ይህችን ምድር የተቀላቀሉት በ1935 ዓ.ም ሲሆን፣ የትውልድ ቦታቸው ደግሞ በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ አንቆርጫ በሚባልበት አካባቢ ነው። ከአርሶ አደር ዋቄ በሻ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ድምቡሼ ጎረንጦ የተወለዱት እኚህ ሰው ክርስትና የተነሱትም ሆነ ፊደል የቆጠሩት የካ ሚካኤል ነው።
ከአንድ እስከ ስምንት ያለውን ትምህርት የተማሩት ወንድይራድ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 9ኛ ክፍልን ተከታተሉ። ቀሪውን የአሁኑ ዩኒቨርሲቲ የዚያኔው ኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከጨረሱ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተፈጥሮ ሳይንስ የሂሳብ ትምህርት ሲያጠኑ ነበር። ይሁንና በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳሉ ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአብራሪነት ሰዎች ፈልጎ ኖሮ ድንገት ሳያስቡት ጓደኞቻቸውን ተከትለው በሄዱበት ተፈትነው በማለፋቸው ድርጅቱን በአብራሪነት ሙያ ይቀላቀላሉ። ይህ ሲሆን ወቅቱ 1965 ዓ.ም ነበር።
በወቅቱ ለአብራሪነት ይሰልጥኑ እንጂ ጥሩ አብራሪ መሆን እንደማይችሉ ሲረዱ ስልጠናውን ሳያጠናቅቁ በእርሳቸው አባባል ወድቀው ወደ ንግድ ክፍል ተዛወሩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለ27 ዓመታት በአየር መንገዱ የተለያዩ ቦታዎችና በተለያዩ ደረጃዎች ሲሰሩ ቆዩ።
እኚህ የዛሬው እንግዳችን ለግማሽ ምዕተ ዓመት አብሯቸው ከዘለቁ
ባቤታቸው ጋር አምስት ልጆች ያፈሩ ሲሆን፣ ስምንት የልጅ ልጅም ማየት ችለዋል።የመጀመሪያ ልጃቸው ሴት ስትሆን፣ እርሷን ጨምሮ የአራት
ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ናቸው። ለልጆቻቸው ምን አይነት አባት እንደሆኑም ሲጠየቁ ጓደኞቻቸው መሆናቸውን ይናገራሉ። እኚህ
ሰው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ 14ኛ ስራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ በአየር መንገዱ በቆዩባቸው ጊዜያና በስራ አስፈጻሚነት በመሩባቸው ወቅት
ታላቅ ለውጥን ያስመዘገቡ ናቸው። አዲስ ዘመን ረቡእ ዛሬ ይዛ የቀረበችው እንግዳ የቀድሞውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ
የሆኑትን አቶ ግርማ ዋቄን ሲሆን፣ በተለይ በአየር መንገዱ አሰራርና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ አነጋግረናቸዋልና መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- አየር መንገዱን ለቀው የወጡት ለምንድን ነው?
አቶ ግርማ፡- ከ27 ዓመት በኋላ አየር መንገዱን ለቅቄ የወጣሁት በፍላጎቴ ነው። ወቅቱም ኢህአዴግ ሲገባ አካባቢ ሲሆን ያኔ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ነበር። በዛ ኮሚቴ ውስጥ ነበርኩ። አካሄዱም ሆነ ሁኔታው አላማረኝም። ስለዚህም አልስማማም አልኩ። ስለዚህም አልሰራም ብዬ ወጣሁ።
አዲስ ዘመን፡- ምን ይሆን ያላመኑበት ነገር?
አቶ ግርማ፡- የፖሊሲ ነገር ነው። በወቅቱ አየር መንገዱ ይጠና ተብሎ አቶ ስዬ አብርሃ የሚመራው ነበር። የአየር መንገዱ አሰራር ይለወጥ የሚል ስለነበር በዛ ጥናት ላይ እኔ ማኔጅመንቱን ወክዬ ከሌሎቹ የስራ ባልደረቦቼ ጋር እሄድ ነበር።እዛ ላይ አንዳንድ ለአየር መንገዱ የማይመች ነገሮች ሲንፀባረቁ ይህ ትክክል አይደለም በማለት እከራከራቸው ነበር።‹አይ ትሰራ እንደሆን አርፈህ ስራህን ስራ አለዚያ…› ሲሉኝ አላስፈላጊ ደረጃ ምን አዳረሰኝ፤ ልልቀቅላችሁ ብዬ ስራዬን ለቀቅሁ።
ከ27 ዓመት በኋላ አየር መንገዱን ለቅቄ ለአንድ አምስት ወር ቤቴ ከተቀመጥኩ በኋላ የገልፍ አየር መንገድ ተቀጥሬ ሄድኩ።በገልፍ አየር መንገድ ስሰራ ቆይቼ ወደ ዲኤችኤል በተውሶ ለሁለት ዓመት ወሰዱኝ።ይሁንና በድጋሚ የገልፍ አየር መንገድ እንፈልግሃለን ሲሉኝ ተመልሼ ወደዛው አቀናሁ።በኢትዮጵያ አየር መንገድ እስክጠራ ድረስ በዛው የካርጎ ኃላፊ ሆኜ ቆየሁ።
አዲስ ዘመን፡- ጥሪውን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የመጡበት ጊዜ መቼ ነበር?
አቶ ግርማ፡- እኤአ 2004 ጥር ስራ ጀመርኩ። ያነጋገሩኝ ታህሳስ ወር ነው። የነበርኩበትን የመልቀቂያ ፈቃድ እስክጠይቅ ድረስ የአንድ ወር ያህል ጊዜ ወስዶብኛል። ይህ ጊዜ ማለት በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር 1997 ነው። በወቅቱም የአየር መንገዱ ስራ አስፈጻሚ ሆኜ ስራዬን ቀጠልኩ።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በቆዩበት 27 ዓመታት ውስጥ የተሰራው ምን ምን ስራ ነበር?
አቶ ግርማ፡- 27ቱን ዓመታት በተለያዩ ቦታዎች ስሰራ ነው ያሳለፍኩት።አንደኛ ጅማ ሰርቻለሁ።ከጅማ መልስ ደግሞ በአየር መንገዱ የንግድ ክፍል ውስጥ አስተማሪ ሆኛለሁ። በመምህርነቱ ለአንድ አራት ዓመት ተኩል ያህል አገልግያለሁ። ከዚያም በመቀጠል በአየር መንገዱ የፕላኒግ ስራ የሚሰራ ማለትም ካፓሲቲ ፕላኒግ የሚለውን ስራ የጀመርኩት እኔ ነኝ። በዚህም ውስጥ አንድ አምስት ዓመት ያህል ሰርቻለሁ። ደርግ ሲመጣ ደግሞ አየር ማረፊያ አካባቢ ኃይለኛ ችግር ስለነበር የአየር መንገዱ ማናጀር ሆኜ ሰርቻለሁ።
ከዛ ቀጥሎ ጋና፣ ታንዛኒያ እንዲሁም ጀርመን ተቀያይሬ ሰርቻለሁ። ተመልሼ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጣቢያዎች ሁሉ ኃላፊ ሆኜ አዲስ አበባም ሰርቻለሁ። የካርጎ አውሮፕላን አየር መንገዱ መግዛት ሲፈልግ ፈቃደኛ ሆኜ የካርጎ ዳይሬክተር ሆኜ ሰተርቻለሁ።በዚህን ጊዜ ነው እንግዲህ ኢህአዴግ የመጣው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድን የለቀቁት መቼ ነው ማለት ነው?
አቶ ግርማ ዋቄ፡- እኤአ 1999 ነው።
አዲስ ዘመን፡- መጀመሪያም ለቀዋልና ለሁለተኛ ጊዜስ የለቀቁበትስ ምክንያት ምንድን ነው? የመጀመሪያውም የአሁኑንም ግልፅ ቢያደርጉልን?
አቶ ግርማ፡- በእርግጥ አየር መንገድን የለቀቁኩት ሁለት ጊዜ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ኢህአዴግ እንደገባ ነው። በወቅቱ የለቀቅኩበት ምክንያት የሐሳብ ልዩነት በመኖሩ ነው። እናም ሁኔታው የሚያግባባኝ ሳይሆን ሲቀር በራሴ ፈቃድ መልቀቄን ከላይ ገልጫለሁ።በወቅቱ የነበሩት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ነበሩና እርሳቸው ዘንድ ቀረብኩ።
እርሳቸውም በወቅቱ ‹አርፈህ ትሰራለህ አትሰራም›
አሉኝ። እኔ ደግሞ መልሼ ‹እኔ የማላምንበትን ነገር አልሰራም› ስል መለስኩላቸው። እርሳቸውም መለስ ብለው ‹አይ እንግዲያው የምናደርገውን እናውቃለን› አሉኝ። እኔ ደግሞ በተራዬ ‹አይ እናንተ ምን አደከማችሁ፤ክፉ ማድረግም አይጠበቅባችሁም። እኔው ራሴ ልልቀቅላችሁ› አልኳቸው። ወዲያውኑም የመሰናበቻ ወረቀት አቀርብኩላቸው። እርሳቸውም ‹ሂድና ለአለቃህ ስጥ›አሉኝ። በወቅቱ አለቃዬ አቶ ዘለቀ የሚባል ነበር። እናም ለአለቃዬ ሰጠሁና ተሰናበትኩ።
አዲስ ዘመን፡- ያለመግባባቱ ምን ላይ ነበር? እርስዎ ያላመኑበት ነገር ምንድን ነበር?
አቶ ግርማ፡- የአሰራር ልዩነት ነበር። እነሱ ሲመጡ (ኢህአዴግ) ማለት ነው፤ ደርግ ሲጀምር እንዳለው ሁሉ የአየር መንገድን አሰራር በተመለከተ ምን ያስፈልጋል የሚል አመለካከት ነበራቸው። ሁለተኛ ደግሞ አየር ኃይሉ በዚያ በደርግ ጊዜ ‹አጥቅቶናል፤ወግቶናልም› የሚል አተያይ ነበራቸው። በርካታ የአየር ኃይል ልጆች ደግሞ በወቅቱ አየር መንገድ ውስጥ ነበሩ። በዚያን ጊዜ ከአየር መንገዱ አብራሪዎችም ታስረዋል።እነዚህ ደግሞ በወቅቱ አየር ኃይል የነበሩና ወግተዋል የተባሉቱ ናቸው።
ስለዚህ እነርሱ ስለ አየር መንገድ ያላቸው አስተያየት ከአየር ኃይሉ የተለየ አልነበረም።ሁለተኛው ደግሞ አካሄድ ላይ እንለውጠዋለን የሚል እይታ ነበራቸው። በእርግጥ መለወጣቸው መጥፎ አልነበረም።አዲስ ሐሳብ መምጣቱም የሚጠላ አልነበረም።ነገር ግን ሊሆን የማይችል ነገር ማለትም አንዳንድ ሐሳቦችን ሲያመጡ የለም፤ይህ ሊሆን የማይችል ነገር ነው ብለን ስለተከራከርናቸው ትንሽ ወዳልሆነ መንገድ ሲያመሩ እኔ ለቅቄ ሄድኩ።
አዲስ ዘመን፡- እንግዲህ አየር መንገዱን ለቀው ከሄዱ በኋላ ተመልሰው መጥተዋልና ችግሩ ተስተካክሎ ነው የተመለሱት?
አቶ ግርማ፡- ወቅቱ 1993 ዓ.ም ሲሆን፣ የተመለስኩትም ከ11 ዓመት በኋላ መሆኑ ነው። ሲጠሩኝ ነው የመጣሁት።ከዛ በፊት ግን ከአቶ ስዬ አብርሃ ጋር ነው የተጨቃጨቅኩት።በወቅቱ እርሳቸው በአየር መንገድ ውስጥ ለተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበሩ።በወቅቱ እርሳቸው በማናጅመንቱ ውስጥ የነበሩትን 35ቱን አስወጥተው የራሳቸውን ሰዎች አምጥተው በአየር መንገዱ ውስጥ አስገብተው ነበር።በወቅቱ እኔ በራሴ ፈቃድ ለቀቅኩ።አንድ የራሳቸውን ሰው ከእንግሊዝ አገር አስመጥተው ስራ አስኪያጅ አደረጉ።
የመስሪያ ቤቱንም ፖሊሲ ሆነ አካሄድ ‹ይህ የደርግ ፖሊሲ ነው እያሉ፣ እያራከሱ መስሪያ ቤቱን አፈራርሰውት ነበር።በመጨረሻም አቶ ስዬ የቦርድ አባል ሆነው ሲያዩት ነገሩ አላምር አላቸው።በጊዜ ሂደት አየር መንገዱ እየወረደና እየቀነሰ፤ሰውም እየለቀቀ መጣ። የገቡት ሰዎች ደግሞ የማያውቁትን እንሰራለን ሲሉ ድራሹ እየጠፋ እንደሆነ ገባቸው። ስለዚህም አካሄዱ አልሆን ሲላቸው መቀየር ፈለጉ።ጉዳዩን ሲያስቡት ደግሞ እኔን ‹ተመለስ› ብለውኝ ነበር። እኔ ደግሞ ‹አሻፈረኝ› አልኳቸው።በዚያን ጊዜ አቶ ብስራትን ጀነራል ማናጀር አደረጉትና እነዚያን ሰዎች አስወጧቸው።እናም ስራው ወደ አየር መንገድ አሰራር እንዲመለስ አደረጉት።
እኔ እንደገና በደወሉልኝ ጊዜና ‹ተመለስ› ባሉኝ ወቅት፣ አሁን እድሜዬም 60 እየደረሰ ነው፤ይህ እድሜ ደግሞ የጡረታ እድሜ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እኔ ከአየር መንገዱ አሰራር ተለያይቻለሁ። እዚያው አየር መንገዱ ውስጥ በውጣ ውረድ የደከሙ ሰዎች ስላሉ አልመለስም ብዬ ነገርኳቸው።በዚህን ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን ‹አይ እኔ አላነጋገርኩህምና›› አሉኝ። በወቅቱ በስም በስተቀር አቶ ስዩምን አላውቃቸውም ነበር።እኔም ችክ ካልኩበት መለስ ብዬ የት ነው የሚያነጋግሩኝ? ስላቸው ‹ያለህበት አገር እመጣለሁ›አሉኝ፤ይሁንና እርሳቸው የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሳሉ እኔን ፍለጋማ ያለሁበት ድረስ መምጣት የለብዎትም፤የዚያን ያህል የምትፈልጉኝ ከሆነ እኔ ቅዳሜ ቅዳሜ እረፍት ላይ ስለሆንኩ መምጣት እችላለሁ።ስለዚህ በቅዳሜ ቀን መስሪያ ቤት ገብታችሁ የምታነጋግሩኝ ከሆነ እመጣለሁ አልኳቸው።
በዚህም መሰረት በአንዱ ቅዳሜ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቀናሁ። በተባባልነው መሰረት እየጠበቁኝ ስለነበር ወደ ውስጥ ስዘልቅ ካፕቴን መሀመድ የድሮ አለቃዬ፣ኮሎኔል ስምረት ደግሞ የመጀመሪያ አለቃዬ እና ሌሎችም ተቀምጠው አገኘኋቸው። እነርሱ የቦርድ አባላት ነበሩ። ለምን እንደሚፈልጉኝ ጠየቅኳቸው።‹እንድትመለስና ጀነራል ማናጀር እንድትሆን ነው የምንፈልገው› አሉኝ። እኔም ቅድም እንደገለፅኩት አይሆንም፤ እድሜዬም 60 ሊሞላ ነው። በመስሪያ ቤቱ የደከሙ ሰዎች እያሉ እኔ ከውጭ መጥቼ የእነርሱን ቦታ መጋፋት አልፈልግም አልኳቸው።
በዚህ ጊዜ ‹የለም፤አየር መንገዱ ችግር ላይ ነው። ከውስጥ ያሉትን ሰዎች የሚያዘጋጃቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህም አንተ መጥተህ ሰው እንድታዘጋጅልን ነው የምንፈልገው› አሉኝ። በተጨማሪም አንዳንድ ነገሮችን መስመር እንድታስይዝልን እንሻለን›አሉ። ማንገራገሬን ያዩ የቀድሞዎቹ አለቆቼ ‹እንዴ ያሳደገህን ቤት ጥለህ ምነው› ሲሉኝ እሺ አልኳቸው። እኔ በወቅቱ እሰራበት በነበረበት ቦታ የማገኘው በጣም የተሻለ ደመወዝ ነው።እናንተ እንዳላችሁት መመለስ ካለብኝ እመለሳለሁ፤ነገር ግን ቅድመ ሁኔታች አሉኝ። ስላቸው ‹ምንድነው?› ሲሉ ጠየቁኝ። እኔ ጀነራል ማናጀር ሆኜ ስመለስ እከሌን ሹም፤እከሌን ደግሞ ሻር፤ወደዚህ ቦታ ክፈት፤እንዲህ አይነት አውሮፕላን ግዛ፤ እከሌን ቅጠር ማለት አትችሉም። ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት አልፈልግም። ይህ የሚኖር ከሆነ አልመጣም አልኳቸው።
‹ሌላስ› አሉኝ፤ሌላ ምንም አልፈልግም አልኳቸው። እኔ በዓመቱ መጀመሪያ የዓመቱ እቅዴን እንግራችኋለሁ።ቦርዱ ያይና ይህ ይቀነስ፤ይህኛው ደግሞ ይጨመር የሚለውን መነጋገር ይችላል። ከተስማማን በኋላ ግን ጣልቃ እገባለሁ ብትሉ አልሰማም አልኳቸው። ‹ደመወዝህስ› አሉኝ። የማገኘው የወር ደመወዝ ይህ ነው፤ይህንን ደግሞ ኢትዮጵያ ትከፍለኛለች ብዬ አልጠብቅም።ሁለተኛ ደግሞ ከእኔ በፊት ለነበረ ሰው ያልከፈላችሁትን ደመወዝ ለእኔ እንድትከፍሉኝም አልፈልግም። ሌላው ደግሞ ያልሆነ ደመወዝ ከእናንተ ብትሰጡኝ ሌላውን ሰው የለም ለአንተ የደመወዝ ጭማሪ አያስፈልግም የማለት እና የመናገር ሞራልም የለኝም።ስለዚህ እኔ ከሰራተኛው የተለየ እስከዛሬ ድረስ ከሚከፈለው ደመወዝ የተለየ አልፈልግም።ከመጣሁ መምጣት ያለብኝ ለመስራት ነው የምመጣው እንጂ ለገንዘብ አልመጣም። በፊትም የለቀቅኩት ለገንዘብ ብዬ አይደለም። ስላቸው ‹አሺ› አሉኝ፤ተመልሼ መጣሁ። እኤአ ርዕይ 2010 የሚል እቅድ አወጣን።ይህ ርዕይ እኤአ በ2004 አውጥተን በ2005 ስራ ላይ ያዋልነው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ርዕይ 2010 ምን ነበር የያዘው?
አቶ ግርማ፡- እኔ ወደ ኢትዮጵያ በምመጣበት ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኛ በዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ነበር። በኋላ ላይ ይህን ቁጥር እኤአ በ2010 ላይ ወደ ሶስት ሚሊዮን መንገደኛ እናደርሳለን የሚል እቅድ አወጣን።ሌላው እቅዳችን በዚያ ጊዜ የዓመት ገቢያችን 390 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ይህን ቁጥር ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር እናደርሰዋለን ብለን አቀድን። የአውሮፕላኑንም ቁጥር በርከት የማድረግ ርዕይ ነው የያዝነው። እንዲሁም የመዳረሻ ጣቢያዎችንም እንጨምራለን ብለን ነበር ወደስራው የገባነው። ይህንን በምናቅድበት ጊዜ ‹አስረዱ› ተባልንና ስናስረዳ ‹አይ፤ ይህ ነገር ቅዠት ነው። ስለዚህም ሊሆን አይችልም። ይህ አየር መንገድ በ60 ዓመቱ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን መንገደኛ መሸከም የደረሰ እንዴት ሆኖ ነው በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሶስት ሚሊዮን መንገደኛ መድረስ የሚችለው› በሚል ሐሳብ ሲመጣ ሁሉም ሰው ተጠራጠረ። እኔ ግን እንደሚሳካ አመንኩበት።
እቅዱን ለሰራተኞችም ስናወረድ ብዙዎቹ ‹አይ፤ ይህ ዝም ብሎ የአረብ ቅዠት ነው› አሉ። እኔም አይ ግዴለም ይደረስበታል ማለት ስንጀምርና በተከታታይም ስናስረዳ በመጨረሻ ሁሉም ወደ ማመን መጣና እቅዱን ስራ ላይ አዋልነው። በ2010 እንደርስበታለን ያልነውን ግብ በ2009 በሙሉ አንድ ዓመት አስቀድመን ደረስንበት።ስኬታማ ከሆን በኋላ የ2010 ርዕይም ስለሚያልቅ አሁን ማቀድ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ተረዳን።
እንደዛም ሆኖ በሰራንባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ በርካታ ችግሮች አጋጠሙን። ከእነዛም መካከል አንዱ ቀደም ተብሎ አውሮፕላን መታዘዝ ሲኖርበት ባለመታዘዙ ለምንፈልገው አይነት እድገት አውሮፕላን ማግኘት አልቻልንም። ብናገኝም ከሌላ ከተለያዩ አየር መንገዶች ተከራይተን እንጂ ለእኛ የተሰራ አውሮፕላን አይደለም።በዚህ ጊዜ ደግሞ አንደኛ ኪራዩም ይወደድብናል።ሁለተኛ ደግሞ አውሮፕላኖቹ አይመሳሰሉም።ውጪያቸው የኢትዮጵያን አየር መንገድ ዓርማ ያመልክት እንጂ አንድ አይነት አይደሉም።የውስጥ መዋቅራቸው የኢትዮጵያን ገፅታ የጠበቀ ሆኖ አልተገኘም።
ስለዚህ እንደ ድሮው የአምስት ዓመት እቅድ ሳይሆን የ15ዓመት እቀድ እናውጣ። ይህ ከሆነ አውሮፕላንም አስቀድመን ማዘዝ እንችላለን።የገንዘብ ብድርም አስቀድመን እንፈልገጋለን።የሰው ኃይሉንም በአግባቡ ለማዘጋጀት ያስችለናል በማለት ርዕይ 2025 የሚለውን መቅረፅ ጀመርን።እኔ ከመውጣቴ በፊት ይህን ርዕይ ማቀድ ነበረብኝና አወጣን።ይህን ርዕይ ስናወጣ ወቅቱ አስቀድሜ እንደገለፅኩት በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር 2003 አካባቢ ነበር።በዚህ ርዕይ በየዓመቱ ምን ያህል አውሮፕላን እንደምንገዛ፣ ምን ያህል አብራሪ እንደምናሰለጥን፣ ምን ያህል መካኒክ እንደምናሰለጥን፣ምን ያህል ሰራተኛ እንደምንቀጥርና እንደምናሰለጥን በሙሉ በየዓመቱ እቅዱን አወጣን። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ደርጅቱ መዘጋጀት ያስችለዋል።ሌላው ደግሞ የማሰልጠኛ ዲፓርትመንት የነበረውን ወደ አካዳሚ ለውጠን ትልቅ አድርገን ሰራን። ምክንያቱም ያልሰለጠነ የሰው ኃይል ምንም ነገር ሊሰራ አይችልም። ስለዚህም ሁሉም ርዕዩን እንዲረዳ አድርገን ርዕይ 2025ን በ2010 አዘጋጅተን ጨረስነው።
ይህ ርዕይ 2025ን የሰራነው፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ነን፤አንድም የውጭ አማካሪም አላስገባንም።በ2010 ላይ ኮንሶልታንት አስገብተን ነበር፤በ2010ም ቢሆን የራሳችንን ሰው ከእነ ኤርነስተን ያንግ ጋር አሰርተን ልምድ እንዲገኝ አድርገናል። ርዕይ 2025ን እንደጨረስን አሁን እኔ መሰናበት አለብኝ፤ ይህን ርዕይ በአዲስ ጉልበት አዲስ ሰው መጀመር አለበት ብዬ ለቦርዱ አመለከትኩ፤ትንሽ ከተከራከርን በኋላ አሳመንኳቸው።በ2010 መጨረሻ እኔን የሚተካ ሰው ፍልጌና አዘጋጅቼ በማቅረብ እኤአ ጥር 11 ላይ ከአየር መንገዱ በ65 ዓመቴ በጡረታ ወጣሁ።
አዲስ ዘመን፡- አቅምዎ ታምኖበትና ለስራውም እየተፈለጉ ለምን ለመውጣት ፈለጉ?
አቶ ግርማ፡- (ለሰኮንዶች ያህል አሰብ ካደረጉ በኋላ) ሁለት ነገር አለ። የመጀመሪያው 65 ዓመት ለእንደዛ አይነቱ የሩጫ ስራ አያመችም።ወጣቶች ቢሰሩ የተሻለ ነው በሚል ነው። ወጣቱ ክፍል ቀጣይ ነው፤እኔ ከዛ በኋላ ብቀጥል ሁለት ሶስት ዓመት ነው። አንድን ነገር ጀምሮ መሃል ላይ መተው ልክ አይመጣም። ስለሆነም የሚጨርሰው ሰው ቢጀምረው መልካም ነው የሚል እምነት ነበረኝ።ሁለተኛው ደግሞ ልጆቹን ሳያቸው የተዘጋጁ ናቸው።ስለዚህም የእኔ መቆየት ምንም ትርጉም አይኖረውም።እኔ ብወጣ አየር መንገዱ አይጎዳም። ልጆቹ ግን ጥለውት ቢሄዱ የሚያገለግሉትን ሰዎች ነው የሚያጣው። ተስፋ ካጡ ትተው ይሄዳሉ።በዚህ ጉዳይ ቦርድ ላይ ብዙ ብንከራከርም የወጣሁት አሳምኛቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በጡረታ ከወጡ በኋላ ወደየት ነው የሄዱት?
አቶ ግርማ፡- ወደ ቤቴ ነው፤ አንድ ዓመት እንዳረፍኩ የሩዋንዳ መንግስት አየር መንገድ ያቋቁም ነበርና እርዳን ሲሉ ጠየቁኝ። ሄጄ ለሶስት ዓመት እዛ ቆይቼ አየር መንገዱን አቋቋምኩላቸው። ካቋቋምኩላቸው ከሶስት ዓመት በኋላ ደግሞ በወር አንድ ሳምንት ለሁለት ዓመት ያህል እየሄድኩ የሚሰራውን እቅዳቸውን በእቅዱ መሰረት መሄድ አለመሄዳቸውን እያረጋገጥኩ ቆየሁ። በጥቅሉ ለአምስት ዓመት ያህል ሩዋንዳ ቆይቻለሁ። በቆይታዬም በመጀመሪያ በማቋቋም ቀጥሎም የሩዋንዳ አየር መንገድ የቦርድ ሊቀመንበር ሆኜ እስከዛሬ ሁለት ዓመት ድረስ ሰራሁ።
ከዛ ተመልሼ መጣሁ፤እንደገና ቶጎ ረዳት ያስፈልገና ስላሉ ቶጎ የመንግስት አማካሪ ሆኜ በአቬይሽንና በቱሪዝም አማካሪ ሆኜ እረዳቸዋለሁ። ይህንን ስራዬን አሁንም ድረስ በወር አንድ ሳምንት እነርሱ ዘንድ እየሄድኩ እሰራለሁ። ሌሎችም አየር መንገዶች ችግር ሲኖራቸው ይጠሩኛል፤እሄድና ከረዳኋቸው በኋላ እመለሳለሁ።በአሁኑ ሰዓት የእኔ ስራ ሄዶ ምክር መምከር፣አየር መንገዶችም እንዲቀራረቡ ማድረግና እንዴት አድርገው አሰራራቸውን ቢያሻሽሉ መልካም እንደሆነ እመክራቸዋለሁ።መንግስትም ባላስፈላጊ ሁኔታ ዝም ብሎ አየር መንገዱ ውስጥ ጣልቃ እየገባ እንዳይስተጓጉል እመክራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ለኢትዮጵያ አየር መንገደ ስንተኛ ስራ አስፈጻሚ ነዎት?
አቶ ግርማ፡- የመጀመሪያዎቹ ሰባት ስራ አስፈጻሚ/አስኪያጆች ፈረንጆች ሲሆኑ እነርሱም አሜሪካውያን ነበሩ። ከእኔ በፊት ደግሞ ስድስት ኢትዮጵያውያን ስራ አስኪያጆች የነበሩ ሲሆን፣ እኔ ሰባተኛው ኢትዮጵያዊ ስራ አስኪያጅ ስሆን ለአየር መንገዱ ደግሞ 14ኛ ስራ አስኪያጅ ነኝ። የተረከብኩትም ከአቶ ብስራት ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንዲያው በተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ ውጤታማ ስራ ሰርተዋልና በቆይታዎ ያገኟቸው ሽልማች ምን ምን ናቸው?
አቶግርማ፡- (ረዘም ካለ ዝምታ በኋላ) አንደኛ የአፍሪካ ኤየርላይን አሶስሽን ድሮም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው ረድቶ ያቋቋመው፤ እንዲያውም የመጀመሪያ ስራ አስኪያጃቸው የነበረው ኮሎኔል ስምረት ነው። ከሚኒስትርነት እዛ ሄዶ ነው። እና ያ እንዲጠናከረ በማድረጌ ከእነርሱ እውቅናን አግኝቻለሁ። በኢትዮጵያ አየር መንገድ እድገት በርከት ያሉ ሽልማቶች አግኝቻለሁ። በአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ በሚባልበት ጊዜ፣በአፍሪካ ምርጡ ስራ አስኪያጅ በሚባልበትም ጊዜ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቻለሁ። ከአሜሪካኖቹ፣ ከአውሮፓውያኑም አግኝቻለሁ። የገልፍ አየር መንገድም እዛ በነበርኩበት ጊዜ ከማናጅመንቱ መካከል እያወዳደሩ በርከት ያሉ ሽልማቶችን ሰጥቶኛል። በተጨማሪም አገሪቱም የሸለመችኝ አለ። ባህሬንም አቡዳቢም ሸልመውኛል። አያታም ላይ የቦርድ አመራር ውስጥ እሰራ ስለነበር ተሸልሜያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከተሸለሟቸው ሽልማች መካከል በልብዎ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሰጡት ሽልማት ይኖር ይሆን?
አቶ ግርማ፡- (ትንሽ በዝምታ በሐሳብ ወደኋሊት ከሄዱ በኋላ) በእርግጥ ለሁሉም ትልቅ ክብር አለኝ።ነገር ግን ካገኘኋቸው ሽልማቶች ውስጥ ሁሉ ትልቅ ግምት የምሰጠውና ዋጋ አለው ብዬ የምለው አንዱን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን አየር መንገድን ለቅቄ የወጣሁ እለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች፣ ጡረተኞች እንዲሁም ማናጅመንቱ በአንድ ላይ ሆነው ምንም እንኳን የመኪና ችግር ባይኖርብኝ እነርሱ ግን መኪና ገዝተው፣ በቆይታዬ የተነሳኋቸውን ፎቶ ግራፎች አሰባስበውና በፎቶ አልበም አድርገው የሰጡኝ ስጦታ ከሁሉም በላይ ትልቅ ግምትና ዋጋ እስጠዋለሁ።
በነበርኩበት ጊዜ ለሰራተኛው ምንም የተለየ የሰራ ሁለት ነገር የለም። ነገር ግን እነርሱ እንደሚሉት አንደኛ ድርጅታችንን አሳደገልን፤ ሁለተኛ ደግሞ ሁላችንንም የሚያየን በአንድ አይን ነው፤ ያጠፋውንም አጥፍተሃል የሚል ነው። ያለማውንም ያመሰግናል። አልፎም ያሳድጋል፤ ይሸልማል በማለት ነበር የሸለሙኝ።
አዲስ ዘመን፡- በአየር መንገዱ ቆይታዎ ውስጥ ስኬትም ተግዳሮትም ይኖራልና ይህን እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ግርማ፡- ውጤቱ ያው እንዳያችሁት ነው።ጥሩ የሚባል ውጤት ነበረው። በመሃከል አንዳንድ ጊዜ ፈተና ይኖራል።ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ጊዜ ቢፒአር የሚሉት ነገር ተጀምሮ ነበር።ይህ ቢፒአር የሚሉት ነገር ሁሉም መስሪያ ቤት ውስጥ እንዲገባ ተብሎ ግዳጅ መጣ። ይህን ቢፒአር የሚሉትን ነገር ሳየው ለእኛ መስሪያ ቤት በጣም ደረጃው ዝቅ ያለ ነገር ሆኖ ታየኝ። ደግሞም ወደምንፈልገው ግብ የሚያንደረድረን ነገር ሆኖ አላገኘሁትም።እኛ ‹ኤ.ኤስ.ኤ› ብለን ከምንሰራው በጣም ያነሰ ነው።ስለዚህም ይህን ቢፒአር የምትሉትን ነገር ስራ ላይ አላውልም አልኩ። ምክንያቱም እኛ የተሻለ ስርዓት አለንና ወደሌላው አልመለስም ብዬ ተናገርኩ። ‹አይ አገሪቱ በሙሉ በዚህ ነውና የምትሰራው አንተም በዚህ ነው መስራት ያለብህ› አሉኝ። እንግዲያውስ በዚህ እንዲሰራ ግድ የምትሉ ከሆነ እናንተ መጥታችሁ ስሩ እንጂ እኔ በዚህ አልሰራም፤ ትቼ ወጣለሁ ስል ጩኸት አመጡ። በዚያ ጊዜ የነበሩት የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ ጁነይዲ ሳዶ ነበሩ፤ እርሳቸው ደግሞ ይህ አሰራር በአየር መንገድ ውስጥ ካልገባ ሞቼ እገኛለሁ አሉ። እኔም እንግዲያውስ ማስገባት ከፈለክ እኔን አንስተህ ማስገባት ትችላለህ፤ እኔ ግን እያለሁ የተሻለ አሰራር ትቼ ወዳልተሻለ አሰራር አልሄድም። አገር ይህን መረጠች ብዬም የተሻለውን አልጥልም ብዬ በአቋሜ ፀናሁ። ‹እኔ ሚኒስትር ሆኜ እያለሁ እምቢ አለኝ› ሲል ለሁሉም ተናገረ። በኋላ ላይ በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹እስኪ ቆይ፤ ሌላው ዘንድ መስራቱ ይታወቅ፤ ተውት። የእነሱ መስሪያ ቤት በደንብ እየሰራ ነው።ስለዚህ የሚሰራውን ነገር ከማበላሸታችን በፊት ሌላው መስሪያ ቤት መስራቱን እናረጋግጥ፤እነርሱን ተዋቸው› አሉ። ሁሉም ሚኒስትሮች ተናደዱ።
አዲስ ዘመን፡- አየር መንገዱ ሲከተለው የነበረው አሰራር ምን የሚባል ነበር?
አቶ ግርማ፡- ኤ.ኤስ.ኤ (አቺቪንግ ሰርቪስ ኤክስለንስ) ይባላል።ይህም የተሻለ አሰራር ነው። በኋላ ላይ እነርሱን ተው ተባለ። ቢፒአርም በየመስሪያ ቤቱ ምን ያህል እንዳበጣበጠ ይታወቃል።እኛ ግን ባለመግባቱ ነፃነታችንን እንደያዝን ቀጠልን። በዚያ መልክም ሪፖርት አድርግ ሲሉኝ አምቢ አልኩ። በመሆኑም እንዲህ አይነትም ውጣ ውረድ አልፎ አልፎ አለ።
ሁለተኛው ተግዳሮት ደግሞ አንድ ጊዜ ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር የሚባል በየመስሪያ ቤቱ ይቋቋም ተባለ። ለእኔ እሱ አይነት አካሄድ ካድሬ ማለት ነው። ለእኔም ለአየር መንገዱ ሰው መደቡና ላኩልኝ። የተመደበው ሰውዬ መጣ፤ የተመደበበትን ደብዳቤውን ሰጠኝ። ደብዳቤውን ገልጬ ስመለከት ከዛሬ ጀምሮ ይህ ሰው የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ሆኗል ይላል። የኔ ወንድም አንተ ኢትዮጵያዊ ነህ፤ ስራም ፈላጊ ነህ። አንተ ጥሩ የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር መሆን የምትችል ከሆነ እኛ ቦታው ሲኖረን አመልክትና እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ማለፍ ስትችል ግባ። ዛሬ ግን እኔ አንተን በትዕዛዝ አልቀበልህም። የአየር መንገዱን መስፈርት አሟልተህ መግባት መብትህ ነው አልኩት። ‹እንዴ! እኔ እኮ የመጣሁት ተመድቤ ነውና እገባለሁ› አለኝ። አይ በምደባ አትገባም፤ ምንም ደግሞ ሊመድብህ አይችልም። ይልቁኑ እዚህ ለመግባት ፍላጎት ካለህ አመልክት፤ ከዛ በችሎታህ ትቀጠራለህ። ካልቻልክ ደግሞ አትችልም ትባላለህ አልኩት። ‹አንተ ከማን ትበልጣለህ? መንግስት ያደረገውን አንተ ማን ነህነና ነው አልቀበልም የምትለው› አለኝ። የእኔ ልጅ አንተ ስራ ፈላጊ ነህ፤ ስለዚህም አንተ እና እኔ ክፉ መነጋገር የሚያስፈልገን አይመስለኝም። አንተ ስራ ፈላጊ ነህ፤ እኔ ደግሞ ድርጅቱ በህጉ መሰረት እንዲሰራ ፈላጊ ነኝ። ሂድና ተመድበሃል ያሉህን ሰዎች ‹‹አልተቀበለኝም›› በልና ንገራቸው። እነሱ ቢፈልጉ እኔን አንስተው የእኔን ቦታ ለአንተ ይስጡህ እንጂ አንተ በትዕዛዝ አትገባም አልኩት። ሰውዬው ዛሬም ድረስ አለ። የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር በወቅቱ አቶ በረከት ነውና እርሱ ዘንድ ሄዶ ‹አላስገባም ብሎኛል› ሲለው አቶ በረከትም ልክ ተቀጣሪው ያለውን አይነት ቃል ‹አንተ ማነህና ነው የማትቀበለው› አለኝ። በረከት እኔ ግርማ ነኝ። ስለዚህም የአየር መንገዱን ህግ ነው የማስከብረው። በአየር መንገዱ ህግ ደግሞ መንግስት መሾም የሚችለው ስራ አስኪያጁን ብቻ ነው። ሌላውን ስራ አስኪያጁ ነው የሚሾመው። እሱም ቢሆን የራሱ የሆነ ቅደም ተከተላዊ አካሄድ አለው። በመሆኑም በዚህ መስሪያ ቤት ውስጥ ያለውን ህግ ሊጥስ የሚችል አሰራር አልፈቅድም። ሰውዬው ከፈለገ ይወዳደርና ይግባ። እኛ ደግሞ የምናምንበትና ይችላል የምንለው የራሳችን ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አለን። እናንተ አትመርጡልንም። ስለዚህ አልቀበልም ስለው አቶ በረከት ‹ኡኡ› አለ።
በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዩም ጠሩኝ። ‹እንደው እባክህ ምን አጨቃጨቀህ፤ ተወው› አሉኝ። እኔ ለእኔ ሳይሆን የአየር መንገዱን አሰራር ለመከተል ነው። ዛሬ ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ተቀበል ትሉኛላችሁ፤ ነገ ደግሞ ምክትል ዳይሬክተር ሹም ትሉኛላችሁ። ተነገወዲያ ደግሞ የእገሌን ልጅ አስገባ ልትሉ ትችላላችሁና ይህንን አካሄድ ልቀበለው አልችልም። ለዚህም አሰራር ደግሞ በር አልከፍትም። ነገሩ እንደገና ላይ ወጣና ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረሰ። እግዚአብሄር ይስጣቸው እርሳቸውን እኔ አላነጋገርኳቸውም።ነገር ግን በኋላ ላይ በረከትን ‹እረፍ› አሉት። የተከለከለው ሰው በኋላ ላይ በግድ ሲቪል አቬሽን እንዲገባ ተደረገ።ሲቪል አቬሽንን አንዴ አተራመሰው። እንዲያም ሆኖ አልፎ አልፎ እንዲህ እንዲህ አይነት ነገሮች ይከሰታሉ። እውነቱን ለመናገር እኔ በነበርኩበት ሰባቱን ዓመታት መንግስት ‹እከሌን ቅጠር፤ እከሌን ሹም› የሚል የጉልበት አሰራር አልቻለም። የሚሞክር ሰው ካለም በጀ እንደማልላቸው ያውቃሉና አርፈው ይቀመጡ ነበር።
አንዴ ደግሞ አስታውሳለሁ፤ ቴሌቶን በሚል መዋጮ አይነት የገንዘብ መሰብሰቢያ ዘዴ ነበር። እያንዳንዱ ድርጅት ገንዘብ አውጣ ይባል ነበር። ቴሌቶን በተዘጋጀ ጊዜ መሰሪያ ቤቶች ይደውሉና ይህን ያህል ሚሊዮን በማለት ሲናገሩ እኔ ግን አንድም ቀን ለአንድም ድርጀት ብር ሰጥቼ አላውቅም። ትግራይ፣ ኦሮሚያም ሆነ ሌላው በሚጠይቅበት ጊዜ መብራት ኃይል ቴሌ ሰጥቷል። ስለዚህ ምንድን ነው አየር መንገድ ብቻ የማይሰጠው? እርሱ ማነውና ነው? ሲሉ የማንን ገንዘብ ነው ለማን የምሰጠው፤ ሌላው ደግሞ ሐሳቡ ቦርድ ላይ ቀርቦ ሐሳቡ ተቀባይነት ሲኖረው ነው እንጂ እንዲያው ብድግ አድርጌ የምሰጠው የአባቴ ገንዘብ አይደለምና አልሰጥም። እላለሁ።አንዴ ትዝ ይለኛል፤ የቴሌቶን ዝግጅትን ሸራተን አዲስ ላይ አዘጋጅተው ‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ…› ሲሉ የመብራት ኃይል ኃላፊው ደወለልኝና አረ ባክህ አየር መንገድ እየተጠራ ነውና እንዲያው አንድ ሚሊዮን ብር እንኳ ቢሆን ደውልና ተናገር እንጂ ሲለኝ፣ እኔ አንድ ብርም ቢሆን አልሰጥም አልኩት። ምክንያቱም እኔ በዚህ ነገር አላምንበትም። እርዳታ መስጠትም ካስፈለገ ፕሮጀክት ተቀርፆ አዋጭነቱ ታይቶ ነው መሰጠት ያለበት እንጂ የኢትዮጵያን ገንዘብ ለፖለቲካ ፓርቲ አልሰጥም። በመስሪያ ቤቱም ቢሆን የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያሰሙ አልፈቅድም ነበር። የትኛውም ግለሰብ በፓርቲ ውስጥ መደራጀት መብቱ ነው። ነገር ግን የፓርቲውን ስራ አየር መንገድ ይዞ መምጣት የለበትም። ይህ አይነቱ አሰራር ለሁሉም መስሪያ ቤት ነው እንዲሰራ የምፈልገው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ልምድ ከየት የመጣ ነው? በትምህርት የተገኘ ወይስ በስራ?
አቶ ግርማ፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከወጣሁ በኋላ በርካታ የማናጅመንት ኮርሶችን ወስጃለሁ። ሌላው ደግሞ አሜሪካ ማናጅመንት አሶሴሽንም ሄጄ ስልጠና ወስጃለሁ። አውሮፓም ሆነ እንዲሁ ሌሎች ዘንድ በመሄድ ስልጠናዎችን ወስጃለሁ። የመጨረሻውን ማናጅመንት ስልጠና የወሰድኩት በካናዳ ነው። ለእኔ ግን ከሁሉ በላይ ያስተማረኝ የተለያየ ባህል ባላቸው የተለያዩ አገራት ውስጥ መስራቴ ነው። በአፍሪካ ውስጥ ጋና እና ታንዛኒያ እንዲሁም ናይጀሪያ ሰርቻለሁ።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቅቄ የብዙ አገር አየር መንገድ በሆነው በገልፍ አየር መንገድም መስራቴ ጠቅሞኛል። የፕራይቬት የሆነ ድርጅት በዲኤችኤልም ውስጥ ሰርቼ ምን አይነት ድፍረት እንዳላቸውና የአስተዳደር ክህሎታቸውን አስተውያለሁ። ከስራዎቼ በተጨማሪ ደግሞ ከማነባቸው መፅሐፎችም እንዲሁ ልምድ አካብቻለሁ ብዬ አስባለሁ። በህይወቴ አጥብቄ የምከተለው መመሪያ በአንተ ሊደረግብህ የማትፈልገውን በሌላው ላይ አታድርግ የሚል ነው። በዚህ መመሪያ እገዛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግስት ባለስልጣናት ከአንድ ቦታ ወደሌላው ቦታ በአውሮፕላን ሲንቀሳቀሱ ይከፍላሉ?
አቶ ግርማ፡- አዎ! በሚገባ። እንዲያውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው። ጃንሆይ ሆኑ መንግስቱ ኃይለማርያም እንዲሁም የኢህአዴግ ባስልጣናቱ በሙሉ ከፍለው ነው። ደርግ ያንን ያህል ጦርነት በሚያካሂድበት ጊዜ አውሮፕላን ሲወስድ ይከፍል ነበር። ስለዚህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለክፍያ አያስተናግድም፤ ህጉም አይፈቅድለትም። ግን ህጉን ማሻር ይችሉ ነበር፤ የሌሎች እንደተሻረው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስታር አሊያስ አባል መሆኑ ጥቅሙ ምንድን ነው? እንደ ስታር አሊያንስ አይነቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ያህል ናቸው ያሉት?
አቶ ግርማ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ አራት አሊያንሶች አሉ። ትልቁ ስታር አሊያንስ ሲሆን፣ከዚያ ቀጥሎ ዋንዎርልድ የሚባው ነው። ስታር አሊያንስ ማለት እነ ሉፍታንዛ፣ ሲንጋፖር አየር መንገድ፣ ዩናይትድ አየር መንገድ፣ የቻይና ዋናው አየር መንገድ፣ ብራስልስ ያሉበት የአየር መንዶች ማህበር ነው። ከአፍሪካ ውስጥ ያሉበት ግብፅና ደቡብ አፍሪካ ናቸው። እነሱ ከእኛ በፊት ነበሩ፤እኛ እንዳንገባ እነሱ ከተቃወሙ መግባት አንችልም።
እኔ በመጀመሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲቀላቀል የፈለኩት በዋንዎርልድ ነበር። ምክንያቱም የሚመራው የብሪታኒያ አየር መንገድ ነው። የምርጫዬም ምክንያት አንደኛ እንግሊዝኛ ተናጋሪ አየር መንገድ መሆኑ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከእንግሊዝ አየር መንገድ ጋር በርካታ ስራ ስለምንሰራ ነበር።ስለዚህም የብሪታኒያ አየር መንገድ ስራ አስኪያጁን ዋንዎርልድ ለመግባት እንፈልጋለን ብዬ ሐሳብ ሳቀርብ ቅድመ ሁኔታ እንዳለ ጠየቁኝ። እሱም አሜሪካና ካናዳ የሚባል አገር በፍፁም አትገቡም፤ለእኛ አየር መንገድ አስረክባችሁ ትሄዳላችሁ የሚል ነበር፤ በወቅቱ ደግሞ ዋሽንግተን መብረር ጀምረን ነበርና እሷኑ አቋርጡ አሉ። እንደማንኛውም አየር መንገድ መብረር መብታችን ነው በማለት አልቀበልም አልኩት። አትገባም አለኝ። ተውኩት።
የሉፍታንዛው ስራ አስኪያጅ ኃላፊነቱን ከመረከቡ በፊት እኔ ጀርመን በነበርኩበት ወቅት ወዳጄ ነበር።አገኘሁትና ስታር አሊያንስ መግባት እንፈልጋለን ግን ከአፍሪካ ሁለት አገር አላችሁና እንዴት ነው ብዬ ጠየቅኩት። እሱም እናንተ ለስታር አሊያስ የምታመጡት የተሻለ ነገር ምንድን ነው ሲል ጠየቀኝ፤ ግብፅ ላይኛው አካባቢ፣ ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ታች ነውና አንድ መንገደኛ ከመሃል አካባቢ ናይሮቢ መሄድ ቢፈልግ ታች ወርዶ ወደላይ ሊመለስ ግድ ይለዋልና በሜዳ ላይ የቀረው መሃሉ አፍሪካን ማገናኘት የሚችለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብቻ ነው።ስለዚህ መሃሉን እንይዝላችኋለን ባልኩት ጊዜ ሐሳቡ መልካም እንደሆነ ነገረኝና ሁለቱ አገሮች ከተቃወሙን በህጋችን መሰረት ልንቀበላችሁ አንችልምና እነሱን አሳምን አለኝ። ይሁንና የሁለቱን አገር የአየር መንገድ ስራ አስኪያጆችን ስጠይቃቸው የደቡብ አፍሪካዋ ሴት ናት፤ስጠይቃት ‹እናተን እንድንቃወም በመንግስታችን ተነግሮናልና አትገቡም‹ አለች። ይሁንና በብዙ ማግባባት አለሳልሼ ወደ ግብፅ ደግሞ ሳቀና እንዲሁም ለእኛ መልካም ነገር የላቸውምና እምቢ አሉኝ። ግን በሌላ ጊዜ ነገሮች ተስተካክለው ለማግባባት ደግሜ ሞከርኩ፤ የሉፍታንዛውም ጫና በመፍጠሩ በመጨረሻም አቶ ተወልደን ለጉዳዩ ግብፅ ልኬ 40 ዓመት ከበረርንበት ከግብፅ አየር መንገድ ለቃችሁ ስትቀጡ ነው የምንቀበላችሁ የሚል ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጣቸው በዚሁ ተስማምቶ የስታር አሊያንስ አባል ለመሆን በቃን። ዛሬ በአፍሪካ ውስጥ ከሁሉም የበለጠ አየር መንገድ የኢትዮጵያ ነው። መቀላቀላችን አሰራራችንን የዘመነ እንዲሆን ያስችለዋል።ጥቅሙ በርካታ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ባወጣው እቅድ ለግል ከሚሸጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ አየር መንገድ ነበርና የእርስዎ ሐሳብ እዚህ ላይ ምንድን ነው?
አቶ ግርማ፡- የሚጠቅመው መሆኑን እስካመነበት ድረስ መንግስት የፈለገውን የማድረግ መብት አለው። ነገር ግን እንደ ድርጅትና እንደ አገር በሚታይበት ጊዜ ምናልባት መንግስት የሚሸጥበት ምክንያት የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ከሆነ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ተነጋግሮ እንዲያመጣ ማድረግ ይችላል። እኔ እንደሚመስለኝ በደንብ ቢታይ መልካም ነው። አየር መንገዱ ከመንግስት ገንዘብ ሳይጠይቅ በደንብ እየሰራ እያለ ለምንድን ነው ለመሸጥ የሚቸኮለው። መሸጥስ ከታሰበ መንግስት ከአየር መንገዱ የሚያገኛቸው ጥቅሞች ይቀራሉ ወይስ ይቀጥላሉ የሚለው ሁሉ ቢታይ ይሻላል፤ ባንቸኩልም መልካም ነው። እንዲያውም አየር መንገዱ ከዚህም በላይ ብዙ ነገር ማድረግ የሚችል ነውና መተው ነው የሚሻለው።አየር መንገዱ በ2025 ያወጣውን እቅድ ከአራት ዓመት በፊት አስቀድሞ ይጨርሳል። ከታሰበው በላይ እየሄደ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአሁኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈፃሚ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬታቸውን በተቀበሉበት ወቅት የእርስዎን ስም በመልካም ሲያነሱ ነበርና ቀረቤታችሁ ምን ያህል ነው? ድጋፍዎትን ፈልገው ድውለው ያውቁ ይሆን?
አቶ ግርማ፡- ተወልደ ገና በአየር መንገዱ ሲቀጠር ጀምሮ አውቀዋለሁ። ቀጥሎም በአሜሪካ አገር የአየር መንገዱ የሽያጭ ኃላፊ ነበር። አሰራሩን ሳይ ከአሜሪካ አመጣሁትና የንግድ ክፍል ኃላፊ አደረኩት። ከእኔ ጋር ብዙ በመስራቱ ጥንካሬውን ማስተዋል ችያለሁ፡ወደፊት መግፋት የሚችል እንደሆነ ተረድቻለሁ። ቺፍ ኦፐሬቲን ኦፊሰር አድርጌ ወደላይ አመጣሁት። በጣም በርካታ ስራዎችን ሲሰራ የተሻለ ነገር እንዳለው በማስተዋሌ እኔ አየር መንገዱን ለመልቀቅ ስወስን በስራው ጠንካራ ነውና ለቦርዱ ይህ ልጅ ቢተካኝ ይሻላል ብዬ ነው ሐሳብ የሰጠሁት። ቦርዱም ይህንን ነው ያደረገው።የስራ አስፈፃሚነቱን ቦታ የሰጠው ደግሞ የራሱ ጥንካሬ ነወ። ምናልባት የድፍረቷን ነገር ከእኔ አይቶ ሊሆን ይችላል፤ ግን በጥቅሉ የራሱ የሆነ ጥሩ ጥንካሬ ያለው ልጅ ነው። ከወጣሁ በኋላ በተለያዩ ጊዜያ ተቀምጠን እንነጋገራለን።
አዲስ ዘመን፡- ለአየር መንገዱ ቢሟላ መልካም ነው የሚሉት ነገር ይኖር ይሆን?
አቶ ግርማ፡- ትንሽ የፖለቲካ ሁኔታ የገባበት ነገር አለ፤እንደሚመስለኝ እሱ አይጠቅምም። እንደ እሱ አይነት ወደአየር መንገዱ በሚገባበት ጊዜ ሰራተኛውንም በመንፈስ ያለያያል።ይህን ማናጅመንቱም ሆነ ቦርዱም እየተነጋገሩ ይፈቱታል ብዬ አምናለሁ። ከዚህ ውጪ አካሄዱ መልካም ነውና በያዘው መንገድ መቀጠል አለበት ብዬ አምናለሁ።
ለመንግስት ያለኝ አስተያየት ለአንድ መስሪያ ቤት አንድ ሰው በሚሾሙበት ጊዜ የሚሾመው ሰው የዚያ መስሪያ ቤት ባህል ያውቀዋል ወይ?ለስራውስ ብቁ ነው ወይ ተብሎ ነው መታሰብ ያለበት እንጂ በዘር፣ በፖለቲካና በኃይማኖት መሆን የለበትም። ብቁ የሆነ ሰው ከተሾመ ስራውን ለሰውየው መተው ይገባል። መንግስት ጣልቃ መግባት አስፈላጊ አይደለም። መንግስት ከድርጅቶች እጁን ካስወጣ በርካታ ድርጅቶች እንደ ልብ ማደግ ይችላሉ። አየር መንገዱ የተለየ ተቋም ሆኖ አይደለም ውጤታማ የሆነው።ተቋሙ ያገኘውን ነፃነት ሌሎችም ድርጅቶች ማግኘት አለባቸው። ተቋማትን ማጠናከር ላይ መንግስት ጠንክሮ መስራት አለበት። ዛሬ ተቋማት እየተዳከሙ ነውና ይህ መቀየር አለበት።ግለሰብ ሲሄድ የሚሄድ ነው፤ ተቋማት ሲጠነክሩ ነው አገር የሚጠነክረው። ኢኒስትቲዩት የሚጠነክረው ደግሞ ትክክለኛ አሰራር ሲዘረጋ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
አቶ ግርማ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ 13/2011
አስቴር ኤልያስ