ክልሉ በዓመቱ መጨረሻ ሁለት የቱሪስት መዳረሻ ሪዞርቶች ሊያስመርቅ ነው

አዲስ አበባ፡– በክልል በ2017 ዓ.ም መጨረሻ ሁለት የቱሪስት መዳረሻ ሪዞርቶች የግንባታ ሥራቸው ተጠናቆ ለምርቃት እንደሚበቁ የሲዳማ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።

የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ማሪሞ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ጋራምባ ተራራ ላይ “ጋራምባ ኢኮ ሪዞርት” እና በዓባያ ሐይቅ በሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ደግሞ “ሳፋሪ ሎጅ” የተሰኙ ሁለት የቱሪዝም መዳረሻዎች እየተገነቡ ይገኛል፡፡

የሪዞርቶቹ ግንባታ የተጀመረው በ2016 ዓ.ም መሆኑን አውስተው፤ ጋራምባ ተራራ ላይ የሚገነባው ሪዞርት የግንባታ አፈጻጸሙ 70 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በዓመቱ መጨረሻ ሐምሌ ወር ላይ ለምርቃት ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዓባያ ሐይቅ የሚገነባው ሌላኛው የቱሪስት መዳረሻ ሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ይመረቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ጋራምባ ተራራ ላይ የሚገነባው ሎጅ 50 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሆነ አመልክተው፤ በሎካ ዓባያ የሚገነባው ሪዞርት ደግሞ በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሀገር የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሪዞርቶች፤ ሎጆች አብዛኛው ጊዜ የሚለሙት በግል ባለሀብቱ ነው ያሉት አቶ አበበ፤ ነገር ግን ኢንቨስትመንት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች መንግሥት ራሱ ወጪ አድርጎ ይገነባል፡፡ ከዚህ አኳያ የሚገነቡት ሪዞርቶች በመንግሥት በጀት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሀብት አላት፡፡ ነገር ግን በተደራጀ መልኩ ተሠርቶ ለጎብኚዎች በቂ መዳረሻ የለም፡፡ አብዛኛዎቹ ሐይቆች፣ ፏፏቴዎች እና ሌሎች የቱሪዝም ሀብቶች አቅራቢዎች የተደራጁ ሆቴሎችና ሪዞርቶች በበቂ መጠን የሉም፡፡

በክልሉ ያሉት የቱሪዝም ሀብቶች ከማስተዋወቅ በተጓዳኝ፤ እንደ ሀገር በዘርፉ ያለው ችግር የመዳረሻ እጥረት እንደሆነ ገልጸው፤ ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ ገንዘብ እና የሰው ኃይል ወጥቶበት የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ክልሉን የሚጎበኙት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም፤ እስካሁን በክልሉ የቱሪስት መዳረሻ የነበሩት ይርጋዓለም፣ ወንዶ ገነት፤ ሀዋሳ እና አካባቢዋ ብቻ የለሙ የቱሪስት መዳረሻዎች መሆናቸውን አውስተው፤ የቱሪስት ፍሰቱን በእጥፍ ለማሳደግ ከከተማ 90 እና 120 ኪሎ ሜትር ርቀት የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች እየለሙ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህም በክልሉ ቱሪስቶች በአማካኝ ሦስት ቀን የሚያሳልፉ ሲሆን፤ ይህን ወደ ስድስት ቀን ለማሳደግ መዳረሻዎችን በስፋትና የማልማት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት አራት መዳረሻዎች ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You