እንቅልፍ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት በቀን ቢያንስ የ7 ሰአት እንቅልፍ ማግኘት አለብን። የአንድ ቀን እንቅልፍ መዛባት እንኳ ንጭንጭ እና ስንፍናን ያመጣል። በአግባቡ ስራ ለመስራት፣ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግም ሆነ ጤነኛ ምግቦችን ለመብላት እንሰንፋለን።
እንቅልፍ እጦት ለረጅም ግዜ ከተደጋገመ ለዘላቂ ጤና ችግሮች ያጋልጠናል። የሰውነት ክብደት መጨመር፣ የስኳር በሽታ፣ ከፍተኛ ደም ግፊት እና የልብ በሽታ በተደጋጋሚ እንቅልፍ እጦት ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ ህመሞች ናቸው። በቂ እንቅልፍ አለማግኘት ለአእምሮ ጤናም አደገኛ ነው። ድብርት እና ጭንቀትን ያስከትላል። አዲስ ጥናቶች እንደሚናገሩትም ከሆነ እንቅልፍ እጦት ለብርድ ይበልጥ ተጋላጭ ያደርገናል
የተለመደ ባይሆንም እንቅልፍ እጦት አደጋ ውስጥ ሊከተን ይችላል። እንቅልፍ ያጣ ሰው በቀን ከፍተኛ የድካም ስሜት ከመሰማቱም በላይ ለማይክሮ እንቅልፍ (microsleeps) ሊዳረግ ይችላል። ማይክሮ እንቅልፍ ማለት በቀን የሚከሰት ለተወሰኑ ሰኮንዶች ብቻ የሚዘልቅ እንቅልፍ ነው። ሌክቸር ወይም ስብሰባ ላይ ተቀምጠው ለተወሰኑ ሴኮንዶች እንቅልፍ ወሰድ ሲያደርግዎ ማይክሮ እንቅልፍ ላይ ነዎት ይባላል። በዛ ቢባል ከ10-15 ሴኮንዶች የሚዘልቅ እንቅልፍ ሲሆን መኪና ለሚያሽከረክሩ ሰዎች አደገኛ ሁኔታ ይፈጥራል።
በማይክሮ እንቅልፍ ወቅት አእምሮ ከውጪ የሚመጣን ድምጽም ሆነ ሌላ ስሜት አያስተናግድም። በአካባቢዎ ለሚፈጠር ነገር ድንዝዝ ነዎት። ማይክሮ እንቅልፍ ሲጀምር አጢኖ ማስቆም ስለሚከብድ በእንቅልፍ ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶች እየጨመሩ መተዋል።
ታዲያ የእንቅልፍ እጦትን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ከሁሉም የተሻለው መንገድ ምን ያህል እንቅልፍ እንደሚያስፈልገን አውቀን ሳንቀያይር
በየቀኑ ለዛ ሰአት ያክል መተኛት ነው። ቅዳሜ እና እሁድም ሆነ በአመት በአል ግዜ ለተመሳሳይ ሰአት መተኛት ተገቢ ነው። ለእንቅልፍ የሚረዱ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦችም ማከናወን ጥሩ ነው። አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እና ቡናን አለማዘውተር ሌላ ልናደርጋቸው የምንችላቸው መፍትሄዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011