27 ዓመታት ወደ ኋላ…
ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም…
በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የመንግሥት ሥርዓት ለውጥ የተደረገበት ታሪካዊ ቀን። ይህንን ቀን ወንድም ወንድሙን አሸንፎ ስልጣን የያዘበት እለት ብቻ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም። ይልቁንም በዘመኑ ይፈጸሙ የነበሩ ኢሰብዓዊ በደሎች ሁሉ መቋጫቸው የተበሰረበት ስለሆነም ጭምር ብዙዎቹ አደባባይ ወጥተው ቀኑን አክብረውታል። ይህ በትግሉ ውስጥ ላለፉት ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ኩራት የሆነ ቀን ስለነበር በዚህ መልክ መታሰቡ ተገቢ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም። በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሐውልት መቆሙንም ሳንዘነጋ ማለት ነው።
ከዚያ መልስ ግን፤ አዎን ከዚያ መልስ ግን… በዚያ ዘመን ላይ ሆኖ ከመንግሥት የሰብዓዊ መብት አያያዝ አንጻር ዛሬን በዚህ መልኩ ማሰብ ነብይ መሆን ይጠይቅ ነበር። ከ27 ዓመታት በፊት በምንም ታምር «ብሶት የወለደው» ብሎ የሥርዓት ለውጥ ማድረጉን ለዓለም ባበሰረ ድርጅትና መንግሥት አባላት ምክንያት ካለፈውም የከፋ በደል ፈጽሞ ብሶት ፈጣሪ ይሆናል ብሎ መናገር እብድ ያሰኝ ነበር። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ከ1983 ዓ.ም በፊት አውግዘን በግንቦት 20 ቀን 1983 ተሰናብተነዋል ያልነው ግፍ በብዙ መልኩ በዝቶና ተባዝቶ አይተነዋል፤ ሰምተነዋል።« ብሶት የወለደው ጀግናው …» ብሎ ድሉን ለዓለም ያበሰረ ድርጅትም ራሱ ብሶት የሚፈጥር ሆኖ አርፎታል። ይሄ እንደ አገር ያሳዝናል፤ ያሳፍራልም።
«የበላችው ያቅራታል በላይ በላዩ ያጎርሳታል» እንዲል ተረቱ፤ የዝርፊያውን ታሪክ ሰምተን ከገባንበት የኀዘንና የቁጭት አንጎበር ሳንወጣ ሌላ አንገት አስደፊ እንባም አርጋፊ ግፍ በገፍ ሰምተናል። ተመልሰንም ሌላ የቁጭትና የኀዘን ባህር ውስጥ ገብተናል። በፈጸሙትም ይሆን ባልፈጸሙት ወንጀል ከህግ ውጭ ተይዘው፣ ከህግ ውጭ ተዳኝተው፣ ከህግ ውጭም የተቀጡ ወገኖቻችን ግፍና መከራን መልሶ ማሰብ የግፉን ፈጻሚዎች ዓይነት ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰብዕና እና ሞራል ያስፈልጋል። የሰው ልጅ ፈልጎ ባልያዘው ማንነቱና መርጦ በያዘው የፖለቲካ አቋሙ ብቻ ተይዞ የተባለው ዓይነት ግፍ ሁሉ የሚፈጸምበት አገር ሆነን መገኘታችን በእርግጥም ያማል፤ ያሳፍራልም።
የተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ይሄ ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ወገኖች ዳግም የሞቱበት ነው። በአደባባይ «ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማዕታት» እያሉ በጓዳ የትግሉ ሰማዕታት አምርረው የታገሉለትንና የሞቱለትን ተግባር መፈጸም ከሀዲነት ነው። ይህ በወገኖቻችን ላይ በራሳቸው ወገኖች የተፈጸመው ድርጊት በእርግጥም ክብርና ሞገስ ለሚገባቸው የትግሉ ሰማዕታት ዳግም ሞት ነው።
የቀይሽብር ሰማዕታትን መቃብር ምሶ፤ አጽም አውጥቶ ህዝብን በአደባባይ አስለቅሶ መሀል ከተማ ላይ ሐውልት ያቆመ መንግሥትና ድርጅት፤ ከ100 ዓመታት በፊትም ተፈጽሟል ብሎ ላመነበት ድርጊት ወደ ኋላ ጭምር ተመልሶ ሐውልት ያቆመ መንግሥትና ድርጅት ሌላ ሐውልት የሚያስቆም ድርጊት መፈጸም ከበደልም በላይ ነው። በህግ ጥላ ስር ናቸው ተብለው ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ዜጎች ላይ ለተፈጸመው በደል ሐውልት ይቁም ቢባልስ መንግሥት እንቢ የማለት ሞራል አለው ወይ? በጭራሽ!
አገራችን የገባችበት ለውጥ ዳግም የዚህ ዓይነቱን ግፍና ሰቆቃ እንዳያስተናግድ ሁሉም ወገን ለውጡንና በለውጡ ውስጥ ሆነው ይህንን አገር በየደረጃው እያስተዳደሩ ያሉትን አካላት መደገፍና ሲያጠፉም ከስር ከስር ማረም ያስፈልጋል። ዛሬ የሰማነው ግፍና በደል በአንድ ጀንበር በካበተ የጭካኔ ልምድ የተፈጸመ አለመሆኑን ማሰብ ተገቢ ነው። «ምነው በእንቁላሉ በቀጣሽኝ» እንዳለ ተረቱ ያኔ ከስር ከስር መንግሥት ታርሞ፣ የተነገረውንም ሰምቶ፣ ያረሙትንም አክብሮ ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ ባልሆነ ነበር።
ስለሆነም የዚህ ዓይነቱ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ግፍና በደል ዳግም እንዳይደገም መንግሥት ከአንገት ሳይሆን ከአንጀቱ ይስራ። ለቀይ ሽብር ሰማዕታት ሐውልት የቆመው ግፉ «እንዳይደገም» በሚል ቅን እሳቤ ነበር። ነገር ግን ከሐውልቱ ጀርባ የነበረው የእንዳይደገም ቁጭት ከአንገት እንጂ ከአንጀት ስላልነበር ያንን የሚያስከነዳ፣ አንጀት የለሽ የሚያስብልም ግፍ ዛሬ ተደግሟል። ስለሆነም ግፉና የግፈኞች ሴራ ዛሬም፣ ነገም መቼም እንዳይደገም ያለምንም ሴራ ይሰራ።
አንገታችንን ያስደፋንን ይህንን ግፍ የሰሩ ሁሉ ትናንት ግፍ ሰርተዋል ተብለው የተዳኙ ወገኖች የተዳኙበት ህጋዊው እርምጃ ይደገም። ይደገም ስንልም ግፉ እንዳይደገም ስለሆነ ያለምንም ልዩነት አጥፊዎች በህግና በህግ ብቻ የዘሩትን ይጨዱ። ይህንን አለማድረግ እንዳይደገም የምንፈልገው ግፍና መከራ ነገ ላለመደገሙ ምንም ዋስትና አይኖረንም። ስለሆነም የማይደገመው አይደገም! የሚደገመው ደግሞ ይደገም።
የዚህ ሁሉ ግፍና መከራ ሰለባዎችን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምክር ቤት ባደረጉት ንግግር አስቀድመው በመንግሥት ስም ይቅርታ ጠይቀዋል። ይህ የይቅርታ ጥያቄ መንግሥትን ቢያስመሰግነውም ሌላ ተጨማሪ ዕዳ እንዳለበትም ማወቅ አለበት። እነዚህ ወገኖች በደላቸውን ባይሽረውም፤ የጎደለውን አካል ባይመልስላቸውም፤ የተሰበረውን ሞራላቸውን ባይጠግነውም፤ የሞቱትንም ባይመልስልንም ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ህክምና፤ ካሳ ለሚገባቸውም ካሳ ይገባቸዋልና መንግሥት «የት ወደቃችሁ?» ብሎ ሊጎበኛቸው ይገባል። ይህንን አለማድረግ የግፉን ሰለባዎች ዳግም በግፍ ውስጥ እንደመተው ይቆጠራልና መንግሥት የማይደገመው እንዳይደገም፤ የሚደገመው እንዲደገም ፈጥኖ ይስራ!