
አዲስ አበባ፤– በመትጋታችንና በመልፋታችን በእቅዳችን ልክ የሚታይ የሚጨበጥ ውጤት ለማየት ችለናል፤ ስኬታችን ሳያዘናጋን ለበለጠ ከፍታ የሚያነሳሳን ሊሆን ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መጀመሩን በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፤ በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ የ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም መገምገም ጀምረናል። እስካሁን ያሳካነው የሥራ ውጤት ሰፊ ቢሆንም ስኬታችን ሳያዘናጋን ለበለጠ ከፍታ የሚያነሳሳን ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ካቀድነው እቅድ አንፃር የአፈጻጸም ውጤቱ በጣም ከፍተኛ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ካቢኔው ሪፖርቱን ድጋሚ እንዲያይ የምፈልገው ትጋት ስኬት ይወልዳል፤ በመትጋታችን፣ በመልፋታችን በእቅዳችን ልክ የሚታይ የሚጨበጥ ውጤት ለማየት ችለናል ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን ስኬት መልሶ ትጋት እንደሚፈልግ አመልክተው፤ ተሳክቶልኛል፣ ያሰብኩትን ከውኛለሁ የሚል ኃይል ይዘናጋል። ስኬትን ትጋት ገዳይ ሳይሆን ትጋት ተጨማሪ ትጋት ወላጅ አድርገን መጠቀም ከቻልን በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ካሰብነው እቅድ በላይ አሳክተን የተሟላ ስኬት ማስመዝገብ እንችላለን ብለዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽ፤ አሁን ተሳክቶልናል በምናስበው ልክ ሠርተናል የሚል ግምገማና አንድምታ ካለ ስኬት ትጋት ስለሚገድል ማድረግ የሚገባን ተጨማሪ ልፋቶች ይቀንሳል፤ በምንፈልገው ልክ የተሟላ ውጤት አያመጣም። የለውጥ ገቺ ተብለው ከሚወሰዱ ነገሮች አንዱ ስኬት ስለሆነ ስኬትን ትጋት ጨማሪ አድርገን መጠቀም ይኖርብናል።
“ተሳካልኝ የሚል ደሃ፣ መካከለኛ ገቢ ሲደርስ ታስሮ የሚቀር ባገኘው መጠነኛ ስኬት ስለሚረካ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የለውጥ ጉዞ ወጥመድ ስኬት ስለሆነ በየአንዳንዱ ዘርፍ ያገኘነው ውጤት ለተጨማሪ ልፋት፣ ለተጨማሪ ጥረት የሚያነሳሳን ከሆነ በሀገር ደረጃ የሚታሰበውን ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡
የዓለም ኢኮኖሚ በ2025 በ3 ነጥብ 3 በመቶ የሚያድግ መሆኑ የተተነበየ መሆኑም የተገለጠ ሲሆን ከሰሐራ በታች ያለውን የአፍሪካ ክፍል ጨምሮ አብዛኛው የዓለም ክፍል አዎንታዊ እድገት እንደሚያስመዘግብ መገለጹን ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ 8 ነጥብ 4 በመቶ እንደሚያድግ ተተንብያል። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም መርሐ ግብር የተረጋጋ ሆኖ የቁጠባ እና የኢንቨስትመንት እድገትም አሳይቷል። የውጭ ዕዳ ከሀገራዊ የምርት መጠን (ጂዲፒ) ያለው ምጣኔ 13 ነጥብ 7 ከመቶ በመድረስ ትርጉም ባለው መጠን መቀነሱ ተብራርቷል።
በተጨማሪም አዲስ የውጭ ምንዛሪ አሠራር መዘርጋቱም ከውጭ የሚላክ የውጭ ምንዛሪ እንዲጨምር በማድረግ የሀገራችንን የውጪ ምንዛሪ ክምችት ጨምሯል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም ከግብርና፣ ከማዕድን፣ ከኢንዱስትሪ እና ኤሌክትሪክ የተገኙ የውጭ ንግድ ገቢዎችም እድገት እንዳሳዩ ተመልክቷል።
ቡና፣ ወርቅ፣ ጥራጥሬ፣ የዘይት ምንጭ ፍሬዎች፣ አበባ እና ኤሌክትሪክ አምስቱ ቀዳሚ የውጭ ንግድ ምርቶች ሆነዋል። ግምገማው ታላላቅ የመሠረተ ልማት እና ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችንም አፈፃፀም ተመልክቷል። ለአብነትም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 98 ነጥብ 66 ከመቶ አፈፃፀም ላይ የደረሰ ሲሆን ስድስት ዩኒቶቹም ወደ ሥራ ገብተዋል ሲሉ የዘጠኝ ወራቱን አፈጻጸም ግምገማ በአብነት መጠቀሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
ሳሙኤል ወንደወሰን
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 ቀን 2017 ዓ.ም