ዘመናዊ ቴአትር ከደራሲ ምናብ መንጭቶ፣ በተውኔት መልክ ተጽፎ በአዘጋጁ እና በተዋናዮች፣ “ዲዛይነሮች”፣ የድምጽና የመብራት ባለሙያዎች ተሳትፎ ለተመልካች የሚቀርብ የቡድን ስራ ውጤት ነው። የራሱም የሆነ የሰዓት ገደብ፣ ቅርጽ እና መልዕክቶች (ነጠላ ወይም ብዙ) አሉት። የተውኔት አላባዎችን መሰረት ተደርጎም ይጻፋል። ለምሳሌ ገቢር እና የትዕይንት አከፋፈል ግልጽ እና ምክንያታዊ እንዲሁም መቼት፣ ገፀ ባህሪያት፣ የተስተካከለ እና የተዋቀረ ሴራ፣ ቃለ ተውኔት ፣ጭብጥ ፣ የመድረክ እንቅስቃሴ መግለጫ አለው። ይህም የተውኔቱን መቼት፣ አልባሳት ፣ቁሳቁሶች የድምጽና የመብራት ግብአቶችን በአግባቡ ለመጠቀም ይረዳል።
እንደ ዘርፉ ባለሙያዎች ገለጻ፤ ዘመናዊ ተውኔት የራሱ የሆነ እውቂያ፣ ጡዘት እና ልቀት ይኖረዋል። ተውኔታዊ ልማዶችንም ይጠቀማል። የራሱ የሆነ ዘውግ ፣ የአጻጻፍ ስልትም አለው። ታዲያ እኛም ከዚህ ቀደም ተሰርተው ማህበረሰብ ላይ ለውጥ ያመጡ ቴአትሮችን ለዚሁ ዘመን በሚመጥን መልኩ እንዴት እየተሰሩ መሆኑን እናስቃኛችኋለን። ለመሆኑ እነዚህ ቴአትሮች የትኞቹ ናቸው? ጥቂቶቹን እንበላችሁ። ነቃሽ፣ ከመጋረጃው ጀርባ፣ ባቢሎን በሳሎን… በዋናነት ይነሳሉ።
ለዛሬ በድጋሚ ወደ መድረክ ከመጡ እና ወቅቱን ያገናዘበ ነው ከተባሉ ቴአትሮች መካከል “ከመጋረጃው ጀርባ”ን መረጠን። ህብረተሰብን ለማረቅ እና ለማስተማር ቴአትሩ በተለያዩ ክልሎች ጉዞ ማድረግ መጀመሩ ይታወቃል። እናም ከቴአትሩ ተዋናይ ከሆነው አርቲስት ይገረም ደጀኔ ጋር ስለቴአትሩ የጉዞ ዓላማ ጭብጥ እና ከቴያትር ጋር የተያያዙ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ አጭር ቆይታ አደረግን።
አርቲስት ይገረም “ከመጋረጃው ጀርባ” ቴአትር ዳግም ወደ መድረክ የተመለሰበት ምክንያት ሲያስረዳ ቴአትሩ ዘመን መሻገር የሚችል መካሪ፣ አራቂ እና ሰላም ሰባኪ ስለሆነ ወቅቱን ለመዋጀት የሚችል አቅም እንዳለው ስለታመነበት ነው ይላል።
እንደ አርቲስት ይገረም ገለጻ፤ አሁን ያለው የተዘበራረቀው ነገር፣ የሰላም እጦት፣ አለመተማመን …ብዙ ልናነሳቸው የማንችላቸውን ጉዳዮች በአጭሩ መድረክ ላይ አምጥቶ የሆነውን ከእነ ችግሩ እያሳየ መሆን ያለበትን የሚጠቁምና ወቅቱን ያገናዘበ መድሐኒት የሆነ ቴአትር ነው። በተጨማሪም ይላል አርቲስቱ፤ በተጨማሪም ስለሰላም ብዙ ማለት ይቻላል። ብዙም ተብሏል፤ ተዘምሯልም።
ሰላም በገንዘብ የማይተመን ዋጋ እንዳላት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተከሰቱ ግጭቶችና መዘዛቸው ዋነኛ ማሳያ ናቸው። ሰላም የጎደለው ቤት እንደ ዝናብ ከሚወርድ ጥይት እንደማያድን ከሶሪያ ዜጎች መማር ይቻላል። ልሂቃኖችን የሚያፈሩ ትምህርት ቤቶች ሰላም ከሌለ መጠለያ ናቸው። ሰላም በሌለበት አገር ሕፃናት ገና ድክድክ ማለት ሲጀምሩ ከተኩስና ፈንጂ ለማምለጥ እግሬ አውጪኝን ይማራሉ። አገራቸው ወደ ጦር ዓውድማነት የተለወጠባቸው፣ ቤታቸው ከፈንጅ የሚያድናቸው ጉድጓድ ምሽግ ይሆናል። ሰላም ባጣ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በአገራቸው ስደተኞች፣ በቤታቸው እንግዶች ናቸው። ቀን ከሌት ሳይሉ እግር ወደ ጠራቸው የሚነጉዱ መንገደኞችም ናቸው።
በአሁኗ ቅፅበት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጦርነት ሸሽተው ወደ ጎረቤት አገሮች እየገቡ ነው። በርካቶችም ሕይወታቸውን እያጡ እና ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ ነው። በመካከለኛው ምሥራቅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የየመንና ሶሪያ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ዕድለኛ የሆኑት በየአገሩ የስደተኛ ጣቢያዎችን የሙጥኝ ብለዋል። ያላደላቸው በመንገድ ላይ በረሃ በልቷቸዋል፣ ባህር ውስጥ ሰጥመው የአሳ ነባሪ ሲሳይ ሆነዋል። እናም እዚህ ደረጃ ሳንደርስ መወቃቀስ ፣ መመካከር አለብን። ከዚያም ፊታችንን ወደ ሰላም እና ልማት ማዞር ይገባናል።
ጉዞ ማድረጉ ደግሞ ለተመልካች ብቻ ሳይሆን ለእኛ ለተዋንያን መልካም አጋጣሚ ነው የሚለው አርቲስቱ፤ ቴአትር ቀድሞ በነበረው ጊዜ የአዲስ አበባውን ስራ እንደጨረሰ በአጭር ጊዜ በየክልል ይጓዝ ነበር። አሁን ግን በተለያዩ ምክንያቶች ይህ የለም። ሙያተኛውም ቢሆን በየክልሉ ያሉትን አድናቂዎች ፊት ለፊት የማግኘት ዕድሉ ጠባብ ነው፤ ይህ ጅማሮ ግን ለሁላችንም ተዋንያን አድናቂዎቻችንን የምናገኝበት ዕድል ሆኖልናል።
የተውኔቱ ወደ መድረክ የመምጣቱን ጥቅም አርቲስቱ ሲያብራራ “አሁንም አዳዲስ ተውኔቶች ይወጣሉ፤ ነገር ግን የድሮዎቹም በድጋሚ መሰራታቸው ያላየው ትውልድ እንዲመለከተው ዕድል የሚሰጥ ነው”፤ አዳዲስ ተውኔቶች ቢፃፉና ለዕይታ ቢበቁ ምርጫው እንደሆነ ይናገራል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ተውኔቶች ለዓመታት መድረክ ተፈናጠው የሚቆዩበትን ምክንያቶች የተውኔት ፅሁፍ አለማግኘት፣ ደራሲዎች ከሚያገኙት ክፍያ ጋር በተያያዘ ከተውኔት ይልቅ ፊልምን መምረጣቸውና ከተውኔት መሸሻቸውን ከብዙ በጥቂቱ ይዘረዝራል።
የተውኔት ዘርፉ ከድርሰት ጋር በተያያዘ ካለበት ፈተና በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶችን እንደሚያስተናግድም ተደጋግሞ ይነሳል። “አበረታች አይደለም፤ ለባለሙያዎች ጥሩ ክፍያ መክፈል አልተቻለም፤ ቢሮክራሲው፣ የትኬት ቀረጥ፣ የመግቢያ ዋጋ አነስተኛ መሆኑ ኢንዱስትሪውን ቁልቁል እንዲሄድ አድርጎታል” ሲል ያስረዳል። በተለይ በግል ተውኔትን ለሚያቀርቡት ፈተናው ያይላል ባይ ነው።
“ፊልሞች በተውኔት ላይ ተፅዕኖ አሳድረው ነበር፤ አሁን ግን እየተመለሰ ነው” የሚለው አርቲስቱ፤ ለዚህም የቀደመው ትውልድ የሚያስታውሰውን መድገሙ አስተዋፅኦ ሳይኖረው እንዳልቀረ ይናገራል። በመሆኑም የቀደሙት ተውኔቶች ድጋሚ መቅረባቸው ሊበረታታ እንደሚገባ ያስረዳል።
ቴአትርን ይዞ መጓዝ ትልቁ ችግር በጀት ነው። ልክ እንደ ፊልም አንድ ሲዲ ተይዞ አይደለም የሚኬደው፤ ከተዋንያን ብዛት ያልተናነሰ ከመድረክ ጀርባ የሚሰሩ ባለሙያዎች አሉ። ይህንን ሁሉ ይዞ ለመሄድ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። ይህንን ልክ “ከመጋረጃው ጀርባን” ቴአትርን ይዘን እንድንሄድ እንደደገፈን እንደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ሁሉም የዘርፉ ደጋፊ እንዲህ ቢያደርግ እንዲህ ያሉ አገርን ከመበታተን የሚያድኑ ሰላምና ፍቅርን የሚሰብኩ ተውኔቶችን ይዞ ለመሄድ ያስችለናል ብሏል።
‹‹ጥበብ በአገር ግንባታ ላይ የጎላ አስተዋጽኦ አላት፤›› ያለው አርቲስት ይገረም ደጀኔ፤ በኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ የጥበብ ሥራዎችን ለሰላም መጠቀም ብዙ አልተለመደም። ስለሆነም በቀጣይ በአገሪቱ ያለውን የሰላም ሁኔታ ለማሻሻል ከኪነጥበብ ባለሙያ ጋር መስራት አንዱ መንገድ ሊሆን እንደሚገባ ይገልጻል። ‹‹አገር በችግር ውስጥ ስትወድቅ ሕዝቦቿ ብርቱ እንዲሆኑና እጃቸውን እንዳይሰጡ ጥበብ ከፍተኛ ሚና አላትና የኪነጥበብ ባለሙያውም የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት በጋራ አብሮ መስራት ይኖርበታል።» ብሏል።
“ከመጋረጃው ጀርባ” ምን አለ? ምንስ እያከናወነ ነው? እሁድ በ8:00 ሠዓት በሀገር ፍቅር ቴአትር መጋረጃው ሲገለጥ ከታደሙ ብዙ ሳቅና ሀገራዊ ቁም-ነገር ይገበያሉ። ከመጋረጃ ጀርባ በምርጥ ቴክኒክ የተቀመረ ድርሰት የተዋጣለት ዝግጅት ከፍ ባለ የትወና ብቃት የቀረበ ስሜታችሁ እና ሀሳብ የሚነካ ቴአትር ነው። እናም ይህን ቴአትር ጋበዝን። መልካም ሰንበት!
አዲስ ዘመን ሀምሌ 7/2011
አብርሃም ተወልደ