የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት እውን ከሆነ 24 ዓመታት ተቆጥረዋል። በእነዚህ ዓመታትም በሕገመንግሥቱ ጥላ ስር የተከናወኑ በርካታ አወንታዊና አሉታዊ ተግባራት ይጠቀሳሉ። በሕገመንግሥቱ አንዳንድ አንቀፆችም ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ እነዚህን ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ ማስተናገድ ሳይቻል ቆይቷል።
አሁን በአገራችን የመጣውን ሁለንተናዊ ለውጥ ተከትሎ ደግሞ አንዳንድ ጥያቄዎች ሲነሱ ይስተዋላል። በተለይ ሕገመንግሥቱን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግና በሕገመንግሥቱ ጥላ ስር በመሆን የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች ለማረጋገጥ በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች በመከናወን ላይ በሚገኙበት በዚህ ወቅት የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎች ተገቢ ቢሆኑም ለእያንዳንዱ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ጊዜ እንደሚያስፈልግም ሊረሳ አይገባም። ለውጡን ተከትሎ «ጥያቄዎች ሁሉ በአንድ ጀምበር ካልተመለሱ ሞቼ እገኛለሁ» የሚሉ አካሄዶችም ጥንቃቄን የሚፈልጉና ሊታሰብባቸው የሚገቡ ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ከሚነሱ ሕገመንግሥታዊ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ደግሞ «የክልል እንሁን» ጥያቄ ነው። በተለይ ቀደም ሲል ጀምሮ ሲንከባለል የቆየውና ለውጡን ተከትሎ ጎልቶ መውጣት የቻሉ የተለያዩ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ረጅም መንገድ ተጉዘው የሕዝቡን ፍላጎት በሚመልስ መልኩ እየተሰራባቸው ምላሽ እነዲሰጥባቸው እየተሰራ ይገኛል። እስካሁን ባለው ሂደትም የአንዳንዶቹ ጥያቄ ለብሔረሰብ ምክር ቤት ቀርቦ ተቀባይነት ያገኘ ሲሆን ሌሎች ቀጣይ ሥራዎች ግን በሂደት ላይ ይገኛሉ።
የክልል እንሁን ጥያቄዎች ጎልተው መውጣት የቻሉት ለውጡን ተከትሎ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ የለውጥ ወቅት ደግሞ በርካታ ተቋማት በአዲስ መልኩ እየተገነቡ መሆናቸው ይታወቃል። በተለይ ለእንዲህ ዓይነት ሕገመንግሥታዊ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ትልቅ ሚና ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስ መልኩ የተዋቀረ መሆንና ሌሎች ተቋማትም በዚሁ ልክ እውነተኛና ዴሞክራሲያዊ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ለማስቻልና አቅማቸውን ለመገንባት የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። ይህ በሆነበት ሁኔታ ደግሞ እንዲህ ዓይነት የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ፈጥኖ ለማስተናገድ ከባድ መሆኑ አይቀርም።
በዚህ ሂደት ውስጥ ግን አንዳንድ አካላት ይህ የክልል እንሁን ጥያቄ አሁኑኑ ካልተመለሰ ሞቼ እገኛለሁ የሚሉ ፉከራዎችን በማሰማት ላይ ይገኛሉ። ይሁንና በተለይ ዝርዝር ጉዳዮችን አይቶ ውሳኔ ለመስጠት በርካታ የሕግ ክፍተቶች ባሉበት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን ትክክለኛና ፍትሃዊ ምላሽ እንዲያገኙ ጊዜ መስጠት ተገቢ ነው።
የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት ለማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ በማንኛውም ጊዜ ክልል የመሆን ሕገመንግሥታዊ መብት ቢያጎናፅፍም አፈፃፀሙ ላይ ግን ክፍተቶች እንዳሉ ይታያል። በተለይ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን ተግባራዊ ከማድረግ አስቀድሞ ሊከሰቱ የሚችሉ ጥያቄዎችን መፍታት ላይ የግልፅነት ጥያቄዎች ይነሳሉ። ለምሳሌ ከዕዳና ንብረት ክፍፍል ጋር ተያይዞ በሕገመንግሥቱ በግልጽ ያልተመለሰ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች የሚመለሱበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።
በሌላም በኩል የክልል እንሁን ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 3/ሀ-ሠ የተዘረዘሩ ነገሮች ሲሟሉ እንደሆነም ሊታወቅ ይገባል። በዚህ አንቀፅ ከተዘረዘሩ ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሕዝበ ውሳኔ በማደራጀት ምርጫ ቦርድ እንዲያስፈጽምለት ሲጠይቅ ነው የሚል ሃሳብ ሰፍሯል። ይህ ከሆነ በኋላ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔውን አካሂዶ በአብላጫ ድምጽ ተቀባይነት ሲያገኝና ክልሉ ሥልጣኑን ሲያስረክብ ክልልነቱ ሊረጋገጥ ይችላል።
ይሁን እንጂ አሁን የምንገኝበት የለውጥ ወቅት ከመሆኑ አንፃር መንግሥት ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚቀርቡ ዘርፈብዙ ጥያቄዎችን ለመመለስ በሩጫ ላይ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ ግጭቶችና የዜጎች መፈናቀልን ለማስቀረትና አስተማማኝ ሰላምና መረጋትን ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ያለበት ወቅት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማሻሻል በሩጫ ላይ ነው። ከዚህም ጎን ለጎን በመጪው ዓመት የሚካሄደውን አጠቃላይ አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት የሚደረግበት እንዲሁም አጠቃላይ የሕዝብ ቆጠራ ለማካሄድ ቅድመዝግጅት እያደረገ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል።
በሌላ በኩል መንግሥት የጀመራቸውን ዘርፈ ብዙ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለማደናቀፍ የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አካላትን በማሰማራት የሚፈጠሩ ችግሮችንም ለመፍታት መንግሥት በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ይገኛል። በአደባባይ የለውጥ አመራሮችን ለመግደልና በቀጥታ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረጉ ሙከራዎችም የዚሁ አካል ናቸው። በቅርቡ ተሞክሮ የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥትም የሚታወስ ነው።
በመሆኑም መንግሥት ለሚነሱ ጥያቄዎች ሕገመንግሥቱን መሠረት በማድረግ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ጥረት እያደረገ ባለበት ሁኔታ በክልል እንሁን ጥያቄ ስም ግጭት ለመፍጠርና ሰላምን ለማደፍረስ መሞከር አገርን የሚያፈርስ ተግባር መሆኑ ፈጽሞ ሊረሳ አይገባም። በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውም መብት ተግባራዊ የሚሆነው፤ ሰላምና ጸጥታ ብሎም ምቹ ሁኔታዎች ሲኖሩ ነው። ሰላምና ጸጥታ ባልተረጋገጡበት ሁኔታ ክልል ለመሆንም ሆነ በሰላማዊ መንገድ አገርን ለመገንባት አዳጋች በመሆኑ ሊታሰብበትና ጥቄያዎችን በሰላማዊ መንገድ ብቻ ማስመለሱ ላይ ሊተኮር ይገባል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2011