በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልላዊ መንግስት ሳውላ ዞን በቡልቂ በሚባል አካባቢ ከዛሬ 70 ዓመት በፊት ተወለዱ። እስከ ስምንተኛ ክፍል እዛው ሳውላ ከተማ የተማሩ ሲሆን ስምንተኛ ክፍል ከጨረሱ በኋላ ግን ወደ ንግድ ስራ ትምህርት ቤት መጥተው በፅህፈት ስራ አራት አመት ሰለጠኑ። ትምህርት ቤቱ እዛው እንዲሰሩ በአስተማሪነት ስለቀጠራቸው አራት አመት አገልግለዋል። በቆይታቸውም ትምህርት ቤቱ በገባላቸው ቃል መሰረት ወደ ህንድ አገር ለመሄድ የትምህርት እድል በመጠባበቅ ላይ ሳሉ ወደ አሜሪካ የመሄድ እድሉን ያገኛሉ። በዳላስ አካባቢ በአንድ የንግድ ኮሌጅ ውስጥ በንግድ ስራ አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል። ከዚያ በኋላም ለ22 ዓመት በአሜሪካ አገር በስራ፥ በትዳር፥ ልጅ ወልደው ኖረዋል።
ይሁንና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵውያን ወደ አገራቸው መጥተው እንዲሰሩ ባቀረቡት ጥሪ ያለምንም ማቅማማት ይቀበላሉ። ወደ አገራቸው ተመልሰው ለመስራት ጉጉት ያድርባቸውና ስራቸውንና የሞቀ ትዳራቸውን እዛው አሜሪካ ጥለው እትብታቸው ወደ ተቀበረባት እናት አገራቸው ተመለሱ። ዳሩ ግን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ፤እርሳቸውም እንደጠበቁት ለመስራት የሚያስችል የፖለቲካ ምህዳር ሆኖ አላገኙትም። ይልቁንም እርሳቸው በአገራቸው ውስጥ በነበሩበት ወቅት ያልነበረ የገዢና የተገዢ የመደብና የብሄር ልዩነት ሰፍኖ ህዝቡም በዚያ የጭቆና ቀንበር ውስጥ እየኖረ መሆኑን ያስተውላሉ። ይህ ሁኔታም አገራቸውን ጥለው ከመሄድ ይልቅ እዚሁ ሆነው ህዝብን ከጭቆና ቀንበር ለማላቀቅ ይወስናሉ። በዚያ መሰረትም በ1997ዓ.ም ቅንጅት ውስጥ ገብተው በመወዳደር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ለአምስት አመት አገልግለዋል።
በምክር ቤት በነበራቸው ቆይታም በርካታ ህዝብ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለሰን በድፍረት በመሞገትና በመከራከር ያውቃቸዋል። ለአገራቸው ባላቸው ልዩ ፍቅር የተነሳ አሜሪካዊቷን ሚስታቸውንና ልጃቸውን ትተው ቢመጡም ከሁለተኛዋ ኢትዮጵያዊት ሚስታቸው ሁለት ልጆች ወልደው ከብረዋል። በአሁኑ ወቅትም የአሜሪካ መንግስት ላገለገሉበት ጡረታ ይከፍላቸዋል። በተለየየ ምክንያት ወደ አሜሪካ ሄድ መጣ ቢሉም የተወለዱባትን እናት አጋራቸው ከነጭራሹ ጥለው ለመሄድ አልወደዱም። ከዛሬው የዘመን እንግዳችን አቶ ተመስገን ዘውዴ ጋር በተለየዩ አገራዊ፥ ፖለቲካዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ከውጭ አገር ጓዞትን ጠቅልለው ከመጡበት አገርን የማገልገል እሳቤ አኳያ አገሬን አገልግያለሁ ብለው ያምናሉ?
አቶ በተመስገን፡- እኔ ምንም እንኳን 22 አመት አሜሪካ ብኖርም ልቤ ሁልጊዜም የነበረው ከአገሬና ከአገሬ ህዝብ ጋር ነበር። ዜግነቴንም ቢሆን አልቀየርኩም። አሁንም ትናንትም ኢትዮጵያዊ ነኝ። እናም እነ አቶ መለስ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ለጎሳ ልዩነት ለተሰጠው ክብደት አግባብ ወደአልሆነ ሁኔታ ሊወስደን ይችላል በሚል ስጋት ስለነበረኝ የራሴን አስተዋፅኦ ለማበርከት ወደ ፓርላማ በመግባት ለአምስት ዓመታት አገልግያለሁ። በዚህም ወቅት የሚገባኝን ያህል አስተዋጽኦ አበርክቻለሁ ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ኢዴፓን የተቀላቀሉበትን አጋጣሚ ያስታውሱን?
አቶ ተመስገን፡- እኔ በመጀመሪያ በግሌ ነበር የተወዳደርኩት፤ በግሌ ተወዳድሬ ህጉ የሚፈቅደውን ፊርማ ካስፈረምኩና ህጋዊ መስፈርቶችን በሙሉ ካሟላሁ በኋላ የኢዴፓ ሊቀመንበር የነበረው አቶ ልደቱ አያሌው ስልክ ደውሎልኝ ሊያነጋግረኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ። ተገናኝተን የፖለቲካ ፕሮግራሞቻችን ላይ ተወያየን። በዚያ ወቅት በአጋጣሚ እኔ የማስበውና የእነሱ ፕሮግራም ተመሳሳይ ስለነበር ከእኛ ጋር ብትሰራ የበለጠ ጥቅም ሊኖረው ይችላል ስላሉኝ እኔም ስላመንኩበት በመጀመሪያ ኢዴፓን ነው የተቀላቀልኩት። በዚያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እያለን ኢዴፓ ደግሞ ቅንጅትን ተቀላቀለ። ስለዚህ በምርጫው ወቅት ተወዳድሬ ፓርላማ የገባሁት ቅንጅትን ወክዬ ነው። በወቅቱ ከኢዴፓ ስለመጣችሁ ቅንጅት አይደላችሁም የሚል ክርክር ነበር። እኔ ግን በምርጫ ቦርድ ያገኘሁት ህጋዊ መታወቂያ የቅንጅት አባል መሆኔ ነው። የተወዳደርኩትም በቅንጅት ነው። ሕዝብም የሚያውቀኝ በቅንጅት ተወዳዳሪነቴ ነው። ሆኖም ያንን የክርክር ሁኔታ በቀላሉ አልፈነው ህጉ የሚፈቅድልንን የፓርላማ አገልግሎት ዘመን አጠናቅቄ ወጥቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በ1997 ዓ.ም የምርጫ ወቅት በቅንጅት አባላት መካከል በነበረው አለመግባባትና ዛሬም ድረስ ከሚወቀሱ ግለሰቦች መካከል አንዳንዶቹ የኢዴፓ አባላት እንደመሆናቸው እርሶ እስቲ በወቅቱ የነበረውን እውነታ ያስታውሱን?
አቶ ተመስገን፡- እውነቱን ለመናገር እኔ ኢዴፓ ውስጥ ከሶስት ወር የበለጠ ቆይታ አልነበረኝም። ከቅንጅት አንዳንድ አመራሮች ጋር የነበራቸውን ንትርክ በቅርበት አልተከታተልኩም። ምክንያቱም አንዱ የቅንጅት ስህተት የነበረው ተመራጮችንና በቅንጅት ስም የተወዳደሩትን ሰዎች ብዙ የማወያየት ነገር አለመኖሩ ነው። እኔና አንዳንድ ሰዎች በአብዛኛው መረጃዎችን የምንሰማው ከጋዜጣና ከሌሎች መገናኛ ብዙሃን ነው። በመጨረሻ ላይ እዛ ደረጃ ላይ መድረሱ፥ በኢዴፓና በቅንጅት መካከል የነበረው ሁኔታ እዛ ደረጃ መድረሱ በግሌ በጣም ያሳዝነኛል። በተለይም አዲስ አበባ ከተማን አለመረከባችን በጣም ያስቆጨኛል። ሆኖም በጥልቀት ስለጉዳዩ አላውቅም፤ እንዳልኩሽ መረጃዎችን የማገኘው እንደማንኛውም ሰው ከጋዜጣ ነው። እኔ ወደ ፓርላማ ልግባ አልግባ ብዬ የወሰንኩትም በራሴ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅትም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመስርተዋል፤ እንደ ኢ.ዜ.ማ ያሉ ፓርቲዎችም ህብረት ፈጥረዋል፤ በአጠቃላይ ያለውን የፖለቲካ ድባብና ምህዳር እንዴት ያዩታል?
አቶ ተመስገን፡- የፓርቲዎች ተሳትፎ
እየተሻሻለ
ነው
የመጣው
የሚል
እምነት
አለኝ።
እንደ
እኔ
ግን
107
ፓርቲ ኢትዮጵያ አያስፈልጋትም። ከኢጎና ከግል ስሜት ጋር፥ ከግል እውቅና ጋር ፣ እኔ የፓርቲ ሊቀመንበር ነኝ ከማለት ጋር የተያያዙ ስሜታዊ ጉዳዮች አሉ። ይሄ ደግሞ ለአገርም የሚበጅ ጉዳይ አይደለም። አብዛኞቹ «ፓርቲ ነን» ብለው የተቋቋሙትን እናውቃቸዋለን ። በአስር አመት ውስጥ አንድ ጊዜ እንኳ ስብሰባ አካሂደው አያውቁም። የሚጠበቅባቸውን መስፈርት ሳያሟሉ ነው ምርጫ ቦርድ አግበስብሶ የያዛቸው። ይህ በመሆኑ የመንግስት ሃብትና ንብረት እየባከነ ነው። ሰዎቹም በኢትዮጵያ ህዝብ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማህበረሰብ ግንኙነት ህይወት ላይ እየቀለዱ ነው። ይሄ በእኔ በኩል ተቀባይነት የለውም። ከሚስቱና ከልጆቹ በስተቀር ምንም የህግ አግባብ የሌለው፥ ማንም የማያውቀውና ቀበሌ ወረዳ ውስጥ ወጥቶ ህዝቡን አስተባብሮ ውጤታማ ስራ ያልሰራ ሰው የአንድ ፓርቲ አባል ስላለ ብቻ ልንቀበለው አይገባም።
በነገራችን ላይ ምርጫ ቦርድ እነዚህን ሰዎች ለመለየት ሩቅ መሄድ አይጠበቅበትም። በቀላሉ ለህዝብ ይፋ ሊሆን የሚችል ጉዳይ ነው። ሌላው ይቅርና በ2007ዓ.ም በነበረው ምርጫ እነዚህን ሰዎች ምን ያክል ድምፅ አገኙ ብሎ ማጣራት ያስፈልገው ነበር። እኔ ባለኝ መረጃ 50 ድምፅ እንኳ ያላገኘ ፓርቲ አለ። ግን አሁን ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋር ሆነው ስለፖለቲካ ጉዳይ ሲመክሩ እናያለን። ይሄ አግባብነት የሌለውና በህዝብ የፖለቲካ ህይወት ላይ መቀለድ ነው። በአገር ኢኮኖሚ ላይ መቀለድ ነው። ባለፈው ፓርቲ ለመሆን 1ሺ500 ሰው ብቻ ማስፈርም ነበር የሚጠበቀው። በአሁኑ ወቅት ይህንን አሰራርና መስፈርት የቀየሩት ይመስለኛል። ይሄ መስፈርት በየጊዜ እየጠነከረ መምጣት አለበት። አሁን ፖለቲካ የቦዘኔዎች ስራ ሆኗል። ስራ ከምፈታ ፖለቲከኛ ልሁን የሚባልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። እኛን ግን ፖለቲከኛ ያደረገን ግፉ ነው። ጫፍ የነካ አምባገነንነት፥ ጫፍ የነካ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፥ ጫፍ የነካ የማን አለብኝነት ስርዓት ነው። ይሄ በሌለበት ሁኔታ ሰው ፖለቲካን የጊዜ ማሳለፊያ ነው ያደረገው። ማንም ሰው መብት አለው ተብሎ በህዝቡ ፖለቲካ ላይ መጫወት ይችላል ማለት አይደለም። አሁን ባለው ፖለቲካ ይሄንን ነው እያየሁ ያለሁት።
በሌላ በኩል ግን እንደ ኢ.ዜ.ማ ያሉ ፓርቲዎች አንድ ላይ ተሰባስበው እያደረጉት ያሉት እንቅስቃሴ በጣም የሚያበረታታ ነው የሚል እምነት አለኝ። የሚያበረታተው ምንድንነው ካልሽኝም እነሱ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ቁጭ ብለው እንቅስቃሴ አለማድረጋቸው ነው። አባሎቻቸውን ወርደው እስከ ቀበሌና እስከ መጨረሻው የኢትዮጵያ ጫፍ ድረስ ሄደው ህዝብ አደራጅተው ነው አሁን ወደአሉበት አቋም የመጡት። ህዝቡን ያውቃሉ፤ ህዝቡን አወያይተው ፍላጎቱን ለመረዳት ጥረት አድርገዋል። ሌሎችም ፓርቲዎች ከኢ.ዜ.ማ ጋር ለመቀላቀል የምርጫ ቦርድ ሰርተፊኬት ቢቀዱ የተሻለ ነው የሚል ምክር አለኝ። ይህን የሚለው ኢ.ዜ.ማ ስለሆነ አይደለም፤ አቅምና ህገመንግስታዊ ድጋፍ ያለው በመሆኑም ጭምር ነው።
በመሆኑም ሚስትና ልጆቹን አስፈርሞ «እኔ የፖለቲካ ፓርቲ ነኝ» ማለት ቅዠት ነው የሚመስለኝ። መላ ሊበጅለት ይገባል የሚል እምነት አለኝ። አሁን ባለንበት ሁኔታ 107 ፓርቲ አያስፈልገንም። 380 ሚሊዮን ህዝብ ባለባት አሜሪካ እንኳ ያለው ሁለት ብቻ ነው። እናም እዚህ የአገር ሃብት በዚህ የሚባክንበት ሁኔታ ስርዓት ማስያዝ ይገባል። ይሄ የፖለቲካ ፓርቲ የሚባለው ነገር የቦዘኔዎች ጊዜ ማሳለፊያ ነው። ይሄ መቅረት አለበት። ለእኛም ጥሩ አይደለም፤ ለሚሰማውም ጥሩ አይደለም። አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ከሌላው ጋር አንድ አይነት ርዕዮተ ዓለም እየተከተለና ተመሳሳይ ፕሮግራም ይዘው አብረው ሊሰሩ ካልቻሉ እንዴት ነው የኢትዮጵያን ህዝብ አስተባብሮ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉት?። እዚህ አጠገቡ ካለው የፖለቲካ ፓርቲ ጋር አብሮ መስራት ካልቻለ እንዴት ነው ከሌሎች አገራት ጋር መስራት የሚችለው?።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ፍትሐዊና ገለልተኛ ለመሆን የሚያስችል ብቃት የለውም ብለው የሚተቹ አካላት አሉ። እርስዎ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ተመስገን፡- አይ አልስማማም፤ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ብቃት ያላትና አስተዋይ መሪ ናት። ደግሞም የጭቆናን የዲሞክራሲ ማጣትና የሰብአዊ መብት ረገጣ ገፈት ቀማሽ ናት። በተቻለ መጠን ነፃና ገለልተኛ የሆነ ተቋም ምርጫውን እንዲካሄድ አስተዋፅኦ ታደርጋለች ብዬ አስባለሁ። አንዳንዶች እንደሚሉት ምርጫው አሁን ላይ መካሄድ የለበትም ብዬ አላምንም። በእኔ እምነት ከዚህ የተሻለ ጊዜ አይኖርም። ነገ ከዛሬ የተሻለ ቀን ነው የምንለው የግል ተስፋችን እንጂ ምንአልባት ነገ የባሰ ሊሆን ይችላል።ምን አልባት እንደዚያ ማሰቡ ጨለምተኛ ሊያስብለን ይችላል እንጂ ማንም ስለወደፊቱ መሻል ዋስትና ሊሰጥ አይችልም። ይህንን ለማለት ነብይነት ይጠይቃል። ስለዚህ በዚያ መስፈርት የተሻለ ነገር ማስተላለፍ አይቻልም። ማስተላለፉ ሌላ ብዙ ጣጣዎችን ሊያመጣብን ይችላል። ህጋዊ እውቅና ያለው መንግስት ነው አገሪቱን ሊመራ የሚችለው። ጊዜው ከተራዘመ የመንግስት ህጋዊ እውቅናው ይጠፋል ማለት ነው። ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መካሄድ አለበት። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ሰው የራሱን በጎ አስተዋፅኦ ማበርከት ይገባዋል። ኢትዮጵያ በአንድነት በሰላም መሄዷ ቢስተጓጐል ሁላችንም ተጎጂዎች ነን። አንዳንዶች ቃላቶችንን እየመዘዙ የሚዲያ መጫወቻ አድርገውታል። እኛ በሰላም አገራችን እንድትኖር ነው የምንፈልገው። በሰላም ወጥተን እንድንገባ እና መንግስታችን በሰላም ወደፊት እንዲቀጥል ነው የምንፈልገው። ይሄ ደግሞ ህዝብ የመረጠው መንግስት ሲኖር ነው። ስለዚህ ምርጫው መራዘም አለበት ሲባል አሁን ያለው ጊዜ መጥፎ ነው፤ ነገ ደግሞ ከዛሬ የተሻለ ጊዜ ይሆናል ከሚል የሚመነጭና ተስፈኝነትን የያዘ ከመሆኑ ባሻገር ምንም ማረጋገጫ የለንም።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ በአማራ ክልል ውስጥ ያሉ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም በነበረው ምርጫ ህዝባችን በአግባቡ አልተቆጠረም፤ የተወሰደንም መሬት አልተመለሰም ስለዚህ ምርጫው እነዚህ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ምርጫ መካሄድ የለበትም በማለት ሃሳብ ያቀርባሉ? እነዚህን ጥያቄዎች አለመመለሱ በራሱ ሌላ ችግር አያመጣም?
አቶ ተመስገን፡- በእኔ እምነት የህዝብን ቁጥር ማስሊያ መንገዶች አሉ። ነገሮች ሲመቻቹ አንድ ሁለት ሶስት ብሎ ችግሮችን መቁጠር ይቻላል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ግን እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚችል ነገር የለም ብሎ መንግስት ከወሰነ ምርጫ መስተጓጎል የለበትም። ይሄ መሬት የእኔና የኛው ህዝብ የእኔ ነው የሚለው ነገር ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ የሚፈታ ነው የሚሆነው። ይሁን እንጂ ከዛ በፊት ምርጫ አይካሄድም የሚባል ነገር የለም። ሃላፊነቱ የሚመለከታቸው ሰዎች እና ህገመንግስቱ ሃላፊነት የሰጣቸው ተቋማት ምርጫውን ማካሄድ ይችላሉ። የህዝቡን ቁጥር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚደረስበት ሁኔታ ይኖራል። እነሱ እንደሚሉት የእነሱም ጥያቄ መቶ በመቶ ተፈቶ፤ የህዝቡ ቁጥርም ተስተካክሎ ነው ምርጫ ይካሄደው ካልን ረጅም ጊዜ ይፈጃል።
ህገመንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ስለሆነ ነው በእርሱ የምንተዳደረው። ያ እንዳለ ሆኖ ምርጫ ከመደረጉ በፊት ይሄ መፈታት አለበት የሚል ነገር የለም። በዚሁ ጉዳይ ላይ ችግሩ እንዳለ እናውቃለን፥ የአፈታቱን ዘዴ አሁን ላንስማማበት እንችላለን፤ ግን ምርጫው ይካሄዳል። ከዚያ በኋላ ደግሞ ህጋዊ የሆነው የስልጣን አካል ይህንን በሚፈታበት መንገድ ይፈታዋል። ለዚህ ደግሞ የሁላችንም በጎ ፈቃድ ያስፈልጋል። ፖለቲካውን ለደቂቃ ወደ ጎን ትተን አገራችንን ወደፊት ለማስቀጠል በጎ ፈቃደኛ ልንሆን ይገባል። ከፊታችንን ያለውን ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በሰላም ለማካሄድ ሁላችንም መተባበር አለብን። ይህ ጉዳይ የምርጫ ቦርድ ጉዳይ ብቻ መሆን የለበትም።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአካባቢ ምርጫ ሳይካሄድ መቆየቱ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ምን አሉታዊ ሚና ይኖረዋል?
አቶ ተመስገን፡- ልክ ነው የአካባቢ ምርጫ መካሄድ አለበት። በተለይ እኛ በተቃዋሚ ጎራ የነበርነው በምክር ቤትና በፌደራል ደረጃ ትንሽ ውድድር ለማድረግ ሞክረናል እንጂ ወደ ቀበሌና ወረዳ እንድንገባ አይፈለግም ነበር። የገቡ ሰዎችም ዋጋ ከፍለዋል። ያልተሳተፍነው ግን እኛ ስላልፈለግን ሳይሆን ያለፈው መንግስት በዚህች አታልፉም ብሎ ስላሳደደን፥ ስለገደለን ነው። አሁን ግን የሚቻልበት ሁኔታ እየመጣ ነው።የአካባቢ ምርጫ ለማድረግ ነገሮች እየተመቻቹ ይመስለኛል። ስለዚህ ይህ ጉዳይ ተፈፃሚ እንዲሆን ሁላችንም ትብብር ማሳየት ይጠበቅብናል። የዶክተር አብይ መንግስትን ተቃዋሚዎች መጠየቅ ያለባቸው ወደ ቀበሌ እንውረድ ብለው ነው። በነገራችን ላይ የአካባቢ ምርጫ ባለመደረጉ ተጎጂዎቹ እኛ ነን። እዚህ ከተማ ፥ ወረዳና ቀበሌ ውስጥ ብዙ የልማት ስራዎች እንዲሰሩ፥ ህዝቡ ያለፍርሃት እንዲኖር፥ ሃሳቡን እንዲገልፅ፥ እንዲተባበር እንዲገናኝ እንፈልጋለን።
ይህንን ባለፈው ልናደርግ አልቻልንም። ወደ ቀበሌ ወርደን ህዝብ ማነጋገር በግልፅ አልተፈቀደላችሁም ነበር እኮ ስንባል የነበረው። አሁን እንደዚህ አይነት እድል አለ። ዶክተር አብይ ግን እኔ ራሴ ልወስንላችሁ አላለም፤ ከዚያ ይልቅ የሚመለከተው አካል እንዲወስን ግን በሩን ክፍት አድርጓል።አንዳንድ ነገሮች መቶ በመቶ ትክክል እስከሚሆኑ ድረስ መጠበቅ የለብንም። ያንን ትክክለኛነት የምናመጣው እኛ ነን። በእኛ ተሳትፎ፤ በእኛ የአገር ተቆርቋሪነት ነው ሊመጣ የሚችለው። አንዳንድ ጊዜ ዝም ብሎ ተቀምጠው ለማናገር ያህል ብቻ የሚናገሩና በአገር ጉዳይ ላይ ያልሆነ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች አሉ። በአጠቃላይ በእኔ እምነት ምርጫው ለነገ የሚተው ሳይሆን ዛሬ ነው መካሄድ ያለበት፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ ሸክም አለውና ነው። የዛሬ አመት የተሻለ ይሆናል ብሎ በፊርማው የሚያረጋግጥልን ሰውም ድርጅትም የለም።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ወደ ተቃዋሚ ጎራ ለመግባት ያስገደዶት በአገሪቱ ላይ የነበረው የብሄር ጭቆና እንደሆነ ገልፀውልኛል፤ አሁን ይህ የጭቆና ቀንበር ሙሉ ለሙሉ ተነስቷል ብሎ ማለት ይቻላል?
አቶ ተመስገን፡- እንዳልሽው እኔ ወደ ተቃዋሚነትም ሆነ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመግባት የተገደድኩት፤ በነበረው የብሄር ጭቆና ግፊት ነው። ሌላው ይቅርና በምንናገረው ነገር እንኳ ማንነታችን ጥያቄ ውስጥ ይገባ ስለነበር እንሰጋ ነበር። በዚህ ምክንያት ላለፉት 27 ዓመታት ስንናገርም ሆነ ስንቀሳቀስ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ነበር። እኔ የምክር ቤት ተመራጭ ሆኘ እያለሁ እንኳን እፈራ ነበር። አንዳንድ ወዳጆቼ እንዳውም «ልብስህን አጣጥፈህ አዘጋጅተህ ጠብቅ በቀደም ምክር ቤት ውስጥ የተናገርከው አልተወደደልህም»ያሉኝ ጊዜ ነበር። እንግዲህ እግዜር ያሳይሽ እኛ ያለመከሰስ መብት ያለን የምክር ቤት ተመራጮች እንኳ እንፈራ ነበር። የምንናገረውን አስተውለን ነበር። ስንናገርም ብዙ ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስብን ነበር። ህዝቡ ደግሞ ከዚህ በባሰ ስጋት ውስጥ እንደነበር ማሰብ አይከብድም። አሁን ዶክተር አብይ የመናገር መብት ከማንም የሚሰጥ ስጦታ አለመሆኑን አረጋግጦ ነግሮናል። እስካሁን እያየን ያለው ይህንኑ ነው።
በእርግጥ የተለየዩ ሰዎች የተለያየ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ። እኔ ግን የማየው በዚህ ጫፍ በነካ የጭቆና ስርዓት ውስጥ ለ27 ዓመታት የኖረ ህዝብ አሁን ሙሉ ለሙሉ ተለቋል ማለት ይቻላል። ግን የምናየው እሱን አይደለም። እንግዲህ አሁን የምናየውን አለመረጋጋት ይሄ አስተዳደር በሚሰራው ስራ የመጣ አይደለም። እሱን ምስክርነት መስጠት ይቻላል። በዚህ አንድ አመት ውስጥ ጭቆና ደርሶብን፥ ታፍነን ኦክስጅን ፍለጋ የምናደርገው መጠፋፋት አይደለም። ይሄ የቆየ ጉዳይ ነው። የቆየ በደል ውጤት ነው። ጫፍ የነካ ግፍ የወለደው ነው። የተነገረን አጥፊ ሃሳብ ድምር ነው። አንዳችሁ የአንዳችሁ ጠላት ናችሁ ተብሎ በአዕምሮችን እንዲሰርፅ የተደረገ ነው ዛሬ እየገነፈለ እየፈሰሰ ያለው። በእኔ እምነት አሜሪካ ውስጥ የማጣጥመውን ነፃነትና በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው አይበልጥም። እንዳውም በአጭር ጊዜ ሂደት ውስጥ ይህንን ያህል መናገር መቻሌ ሊደነቅ የሚገባ ነው። አሜሪካ ይህንን አይነት ነፃነት የመጣው በ200 ዓመት ትግል ውስጥ ነው። እኛ ጋር የመጣው በአንድ አመት ነው። የ27 ዓመት ይገሉኛል፤ ያሳድዱኛል፤ ያስሩኛል፥ የሚለው የፍርሃት ዘመን መነሳቱ ትልቅ መገንፈልን አምጥቷል። ያ መገንፈል ወደፊት ይሰክናል።
አዲስ ዘመን፡- አያይዘው እስቲ እርስዎ ምክር ቤት በነበሩበት ወቅትና አሁን ያለውን የምክር ቤት የመናገር ነፃነትን ሁኔታ ያነፃፅሩልኝ?
አቶ ተመስገን፡- እንዳልኩሽ እኔ ምክር ቤት በነበርኩበት ወቅት ወይ እገደላለሁ፥ ወይ ደግሞ እታሰራለሁ የሚል ስጋት ነበረን። ቢሆንም ግን የኢትዮጵያን ህዝብ የልብ ትርታ እናገራለሁ በሚል በራሳችን ቆርጠን ነው የምናገረው የነበረው እንጂ ነገሩ የሚያደፋፍር ሆኖ አልነበረም። ያን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስታውሰውን ንግግር ስንናገር የነበረው በሁለት ደቂቃ ጊዜ ውስጥ ነው። ራሳችን መስዋዕትነት ለመክፈል ነበር ወስነን ነበር የምንናገርው። የምናገራቸው ነገሮችን ግን የህዝብን ሮሮ በግልፅ የሚያሳዩ ነበሩ። ሆኖም በፓርላማ ውስጥ ተቃዋሚ ማለት በነፃነት የሚንቀሳቀስ የፓርላማ አባል አልነበረም። ግን እንደዛም ሆኖ በዚህ ፍርሃት ውስጥ እንነናገር ነበር።
አሁን ግን በተለይ በቅርቡ ፓርላማው ነፍስ ያለው እየሆነ ነው። አባላቱ ሃሳባቸውን ያለምንም ፍርሃት እያነሱ እየጠየቁ ነው ያሉት። ፈረንጆቹ እንደሚሉት ስራ አስፈፃሚው የሚያመጣውን ሁሉ ነገር ተቀብሎ ማህተም አድርጎ የሚሸኝ ነው። አሁንም መቶ በመቶ የኢህአዴግ
ፓርላማ ነው። ከላይ ወርቅ ቢያዘንብ በጥርጣሬ መልክ ልናየው ይገባል። ምክር ቤት የሃሳብ ፍጭት የሚደረግበት ነው እንጂ የመንግስት ተወካይ ሚኒስትር ይህ ተናገሩና በዚህ ጉዳይ ላይ ምረጡ የሚልበት ሁኔታ መኖር የለበትም። እርግጥ ዶክተር አብይ ከመጡ በኋላ ምክር ቤቱ የመነቃቃት መንፈስ ይታይበታል። ግን ያለፈው ታሪኩና ያለፈው ሸክሙ አሁንም በጥርጣሬ አይን እንድናየው ነው የሚያደርገን። መቶ በመቶ የአንድ ፓርቲ አባል ባለበት ስብስብ ውስጥ ፍትህ ይሰፍናል ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም ነገር ይደረጋል ለማለት ይቸግረናል።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ስናገር የሆነ ነገር ይደርስብኛል በሚል ስጋት ውስጥ እንደነበሩ አጫውተውኛል፤ እንደ አብዛኞቹ የቅንጅት አባላት በግልዎ የደረሰብዎት ጥቃት አለ? በተለይ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ጋር በነበረዎ አለመግባባት እስርና እንግልት አጋጥሞት ይሆን?
አቶ ተመስገን፡- እንግዲህ በቀጥታ ብዙ ሊገፉኝ አልፈለጉም ነበር። ምክንያቱም ከውጭ በመምጣቴ ይመስለኛል። ይህም ሲባል የመጣሁት የፖለቲካ ስልጣን ፈልጌ እንዳልሆነ ስለሚረዱ ነው ብዙ ገፍተው ያልሄዱት የሚል እምነት አለኝ። የምናገራቸው ነገሮች ሁሉ በአደባባይ ልክ ነው ለማለት ቢያስቸግራቸውም ሃቅ እንደሆነ ያውቃሉ። ግን ደግሞ በሚኒስትሮቻቸው በኩል ከአንድ ሁለት ጊዜ አርፈህ ልጆችን አሳድግ የተባልኩበት ጊዜ አለ። ትንሽ መስመር እያለፍክ ነው ተብዬም ነበር። ነገር ግን ማስፈራሪያውን ከማንም አልቀበልም ነበር። ይህን ስል አቅሙ ስላለኝ ወይም ራሴን መከላከል እችላለሁ ብዬ ሳይሆን ፈርቶ የሚቀመጥ ህሊና ስለሌለኝ ነው። ይህንንም ነግሬአቸዋለሁ። በወቅቱ የተደረገብኝን ዛቻ በሚመለከት ለህዝቡ በአሜሪካ ድምፅ ተናግሬያለሁ። ግን ከማስፈራራት ባለፈ ችግርና እንግልት በእኔ ላይ አልደረሰም።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ያደረጉት ትግል ፍሬ አፍርቷል ብለው ያምናሉ?
አቶ ተመስገን፡- አዎ አፍርቷል፤ ዶክተር አብይን አፍርቷል፥ የእኔ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወገኖችም ተደምረን ስናደርግ የነበረው ትግል ነው ቢዘገይም ዶክተር አብይን አመጣ። ይህንን ደግሞ ዶክተር አብይም ራሱ የሚያውቀው አይመስለኝም። እኛ ነን ያመጣነው፤ እኛ ነን የዚያን ጊዜ መስዋትነት እንከፍላለን ብለን በምክር ቤት የገባን ሰዎች በውጭ ሆነን የታገልን ሰዎች ጥረት ነው ያመጣው። ይህ ማለት የእኔ የግሌ ጥረት አመጣሁ ማለቴ እንዳልሆነ ልታሰምሪበት እፈልጋለሁ። በተለይም በ1997ዓ.ም በአደባባይ በጥይት የተረሸኑ ሰዎች ደም ነው ዶክተር አብይን ያመጣቸው። እናም እኔ በተለይ በኢኮኖሚ በኩል አቶ መለስ የኢትዮጵያን ህዝብ አይን ለመሸፈን የሚያደርገውን ጥረት እረዳለሁ። የዚያን የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አሁን እያጨድን ነው። አሁን ብራችን ዋጋ የለውም። ዛሬ ሱቅ የገዛነው ነገር ነገ ጨምሮ ነው ያለው። በርካቶች በሚያገኙት ገንዘብ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር አልቻሉም። የዋጋ ግሸበቱ ሰማይ ወጥቷል።እኛ እኔና ሌሎችም ሰዎች ስንናነገር የነበረው ይሄንኑ ነበር። ሃላፊነት ሊኖር ይገባል።
በእኔ እምነት ይህንን ለውጥ ለማምጣት 27 ዓመት መፍጀት አልነበረበትም። አሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ውጤት አምጥተናል፤ ዶክተር አብይ በሚባል ሰው ይታያል። ለ27 ዓመታት አገሪቱን በመሩት ሰዎች ልብ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ባንችልም እንደዚህ አይነት ለኢትዮጵያ የሚያስብና ለኢትዮጵያውያኖች ደህንነት የሚቆረቆር ኢትዮጵያዊነት በልቡ የተቀረፀ ሰው አፍር ተናል። እናም እኔ ሙሉ በሙሉ ደስተኛ ነኝ።
ዶክተር አብይ ስንፀልይ የነበረው በትግላችንም ስናስበው የነበረ ሰው ነው። ኢትዮጵያዊ መሪ እንፈልግ ነበር። ነገሮችን ሰፋ አድርጎ የሚገነዘብ፤ ከራሱ መንደራዊ አስተሳሰብ የወጣ፤ ከራሱ የመንደር ልጆች ውጪ የሚያስብ ሰው ኢትዮጵያን እንዲመራት እንፈልግ ነበር። ይህንን ሁሉ ነገር በዶክተር አብይ አየነው። እኔ በእርግጥ በተቃዋሚነት ከታወኩበት ጊዜ ጀምሮ መንግስትን አመስግኜ አላውቅም ነበር። የማላመሰግነው በሚሰሩት ስራ ነው። አሁንም ቢሆን አክብሮቴ ከዶክተር አብይ ጋር እንጂ ኢህአዴግ ከሚባል ፓርቲ ጋር አይደለም። ቁም ነገሬ ካሳደደን ፥ ከገደለን፥ ካሰረን፥ የምርጫ ኮሮጆ ከገለበጥብን ፓርቲ ጋር አይደለም። ግን ከዛ ውስጥ አንድ ሰው አግኝተናል፤ እሱም ዶክተር አብይ ነው። እናም በእኔ እምነት በዶክተር አብይ የተሻለ ጊዜ እየመጣ ነው። ግን እየረዳነው አይደለም። በጣም የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር እንደዚህ አይነት ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከሰት ሁሉም ወደ መንደሩ ተመልሶ ስለመንደር ፖለቲካ ነው መናገር የሚፈልገው። እኛ የምንናገርው የነበረው ስለኢትዮጵያ አንድነት ነበር። ለዚህም ነው ዋጋ የከፈልነው። እኔ ከተደላደለ የአሜሪካን ኑሮ ወጥቼ የችግርና የስቃይ ጊዜ ያሳለፍኩት እንደዚህ አይነት ነገር በአገሬ እንዲመጣ ስፈልግ ስለነበር ነው። አሁን ያንን ጊዜ እያየን ነው።
አስቀድሜ እንዳልኩት የኢኮኖሚ አስተዳደር ጥፋቶች ቀደም ብለው የተከሰቱ ርዝራዡ አሁን እያስቸገረ ነው።ኢትዮጵያውያኖች እኮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበርንበት የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ነው። እየዞረ በየሀገሩ ዜጎቹን የሚያስፈታ ብቸኛው መሪ አብይ ነው። እኔ እንኳን 22 ዓመት አሜሪካን ስኖር የኢትዮጵያ አምባሳደር ማን እንደሆነ ምን እንደሚሰራ የማውቀው ነገር አልነበረም። አሁን ግን ግዴታው ነው። እኛ ኢትዮጵያውያኖች ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ቁጥር አንድ ጉዳዩ ሆነናል። ይህ በዶክተር አብይ ነው የመጣው። ከዚህ ቀደምም ስንናፍቀው የነበረው ይህንን ነበር። እነዚህ ለውጦች ደግሞ ስር እየሰደዱ ሲመጡ የበለጠ እድገት ይመጣል። ወደ መካከለኛ ገቢ በእርግጠኝነት እንገባለን ብዬ አምናለሁ። በአንድ አመት ውስጥ ያየነው ነገር ጥሩ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች በምናባቸው የሚያስቡት እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ እውን ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ አልነበረም። በፊት የነበሩት እኮ ጠባቦች ጎሰኞች እኛ ብቻ ነን የተሻልን ብለው የሚያስቡ ሰዎች የነበሩበት ቦታ እኮ ነው። በእነሱ ግምት እኮ ከእነሱ ውጭ ሌላ ሰው አልነበረም። አሁን ሁላችንም እናስፈልጋለን። በአጠቃላይ ዶክተር አብይ ኢትዮጵያ በፀሎት ያገኘችው እንጂ የሚገባት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በክልሎች መካከል ያሉ ግጭቶችን ከማስቆም አኳያ ዶክተር አብይ አሉባቸው የሚሉት የቤት ስራዎች የሉም?
አቶ ተመስገን፡- እኔ እንደሚገባኝ ዶክተር አብይ እንደሰለጠነ ሰው ነው አገሪቱን እየመራ ያለው። የሰለጠነና እና አዕምሮ ያለው ህዝብ በፍቅር በአንድነት በመደመር ያምናል። እኔም ከእነሱ ጋር አብሬ ልደመር ማንም ሳያስፈልገን አብረን እንብላ አብረን እንጠጣ ተሳስበን እንኑር የሚለውን ስሜት በህዝቡ መካከል ለመፍጠር ጥሩ ሙከራ አድርጓል። ግን አልገባንም፤ ማኬቤሌ የሚባል የፖለቲካ ፍልስፍና ፀሃፊ እንዳለው ከሚወደድ መንግስት ይልቅ የሚፈራ መንግስት ለአገር የተሻለ ይሆናል። ዶክተር አብይ በጣም የላቀ የፍቅር ፥ የአንድነት፥ የመደመር ስሜት ለህዝባችን ጥቅም ቢኖረውም ከዚያ ትንሽ ከፍ አድርጎ የህግ የበላይነትን ማስከበር አለበት። ኢንቨስት ማድረግ ያለብን የህግ የበላይነትን በሚያስከብሩ አካላት ላይ ነው። ይሄ ቁጥር አንድ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። መንግስት በመጀመሪያ ደረጃ ሊገነዘብ የሚገባው ጉዳይ የህግ የበላይነትን ማስከበር ነው። ይህንን የምናውቀው በንድፈ ሃሳብ ብቻ አይደለም ፤ በልምድም ጭምር እንጂ። እንዳልኩሽ አሜሪካ አገር በነበረኝ ቆይታ ትንሽ እንኳ ህጋቸውን ብተላለፍ የሚከፈለው ዋጋ አሰቃቂ እስር ነው። ስለዚህ የሰው ልጅ የሀገሩን ህግ ማክበር አለበት። እኛ ፍቅርን በተግባር የምንተረጉም ሰዎች አይደለንም፤ እኛ የህግ የበላይነት እንዲነግረን ያስፈልገናል። አሁን መደረግ ያለበት ነገር በክልሎችም ሆነ በፌደራል መንግስት ደረጃ ዜጎች መብት አላቸው። ግዴታም አለባቸው። ያንን ግዴታቸውንና መብታቸውን በተመጣጠነ ሁኔታ ተጠቃሚ መሆን ነው የሚያስፈልገው። እኔ የሚታየኝ እንደዚያ ነው። በእርግጥ ዶክተር አብይ ብዙ አማካሪዎች ስላሉት የተለየ ሊመክሩት ይችላሉ። እኔ ግን ህግ መከበር አለበት ነው የምለው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ያለው የደቡብ ክልል ፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ያዩታል? በተለይ የሲዳማ ዞን ክልል የመሆን ጥያቄ ጉዳይ ወዴት ያመራል ምንስ ያስከትላል ብለው ያስባሉ?
አቶ ተመስገን፡- ከባድ ጥያቄዎች ነው የጠየቅሽኝ! እኔ በደቡብ ክልል ውስጥ እንደ መወለዴ የአብዛኛው ህዝብ አናኗርና ባህል አውቃለሀ ብዬ አስባለሁ።የደቡብ ህዝብ በጣም ደግ፥ ገር ፥ እንግዳ ተቀባይ ነው። ምንም እኩያ የማይገኝለት ቅን ልቦና የማይገኝለት ህዝብ ነው። አሁን አሁን እዛው በተወለድኩበት አካባቢ እንኳ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› የሚባል ነገር መጥቷል። እኔ ስለማላውቀው አካባቢ ህዝብ ቢነገረኝ ብዙ ላይገርመኝ ይችል ነበር። ይህንን ጉዳይ ምንአልባት ወደፊት ብዙ የታሪክ ተመራማሪዎችና ሶሾሎጂስቶች ተመራምረው ሊፅፉበት ይችላሉ። ሆኖም ግን የክልል ጥያቄ ህገመንግስታዊ ጥያቄ ነው፤ ማቅረብ ይቻላል። መልስ እስኪሰጥ ግን መጠበቅ አስፈላጊ ነው።
ሁለተኛ ነገር በጉልበት ይህንን እንለውጣለን የሚሉ አካላት ካሉ የህግ የበላይነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል። እኛ በዚያ ምክንያት ነው በዚህች መሬት ላይ የምንኖረው። ጉልበተኞች መሬታችንን፥ ቤታችንን፥ ያጎሳቁሉናል ብለን አይደለም፣ የህግ የበላይነት ስላለ ይቆጣጠራቸዋል ብለን የምናምነው። አሁንም ቢሆን የክልልም ይሁን ሌሎች ጥያቄዎች በሚሆነው መንገድ መልስ ያገኛሉ ተብሏል።
ይህንን ስልጣን ህገመንግስቱ የሰጠው ለፌደራል መንግስት ነው። መልሱ አይሆንም ሊሆን ይችላል። ይህንን በፀጋ ተቀብሎ ወደፊት መራመድ ይቻላል። ይህንን መንግስት የሚወስነውን ውሳኔ በጥሞና አንቀበልም የሚሉ ሰዎች ካሉ በህጉ ሊጠየቁ ይገባል። እያንዳንዱ እርምጃ ሌላ ተመጣጣኝ የሆነ አፀፋዊ እርምጃ አለው። ልክ መንግስት እንደሌለበትና ስርዓት አልባ አገር የፈለጉትን ማስወሰን የሚቻልበት ቦታ የለም። እንደዛ ከሆነ መንግስት የለንም ማለት ነው። መንግስት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ደግሞ እኛ እየጠየቅን ነው ያለነው። በምንከፍለው ግብር መንግስት በትክክል ሊያስተዳደርን ይገባል። የእኛም መብት እንዲጠበቅ እንፈልጋለን። የእኛ መብት የሚጠበቀው ደግሞ ሰዎች በህግ ጥላ ስር ሆነው መተዳደር ስንችል ነው። ደቡብ ክልል ማንም መስፈርቱን ካሟላ ክልል የሆነ መብቱ የተጠበቀ ነው እስካለ ድረስ መብታቸው ቢጠበቅላቸው ደስ ይለኛል። ግን አይቻልም ካለ ይህንን ማክበር ይገባል። በነገራችን ላይ ይህንን ጉዳይ ተገን በማድረግ እሳት ማራገብ የሚፈልጉ ወገኖች አሉ። በጣም ትናንሽ አስተሳሰብ ያላቸው የኢትዮጵያን ደህንነት የማያውቁ ግለሰቦችና ድርጅቶችም አሉ። እነዚህ የትም አይደርሱም። ምክንያቱም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ህዝብ ነው። እዚህም እዚያም የሚገነፍለው ነገር የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ይቀዘቅዛል።
አዲስ ዘመን፡-ግን ህገመንግስቱ በራሱ ለዘጠኝ ክልሎች እውቅና ሰጥቶ እያለ በሌላ በኩል መስፈርቱን ካሟሉ ክልል መሆን እንደሚችሉ ማስቀመጡ በራሱ የተምታታ ነገር አለው ለማለት አያስደፍርም?
አቶ ተመስገን፡- ልክ ነሽ፤ ከምርጫ በኋላ ሊታይ ይገባል ካልኳቸው ነገሮች አንዱ የህገመንግስቱ ጉዳይ ነው። ከምርጫው በኋላ ህጋዊ እውቅና ያለው መንግስት ህገመንግስቱን ማሻሻል ይችላል። አንቺ የምትያቸው ቅራኔዎች የዚያን ጊዜ ሊታረሙ ይችላሉ። እኛም እኮ ምክር ቤት በነበርንበት ወቅት ህገመንግስቱ ውስጥ መሻሻል አለባቸው ብለን ስንሞግት የነበረው። ከምርጫ በፊት ግን ማንም ስልጣን ያስኩ ብሎ ሊያስተካክለው የሚችለው ነገር የለም። በነገራችን ላይ አብዛኛዎቻችን ህገመንግስቱን አናውቀውም፤ ተሰጠን እንጂ አልተወያየንበትም። እናም ይሄ ይስተካከላል ብዬ አምናለሁ።
በአንድ በኩል ህገመንግስቱን በተለይም አንቀፅ 39ኝን ቁጭ ብለሽ ስታይው እኩይ አመለካከት ያላቸው ወይንም ጥራዝ ነጠቅ የሆነ እውቀት ያላቸው ሰዎች እንደፃፉት ትረጃለሽ። የኢትዮጵያን አንድነትና ወደፊት መቀጠል የማይፈልጉ ሰዎች እንደጻፉት ግልፅ ነው። በዚያ ወቅት ይህንን ለመፃፍ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታም አልነበረም፤ በአለምም ሆነ በአገር ደረጃ ልምዱም አልነበረም።በጣም ጠርዝ የነካ አይነት አፃፃፍ ነው። ያለንን አብሮነትና አንድነት ለመቀነስ ታስቦ የተደረገ ነው። እኛ ካልመራናችሁና ካለስተዳደርናችሁ ትበጣጠሳላችሁ ተብሎ ለማስፈራራት የተፃፈ ነው። ይህንን ጉዳይ በሚመለከት በምክር ቤትም ሆነ በውጭ ብዙ ተሟግተንበታል። ሊኖር የማይገባው አንቀፅ ነው። ለአንድነታችን ጠንቅ የሆነ ሃሳብ ነው። ይህንን አይነት ጥራዝ ነጠቅ አመለካከት ያላቸው ሰዎች አሁንም አሉ። አሁንም ይህንን ጉዳይ እንደማስፈራሪያ የሚጠቀሙበት አሉ። ግን እንዳልኩሽ ቀደም ሲል ይታሰብ የነበረው የማይነካ፥ ከላይ አስቀምጠን የምናመልከው ቅዱስ መጽሃፍ ነበር። አሁን ግን ከምርጫ በኋላ መሻሻል ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ
አቶ ተመስገን፡- እኔም ያለሁበት ስፍራ ድረስ መጥታችሁ ሃሳቤን ስለጠየቃችሁኝ ከልቤ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሀምሌ 6/2011
ማህሌት አብዱል