አርቲስት አስካለ አመነሸዋ ሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩን ሲሆን ሐሙስ ሰኔ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት በባለወልድ ቤተ ክርስቲያን ስርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል። ጥበቡና የጥበቡ ቤተሰቦች ምንጊዜም ያስቧቸዋል።
አርቲስት አስካለ አመነሸዋ በ1923 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለዱ ሲሆን በቤተሰቦቻቸው መለያየት ምክንያት ጅሩ ወደሚገኙት አያታቸው ወ/ሮ ጌጤነሽ ተ/ማርያም ጋር በመሄድ የልጅነት ጊዜአቸውን አሳልፈዋል። ነፍስ ካወቁ በኋላ በአባታቸው ቀኝ አዝማች አመነሸዋ ናዴ ምርጫ ትዳር መስርተው መኖር ቢጀምሩም በ1932 ዓ.ም ከጅሩ ከአባታቸው በመጥፋት እና ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ብቻቸውን መኖር ይጀምራሉ።
ወዲያውም የኢትዮጵያ ነጻነት ከወራሪው ፋሽስት ኢጣሊያን እንደተመለሰ ወደ ድሬዳዋ በመሄድ በዚያ መኖር ይጀምራሉ። በድሬዳዋ ከዚራ አካባቢ ቡና ቤት ከፍተው በመስራት ላይ ሳሉ ትዳር በመመስረት እና የቡና ቤቱን ስራ በመተው ሁለት ልጆችን ወለዱ። ሆኖም ግን የነፍሳቸው ጥሪ እረፍት ስለነሳቸው በዚህ ሁኔታ መኖሩን አልወደዱትም። ፊታቸውን ወደ ኪነጥበቡ አዞሩ።
የቴአትር ጅማሮ ስኬት
መረጃውን ከብሔራዊ ቴአትር ገጽ ላይ እንዳገኘነው በ1941 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ይመለሳሉ። በ1948 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ቴአትር ቤት (በአሁኑ ብሔራዊ ቴአትር) “ዳዊትና ኦሪዮን” የተሰኘው ቴአትር ለሕዝብ ሲቀርብ እህታቸው ወ/ሮ ሙሉ እመቤት የኦሪዮን ሚስት ሆና ስትሰራ በመመልከታቸው የወ/ሮ አስካለ ፍላጎትም ወደ ቴአትር በእጅጉ ተሳበ።
በመሆኑም ፊደል እንኳን ያልቆጠሩት ወ/ሮ አስካለ በቴአትር ቤቱ ለመቀጠር ማመልከቻ ያስገባሉ። ባስገቡት የቅጠሩኝ ማመልከቻ መሰረት ለሙከራ አንድ ሁለት ተውኔት ካሰሯቸውና ችሎታቸውን ከመዘኑ በኋላ በወር ሰባ ብር እየተከፈላቸው ሊሰሩ በቴአትር ቤቱ ተቀጠሩ።
አርቲስት አስካለ አመነሸዋ በ1948 ዓ.ም በግርማቸው ተ/ሃዋርያት ተደርሶ በፍራንስ ዜልቬከር በተዘጋጀው “ቴዎድሮስ” ቴአትር ላይ የእቴጌይቱን ገጸባህርይ በመላበስ የመጀመሪያ የመድረክ ስራቸውን ጀመሩ።
በ1949 ዓ.ም ተዋናይቷ አርቲስት አስካለ አመነሸዋ በፈረንሳዊው ሞሊየር ተደርሶ በሀዲስ አንተነህ በተተረጎመው እና በፍራንስ ዜልቬከር በተዘጋጀው “ስስታሙ መንጠቆ” ላይ ከተወኑ በኋላ እውቅናቸው ባልተጠበቀ መልኩ በመጨመሩ “ይህች ልጅ ተውኔት የምትሰራው ድርሻዋን ሰው እያነበበላት ነው። ትምህርት የላትም።” ተብሎ ለአለቃቸው ተነገረባቸው። በዚህም ምክንያት አለቃቸው “ፊደል ቆጥረሽ ቢያንስ ማንበብና መጻፍ ችለሽ “ጎንደሬው ገብረማርያም” ላይ መተወን አለብሽ የሚል ትዕዛዝ ሰጧቸው።
በቀጣዩም ሶስት ወራት ውስጥ አርቲስት አስካለ አመነሸዋ ንባብና ጽሑፍ ችለው በ1950 ዓ.ም ናቫልዲያን በደረሰው ኮሎኔል ስለሽ ድፋባቸው በተረጎመው እና በተስፋዬ ተሰማ በተዘጋጀው “ጎንደሬው ገብረማርያም” ቴአትር ላይ በመተወን ድንቅ ችሎታቸውን አስመሰከሩ። በመቀጠልም “ማንም ሰው” ቴአትር ላይ የማንም ሰውን እናት፣ “ቂመኛው ባህታዊ” ላይ ጥሩነሽን፣ “ኦቴሎ” ላይ ኢሚሊያን፣ “የከተማው ባላገር” ላይ የባላገሩን ሚስት፣ “ደህና ሁኚ አራዳ” ላይ የሮምነሽን፣ “የድል አጥቢያ አርበኛ” ላይ የፊታውራሪውን ሚስት፣ “ደመ መራር” ላይ ንግስተ ሳባን፣ “አሽርቶስ ንጉስ” ላይ ንግስቲቱን አስተርን፣ “ታርቱፍ” ላይ ዘርፌን፣ “ሻጥር በየፈርጁ” ላይ ዋናዋን ገጸ ባህርይ፣ “የአዛውንቶች ክበብ” ላይ እመቤቲቱን በመወከል ተውነዋል። “አንድ አመት ከአንድ ቀን” እና “ስራሽ ያውጣሽ” የተባሉት ተውነቴቶችም ላይ በድንቅ ብቃታቸው ተውነዋል።
ተሰጥኦዋቸው በቴአትር ብቻ ያልተገደበው አርቲስት አስካለ አመነሸዋ በኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ የመጀመሪያው በሆነው “ሒሩት አባቷ ማነው” በተሰኘው ፊልም ላይ በመሪ ተዋናይነት የቡና ቤቷን ጸጊቱን ገጸባህርይ ተላብሰው ተውነዋል። “ሕይወት ዙሪያ” በተሰኘው ፊልም ላይም የግፈኛው ዳኛ አዛኝቱ ሚስት ገጸባህርይን በመተወን የሙያ ብቃታቸውን እና የላቀ የስነ-ምግባር እመቤትነታቸውን አሳይተዋል። ስራዎቻቸውም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለበርካታ አመታት ቀርበዋል።
ሽልማቶች
ከእነዚህ በተጨማሪ አርቲስት አስካለ አመነሸዋ በሰሜን አሜሪካ ካናዳ ኤክስፖ 67 እና በካርቱም በተካሄደው የትርኢት ዝግጅት ላይ በገጽ-ቅብ (ሜካ አፕ) ባለሙያነት ተመድበው ከልዑካን ቡድኑ ጋር ተሳትፈዋል። በቴአትር፣ በቴሌቪዥን ድራማዎች እና በፊልሞች ላይ እስከ አያትነት የሕይወት ዘመናቸው የተወኑት አርቲስት አስካለ አመነሸዋ በርካታ ሽልማቶችን ተሸልመዋል።
“ስራሽ ያውጣሽ” የተሰኘውን ተውኔት ሲተውኑ በትወናቸው የተማረኩ አንድ ተመልካች አንድ ወቄት የሚመዝን የወርቅ መስቀል ከነ ሀብሉ ሸልመዋቸዋል። “ሒሩት አባቷ ማነው” የተሰኘው የመጀመሪያው ፊልም ላይ በመተወናቸው ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ እጅ የወርቅ ሽልማት ተቀብለዋል። በዊልያም ሼክስፒር በተደረሰውና በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን በተተረጎመውና በተዘጋጀው “ኦቴሎ” ቴአትር ላይ በመተወናቸው በድጋሜ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡
በ2007 ዓ.ም ኢዮሀ ሲኒማ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በጋራ ባዘጋጁት የኢትዮጵያ ፊልም ስራ 50ኛ ዓመት ኢዮቤልዮ በዓል ላይ በፊልም ስራ ላበረከቱት የላቀ አስዋጽኦ ልዩ የክብር ሽልማት እና የእውቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። በ2008 ዓ.ም ደግሞ በሶስተኛው “ጉማ ሽልማት” ላይ በኢትዮጵያ የፊልም ጥበብ የ2008 ዓ.ም ምርጥ የእድሜ ዘመን ተሸላሚ ሆነዋል። ብጡል የሆቴል እና ቱሪዝም አማካሪ የ2011 ዓ.ም የእናቶች የምስጋና ቀን ተሸላሚም ነበሩ።
አርቲስት አስካለ አመነሸዋ ሩህሩህ፣ ደግ፣ ለሰው አዛኝ፣ ሙያቸውን በአግባቡ ለተተኪዎች ሳይሰስቱ ያካፈሉ አንጋፋና ታዋቂ የነበሩ ሲሆን አምስት ልጆች እና ስምንት የልጅ ልጆችንም አፍርተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2011
አብረሐም ተወልደ