
የዝግጅት ከፍላችን ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ፣ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ እንዲሁም በማእከላዊ ኢትዮጵያ ተዘዋውሮ ሰፊ ዘገባዎችን በሚሠራበት ወቅት ከዳሰሳቸው ጉዳዮች ውስጥ የጤናው ዘርፍ ቀዳሚው ነበር።
በጤናው ዘርፍ ላይ በኢትዮጵያ ወረርሽኞች ሳይከሰቱ የመከላከል እና ከተከሰቱም በኋላ የመቆጣጠር ሥራ በተቋማት ይሠራል። ይህንን ተግባር ከሚያከናውኑ ተቋሞች መካከል ደግሞ የሲዳማ ብሔራዊ ከልላዊ መንግሥት የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይገኝበታል። በዛሬው ወቅታዊ የእንግዳ አምድ ላይም የዋና መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ዳመነ ደባልቄ ጋር ቆይታ አድርገን ነበር። ዋናው ርዕሰ ጉዳያችንም በክልሉ ስላለው የወረርሽኝ ስጋት ነበር። በቆይታችን እንደሚከተለው ይዘንላችሁ ቀርበናል። መልካም ንባብ!!
አዲስ ዘመን፦ በክልሉ ዋና ዋና ተብለው የተለዩ የወረርሽኝ አደጋዎች የትኞቹ ናቸው፤ ምን የጥንቃቄ ርምጃዎች እየተወሰዱ ነው?
ዶክተር ዳመነ፦ የሲዳማ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምንሠራቸው ሥራዎች ተላላፊ እና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ እንዲሁም በጥናት እና ምርምር ዘርፍ ላይ ነው። በተለይ በላብራቶሪ እና በመረጃ አያያዝና አስተዳደር ላይ በዋናነት ትኩረት አድርገን እንሠራለን። በተለይ ከተላላፊ እና በወረርሽኝ ነክ ከሚነሱ በሽታዎች አንጻር በአሁኑ ሰዓት ወባ በክልሉ እንደ ችግር ሆኖ እየታየ ነው። ይህ ችግር ከተከሰተ ከዓመት በላይ አልፎታል። በመሀል የመቀነስ አዝማሚያ የነበረው ቢሆንም አሁን ግን ትንሽ ከክረምት ዝናብ ጋር ተያይዞ የመጨመር ምልክቶች አሉ።
ከእዛ ውጪ ግን ሌሎች ወረርሽኖች ኮሌራም ሆነ ኩፍኝ በአሁኑ ሰዓት የለም። ይሁን እንጂ ኮሌራን በተመለከተ ክረምት በመሆኑና ዋና የኮሌራ መተላለፊያ ከንጽህና ጋር ስለሚያያዝ ንጹህ ካልሆኑ የመጠጥ ውሃ ከሽንት ቤት አጠቃቀም ጋር አስፈላጊ የጥንቃቄ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በክልሉ የኩፍኝ ወረርሽንም አምና ነበር ዘንድሮ ግን አልተከሰተም። እሱንም በሚገባ ቅኝት እና አሰሳ ሥራዎች በተገቢው እየተሠራ ነው።
ሌላው እንደ ሀገርም ስጋት ሆኖ ያለው በአሁኑ ሰዓት የዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) ነው። የዝንጀሮ ፈንጣጣ ኦሮሚያ ውስጥ ሞያሌ አካባቢ ነው መጀመሪያ የተገኘው። የሲዳማ ክልልም የትራንዚት መስመር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ ስጋት ቀጣና ሆኖ ነው የሚታየው። ወረርሽኙን ለመከላከል በየጊዜው በየቀኑ የቅኝት ሥራዎች እየተሠራ ነው። ኬዙም ከተገኘ ለይቶ ማከሚያ ተቋም ከሆስፒታል ጀምሮ እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ በሚገባ ተደራጅቷል። ለባለሙያዎችም በየደረጃው ሥልጠናዎች እየተሰጠ ነው። ከመድኃኒት አቅርቦት አንጻር በቂ ዝግጅት አድርገናል። ምልክቶችም ካሉ ላብራቶሪ ምርመራ እየተደረገ ነው።
የላብራቶሪ ምርመራውን በክልሉ ለመጀመር ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር እየተነጋገርን ነው። ደረጃውን የጠበቀ ላብራቶሪ ስላለ ባለሙያዎች ሠልጥነዋል። ናሙናውን በማእከል ከማድረግ ይልቅ እዚሁ ለመሥራት እየተዘጋጀን ነው። በተለይ ተላላፊ እና ወረርሽኝ መልክ የሚነሱ በሽታዎች ላይ ያለው ዝግጅት በክልሉ ይሄንን ይመስላል።
በመሆኑም በዋናነት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ዓለም ስጋት የሆነው ወረርሽኝ የዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) ነው። ሌላው ማሌሪያ ወረርሽን ውስጥ ያለ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ክረምት እየመጣ በመሆኑ የሳኒቴሽን ሃይጂን ሽፋናችን መቶ ፐርሰንት እስካልሆነ ድረስ ኮሌራን እንደ ስጋት ነው የቆጠርነው። ሌላው የምግብ እጥረት እና የተመጣጠነ ምግብ ስርጭት ዋና ዋና ብለን ከያዝናቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ። አጠቃላይ እንደ ኢንስቲትዩት ሰላሳ ስድስት በሽታዎች ተለይተዋል። 24 ወዲያውኑ ተለይተው ሪፖርት የሚደረጉ እና አስራ ሁለቱ ደግሞ በየሳምንቱ ሪፖርት የሚደረጉ በሽታዎች አሉ።
አዲስ ዘመን፦ የስርጭት መጠኑን በተለይ ከወባ ጋር ተያይዞ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ቢገልጹልን?
ዶክተር ዳመነ፦ አምና ከነበረው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ብዙም ከፍ ያለ አይደለም። ነገር ግን ወረርሽኝ ነው ተብሎ ብያኔ ከሚሰጠው አንጻር ያለነው ወረርሽኝ ውስጥ ነው። ወረርሽኝ ነው ለማለት የራሱ ስሌት አለው። ከተቀመጠው ስታንዳርድ በታች እስኪወርድ ድረስ በአግባቡ መሥራት ይጠበቅብናል። አምና በእዚህ ጊዜ በሳምንት አስር ሺ ታማሚዎችን እያከምን ነበር። በአሁኑ ወቅት ሦስት ሺ እና ሁለት ሺ 500 ነው። ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ብዙ አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ ወባ ወረርሽኝ ነው የምንልበት መለኪያ ምንድን ነው?
ዶክተር ዳመነ፦ ለምሳሌ ከሦስት ከአራት ዓመት በፊት ወረርሽኝ ነው የምንለው በሳምንት አንድ ሺህ ከሆነ እና ቁጥሩ በየሳምንቱ እየጨመረ ሲሄድ ነው። መጀመሪያ ከተመዘገበው ቁጥር እያሻቀበ ሲሄድና ከቁጥሩ ጋር ስታነጻጽር ከፍ እያለ ከሄደ ወረርሽኝ ይሆናል።
በመሆኑም በሳምንቱ ከተመዘገበው በታች ነው መሆን ያለበት።
እኛም የምንሠራው ከተመዘገበው ቁጥር ለማውረድ ወይም በእዛው ለመቀጠል ነው የምንሠራው። ስለዚህ በየደረጃው ላሉ ማህበረሰብ ክፍሎች ትምህርት እየተሰጠ ነው። በወባ መከላከል ላይ በማኔጅመንቱ ላይ በመድኃኒት አቅርቦት ላይም ከጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት በደንብ እየሠራን ነው። ዘንድሮም ወረርሽኝ ሆኖ ስጋት እንዳይሆን እየሠራን ነው።
ወባን ለመቆጣጠር የኬሚካል ርጭት እና አጎበር መስጠት አንዱ መከላከያ መንገድ ነው ብለን በሰፊው እንገልጻለን። አጎበር አጠቃቀሙ ላይ ክፍተት አለ በየቦታው ተመሳሳይ ነው ማለት ይቻላል። እሱ ላይ ትምህርት እየተሰጠ ነው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አርጅቷል ብሎ ለሕክምና ከተሰጠው ግልጋሎት ውጪ ወደሌላ ግልጋሎት የማዋል ዝንባሌዎች አሉ።
እሱንም በትምህርት ግንዛቤ በመፍጠር እየተከላከልነው ነው። ሌላው አቅርቦቱም እንደበፊቱ አይደለም፤ ለሁሉም ተጋላጭ ለሆነ አባወራ (ማህበረሰብ) አጎበር የሚደርስበት ሁኔታ የለም። የአጎበር አጥረት አለ። ኬሚካል ከእዚህ በፊት ሀገር ውስጥ ነው የሚመረተው። አሁን ሀገር ውስጥ እየተመረተ አይደለም። ለአካባቢው ብከለት አደገኛ ስለሆነ እንደ ሀገር ኬሚካል የሚያመርት ፋብሪካ የለም። ምርቱ ከውጪ ነው በዶላር ተገዝቶ የሚመጣው።
በክልሉ የተወሰኑ ወረዳዎች ላይ (አምና አራት ወረዳ ላይ) ርጭት ተካሂዷል። ተጋላጭ የሆኑ ወረዳዎች ግን ከእዛ በላይ ናቸው። ካለው የኬሚካል እጥረት አንጻር አራት ወረዳ ላይ ነው ርጭቱ የተካሄደው። አቅርቦት ካለ አሁንም ለመሥራት ዝግጁ ነን። አጎበር አጠቃቀም ላይ ግን ያለውም የተቀደደውንም ሰፍተው እንዲጠቀሙ በሚገባ ግንዛቤ እየፈጠርን ነው።
አዲስ ዘመን፦ አኖፌለስ ስቴፈንሳይ ከምትባለው አዲሲቷ ወባ ትንኝ ለክልሉ ምን ያህል ስጋት ነው?
ዶክተር ዳመነ፦ አኖፌለስ ስቴፈንሳይ በክልላችን መኖሯ የታወቀው አምና ነው፡፡ ‹‹ሀዋሳ ከተማ ላይ አኖፌለስ ስቴፈንሳይ ከእዚህ በፊት የነበረች ነች፤ ወይስ አዲስ የመጣች ነች›› የሚለው ላይ ገና ተጨማሪ ጥናታዊ ምርምር ያስፈልጋል። የነበረውን ነው ያገኘነው ወይስ አዲስ መጣ የሚለው ገና ምርምር ያስፈልገዋል። ለምሳሌ ‹‹የስቴቨንሳይ መገኘት ማለሪያ ላይ ምንድነው አስተዋጽኦ ያደረገው›› የሚለው አልተጠናም፤ ምርምር ተደርጎ ተገቢ ጥናት ይፋ መደረግ አለበት። ይህንን ምርምርና ጥናት ለማድረግ ከኤክስፐርቶች ጋር እየተነጋገርን ነው።
ትንኟን እስከ ጄኖሚክ ድረስ እስከ ዲ ኤን ኤ ድረስ (የትንኟዋ ዲ ኤን ኤ ድረስ) መጠናት አለበት የሚለው ጉዳይ ላይ ስምምነት አድርገናል። የኢትዮጵያ ኅብረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ኢንቲሞሎጅ ቡድን የግድ መጠናት እንዳለበት ተስማምቷል። አንደኛ ‹‹ትንኟ ከሌሎቹ የወባ ዝርያዎች ጋር ምንድነው የሚያመሳስላት፤ በፊት ከነበረችው ኖርማል የወባ ወረርሽኝ ላይ አስተዋጽኦዋ ምንድነው›› የሚለው ላይ ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል።
እሱ ከተጠና በኋላ ነው ‹‹አዲሷ ትንኝ ይሄንን ያህል የወባ ወረርሽኝ አስተዋጽኦ አድርጋለች አይ አስተዋጽኦ የላትም›› የሚለው ላይ ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚቻለው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ኢንተሞሎጂ ቡድኑ ዲ ኤን ኤውን ወስዶ ቀዶ ጥገና ተደርጎ ምርምር ጀምሯል፤ በመሆኑም አጠቃላይ መረጃው ከተሠራ በኋላ ነው ይፋ የምናደርገው። ስለዚህ አዲሱ ወባ ተገኝቷል። ሆኖም ግን ‹‹በወባ ላይ ያለው አስተዋጽኦ ግን ምን ያህል ነው›› የሚለው ተጨማሪ ምርምርና የጥናት ውጤት ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ከዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ምልክቶች እንዳሉ ተረጋግጧል። ይሄን ወረርሽኝ ለመከላከል በክልል ደረጃ ምን ዓይነት ዝግጁነት አለ ?
ዶክተር ዳመነ፦ በጣም ጥሩ፡፡ እንደ ሀገር የዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) ተገኘ ከተባለበት ቀን ጀምሮ ራሳችንን በተጠንቀቅ ላይ አደርገን ለሁሉም ኅብረተሰብ ክፍል እስከ ቀበሌ ድረስ መልእክት ተላልፏል። በተለይ ኤምፖክሲ ምንድነው የሚለው ላይ፤ መተላለፊያ መንገዱ ላይ፤ ምልክቶቹስ ምንድን ናቸው፤ ሕክምናው በምን መልኩ ይሰጣል በሚለው ላይ በደንብ መልእክቶች እየተላለፉ ነው።
መልእክቱ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በብዙኃን መገናኛ፣ በደብዳቤ ለሃይማኖት ተቋማት ለሀገር ሽማግሌዎች በእኩል ለሁሉም ክፍል እንዲደርስ አድርገናል። እሱ ብቻ ሳይሆን እንደ ክልልም ምንድነው ማድረግ ያለብን የሚለውን ከሚመለከታቸው ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመነጋገር አንድ ትልቅ ማዕከል አዘጋጅተናል። ከእዚህ ቀደም በተፈጠረ ወረርሽኝ (ከኮቪድ) ብዙ ነገር ስለተማርን የዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ወይንም ወረርሽኝ ሆኖ ከሰፋ ስለሚወሰዱ የጥንቃቄና የመከላከያ ዘዴዎች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተነጋግረን አጋር ድርጅቶችን ጠርተን ትልቅ ማዕከል አዘጋጅተናል።
ከእዚህ ቀደም የሲዳማ ዞን ጤና ቢሮ የነበረው ግቢ እድሳት ተደርጎበት የሕክምና ቁሳቁስ ገብቶ ባለሙያ መድበን ዝግጅት አድርገናል። እነዚህ ምልክት ያለባቸው ሰዎችን በሙሉ ናሙናው ሄዶ ኔጌቲቭ እስከሚባል ድረስ እዛው ይቆያሉ። ከእዛ በኋላ ከቆዳ ሐኪም ጋር ተነጋግረን ሌላ በሽታ ከሆነ ወይም ኤምፖክስ ካልሆነ የግድ ሌላ ስለሆነ ያንን ከቆዳ እስፔሻሊስት ሐኪሞች ጋር እየተነጋገርን ሕክምና እያገኙ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እናደርጋለን።
ሀዋሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን በሁሉም በክልሉ ከሆስፒታል እስከ ጤና ጣቢያ ድረስ የለይቶ ማቆያ (አይሶሌሽን ሴንተር) እና ማከሚያ ተቋም ተደራጅቷል። በእዛውም ልክ በማግስቱ ወዲያው ወደ አምስት መቶ እና ከእዛ በላይ ለሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመነጋገር የአንድ ቀን ኦሬንቴሽን ሠተናል። በሽታውን ቶሎ ለመቆጣጠር በሚል ሥልጠና ሰጥተን የለይቶ ማቆያ ማእከል በየወረዳው በየጤና ጣቢያው እንዲዘጋጅ አድርገናል። ሌላው ትልቁ ተግባር መከላከሉን ለማጠናከር እየተሠራ ያለው ሥራ ቅኝት ነው። በመሆኑም ቅኝት ይደረጋል።
የዝንጀሮ ፈንጣጣ (MPox) በትክክል መከሰቱን ለማወቅ ቅኝት ማድረጉ ተገቢ ነው። ምክንያቱም በአንዳንድ ሰዎች ላይ የሚታየው ምልክት ሌላ ሽፍታ ሊሆን ይችላል፤ አለርጂክ ሊሆን ይችላል። ይሄ ምልክት እየተለየና ናሙና እየተወሰደ በክራይቴሪያው መሠረት ‹‹ኤምፖክስ ነው፣ አይደለም›› የሚለውን በቅኝት የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው። በእዚህም በተደረገ ቅኝት እስከ ትናንትና ድረስ ሃያ ስድስት ናሙና (ኬዞችን) ነው የወሰድነው። በእዚህ ቅኝት ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ ኔጌቲቭ ውጤት ነው የተገኘው።
አሁን የአንዱ ብቻ ውጤት ነው የሚቀረው ሌሎቹ አብዛኛው ኔጌቲቭ ነው። በክልሉ በቦረቻ ወረዳ ላይ አንድ ሕጻን ብቻ ፖዘቲቭ ነበር፤ እሱም አስፈላጊው ክትትልና ሕክምና ተደርጎለት ወደ ቤቱ ተመልሷል። እስካሁን ያለው ውጤት ኔጌቲቭ ቢሆንም ግን በዋናነት መከላከል ላይ ሕዝቡ ግንዛቤ አግኝቶ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በሰፊው እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፦ መስማት የተሳናቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መረጃን አግኝተው ከእንዲህ ዓይነት ወረርሽኞች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ምን መሠራት አለበት፤ እንደ ክልል ምን ዓይነት ስልት እየተከተላችሁ ነው?
ዶክተር ዳመነ ፦ አዎ ልክ ነው። እንደ ሀገር የእዚህ ዓይነት ችግር መሠረታዊ በሆነ መንገድ ክፍተቶች አሉ። እንዳልከው ግን ለምሳሌ በሲዳማ ክልል ‹‹መስማት የተሳናቸው ሰዎች የት ነው አብዛኛው ያሉት፤ ገጠር ከሆነ የትኛው በየትኛው ሚዲያ ነው እነዚህ ሰዎች መድረስ ያለብን›› የሚለው ላይ መገናኛ ብዙኃንን መምረጥ መቻል አለብን። ለምሳሌ በቴሌቪዥን መልእክት እናስተላልፍ ካልን ቴሌቪዥን በየገጠሩ የለም። በየቤቱ እንደ ግለሰብ ላይኖር ይችላል። ስለዚህ ማድረግ ያለብን እንደ አማራጭ ቅኝቱን ተመሳሳይ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ላይ በማድረግ ለቤተሰቦቻቸው ምልክቶች በማስረዳት ጥንቃቄ እንዲደረግ እየሠራን ነው።
ምልክቶቹ ሲታወቁ ቤተሰብ እነዚህን የተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲደግፉ ማድረግ ይቻላል። በቤተሰብ በኩል ምርመራ እና ሕክምና እንዲያደርጉ ይደረጋል። ሆኖም በከተማ ከሆነ ግን አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ሊደርሰው የሚችልባቸውን ቦታዎች እንጠቀማለን።
አዲስ ዘመን፦ የወረርሽኝ በሽታዎች መከሰት አለመከሰታቸው ለማእከል በምን መልኩ ነው ሪፖርት የሚደረጉት?
ዶክተር ዳመነ፦ የራሱ ቅኝት ሲስተም አለው። የመጀመሪያው የቤት ለቤት ቅኝት ነው። ሌላው ደግሞ የነጻ ስልክ መስመር አለ። በራሳችን የድረ ገጽ ወይንም የነጻ ስልክ መስመር ሕዝቡ መረጃ ይሰጣል። በተመሳሳይ ደግሞ የታችኛው መዋቅር ላይ የራሳችን የተቀመጡ ሰዎች አሉ። የተወከሉት ሰዎች በየቀኑ (በሃያ አራት ሰዓት) ሪፖርት የሚደረጉትን በሽታዎች ወዲያው ሪፖርት ያደርጋሉ። በየሳምንቱ የሚደረጉትን ደግሞ በየሳምንቱ ሪፖርት ያደርጋሉ። በእዚህ መንገድ ነው እየሠራን ያለነው።
አዲስ ዘመን፦ በክልሉ ባሉ የጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦቱ እና ተደራሽነቱ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ዳመነ፦ የወባ መድኃኒት ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው በነጻ ነው፡፡ እጥረቱን እንግዲህ ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ከጤና ሚኒስቴር ጋር እንደውም ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ድርጅት ጋር በመነጋገር ተፈቷል። አምና ወረርሽኙ እንደ ሀገርም ስለነበረ፤ ጫናው በተለይ የወባ ወረርሽኙ ከፍተኛ ስለነበረ ፕሪማኩን የሚባለው መድኃኒት እጥረት ነበረ። ሆኖም ግን በመንግሥት በኩል በሰፊው ሥራ ተሠርቶ አቅርቦቱ ተሻሽሏል።
አንደኛ መድኃኒቱ በነጻ ነው የሚሰጠው፤ ስለዚህ በእኛ በኩል የክልሉ ክምችት በቂ ነው፤ ቅድም እንዳልኩት ከአምናው ጋር ስናነጻጽረው ወባ ቀንሷል ማለት ይቻላል። እሱንም ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም አለ። በመሆኑም እየታየ ያለው ውጤት ጥሩ ነው ብዬ አስባለው።
አዲስ ዘመን፦ ከተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የኢንስቲትዩቱ የምርምር አስተዋጽኦ ምን ይመስላል፤ የቫይታሚን ዲ አጥረትን ለመቀነስ ምን ርምጃዎች እየወሰዳችሁ ነው?
ዶክተር ዳመነ፦ የምግብ እጥረት ልየታ በየወሩ ይካሄዳል። ሁሉም ጋር ሳይሆን በተለይ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል። በእነዚህ አካባቢዎችም ቢሆን ተለይቶ እየተሠራ ነው። እነዛ ተጋላጭ የሆኑ ወረዳዎች በተለይ ቆላማ አካባቢና አልፎ አልፎ ደግሞ ከደጋማ ወረዳዎች ይገኛሉ። በእነዚህ ላይ በየወሩ ልየታ ይደረጋል። በልየታው የሚገኙ ተኝተው የሚታከሙት ተኝተው እንዲታከሙ፤ እየተመላለሰ የሚታከም ደግሞ እየተመላለሰ እንዲታከም ይደረጋል።
ሌላው በቤተሰብ ምክር ተጨማሪ ምግቦችን ቤተሰብ እንዲያቀርብ እየተደረገ ክትትል የሚደረግላቸው ሕጻናቶች አሉ። በእርግጥ እጥረቱ ከአምናው የበለጠ አይደለም። የተረጋጋ ሆኖ እየሄደ ነው። እኛም በእዚህ ላይ በደንብ እየሠራን ነው። በተለይ ጂአይዜድ (የጀርመን ድርጅት) በኒዩትሪሽን ኢንፎርሜሽን ፕላትፎርም ፎር ኒዩትሪሽን በሚል ፕሮጀክት አለ። በፕሮጀክቱ አጠቃላይ ክልሉ ውስጥ ያለው የሥነ ምግብ የአመጋገብ ሥርዓት ምን እንደሚመስል እየተጠና ነው።
አሁን ስድስት ወር ሆኖታል።
ከመሠረቱ ችግሩን ለመፍታት ከአመለካከት ጀምሮ በእጃችን ያለውን ነገር ለመጠቀም እየሠራን ነው።
ለምሳሌ ከእንቁላል ስንጀምር የገጠሩ ኅብረተሰብ ቤት ለልጆቹ ከመስጠት ይልቅ ወደ ገበያ ይዞ የመምጣት ዝንባሌ ስላለው በእጃችን ያለውን ነገር ፕሮቲንም ሆነ ካርቦሀይድሬት ቪታሚን የሚተኩ በቀላሉ የሚያገኛቸውን የምግብ ዓይነቶች አጠቃቀም ላይ መሻሻል እንዲያሳይ እየተሠራ ነው። ይህንን ፕሮጀክት በደንብ ከምሁራን ጋር (ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር) ሆነን አብረን በጥምረት እያጠናን ነው።
አዲስ ዘመን፦ ከእናቶች ጤና ጋር በተያያዘ የምትሠሩት ሥራ ምንድን ነው። በተለይ ከወሊድ ክትትል እና ከፎሊክ አሲድ አጠቃቀም ጋር የክልሉ ሁኔታ ምን ይመስላል?
ዶክተር ዳመነ፦ የእናቶች ጤና ጋር ተያይዞ ያለው ነገር በተለይ በጤና ተቋማት ነፍሰጡር እናቶች ክትትል እንዲያደርጉ ይበረታታል። በአሁኑ ሰዓት በክልሉም በክትትል ወቅት ብቻ ሳይሆን እዛው ጤና ተቋም ውስጥ እንዲወልዱ የማድረግ ሥራ በጣም ውጤት እያመጣ ነው። ክትትሉም ዘጠና አምስት በመቶ በላይ ነው። ክትትሉ የእናቶች በእርግዝና ወቅት የሚደረግ የእርግዝና ክትትል ጠንካራ ነው።
በክትትሉ ሰዓት በየደረጃው በየወሩና በየወቅቱ የሚሰጣቸው ቪታሚኖች አሉ፤ ክትባት አለ። ለምሳሌ አይረን፣ ፎሊክ አሲድ በተለይ ከፅንስ ጋር ያልተፈለገ ወይም ጤናማ ያልሆነ ፅንስ እንዳይፈጠር ለመከላከል የሚረዳ ነው።
ለምሳሌ ፎሊክ አሲድ እንደ ሀገር እጥረት እንዳለ ይታወቃል። በተለይ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባጠናነው ጥናት ላይ የአዮዲን እጥረት ስለነበረ ጨው አዮዲን ተጨምሮና ተደባልቆ ነው እየቀረበ ያለው። ፎሊክ አሲድም እንደ እዛው ነው። ለእናቶች እንደ ጨውም እንደ አዮዲን ያለው ጨው እንደተዘጋጀው በእዛው በተመሳሳይ ፎሊክ አሲድም ፎርቲፋይ እየተደረገ ነው። እስከእዛ ግን በእንክብል መልክ የሚሰጥ ፎሊክ አሲድ በየጤና ተቋሙ በነጻ እየቀረበ ነው። አይረንም እንደእዛው ደማነስ እንዳይከሰት በእርግዝና ወቅት እሱም በተገቢው አቅርቦቱ አለ።
በዋናነት ግን እናቶች ከቤት ይልቅ ጤና ተቋም መጥተው መውለድ እንዳለባቸው በጤና ተቋም ክትትል እንዲያደርጉ በተደረገው ሰፊ ርብርብ በየወረዳው በየጤና ጣቢያው ላይ የተዘጋጀው የእናቶች ማቆያ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። እንደ ክልል የተሻለ ነገር አለ ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የመጪው ዓመት ጥናት ምርምር ልዩ የትኩረት አቅጣጫ ምንድን ነው?
ዶክተር ዳመነ፦ እንደ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዘንድሮ በሲዳማ ክልል የሽንት ቤት አጠቃቀም እና ሽፋኑ ምን ይመስላል በሚለው ላይ አጥንተናል። አምና እና ካቻአምና ኮሌራ አስቸግሮ ስለነበረ ትኩረታችን የነበረው የሃይጂን ሳኒቴሽን ወይም የሽንት ቤት አጠቃቀም ላይ ነበር። እና እሱ ላይ አጥንተን ወደ ሥራ እንዲገቡ ለጤና ቢሮ ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበናል። ዘንድሮ የተጀመረና 2018 ዓ.ም ላይ የሚጠናቀቅ የወባ ጥናት አለ።
የወባ ጫና በሲዳማ ክልል ውስጥ በሚል በሦስት ክፍል የተከፈለ ጥናት ብቻ ሳይሆን እንደ ፕሮጀክት እየተሠራ ነው። ፕሮጀክቱ ትላልቅ ጥናቶች አሉት፤ እነዚህ ወረዳዎች በሦስት ቦታ ተከፍሎ የክልሉ ወረዳዎች አካባቢ ለወባ በጣም ከፍተኛ ተጋላጭ መሀከለኛ ተጋላጭ እና ዝቅተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ኅብረተሰብ ክፍሎች ተብሎ በሦስት ተከፍሎ ጥናት ተጀምሯል። ይህ ፕሮጀክት ትልቅ ነው። በጥቅሉ ለኢትዮጵያም ምሳሌ የሚሆን ነው ብለን እናስባለን። በቀጣይ እንግዲህ እሱ ላይ ሰፊ ርብርብ አድርገን ያለንን አቅም እና ሪሶርስ እንጠቀማለን። ወባ ላለፉት ሁለት ዓመታት ኅብረተሰባችን ላይ ጫና እየፈጠረ ስለሆነ በጥናት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት እና ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት በደንብ እየሠራን ነው።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም