ኢትዮጵያ ውስጥ በየአካባቢው እንደሚ ነገረው ቋንቋ የየግል መጠሪያ ቢኖረውም በአብዛኛው ግን እሬት በሚለው ስሙ ይታወቃል። ብዙዎችም ዛሬም ቢሆን ለጡት ማስጣያነት ይጠቀሙበታል። ለመብቀል ብዙ ክብካቤና ውሃ አይፈልግም፤ በውስጡ ግን በርከት ያለ ውሃ የማጠራቀም ባህሪ አለው።
ከእሬት ዘሮች በተለይ በእንግሊዝኛው ‹አሎይ ቬራ› በመባል የሚታወቀው ተክል ለተለያዩ የመዋቢያ ቅባቶችና ሳሙናዎች መሥሪያነት በመዋሉ በሰፊው ይታወቃል። በሌላ በኩል በምግብነቱ ደግሞ ለጤና በሚሰጠው ጥቅም ተዓምረኛው ተክል፤ ማለትም ‹ዎንደር ፕላንት› የሚል ቅፅል አትርፏል። እሬት በምሬቱ ነው የሚታወቀው፤ ለዚህም ነው እናቶች ጡት አልተው ያሉ ልጆችን ወደዚያ እንዳይመለሱ ለማድረግ የእዚህን ተክል ፈሳሽ ጡታቸው ላይ በመቀባት እንዲመራቸው የሚያደርጉት። ምሬቱን በዘዴ አለዝበው የሚመገቡት ደግሞ አሉ። ታዲያ ሁሉም የእሬት ዘር ወደአፍ አይገባም ለህይወት አደገኛ የሆነ ዓይነት አለውና።
የእሬት ተክል ለመብቀል ምቹ አካባቢን አይፈልግም። በብዛት የውሃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች እንደመገኘቱ ደረቅ ሳይሆን በውስጡ ከፍተኛ ውሃ ማጠራቀም ይችላል። ‹አሎይ ቬራ› በመባል ከሚታወቀው ተክል የሚገኘው ዝልግልግ ፈሳሽም የቆዳን ድርቀት አስወግዶ በማውዛት፣ ያረጀውን የማደስ አቅም እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። ከ‹አሎይ ቬራ› የተዘጋጁ የፀጉር ሻምፑዎች፣ የእጅ፣ የፊትና የገላ ክሬሞች፣ የጸጉር ቅባቶችም በየገበያው ይገኛሉ። ከዚሁ ተክል የተዘጋጁ ጭማቂዎችም እንዲሁ፤ ምሬቱን በስልት እየቀነሱም የሚበሉትም አሉ።
ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙበት ደግሞ አረቦች ሲሆኑ እንደመድሃኒት እንደተጠቀሙበትም አክለው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለዚሁ አገልግሎት የሚውለው የእሬት ዘር በተለይ ኅብረተሰቡ ሴት እሬት የሚለውና እሾህ የሌለው የተክል አይነት እንደ ሆነም ይገለፃል። ከእሬት ዘሮች ‹አሎይ ቬራ› የተባለው በመጀመሪያ ከየት እንደተገኘ እጅግም እንደማይታወቅ ነው የዕፅዋት ሳይንስ ተመራማሪ ዎች ያመለክታሉ። የታሪ ክም ሆነ የእጽዋት ሳይንስ ተመራማሪዎች በጋራ የሚ ስማ ሙበትን ግን ምናልባት ከደቡብ ምዕራብ የአረብ አካባቢዎች (በተለይም ሳውዲ አረቢያና የመን ውስጥ) የተገኘ እንደሆነ ነው።። በአሁኑ ጊዜም ከእሱ የሚገኘውን ጥቅም በሚገባ ለማግኘት ሲባል በተፈጥሮ የሚገኝበት ሳይሆን በማሳደጊያ የአትክልት ስፍራ ክብካቤ እና ማሻሻያ እየተደረገለትም ውስጡ የሚይዘው ፈሳሽ መጠን እንዲጨምር፤ እንደፍላጎቱ መጠን ደግሞ ምሬቱም እንዲቀንስ ተደርጎ ሊያድግ ይችላል።
ምንጭ፡-D.W
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011