
ያለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ያለው የግብርና ሥራ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት ነበር። በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለው የምርት መጨመር ደግሞ በርዳታም ሆነ በግዥ ከውጪ ይገባ የነበረውን ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ አንዳንድ ሰብሎች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከውጪ የሚገቡበትን ሁኔታ ለማስቀረት ያስቻለ መሆኑ ይነገራል።
ለዘርፉ ውጤታማነት አዲስ የተመሠረቱ ክልሎችም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆን፤ እየተጠናቀቀ ያለውን በጀት ዓመት ጨምሮ ያለፉት ተከታተይ ዓመታት ለአዲሱ ማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ዘርፍ ተስፋ የሚሰጡ ውጤቶች የተመዘገቡባቸው ነበሩ። እኛም ለዛሬ የግብርና አምድ ዝግጅታችን በክልሉ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የግብርና እና የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት አቶ ኡስማን ሱሩር ጋር የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አቶ ኡስማን እንደሚያብራሩት፤ የግብርና ዘርፍ ለማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ተጠቃሚነት መሠረት ነው። ይህንን ለማረጋገጥ የክልሉ መንግሥት ማህበረሰቡ ድረስ የዘለቀ የተቀናጀ የግብርና ዘርፍ ንቅናቄዎችን በማካሄድ የመስኖ የበልግና የመኸር የግብርና ልማቶችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
እየተጠናቀቀ ባለው የበጀት ዓመት በመስኖ ልማት 140ሺ ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ከ35 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት በማቀድ ወደ ሥራ ተገብቷል። ይህም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና በከተሞች የሚታየውን የምርት አቅርቦት ችግር ለማቃለል አስችሏል። በአርሶ አደሩ ረገድ ገቢው እንዲጨምርና ይህንን ተከትሎ ኑሮው እንዲሻሻል እያደረገም ይገኛል። ከእዚህ ባለፈ የመስኖ ምርት ተጠቃሚነት እያደገ በመምጣቱ ብዙዎች በዘርፉ መሰማራት ውጤታማ እንደሚያደርግ በመረዳት በልማቱ ለመሳተፍ ተነሳሽነት እንዲፈጠርባቸው በማድረግ የሥራ ባሕልን ለማነቃቃት የሚያስችልም ሆኗል።
ሌላው በክልሉ በሰብል ልማት እምብዛም የማይታወቀውን የጸደይ ወቅትን (ከመስከረም እስከ ጥር) በመጠቀም ዓመቱ የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ነበር። በእዚህም ያለችውን እርጥበት በመጠቀም ቶሎ የሚደርሱ እንደ ሽምብራ፤ ጓያ ያሉ እህሎችን በ35 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ በመዝራት ከ750 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ተችሏል። ይህ ከእዚህ ቀደም በጸደይ ወቅት ሥራ ላይ የማይውል መሬት፣ እርጥበትና ጉልበትን በመጠቀም ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ ለማስገኘት ያስቻለም ነው። ከተመረተው ሽምብራ ግማሽ የሚሆነው ለውጪ ገበያ የሚቀርብ በመሆኑ ሀገራዊ ፋይዳ ያስገኘም ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ከእዚህ ቀደም የጸደይ ወቅት ምርት በክልሉ ከስድስት መቶ ሄክታር ያልዘለለ፣ እሱም በጉራጌ ዞን አካባቢ ብቻ ይመረት ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን በአብዛኛው በክልሉ አካባቢዎች በመመረት ላይ ሲሆን፤ ዘንድሮ ያልጀመሩ አርሶ አደሮች ውጤቱን በማየት ለሚቀጥለው ዓመት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ይህ እንደ ክልል አዲስ የሥራ ባሕል ያስጀመረ አጋጣሚ ለመሆንም ችሏል ይላሉ።
እሳቸው እንደገለጹት፤ ሌላኛው የበጀት ዓመቱ እቅድ የበልግ ወቅት የተቀናጀ ግብርና ማካሄድ ነው። በእዚህ የተፋሰስ ልማት ፣ የበልግ ልማት እንዲሁም የበልግ ወቅት የፍራፍሬና የቡና ተከላ ልማት በእቅዱ ተቀምጠው ወደ ሥራ ተገብቷል። በበልግ ልማት ሥራው በጥቂት ቦታዎች የዝናብ ሁኔታ ቢያስተጓጉልም፤ አብዛኛውን ቦታ በዘር ለመሸፈን ተችሏል።
በእነዚህም ቦታዎች በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የመካናይዜሽን እርሻን በማስፋፋት ረገድ የነበረው እንቅስቃሴ በጣም አበረታችና ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ነበር። የተፋሰስ ልማትም በክልሉ እንደ ባሕል እየተተገበረ የመጣ በመሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ተራሮች እንዲሁም የተጎዱና የተራቆቱ መሬቶች በአፈር ልማትና በውሃ ጥበቃ ሥራዎች በመልማት በእጽዋት እየተሸፈኑ መጥተዋል። ከእዚሁ ጋር በተያያዘ ከአረንጓዴ ልማት የፍራፍሬ ተክሎች ምርት ከመሰብሰቡ በተጨማሪ ለበርካቶች የሥራ እድል መፍጠርና አካባቢንም ማስዋብ ተችሏል።
በተለይ ከእዚህ በፊት በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ተራቁተው የነበሩ የወል መሬቶች፤ ባለፉት ተከታታይ ሁለት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት መሬቶቹ ሕይወት ዘርተው ለወጣቶችና ለሴቶች የመኖና ቅመማ ቅመም ማልሚያ፤ ንብ ማንቢያ ለመሆን በቅተዋል። ይህም ለሴቶችና ለወጣቶች ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር እንደክልል በስፋት ተግዳሮት ለሆነው የሥራ እድል እጦት ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ለማበርከት አስችሏል።
የመኸር ልማት ሥራም ግንቦት አስራ አምስት ጀምሮ በንቅናቄ እየተሠራ ይገኛል። ንቅናቄው የተጀመረው በክልሉ ፕሬዚዳነት መሪነት ሲሆን፤ ከክልል አንስቶ ታች ማህበረሰብ ድረስ ለመውረድ ተችሏል። የእዚህ ዓመት የመኸር ወቅት እርሻ 563 ሺ ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን 54 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ግብ ተይዞ ተጀምሯል። ለእዚህም አመራሩም ሆነ ባለሙያው ኅብረተሰቡን በማነቃነቅ ግንዛቤ በማስጨበጥና ተገቢውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እየሠራ ይገኛል ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት በተቀመጠው እቅድ መሠረት ሁሉም አካባቢዎች በየደረጃው ወደ እርሻ እየገቡ ይገኛሉ። ከእዚሁ ጋር በተያያዘ የክረምት ወቅት የችግኝ ተከላ ሥራ በተለይ የፍራፍሬ፣ የቡና እና የእንስሳት መኖ ልማት በግለሰቦች ማሳና በተቋማት በስፋት እየተከናወነ ነው፡፡ የሌማት ትሩፋትንም በተመለከተ በሦስቱም የንቅናቄ ሥራዎች እንዲካተት ለማድረግ ተችሏል። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም በክልሉ በልዩ ትኩረት በበላይ ኃላፊዎች እየተመራ የሚከናወን ሲሆን፤ ለእዚህም ከአምስት መቶ ሚሊዮን በላይ ችግኞች የሚዘጋጁ ይሆናል።
የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ ብቻ ሳይሆን፤ በቂ የገበያ ትስስር በመፍጠር ነው። አቅርቦትና ፍላጎት ሳይመጣጠን ቀርቶ ምርት ከጨመረ እና ዋጋው የሚረክስ ከሆነ፤ አምራቹን ለጉዳት የሚዳረገው ይሆናል። በመሆኑም የምርታማነት መጨመርን እየተከታተሉ ወደ እሴት ጭመራ መግባትና የተመረተው ምርት ሁሌም ተፈላጊ የሚሆንበትን አቅም መፍጠር እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ።
እንደእሳቸው ማብራሪያ፤ በእዚህ ረገድ በእዚህ ዓመት ብቻ ሰባት የወተትና የወተት ውጤቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች እየተገነቡ ሲሆን፤ አምስቱ ሥራ ጀምረዋል። በእዚህ ረገድ ባለፈው በጀት ዓመት አንድ ወደ ሥራ የገባ ኢንዱስትሪ ነበር። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ራሳቸው አርሶ አደሩ በማህበር እየተደራጀ ባለቤት የሆነባቸው ናቸው። በሌላ በኩል በክልሉ በሌማት ትሩፋት ዘርፍ ትልቅ ፈተና የሆነው የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ አለመስፋፋት ነበር። ይህንን ለመቅረፍ ወጣቶችና ኅብረት ሥራ ማህበራት በመስኩ እንዲሳተፉበት በማድረግ አቅማቸውን የመገንባት ሥራ በስፋት በመከናወን ላይ ነው።
የማዳበሪያ አቅርቦትን በተመለከተም ያለፉት ሁለት ተከታታይ የምርት ዘመናት በመጠንም ሆነ በወቅቱ ከመድረስ አኳያ ትልቅ ተግዳሮት የነበረባቸው ነበሩ። ይህ በክልሉ አቅም ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለማቃለል ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። የማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ሥርዓት ባለው መልኩ እንዲሆን መሥራት የተጀመረው እንደ ክልል ከተደራጁበት ወቅት ጀምሮ ነበር።
ለዘንድሮ የምርት ዘመን አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ የተያዘው እቅድ ከፌዴራል መንግሥት ጸድቆ ወደ ሥራ ተገብቷል። ይህ የሆነው ለእያንዳንዱ አካባቢ የሚያስፈልገው ማዳበሪያ በጊዜና በመጠን ማለትም የትኛው አካባቢ ምን ያህል መቼ ያስፈልገዋል? የሚለው ተጠንቶ ነው።
ተደራሽ በማድረግ ረገድ በአሁኑ ወቅት ማዳበሪያ የሚሰራጨው ከአንድ ማእከል ሲሆን፤ ለአርሶ አደሩም ሆነ ለባለሀብቱ የሚዳረሰው በኅብረት ሥራ ማህበራት በኩል ብቻ ነው። ከእዚህ ውጪ አንድ ኪሎ ማዳበሪያ ይዞ የተገኘ ካለ ማዳበሪያው ይወረሳል፤ አንቀሳቃሹም በሕግ ተጠያቂ ይሆናል። ማዳበሪያውን የጠቆመው ሰላሳ በመቶ የያዘው አካል ሰላሳ በመቶ እንዲሁም የአካባቢው መዋቅር አርባ በመቶውን ወስዶ ለልማት እንዲያውለው የሚደረግ ይሆናል። በእዚህ ዓይነት አካሄድ ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን፤ እስካሁን ባለው ግምገማ ካለ ምንም ችግርና ቅሬታ እየተዳረሰ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። ለቀጣይ አቅርቦቱም ሆነ ስርጭቱ ጤናማ እንዲሆን ተከታታይነት ያለው የቁጥጥርና የክተትል ሥራ የሚከናወን ይሆናል ይላሉ።
የምርጥ ዘር አቅርቦትም በተመሳሳይ በኅብረት ሥራ በኩል የሚከናወን መሆኑን አስታወሰው፤ ክልሉ ውጤታማ ከሆነባቸው ሥራዎች አንዱ ለመሆን ችሏል። የምርጥ ዘር አቅርቦት በየወቅቱ የሚፈተሽና ውጤታማነት መረጋገጥ ያለበት በመሆኑ ባለሙያዎች በየአካባቢው የቁጥጥርና ክተትል ሥራ የሚያከናውኑበት ነው ይላሉ። ጨምረውም የመካናይዜሽን መሣሪያዎች አቅርቦትንም በተመለከተ፤ የአርሶ አደሩ ኅብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ አገልግሎታቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ ላይ ይገኛል። ከእዚህ ባለፈ አርሶ አደሮች አርባ በመቶ በመቆጠብና ከባንክ ብድር በማገኘት ኮምባይነርና ትራክተር ለመግዛት የበቁም አሉ።
እነዚህ አርሶ አደሮች ማሽኖቹን ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ከእነሱ ማሳ በተረፈው ጊዜ የሌሎቹንም መሬቶች እያለሙበት ይገኛል። በተጨማሪ እንደ ኦሮሚያ ካሉ አጎራባች ክልሎችም ኮምባይነርና ትራክተር አምጥተው በማከራየት የጋራ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት አሠራርም ተዘርግቷል። በእዚህ ሂደት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር በቅንጅት ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ ነው። ይህም በአጠቃላይ በክልሉ ያለውን የመካናይዜሽን ልማት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ይህንን ተከትሎ የሚፈጠረውን ምርታማነት መጨመር እያሳደገው እንደሚገኝ ይናገራሉ።
አቶ ኡስማን የወጪ ምርቶችን በማሳደግ ረገድ በክልሉ ለውጪ ገበያ ሊቀርቡ የሚችሉ ብዙ ዓይነት ምርቶች አሉ ይላሉ። እንደ ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር ያሉት ነባሮቹ እንደተጠበቁ ሆነው፤ ባለፉት ሦስት ተከታተይ ዓመታት እንደ ሮዝመሪ ያሉ አዳዲስ ምርቶችም ለወጪ ንግድ ማምረት መቻሉን ጠቅሰው፤ ከአራት ዓመት በፊት ሮዝመሪ ይለማ የነበረው ሰላሳ ሄክታር ላይ ብቻ እንደነበር ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በየአርሶ አደሩ ጓሮ፣ በተቋማትና አሲዳማ መሬቶችን አክሞ በማምረት 15 ሺ ሄክታር ለማድረስ ተችሏል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የሮዝመሪ ምርት ለወጪ ንግድ ለማቅረብ ተችሏል። በተጨማሪ እንደ ኮሰረት ባሉ ምርቶችም አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ለማስገኘት አስችሏል። ዝንጅብልም ባለፉት ስድስት ዓመታት በበሽታ ተጠቅቶ በቂ ምርት እየተገኘበት አልነበረም። አሁኑ ግን በተለይ በሀድያ አካባቢ በስፋት እየተመረተ ለወጪ ንግድ እየቀረበ ይገኛል። እነዚህ በትንሽ መሬት ከፍተኛ ሀብት የሚገኝባቸው አርሶ አደሩም በቀላሉ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው የምርት ዓይነቶች መሆናቸውን ያብራራሉ።
ለቀጣይ የክልሉ የግብርና ዘርፍ የትኩረት ማእከል የሚሆነው ግብርናውን በመዘመን ከድህነት ማውጣት ነው ። ያሉት አቶ ኡስማን፤ ለእዚህ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን መተካት፤ ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ሰብሎችን ማምረት፣ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት፤ ለሁሉም ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ላይ ትኩረት መስጠት ነው። ለእዚህም የምርት ወቅት ከሦስት ወደ አምስት ማደጉ አንዱ ማሳያ ነው። መኸር ፣ በልግ፣ መስኖ ፣ቅድመ በልግ ፣ፀደይ ይህ እንደ አጠቃላይ መነሳሳትን የፈጠረ ሆኗል ብለዋል።
የሚቀጥለው የክልሉ የግብርና ዘርፍ እቅድ ስኬታማ የሆኑ ሥራዎችን ማስቀጠል፤ ክፍተቶችን ማረም፤ የግብአት አቅርቦትን ማሳደግ እንዲሁም እሴት መጨመር ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ይሆናሉ። በክልሉ የትኛውም አካባቢ ያለ መሬት ጦም እንዳያድር የሚደረግ ሲሆን፤ ያለውን የሰው ኃይልም ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም ከግንዛቤ ፈጠራ ጀምሮ የሚሠሩ ሥራዎች ይኖራሉ። በክልሉ ግብርና ቢሮ በኩልም የግብአት ማሟላት፣ የባለሙያ ድጋፍ ማድረግ እና ያልተቋረጠ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት እየተከናወነ ይገኛል። በውጤቱም እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን በዘርፉ እንደ ሀገር የተቀመጡ እቅዶችን ማሳካት ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም