የኢኮኖሚ የስበት ማዕከሏ – ሸገር

ዜና ሀተታ

የተለያዩ አገልግሎቶችን በውስጡ በማካተት ለሀገር ውስጥ እንዲሁም ዓለምአቀፍ ጉባዔዎችን ለማከናወን ምቹ ሆኖ በተገነባው በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል አዲስ ነገር አለና በርካቶች በስፍራው ተገኝተዋል።

አዲሱም ነገር በአዲሲቷ የሸገር ከተማ አስተዳደር አዳዲስ ሃሳብ የያዙ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሳተፉ ባለሀብቶችን ለማበረታታት፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እና አዳዲስ ተጨማሪ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የሚያስችል ሸገር የኢንቨስትመንት ኤክስፖ በዚህ ታላቅ ማዕከል መዘጋጀቱ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ባጸደቀው ደንብ መሠረት ሸገር ከተማ አስተዳደር 160 ሺህ ሄክታር የሚሆን የመሬት ይዞታ ያለው በመሆን ከተመሠረተ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። ከተማው ከምሥረታው ጀምሮ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንዲሆን በማሰብ የተመሠረተ በመሆኑ ምቹ የኢንቨስትመንት መሠረተ ልማትን ዘርግቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑት እና በከተማዋ መዋዕለንዋያቸውን እያፈሰሱ የሚገኙት ባለሀብቶችም ምርት እና አገልግሎቶቻቸውን በመያዝ በአዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል ተሰይመዋል። በሪልስቴት ግንባታ፣ የተለያዩ የቤት እና የቢሮ መገልገያ እቃዎች፣ የቆዳ ውጤት አምራቾች እና ሌሎች በርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አምራቾች በኤክስፖው ላይ ተገኝተዋል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ በኤክስፖ ላይ በመገኘት ካነጋገራቸው የስሪ ኤፍ ኩባንያ ይገኙበታል። የስሪ ኤፍ የሳሪስ የሽያጭ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ሃይሉ የድርጅቱ ምርቶች የሆኑትን አልጋ፣ ሶፋ፣ የቢሮ ወንበር እና ጠረጴዛዎችን ይዘው በማዕከሉ ተገኝተዋል።

እሳቸው እንደሚናገሩትም ድርጅቱ ዓለምገና በሚገኘውም ማምረቻ እና በተለያዩ ቅርንጫፎች ከ400 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል ፈጥሯል። ከሸገር ከተማ አስተዳደር ሌሎችም ከተማዎች ተሞክሮን ቢወስዱ የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ ሚና ይኖረዋል። ኤክስፖውም ጥሩ የገበያ ትስስርን ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን በመወከል አቶ ዘለቀ ሽንቡሬ ድርጅታቸውን ለማስተዋወቅ በስፍራው ተገኝተዋል። ተቋማቸው በሸገር ከተማ ላይ በርካታ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን በተመሳሳይም በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ አካባቢ በመንግሥት እና የግል ዘርፍ ትብብር ለአንድ ሺህ አባወራ የሚሆን ግዙፍ ህንፃን እያስገነባ ነው።

ለህንፃ ግንባታው 13 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ ዘለቀ ሥራው ሙሉ በሙሉ ሲጀመር ለአንድ ሺህ ወጣቶች የሥራ እድልን የሚከፍት መሆኑን ጠቁመዋል።

በሸገር ከተማም ቦረቦሩ የሚባል ትምህርት ቤት አስገንብተዋል። አቶ ዘለቀ ካፌ እና ሬስቶራንት፣ የክሬሸር ማሽን ተከላ እና የሪልስቴት ልማት ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረው በከተማ አስተዳደሩ መልካም ድጋፍ እና ጥሩ አገልግሎት አሰጣጥ እንዳለ አብራርተዋል።

ሌላው የጫማ ምርቶችን ይዞ በኤክስፖው የተገኘው በፋንታዬ የጫማ ማምረቻ ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ማሩ በበኩላቸው የካንቫስ እና የቆዳ ጫማዎችን በመያዝ በኤክስፖ የተገኙ አልሚ ናቸው።

በፋንታዬ የጫማ ማምረቻ ድርጅት አምስት ሺህ 400 ካሬ ቦታ በመያዝ ገላን አካባቢ እንደተገነባ የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ ለ250 ሰው የሥራ እድል መፍጠሩን ገልፀዋል። በአካባቢውም አልፎ አልፎ ከሚከሰተው የሃይል መቆራረጥ ውጪ ጥሩ መሠረተ ልማት እንዳለ ተናግረዋል።

የኢንቨስትመንት ማዕከል በሆነችው ሸገር ከተማ አስተዳደር የሚሰጠው አገልግሎት እና ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ ነው። ለአብነትም ለጫማ አምራች ድርጅቶች ከቀረጥ ነፃ የሆነ ሞልዶች እና ማሽኖች እንዳስገቡ እና ዘርፋ እንዲበረታታ እድል እንደከፈተ ገልጸዋል። የእኒህ ኢንቨስትመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ወንደሰን ተስፋዬ እንደሚናገሩት ተቋማቸው 300 ሚሊዮን ካፒታል ወጪ በማድረግ ለቤት እቃ መሥሪያ የሚሆን የፕላስቲክ ጥሬ እቃን እና ለፍራሽ መሥሪያ የሚሆን የፋይበር ጥሬ እቃን ያመርታል።

ተቋሙም ከኤክስፖ በሚያገኘው የገበያ ትስስር በሙሉ አቅሙ ወደሥራ ሲገባ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያመጣ እና ለበርካቶች የሥራ እድል የሚፈጥር ድርጅት መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ወንደሰን ገለፃ የእኒህ ኢንቨስትመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሸገር ከተማ ሁለት የማምረቻ ማዕከል አለው። ቦታውም የተገኘው ከተማ አስተዳደሩ ለአልሚዎች የመሬት አቅርቦት ለማቅረብ እድሉን በማመቻቸቱ ነው።

ከፀጥታ እና ከደህንነት አኳያም ስጋት የሌለውና ከብዙዎቹ የከተማ አስተዳደሩ ዘርፎች ጋር አልሚዎች ተቀራርበው የሚሠሩበት እድልም መኖሩን አብራርተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት የሸገር ከተማ ምሥረታን በማስመልከት ደንብ ቁጥር 233/2015 በማርቀቅ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች፣ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች በአንድ ላይ በመሆን ከተማዋን መሥርተዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት የቆየው ይህ ኤክስፖ የሸገር ከተማ አስተዳደር ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችን መሳብ ዓላማው በማድረግ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ኤክስፖ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን አዘጋጅቷል።

በኤክስፖው ላይ የሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት አምራች ባለሀብቶች ኢንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ በመገኘት የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስርን እንዲፈጥሩ ፣ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ፣ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ አስችሏል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You