
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ፤ አሜሪካ ላቀረበችው የ60 ቀናት የጋዛ የተኩስ አቁም እቅድ አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱን አስታውቋል። ቡድኑ ባወጣው መግለጫ፣ በተኩስ አቁም እቅዱ ያለውን አቋም ለአሸማጋዮቹ ግብጽና ኳታር አሳውቋል። ‹‹ንቅናቄው ምላሹን ለአደራዳሪዎቹ ገልጿል። ምላሹ አዎንታዊ መንፈስ አለው። ሃማስ ወደ አዲስ የደርድር ምዕራፍ ለመግባት ሙሉ ዝግጁነት አለው›› ብሏል።
ውይይቱን በቅርበት የሚከታtሉ አንድ የፍልስጤም ከፍተኛ ባለስልጣን እንደተናገሩት፣ ሃማስ አጠቃላይ የተኩስ አቁም ማሕቀፉን ቢቀበልም በርካታ ቁልፍ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ጠይቋል። ከነዚህም መካከል ለ20 ወራት የዘለቀውን ጦርነት በዘላቂነት ለመቋጨት የታሰበው ድርድር ካልተሳካ አሜሪካ የእስራኤል ጥቃት እንደማይቀጥል ዋስትና ልትሰጥ ይገባል የሚለው አንዱ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃማስ በአሜሪካ አደራዳሪነት ለቀረበው የጋዛ የተኩስ አቁም ዕቅድ ‹‹በቀና መንፈስ ምላሽ ሰጥቻለሁ›› ማለቱ መልካም እንደሆነ ተናግረዋል። በሚቀጥለው ሳምንት በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊደረስ እንደሚችልም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል። የእስራኤል ባለስልጣናት የሃማስን ምላሽ መቀበላቸውንና ቡድኑ ያቀረበውን ሃሳብ እየተመለከቱት እንደሆነ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በዕቅዱ መሠረት ሃማስ 10 የእስራኤል ታጋቾችን እና የ18 ታጋቾችን አስክሬን ለእስራኤል ሲሰጥ በምትኩ በእስራኤል እስር ቤት ያሉ ፍልስጤማውያን ይለቀቃሉ። በተኩስ አቁሙ የመጀመሪያው ቀን ሃማስ ስምንት እስረኞችን እንዲለቅ ይጠበቃል።
በጋዛ እስካሁን 50 ታጋቾች ሲኖሩ ከነዚህም ውስጥ 20ዎቹ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል። በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንና የፍልስጤም የቀይ ጨረቃ ማኅበርን በማሳተፍ በቂ መጠን ያለው የሠብዓዊ ርዳታ ወዲያውኑ ወደ ጋዛ መግባት እንዲችል በስምምነት ዕቅዱ ውስጥ ተጠቅሷል።
ስምምነቱ ከተጀመረ በኋላ እስራኤል ወታደራዊ ዘመቻዋን ታቆማለች። በቀን ለ10 ሰዓታት ያህል በጋዛ ሰማይ ላይ ወታደራዊና የስለላ በረራዎች አይከናወኑም፤ የእስረኞች ልውውጥ በሚደረጉባቸው ቀናት ደግሞ የበረራ እቀባው ወደ 12 ሰዓታት ከፍ ይላል። የሁሉንም ታጋቾች መለቀቅን፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ መውጣትን፣ የወደፊት የጋዛ የፀጥታ ሁኔታንና አጠቃላይ የጋዛ እጣ ፋንታን ያጠቃለለ ዘላቂ የተኩስ አቁም ድርድር በአሸማጋዮች አማካኝነት ይጀመራል።
ሃማስ ርዳታው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በአጋሮቹ ብቻ እንዲከፋፈል እና በእስራኤልና በአሜሪካ በሚደገፈው የጋዛ ሠብዓዊ ፋውንዴሽን የሚመራው አወዛጋቢ የርዳታ ክፍፍል በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል። በተጨማሪም ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ባይሳካ እስራኤል በተቀናጀ ሁኔታ በምድር እና አየር ላይ በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት እንደማትጀምር አሜሪካ ዋስትና እንድትሰጣቸውም ሃማስ መጠየቁ ተገልጿል።
ሌላው ሃማስ የጠየቀው ቁልፍ ማሻሻያ የእስራኤል ወታደሮች ከተቆጣጠሯቸው የጋዛ አካባቢዎች እንዲወጡ ነው። የእስራኤል ጦር የመጨረሻው የተኩስ አቁም ስምምነት ከመፍረሱ በፊት ወደነበረበት ስፍራ እንዲመለስ ሃማስ አጥብቆ ጠይቋል።
የአሜሪካ ዕቅድ የእስራኤል ወታደሮች ከያዟቸው የሰሜን እና የደቡብ ጋዛ ይዞታዎች በምዕራፍ መውጣታቸውን ያካትታል ተብሎ ይታመናል። ሆኖም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ‹‹ታጋቾች በሙሉ እስከሚለቀቁ እና የሃማስ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም እስኪንኮታኮት ድረስ ጦርነቱን አናቆምም›› ሲሉ ተደምጠዋል።
‹‹ሮይተርስ›› የዜና ወኪል ሁለት የእስራኤል ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የተኩስ አቁም እቅዱ ዝርዝር ነጥቦች ውይይት እየተደረገባቸው ነው። በሌላ በኩል እስራኤል፤ ሃማስ ትጥቅ ካልፈታና አመራሮቹም ጋዛን ለቀው ካልወጡ ወታደራዊ ርምጃዋን እንድትቀጥል የሚያስችል የጽሑፍ መተማመኛ ዋስትና ከፕሬዚዳንት ትራምፕ እየጠየቀች ነው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስራኤል በጋዛ የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማድረግ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት እንደተስማማች ከቀናት በፊት መናገራቸው ይታወሳል። ‹‹ሃማስ ይህን ስምምነት ይቀበላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም የተሻለ አይሆንም፤ እየባሰ ነው የሚሄደው›› ብለዋል። ሃማስ ‹‹የመጨረሻው ዕቅድ›› ሲሉ የጠሩትን ይህንን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲቀበል አስጠንቅቀውም ነበር።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር የተኩስ አቁም እቅዱ ከካቢኔውም ከሕዝቡም ድጋፍ እንዳገኘ ተናግረዋል። የተቃዋሚው መሪ ያኢር ላፒድ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የተኩስ አቁም እቅዱን እንዲቀበሉ የሚያስችላቸውን ድጋፋቸውን ገልፀዋል።
የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን-ግቪር ከገንዘብ ሚኒስትሩ ቤዛሌል ስሞትሪች ጋር በመሆን የተኩስ አቁም እቅዱን መቃወማቸው ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ለስሞትሪች ቅርብ የሆኑ ሰዎች ግን ቤን-ግቪር እቅዱን ለመቃወም ከስሞትሪች ጋር አብረዋል መባሉን አስተባብለዋል።
እስራኤል በአሜሪካ፣ ኳታር እና ግብፅ አደራዳሪነት የተፈረመውና ለስድስት ሳምንታት የዘለቀው የተኩስ አቁም አብቅቶ በመጋቢት ወር አጋማሽ ዳግመኛ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ እንዳሰበችው የቀሩትን እስራኤላውያን ታጋቾችን ማስለቀቅ አልቻለችም። ከእገታ የተለቀቀው ኢዳን አሌክሳደር የተባለው እስራኤላዊ-አሜሪካዊ ወታደር ብቻ ነው። ሃማስ ታጋቹን የለቀቀው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እያደረጉት ላለው ጥረት እውቅና ለመስጠት እንደሆነ ገልጾ ነበር። ወደ 50 የሚጠጉ የእስራኤል ታጋቾች አሁንም በጋዛ ይገኛሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ ቢያንስ 20 ያህሉ በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።
እስራኤል እና ሃማስ ተኩስ ለማቆም በየፊናቸው ያስቀመጧቸው ቅድመ ሁኔታዎች የተራራቁ ሆነው ይታያሉ። እስራኤል ሃማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ ትፈልጋለች፤ ሃማስ በበኩሉ እስራኤል ጠቅልላ ከጋዛ እንድትወጣ ይፈልጋል። ተባብሶ በቀጠለው የጋዛ ጦርነት በርካታ ንጹሃን በየቀኑ እየሞቱ እንደሆነና አስከፊ ሠብዓዊ ቀውስ እንደተከሰተም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል ባለፈው ጥር 11 ቀን ተጀምሮ ለስድስት ሳምንታት ከዘለቀ በኋላ በመጋቢት ወር አጋማሽ የፈረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ሦስት እርከኖች እንዲኖሩት ሆኖ የተቀረጸ ቢሆንም የመጀመሪያውን ደረጃ እንኳን ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። የዚህ ስምምነት ሁለተኛው ደረጃ ቋሚ የተኩስ አቁም ላይ መድረስን፣ በእስራኤል ውስጥ ለታሰሩ ፍልስጤማውያን ምትክ በጋዛ ታግተው የነበሩትን እስራኤላውያን መልቀቅን እና የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ መውጣትን ያካትት ነበር።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም