ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ ያወጣችው ገንዘብ ከ12 በላይ ግድቦች መገንባት የሚያስችል እንደሆነ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡-ኢትዮጵያ በ36 ዓመታት ለወደብ ኪራይ ያወጣችው ገንዘብ እንደ ህዳሴ ግድብ አይነት ከ12 በላይ ግድቦችን ሊገነባ እንደሚችል የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪ አቶ ሰለሞን ተፈራ አመለከቱ ።

በ5ኛው የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ ምርምር ኮንፍረንስ፤ በአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ ያላትን ብሄራዊ ጥቅም በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ሰለሞን ተፈራ ለአዲስ ዘመን እንዳመለከቱት፤ ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ለወደብ ኪራይ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ትከፍላለች። በዚህ ሁኔታ ለ36 ዓመታት ስትከፍል የቆየች ሲሆን፤ እስካሁን የከፈለችው ወደ 72 በሊዮን ዶላር ይደርሳል።

ህዳሴ ግድብ በአምስት ቢሊዮን ዶላር እየተሠራ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ሰለሞን፤ በእነዚህ ዓመታት ለህዳሴ ግድቡ የወጣው ወጪ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ቢደረግ ከ12 በላይ ተመሳሳይ ግድቦችን ማሠራት የሚችል እንደሆነ አስታውቀዋል። ይህም ሀገሪቱ የባሕር በር ማጣቷ ትልቅ የኢኮኖሚ ቀውስ እያስከተለ ስለመሆኑ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ ሰለሞን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር 30 እስከ 40 ኪሎ ሜትር ትርቃለች ከአንዳንድ ሀገሮች ደግሞ ከ120 እስከ 700 ኪሎ ሜትር የምትርቅበት አጋጣሚ አለ። ሌሎች የምዕራብ ሀገራት ያላቸው ርቀት ሲታይ አሜሪካ 10ሺህ ፤ ፈረንሳይ 4ሺህ 300፤ ብሪታኒያ አምስት ሺህ ኪሎ ሜትር ይርቃሉ። ነገር ግን ጅቡቲ ላይ የወታደር ካምፕ እንዲሁም የንግድ ማእከል አላቸው።

ሀገራቱ ከ10 ሺህ ኪሎ ሜትር መጥተው በወታደር ካምፕ እና ለንግድ ማእከል በአካባቢው ኢንቨስት ሲያደርጉ፤ ኢትዮጵያ ግን 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆና ተጠቃሚ መሆን ሳትችል መቅረቷን አመልክተዋል።

ቀይ ባሕር ሶስት አህጉራትን የሚያገናኝ፤ ከዓለም ስትራቴጂክ ቦታዎች አንዱ እንደሆነ ገልጸው ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት አለመሆኗ፤ ከገልፍ ኦፍ ኤደን፤ ከሲውዝ ካናል፤ ከህንድ ውቂያኖስ እና ከሌሎች ባሕሮች ጋር እንዳትገናኝ አድርጓታል ብለዋል። ቦታዎቹ ካለቸው ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አኳያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የደህንነት ውድድሮች የሚደርግባቸው ናቸው፤ ይህም በራሱ የኢትዮጵያን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከውሃ ፖለቲካ አንጻር ሲታይ ጅቡቲን ጨምሮ አብዛኞቹ ጎረቤት ሀገራት የዓረብ ሊግ አባላት ናቸው ያሉት አቶ ሰለሞን፤ የዓረብ ሊግ ሀገራት የአባል ሀገራትን ፍላጎት የማስከበር ግዴታ እንዳለባቸው የተቀመጠ ውል አለ፤ ይህ ደግሞ በአስቸጋሪ ወቅት እንደ ሀገር ትልቅ የህልውና አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ገልጸዋል።

የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመጠቀም የባሕር በር ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሰለሞን፤ የመጀመሪያ ሰጥቶ መቀበል መርህ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋ። ለዚህም ጎረቤት ሀገራት በሀገሪቱ ሜጋ ፕሮጀክቶች ውስጥ ድርሻ እንዲኖራቸው ማስቻል አንድ አማራጭ እንደሆነ አስታውቀዋል።

እንደ ማሳያም፤ በታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚገኘውን የሃይል አቅርቦት የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር፤ በሰላማዊ መንገድ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መንገድ የባሕር በር ማግኘት እንደሚቻል አመልክተዋል።

ሀንጋሪ፤ ኔፓል፤ ቻድ፤ ካዛኪስታ እና ሌሎች በርካታ ሀገራት የዓለም አቀፍ ሕግ ተጠቅመው የባሕር በር ማግኘታቸውን በማንሳት፤ የዓለም አቀፍ ሕጎችን መጠቀም አስፈላጊ ነው። ከምንም በላይ ግን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር ተገቢ መሆኑ ጠቁመዋል።

የባሕር በር ጉዳይ ትልቁ ሁሉንም ዜጋ በአንድነት የሚያሰልፍ ብሄራዊ ጥቅም መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሰለሞን፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ የሲውዝ ካናልን በነጻ መጠቀም አለባት የሚል መግለጫ ሲያወጡ፤ በግብጽ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በጠላትነት የሚተያዩ ግብጻውያን ሳይቀሩ በአንድ ላይ ቆመው የትራምፕን ሃሳብ መቃወማቸውን በምሳሌነት አስታውሰዋል።

በፖለቲካ ዓለም፤ ፓርቲዎች የሚወዳደሩት ጉዳይ እና የሚተባበሩበት ጉዳይ አለ። የብሄራዊ ጥቅም ዋናው የሚተባበሩበት ጉዳይ ነው፤ የባሕር በር ደግሞ ትልቁ የብሄራዊ ጥቅማችን ስለሆነ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You