
ዜና ሀተታ
የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በከንባታ ዞን ሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለች ነች። አርሶ አደሮች የአካባቢውን ፀጋ ተጠቅመው ቡና፣ አቡካዶ፣ ቅመማ ቅመም እና ‹‹የፍራፍሬ ንጉሥ›› እየተባለ የሚጠራውን ጃክ ፍሩት ጨምሮ በርካታ ሰብሎችን ያመርታሉ።
የሀደሮ ምድር የሰጡትን የሚያበቅል ለም አፈር የታደለ ቢሆንም አካባቢው በዝንጅብል እና በቡና ምርት በልዩ ሁኔታ ይታወቃል። በተለይ ከቅመማ ቅመም ዝንጀብል በስፋት ይመረትበታል። ይሁን አንጂ አርሶ አደሮቹ ‹‹ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም የሚተርፍ ዝንጅብል ብናመርትም በደላሎች ምክንያት ልፋታችን መና እየቀረ ነው›› ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ።
የዝግጅት ከፍላችን በስፍራው ተገኝቶ ካነጋገራቸው አርሶ አደሮች መካከል አቶ ብርሃኑ ደሳለኝ አንዱ ነው። ከብት ርባታ፣ አቦካዶን ጨምሮ በጥምር ግብርና ይተዳደራል። አርሶ አደሩ በሚኖርበት በሀደሮ ጡንጦ ወረዳ በአጨጮ ቀበሌ የዝንጅብል ቅመም በስፋት ይመረታል። እርሱም በአምስት ነጥብ አምስት ሄክታር ላይ ተክሏል። ዝንጅበሉን ከፍተኛ ጉልበትና ወጪ አውጥቶ ለምርት የሚያደርስ ቢሆንም የገበያ ትስስር ባለመኖሩ፣ በአካባቢው በቂ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ባለመገንባቱ ምክንያት በደላሎች እጅ መውደቁን ይናገራል።
‹‹አማራጭ ስለሌለን ደላሎቹ በሚወስኑት ዝቅተኛ ገንዘብ ነው ምርቱን እየሸጥን ያለነው›› የሚለው አርሶ አደር ብርሃኑ፤ ምርቱን አንደ ልብ ማምረት እየቻሉ፣ በአካባቢው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለመኖሩና መኪና ወደ መንደራቸው ስለማይገባ ማሳ ላይ እንዳለ ለደላሎች በርካሽ እየሸጡ መሆኑን ይገልፃል።
ደላሎች የራሳቸው የገበያ ሰንሰለት ስላላቸው የአካባቢውን አርሶ አደር ይቆጣጠሩታል የሚለው አቶ በርሃኑ ደሳለኝ መንግሥት የአካባቢውን ፀጋ ተመልክቶ ባለሀብቶች በወረዳው የዝንጅብል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንዲገነባ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጥር ይጠይቃል። አርሶ አደሩም ተጠቃሚ ሆኖ መንግሥትም ተገቢውን ገቢ እንዲያገኝ የደላሎቹ ሰንሰለት መሰበር አለበት ይላል።
በሰባት ሄክታር መሬት ላይ የዝንጅብል ዘር የተከሉት የአጆራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ለገሰ ዳነሞ በበኩላቸው ከማሳቸው ከ300 እስከ 400 ኩንታል ዝንጅብል እንደሚያመርቱ ይገልፃሉ። ይሁን እንጂ በገበያው ላይ ተፈላጊ የሆነውን ቅመም በርካሽ ለደላሎች እንደሚሸጡት ይገልፃሉ። ደላሎቹ ምርቱን በዱቤ እንደሚገዟቸውና እና ገንዘቡ እጃቸው ላይ በሚፈልጉት ጊዜ እንደማይደርስ ይገልፃሉ። አማራጭ በማጣት ለደላሎቹ ለመሸጥ እንደሚገደዱና ለልፋታቸው በቂ ዋስትና እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡
‹‹ትልቁ ገበያ ነው። አርሶ አደሩን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የሚጠቅም ገበያ ሲኖር ነው ሁሉም መሥራት የሚችለው›› የሚሉት አቶ ለገሰ ዳነሞ፤ ይህ ነው የሚባል የገበያ ሥርዓት አለመኖሩን ይገልፃሉ። ደላሎች የሚያመርቱትን ዝንጅብል ከማሳቸው ላይ በዱቤ ገዝተው በኮንትሮባንድ በውድ እንደሚሸጡት ይናገራሉ። መንግሥት ይህንን ሰንሰለት በመስበር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወስድ ጥሪ ያደርጋሉ።
ሌላኛው የዝንጀብል አምራች አርሶ አደር ተስፋዬ ማህሮ የአጆራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፤ እርሳቸው እንደሚሉት አምና በሶሰት ሄክታር መሬት ላይ 380 ኩንታል ዝንጅብል አምርተዋል። ዘንድሮም ተመሳሳይ ምርት ይጠብቃሉ። የሀደሮ ወረዳ በዝንጅል ምርት የምትታወቅ በመሆኑ አርሶአደሩ በስፋት እንደሚያመርት ይገልፃሉ። ይሁ እንጂ በገበያ ትስስር እጦት ምክንያት ለደላሎች ሲሳይ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
‹‹ደላሎች በአካባቢው በስፋት የምናመርተውን ዝንጅብል ከእኛ በርካሽ ነው የሚገዙት። ገበያ ላይ ግን ስንት እንደሚሸጡ መረጃው የለንም›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ ደላሎቹ በቀጥታ ማሳው ላይ መጥተው በርካሽ እንደሚገዟቸው ይናገራሉ። ገበያውን የሚያመጡት እነሱ በመሆናቸው ዋጋ የመቁረጥ መብት እንደሌላቸው ይገልፃሉ።
ሀብታሙ ዮሐንስ (ዶ/ር) የሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ ናቸው፤ እርሳቸው እንደሚሉት በወረዳው አምስት ሺህ 700 ሄክታር መሬት በዝንጅብል ምርት ተሸፍኗል። በቀጣይ ዓመት ሽፋኑን ወደ ስድስት ሺህ ሄክታር ለማሳደግ እየተሠራ ነው።
‹‹የዝንጀብል ምርት ለአካባቢው ልክ እንደ ወርቅ ማእድን ነው። በስፋት በአካባቢው ላይ ይበቅላል›› የሚሉት የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ፤ ይሁን እንጂ በቂ የገበያ ትስስር እየተፈጠረ ባለመሆኑ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለ ይገልፃሉ። ይህንን ክፍተት ለማስተካከል ከክልሉ የግብርና ቢሮ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ያስረዳሉ።
አርሶ አደሩንም ሆነ መንግሥትን በቀጥታ በሚጠቅም መልኩ የአካባቢው ጸጋ የሆነውን የዝንጅብል ምርት በሕጋዊ ገበያ ማስተሳሰር ይገባል የሚሉት የጽህፈት ቤት ሃላፊው፤ ከሶስትና አራት በላይ ደላሎች በአንድ ግብይት ላይ ሰንሰለት በመሥራት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እንደሚያሳጡት ይገልፃሉ። የአካባቢው ሞዴል ገበሬዎች በሄክታር ከ300 እስከ 400 በሄክታር እንደሚያመርቱ ገልፀው በምርቱ ልክ ግን ተገቢውን ጥቅም እንደማያገኙ ገልፀዋል። ይህንን ክፍተት ለመድፈን በወረዳው የዝንጅብል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በግል ባለሀብቶች እና በመንግሥት አጋዥነት ቢቋቋም ችግሩን እንደሚፈታው በመግለፅ ለመፍትሄው ጥሪ አቅርበዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም