
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ታሪክ አንጋፋ ከሆኑ መድረኮች አንዱ በጀግናውና ታሪካዊው አትሌት የተሰየመው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ተጠቃሽ ነው። በርካታ የረጅም ርቀት አትሌቶችን በማፎካከር የሚታወቀው ይህ ዓመታዊ የአርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ፉክክር ትናንት ለአርባ አንደኛ ጊዜ በሃዋሳ የተካሄደ ሲሆን በኢትዮ ኤሌክትሪክና እና በመቻል አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቋል።
በወንዶች ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ15 ነጥብ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ዋንጫ ሲሸለም፣ መቻል በ29 ነጥብ ሁለተኛ፣ ፌዴራል ፖሊስ በ73 ነጥብ ሦስተኛ ሆኗል። በሴቶች ደግሞ መቻል በ16 ነጥብ የዋንጫ አሸናፊ ሲሆን፣ ኦሮሚያ ፖሊስ በ62 ነጥብ ሁለተኛና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ72 ነጥብ ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።
ብርቱ ፉክክር በታየበት ውድድር በወንዶች አትሌት ገመቹ ያደሳ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ቀዳሚ በመሆን ሲያጠናቅቅ፤ ጋዲሳ አጀባ ከመቻል እንዲሁም አሰፋ ተፈሪ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን ፈፅመዋል። በዚህም መሠረት ኢትዮ ኤሌክትሪክ የወንዶቹ ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ መሆን ችሏል።
በተመሳሳይ በሴቶች መካከል በተደረገው ፉክክር አትሌት መሠረት ገብሬ ከኦሮሚያ ክልል የውድድሩ አሸናፊ በመሆን አጠናቃለች። አትሌት አሹማር ዘመናይ እና አትሌት አዝመራ በየነ ከመቻል ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን ፈፅመዋል።
ከ50 ዓመት በላይ አንጋፋ አትሌት ባደረጉት ውድድር በወንዶች ስዩም ደበሌ አሸናፊ ሲሆን፣ ገዛኸኝ ገብሬና አያሌው እንዳለ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነዋል። በአንጋፋ ወንዶች ከ50 ዓመት በታች ፉክክር ደግሞ በቀለ ረታ፣ ጋዲሳ ገረመው፣ አሰፋ ጥላሁን ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
በተመሳሳይ በአንጋፋ ሴቶች ከ50 ዓመት በታች ውድድር አበሩ ዘውዱ ቀዳሚ ስትሆን፣ እህተብርሃን አዳሙና አይሻ ኑር ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘው ጨርሰዋል።
ዓምና በተመሳሳይ በሃዋሳ በተካሄደው 40ኛው የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታ የኦሮሚያ ፖሊስ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል። በዚያ ውድድር በወንዶች የተካሄደውን ፉክክር አትሌት ጎሳ አምበሱ ከኦሮሚያ ፖሊስ በቀዳሚነት ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን፣ አትሌት ጊዜው አበጀ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛ እንዲሁም አትሌት ሳህለሥላሴ ንጉሤ ከኦሜድላ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ነበር የፈፀሙት። በተመሳሳይ በሴቶች መካከል የተካሄደውን ውድድርም አትሌት ኩረኒ ጀሊላ ከኦሮሚያ ፖሊስ አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ አትሌት ሙሉሀብት ፀጋ ከኦሜድላ እንዲሁም አትሌት ያደኒ ዓለማየሁ ከኦሮሚያ ፖሊስ ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመሆን ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።
በየዓመቱ በድምቀት በሚደረገው በዚህ የማራቶን ውድድር ዘንድሮ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች እና ክለቦች የተውጣጡ አትሌቶች እንደተሳተፉበት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሳውቋል። ሰባ ያህል ዳኞች በመሩት የዘንድሮው ዓመት የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን አንጋፋና የግል ተወዳዳሪ አትሌቶችን ጨምሮ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከአስር ክለቦች የተውጣጡ 94 ሴት፣ 288 ወንድ በአጠቃላይ 364 አትሌቶች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።
የውድድሩ ዓላማ ለክልል፣ ለከተማ አስተዳደሮች፣ ለክለቦችና ለግል የማራቶን ተወዳዳሪ አትሌቶች የሀገር ውስጥ የውድድር ዕድል ለመፍጠር፤ በክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ በክለቦች ወዘተ… መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲያገኙ ዕድል ለመፍጠር እና ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት እንደሆነ ተገልጿል።
በማራቶን ውድድሮች አቅማቸውን ለማሳየት እድል ላላገኙ አትሌቶች እድል ለመስጠት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ አትሌቶችን ለማግኘት ተመሳሳይ እና አማራጭ የሀገር ውስጥ የሙሉ ማራቶን የውድድር ሌላ መድረክ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም