መላኩ ግዛው ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው። መሽቶ በነጋ ቁጥር የሚቆለለውን የኑሮ ሸክም ለመቋቋም እየታገለ አንዳንዴም እየተንገዳገደ ከኑሮ ጋር ግብ ግብ ተያይዞታል። ህይወት በሰጠችው እድል ተፈጥሯዊ ጉልበቱን በመሸጥ በቀን ሥራ ይተዳደራል። በህንጻ ግንባታ ዘርፍ በቀን ሰርቶ የሚያገኛት ገቢ ለ30 ቀናት ድሎት ያለው ኑሮ ለመኖር ባያስችለውም ለቤተሰቡ የእለት ጉርስ መደጎሚያ ግን ትሆነዋለች።
አሁን ላይ የግንባታው ዘርፍ መቀዛቀዝ ተሯሩጬ ስሰራ ከነበረው የቀን ሥራ አግዶብኛል የሚለው መላኩ፤ እያደር በሚያሻቅበው የገበያ ሁኔታ በአስከፊ የኑሮውድነት ምክንያት ለችግር መዳረጉና ይባስ ብሎ በእርሱ ገቢ የሚተዳደሩት ቤተሰቦቹ መቸገራቸው ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ሆኖበታል።
ተስፋን ላለማጣት አማራጮችን ለመፍጠር ቢታገልም፤ የሚያገኛቸው አማራጮች ቤተሰቡን ለመምራት በቂ እንዳልሆነ ይናገራል። በዚህ የስራ ዘርፍ እርሱን መሰል በርካታ ወጣቶች ተሰማርተው እየሰሩ መሆናቸውንና ተቋማት ሥራ እያቆሙ በመሆናቸው ሌላ ሥራ እየፈለጉ ስለመሆናቸውም ጠቅሷል።
ሥራ ለማግኘት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድና በዚህ መሀል የሚደርሰውን እንግልት መቋቋም ከባድ በመሆኑ የተቀዛቀዘው የግንባታ ሥራ ቢጠናከርና ችግሮች ተለይተው ማስተካከያ ቢደረግላቸው ብዙ ቀጣሪ ተቋማትን ማግኘት እንደሚቻል ተስፋ አድርጓል።
በሱር ኮንስትራክሽን የኮንስትራክሽን ኦፕሬሽን ኃላፊ የሆኑት መሐንዲስ ፊሊሞን ሀይለማርያም እንደሚሉት፤ በአሁን ሰዓት የግንባታ ሴክተሩ ተቀዛቅዟል። ከባለ ሀብቶች ጀምሮ መንግሥት እስከ ሚያንቀሳቅሳቸው ካፒታል ፕሮጀክቶች ድረስ ከፍተኛ መቀዛቀዝ ይታያል። እንደ አቶ ፊልሞን አገር ቤት ውስጥ ካሉት የግንባታ ግብዓቶች በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች የዋጋ ንረት አሳይተዋል። በዚህ ምክንያት የህንጻ አማካሪዎችና ኮንትራክተሮች ሥራ እያገኙ አይ ደለም።
የህንጻና የመንገድ ግንባታ ሲካሄድ ወጣቶችን በማደራጀት በርካታ ሥራዎች ይከናወኑ ነበር የሚገልፁት አቶ ፊልን፤ አሁን ላይ በመንግሥት የተያዙ አዳዲስ ፕሮጀክቶች አይታዩም። የግንባታው መቀዛቀዝ ምክንያትና ውጤት ብለው የሚዘረዝሩትም፤በቂ የሆነ የዶላር ክምችት ባለመኖሩ ግንባታ ማካሄድ የቅንጦት ሥራ የመስራት ያህል መቆጠሩ፣ አስመጪና ላኪዎችም ማግኘት የሚገባቸውን ገቢ እያገኙ አለመሆኑንና ኮንትራክተሮች የሥራ ማጣት ምክንያት መንግሥት ከእነዚህ አካላት ሊያገኝ የሚገባው ገቢም ቀንሶበታል።
አቶ ፊሊሞን ሂደቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነም በዘርፉ ላይ ተሰማርተው የነበሩት ወደ ሌላ ሥራ ፊታቸውን ለማዞር እንደሚገደዱ ጠቅሰው፤ የውጭ ምንዛሬውን ማረጋጋት፣ በዘርፉ በሁሉም ቦታ ተንቀሳቅሶ መስራት እንዲቻል ሰላምን ማረጋገጥ፣ የዘርፉን ባለድርሻ አካላት ለማነቃቃትና ችግሮችን በሚገባ ለመለየት ብሎም መፍትሄ ለማምጣት የምክክር መድረኮችን ማካሄድ መንግሥት ሊወስደው የሚገባ እርምጃ መሆኑን አመላክተዋል።
ታዳጊ አገራት ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ ከሚችሉባቸው ተግባራት ውስጥ የግንባታው ዘርፍ አንዱ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ፊሊሞን፤ የግንባታው ዘርፍ መቀዛቀዝ በአገሪቷ የማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚያሳድርና በተለይ በዚህ የስራ መስክ ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ግለሰቦችና ተቋማትም ጭምር ተጎጂ እንደሚሆኑ ነው የሚናገሩት።
የሰይፈ ሥላሴ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሰይፈሥላሴ ሀይለጊዮርጊስ፤ በአሁኑ ወቅት በአንጻራዊነት ከባለፉት ጊዜያት የግንባታ መቀዛቀዝ መኖሩን አልሸሸጉም።እንደ አቶ ሰይፈስላሴ በሥራ ተቋራጮች ደረጃ የሚወጡ ጨረታዎች በኮንስትራክሽን ቢሮ በኩል እንዲፈጸሙ መደረጋቸው፤ በእጣና በወረፋ አማካኝነት ስለሚደርስ ረጅም ጊዜን መውሰዱ ለዘርፉ እንቅስቃሴ ማነስ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ። የጨረታ ዋጋዎች ማነስ በአዋጭነትና ተወዳዳሪነት ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩንም ይጠቁማሉ።
አቶ ሰይፈ ሥላሴ የግንባታውን ዘርፍ የተቀላቀሉት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን፤ በወቅቱ በወር ቢያንስ ሁለት ጨረታዎችን በማሸነፍ ሥራዎችን ያከናውኑ ነበር። ዛሬ ላይ ግን አንድ ጨረታ ለማሸነፍ ቢያንስ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ጊዜ እንደሚወስድባቸው፤ ይህም ሥራ እፈጥራለሁ ብሎ የሚንቀሳቀስ ተቋም ረጅም ጊዜ ያለ ሥራ እደሚያቆይ በስሩ ያሉ ሠራተኞችም እንግልት እንደሚደርስባቸው ያስረዳሉ።
የዘርፉ መቀዛቀዝ በግለሰቦችም ሆነ በአገር ላይ የኢኮኖሚ ድቀትን እንደሚያስከትልም አስታውቀዋል። በተለይ ቤተሰብ መስርቶ በዚህ የስራ ዘርፍ ላይ የሚሰማራ ሰው ኑሮውን እንደሚያከብደውና አማራጭ ስራዎችን በመፈለግ ጊዜውን ሊያባክን እንደሚችል አብራርተዋል። መንግሥት በኢኮኖሚው በኩል የሚደርሰውን ግለሰባዊም ሆነ ተቋማዊ ኪሳራን አገናዝቦ የጨረታ አወጣጥ ሂደቱን ማጤን እንዳለበትም መክረዋል።
በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ እንደሚሉት፤ የግንባታው ዘርፍ ሙሉ ለሙሉ ተቀዛቅዟል ማለት ባያስችልም በተወሰነ መልኩ ግን ከባለፈው ጊዜ ጋር ሲነፃጻር የተጀመሩት ግንባታዎች በጀመሩት ፍጥነት ልክ አለመሄድ ችግር ጎልቶ እንዲታይ እንዳደረገው ይናገራሉ። አብዛኛው የግንባታ ግብዓት ከውጭ የሚመጣ በመሆኑ፤ መሳሪያዎችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስፈልግ አሁን ያለው የውጪ ምንዛሬ እጥረት ደግሞ ችግሩን እንዳባባሰው ነው አቶ ኢትዮጵያ የሚያብራሩት።
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ገለጻ፤ ከባለፈው አንድ ወር ወዲህ በተለይ የግንባታ ግብዓት የሆኑ ጥሬ እቃዎች ምርት ላይ እጥረት እንዲኖር የኤሌክትሪክ ሀይል ማነስ ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተጽእኖም አሳድሯል። በተጨማም በዘርፉ ግብዓቶች ላይ ያለው የዋጋ መዋዠቅ ግንባታውን በሚፈለገው መጠን ለማስኬድ የሚያግድ ሌላው ችግር መሆኑም ይናገራሉ።
የግንባታ ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው እድገት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው የሚናገሩት አቶ ኢትዮጵያ፤ በከተሞች ላይ ከኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ከማስፋት ጋር ከፍተኛ የሆነ የግንባታ አማራጮችም መኖራቸውን ጠቁመው፤ አማራጮቹ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ የግንባታ ጥሬ እቃዎች እጥረት ምክንያት መቀዛቀዙ አገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት እንዳይኖረው እንቅፋት እንደሚሆን ገልጸዋል።
ለዚህም መፍትሄ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ዘርፉ ላይ ያሉ ባለሀብቶች፣ ተቋራጮችና አማካሪዎች የውጭ ምንዛሬውን ማግኘት የሚችሉበትን አማራጮች የመፍጠር ሂደት ውስጥ መሆኑን አቶ ኢትዮጵያ ጠቁመዋል። አክለውም ለግንባታው መቀዛቀዝ ትልቅ ድርሻ የነበረው የኤሌክትሪክ ሀይል ማነስ እንዳይኖርና ፋብሪካዎች በተገቢው መንገድ እንዲገለገሉ የማድረግ ሥራዎችን በመንግሥት በኩል በማከናወን ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 5/2011
አዲሱ ገረመው