ሀብት ያልተጠቀመች ሆናለች።
ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ከመጣው የመንግሥት ለውጥ ወዲህ ጅማ ያሉባትን ችግሮች ለይቶ በማቀድ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። አንዱ ሥራ የከተማዋን የቀድሞ የንግድ ማዕከልነት መመለስ ነው።
ጅማ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ትልቅ የንግድ ኮሪደር መሆኗን የሚናገሩት አቶ ጉተማ፣ ከንግድ ባሻገር የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆንም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። ጅማ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ይፋ የተደረገው ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ውስጥ መካተቷን የጠቆሙት
አቶ ጉተማ፣ ካለፈው ዓመት ወዲህም የኮሪዶር ልማትን በአርዓያነት እየተገበረችና ገፅታዋን እየቀየረች መነቃቃት ማሳየቷን ይናገራሉ።
ይህም የከተማዋን ገፅታ መልሶ በመገንባት የቀድሞ ዝናዋን እየመለሰ ይገኛል። ጅማን ከኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴዋ በተጨማሪ የቱሪዝም ኮንፍረንስ ማዕከል ለማድረግ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ ሆቴሎች መገንባት መጀመራቸውንም ያስረዳሉ።
እድሳት እየተደረገለት የሚገኘው የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት ሲጠናቀቅም ትልቅ የቱሪስት መስኅብ ይሆናል ይላሉ። የቦዬ ዙሪያ ሐይቅ ልማትን ጨምሮ የትልልቅ መንገዶች ግንባታም እየተከናወነ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ። በዚህም የተለያዩ ባለሀብቶች በከተማዋ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ እየመጡ ይገኛሉ። ይህም ጅማን ዳግም ወደ ቀደመ ዝናና እድገቷ እየመለሰ ነው። ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠልም የከተማ አስተዳደሩ ለባለሀብቶች የኢንቨስትመንት መሬት ከማዘጋጀት ጀምሮ የተለያዩ አበረታች ሁኔታዎችን እያቀረበ ይገኛል።
ባለቅኔ በብዕሩ…”ትኩስ የቡናዋ ሲሳይ ከተማ፣ ያአባ ጅፋር፣ ያአባ ቡና፣ ያአባ ጂማ” ሲል የተቀኘላት ጅማ በአዲስ መልክ በኮሪዶር ልማቱ አምራ እና ተውባ ለመዝለቅ አሁንም ሥራዎችን በትጋት እየሠራ ነው።
የከተማዋ ከንቲባ ጠሀ ቀመር እንደገለጹት፣ መንግሥት ለከተማዋ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የጅማን የቀድሞ ገናና ስም ለመመለስ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። ጅማን እንደቀድሞው የንግድ ማዕከል ከማድረግ ባሻገር ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግም ጥረቱ እንደሚቀጥል ከንቲባው ጠቁመዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው ዓመታዊ የ”ልወቅሽ ኢትዮጵያ” የሩጫ ውድድር ከአራት አዘጋጅ ከተሞች አንዷ ለመሆን የበቃችው ጅማ፣ ከታሪካዊ ስፍራዎቿ፣ ዝነኛ የቡና እና የእንጨት ምርቶቿ በተጨማሪ የሩጫ መዳረሻ ስፍራ ሆና ከስፖርቱ ቱሪዝም ተጠቃሚ የሚያደርጋትን ዕድል እንዳገኘች የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዳግማዊት አማረ ተናግረዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም