
– 15 ሺህ 960 ፕሮጀክቶች ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ተደርገዋል
አዲስ አበባ፦ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን የመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ትኩረት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። በአዲስ አበባ 15 ሺህ 960 ፕሮጀክቶች ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ተደርገዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ትናንት ፕሮጀክቶቹን ለአገልግሎት ክፍት ሲያደርጉ እንዳስታወቁት፤ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የተገነቡ አጭር እና አቋራጭ መንገዶች፤ የትራፊክ ማሳለጫ ተሻጋሪ ድልድዮች የትራፊክ ፍሰትን በማቀላጠፍ እና ፕሮጀክቶችን በማያያዝ ለነዋሪው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገት ጉልህ ድርሻ ያላቸው ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ ከ50 እስከ 60 ስፋት ያላቸው ድልድዮች፤ እስከ 300 ሜትር ርዝመት ያላቸው ግዙፍ መንገዶች ያካተቱ መሆናቸውን ገልጸው፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን የመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
በአዲስ አበባ 15 ሺህ 960 ፕሮጀክቶችን ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ማድረጋቸውን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከውጪ በሚገኝ ብድር ይገነባል ተብሎ የተጀመረ ቢሆንም ብድሩ ሳይገኝ ቀርቶ በከተማ አስተዳደሩ አቅም መገንባታቸውን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹን ለመገንባት ከተማ አስተዳደሩ የአስተዳደር ወጪዎችንና የበጀት ብክነትን በመቀነስ እንዲሁም ሁሉንም የገቢ አማራጮች በመጠቀም መንቀሳቀሱን ገልጸው፤ በግንባታ ወቅት ጥቂት የወሰን ማስከበር ተግዳሮቶች ቢኖሩም ማህበረሰቡ ባደረገው ትብብር ውጤታማ መሆን መቻሉን አስታውቀዋል ።
በጥሩ ሁኔታ የተገናኘ የመንገድ መሠረተ ልማት የጉዞ ጊዜን፣ የትራፊክ መጨናነቅን እና አማራጭ የመጓጓዣ ዘዴዎች እንደሚፈጥር ገልጸው፤ በተለይ የወጪና ገቢ ንግድ መስመር በሆኑት የቃሊቲ – ቱሉ ዲምቱ እና የቂሊንጦ – ቃሊቲ መንገዶች ላይ የተገነቡት ድልድዮች የከተማዋ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክቱ ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ይነሱ የነበሩ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን መፍታት እንዳስቻሉ ገልጸው፤ ከተማ አስተዳደሩ የኢትዮጵያ የብልፅግና ተምሳሌት ለመሆን በሚያደርገው ጥረት የመንገድ መሠረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች የተገነቡ መንገዶችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ አደራ ብለዋል።
በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ፕሮጀክቶቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የበኩላቸውን ድርሻ ላበረከቱ የአዲስ አበባ ከተማ መንገድ ባለስልጣን፤ የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪ ድርጅቶች እና የአቃቂ ቃሊቲና የቦሌ ክፍለ ከተማ አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።
ከተመረቁት የመንገድ መሠረተ ልማቶች መካከል ከአጉስታ- ወይራ መጋጠሚያ፣ ቱሉ ዲምቱ ኮንዶሚኒየም መቃረቢያ፣ ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ – በአቃቂ ድልድይ-ቱሉ ዲምቱ አደባባይ፣ ከቃሊቲ ቀለበት መንገድ አደባባይ ቡልቡላ-ቂሊንጦ 2ኛ ቀለበት መንገድ አደባባይ፣ የለቡ አደባባይ ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ ከአፍሪካ ህንፃ- ጀሞ መስታወት ፋብሪካ፣ ከቂርቆስ ማርገጃ – ቡልጋሪያ፣ ከቤላ -ፈረንሣይ ፓርክ – ፈረንሣይ አቦ ቤተክርስቲያን፣ ከናሰው ሪል ስቴት አርሴማ ቀለበት መንገድ እና ዮናስ ሆቴል ኬብሮን ፋርማሲ አስፋልት መንገዶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም