በትግራይ ክልላዊ መንግሥት አጋሜ አውራጃ ተንከተ በምትባል አካባቢ በ1953 ዓ.ም ተወለዱ። እስከ ስደተኛ ክፍል አሰፈ በሚባል አካባቢ በሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ከስድስተኛ ክፍል በኋላ ግን የተማሩት በአዲግራት ከተማ ነው። እስከ ስምንተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ግን በአገሪቱ በተከሰተው ፖለቲካዊ ለውጥ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ውትድርና ለመግባት ተገደዱ። ከጦር ሜዳ መልስም የትውልድ ቀያቸውን ለቀው በሽሬ፥ መቐለና ሐረር ኖረዋል። የደርግ መንግሥት ሥልጣኑን ከለቀቀበት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በሐረር ከተማ ጎጆ ቀልሰው ኖረዋል። ወትሮም እንግዳ ተቀባይ የሆነው የሐረር ነዋሪውም የትግራዩን ቤተሰብ እንደ ቤቱ እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ፈጠረለት። የዛሬው የዘመን እንግዳ አቶ ምዑዝ ገብረሕይወት መልካምና ተግባቢ ባህሪ ያላቸው በመሆናቸው ከሐረሪዎቹ ጋር ተቀላቅሎ ለመኖር አልተቸገሩም። በተለይም ደግሞ ለሕዝብ ያላቸው ተቆርቋሪነት በበርካቶች ዘንድ ከበሬታን አሰጣቸው። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ባዩበት ሁሉ መንግሥትን እየነቀፉ እንዲያርም በድፍረት ይናገራሉ።
ይሁንና ይህ ሁኔታቸው ያልጣማቸው የኢህአዴግ ካድሬዎች ከዚህ በፊት የነበሩበት የውትድርና ታሪክ መዘው በማውጣት አሰሯቸው። የሐረር ከተማ ሕዝብ ግን አቶ ምዑዝን ብቻቸውን አልተዋቸውም። ለከተማ አስተዳደሩና ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ሁሉ ያለመታከት አቤት በማለት ከአንድ ዓመት የእስር ቆይታ በኋላ በዋስ እንዲፈቱ አደረገ። ከእስር ከተፈቱም በኋላ ቢሆን የካድሬዎቹ ማስፈራሪያና ዛቻ ያማረራቸው አቶ ምዑዝ ለዓመታት የኖርባትን ሐረርና ሥራቸው ለቀው ወደ አዲስ አበባ መጡ። አዲስ አበባ ከመጡ በኋላም ቢሆን ይህ ለሕዝብ መብት ተሟጋችነት አልለቅ አለቸውና በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ የመልካም ችግሮች እንዲፈቱ መንግሥትን ይሞግታሉ። ይህን የሕዝብ ተቆርቋሪነት ያየው አዲስ አበቤም በተለያዩ ጊዜያት ለሕዝብ እንደራሴነት አጭቷቸዋል። በ36 መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥም የሕዝብ ክንፍ ሆነው በመመረጥ መንግሥት ያላየውን ክፍተት ነቅሰው በማውጣት እንዲፈታ ሰርተዋል። እኚህ ግለሰብ ታዲያ ከአንድ ዓመት በፊት የመጣውን ለውጥ በግንባር ቀደምትነት አደባባይ ወጥተው በመደገፋቸው ምክንያት የቅርብ በሚሏቸው ሰዎች ሳይቀር ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል። ወደ ትውልድ ቀያቸውም በኀዘንና በደስታ እንዳይገቡ ማስፈራሪያና ዛቻ የደረሰባቸው መሆኑን አጫውተውናል። ከአቶ ምዑዝ ገብረሕይወት ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- የሕዝብ ክንፍ ሆነው በአገለገሉባቸው ዓመታት የሕዝብን ቅሬታ መፍትሄ እንዲያገኝ ከማድረግ አኳያ ስኬታማ ነበርኩ ይላሉ?
አቶ ምዑዝ፡- በተመርጥኩባቸው ተቋማት ሁሉ ትክክለኛውን የሕዝብ ጥያቄ በማቅረብ እንዲፈታ የበኩሌን ጥረት አድርጌያለሁ ብዬ አምናለሁ። በተለይ ከለውጡ ሁለት ዓመታት በፊት የሕዝቡ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ባለሁባቸው ኮሚቴዎች ሁሉ በግሌ ጥያቄ እያቀረብኩ በአካል ድረስ በመጎብኘት፥ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ለውጥ እንዲመጣ ታግያለሁ። ለዚህም አብነት አድርጌ መጥቀስ ካስፈለገም ከለውጡ በፊት በቂሊንጦ፥ በቃሊቲ፥ በዝዋይና በሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤቶች በመዟዟር የሚፈፀመውን የሰብአዊ መብት አያያዝ ምን እንደሚመስል በአካል ለማየት ችያለሁ። በወቅቱ ታራሚዎቹ ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀምባቸው በአንደበታቸው ነግረውኛል።
በተለይም በወንዶቹ ብልትና በሴቶቹ ጡት ላይ ውሃ በማንጠልጠል የሚሰራው ኢሰብአዊ የሆነ የምርመራ ሂደት መገንዘብ ችለናል። ይህንን ስር የሰደደ የሰብአዊ መብት ጥሰት ለሚመለከተው አካል ማለትም ለፍትህ ሚኒስቴር፥ ለፌዴራል ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሪፖርት አድርጌያለሁ። በጉብኝታችን ወቅት ጋዜጠኞች ሄደው ከእስረኞቹ ቃል በቃል የሚፈፀሙባቸውን በደል ቢቀርፁም ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮች ወደ ውስጣቸው ተመልክተው ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ችግሩ ለሕዝብ ይፋ እንዳይሆን አገዱት። እኔ ላይም በተለያየ መልክ ጫና ይደርስብኝ ጀመር። እንዲያውም ሊያስሩኝ ቀን ቀጠሮ ይዘው ሳለ ነው ለውጡ መጥቶ ነፃ ያወጣኝ። ለነገሩ ይህ ለውጥ ሳይመጣ በፊትም ቢዘገይም እንኳ ሰብአዊ መብት የጣሱ ለሕግ ተላልፈው እንደሚሰጡ አምን ነበር። በወቅቱ ለሕዝብ መብት ያልቆሙ አላማቸው ሕዝብን ማገልገል ያልሆነ ሰዎች ለሕዝብ ተሟጋችነቴን አልወደዱትምና ከፍተኛ ማስፈራራት ያደርሱብኝ ነበር። የሃሰት ምስክርም ፈልገው ባልሰራሁት ወንጀል ሊያስሩኝ ደፋ ቀና እያሉ ነበር። በማንኛውም ስብሰባ እንዳልሰበሰብም፥ በየትኛውም ሚዲያ ሃሳቤን እንዳላስተላልፍም ክልከላ እስከማድረግ ደርሰው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በቤተሰቦቼ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስባቸው ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ለውጥ መምጣቱ ለሕዝቡ ምን ፈይዷል? ከለውጡ በኋላስ ዛቻና ማስፈራሪያው ቆመ?
አቶ ምዑዝ፡- እንዳልኩሽ ለውጡ ሲመጣ አገሪቱ ብቻ ሳትሆን እኔም ነፃ ወጥቻለሁ። ለዚህም ነው ከማንም በፊት ዶክተር አብይን በይፋ ወጥቼ የደገፍኳቸው። በእኔ እምነት ይህ ለውጥ ባይመጣ ኖሮ አገሪቷ ላይ የነበረው ስር የሰደደ የመልካም አስተዳደር ችግርና የፖለቲካ ውጥረት ወደለየለት ትርምስ ውስጥ ይከተን ነበር። እኔ እንዲያውም የዶክተር አብይ በዛ ወሳኝ ወቅት መምጣት ፈጣሪ አገሪቱን ለመታደግ አስቦ የላካቸው ነው የሚመስለኝ። በተለይም ደግሞ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ አስተዳደሩና የአስተዳደሩ ካድሬዎች የሚፈፅሙት ግፍ ማብቂያ አይኖረም የሚል ስጋት ነበረኝ።
ይህንን ስል ግን ባለፉት 27 ዓመታት ምንም መልካም ነገር አልተሰራም ማለቴ እንዳልሆነ ልብ እንድትይልኝ እፈልጋለሁ። በተለይም በመሠረተ ልማት ዝርጋታ በርካታ የሚጠቀሱ ሥራዎች ተሰርተዋል። በዚህም የቀድሞው የኢህአዴግ አመራር ሊመሰገን ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- የትግራይ ተወላጅ ሆኖ ህወሓትን መቃወም አሁንም እንደነውር የሚቆጠርበት ጊዜ ደፍረው ለመውጣት ያስቻሎት ምን ነበር? በዚህ ምክንያትም በኀዘንም ሆነ በደስታ ከተወለዱበት ቀዬ እንዳይገቡ መከልከሎት ምን ያህል እውነት ነው?
አቶ ምዑዝ፡- የሚሰሩ የመልካም አስተዳደሮችን ይፋ በማድረጌና በመቃወሜ እንዳልሽው ብዙ ክልከላዎች ተደርጎብኛል። በተለይም ደግሞ በኀዘንም ሆነ በደስታ ወደ ተወለድኩበት አካበቢ እንዳልሄድ ተከልክለሃል ያልሽው ትክክል ነው። በባለቤቴ እህት ቀብር ላይ ለመገኘት ለመሄድ በተዘጋጀሁበት ጊዜ ልክ ሰሞኑን በዶክተር አረጋዊ በርሄ ላይ የተፈፀመውን ዓይነት ድብደባና ወንጀል እኔም ላይ ሊፈፀምብኝ እንደሆነ ቀድሜ ሰምቼ ቀረሁኝ። ከዚያ ወዲህ ምንም ዓይነት ነገር ቢፈጠር የትውልድ ስፍራዬ መመለስ አልችልም። በፈጣሪ ድጋፍ እስካሁን ምንም ጉዳት አልደረስብኝ እንጂ ብዙ ጊዜ ሙከራዎች ተደርጎብኛል።
አንድ ካፍቴሪያ ላይ ሁለት ሴቶች ወደ እኔ መጥተው አንዷ አሲድ ሌላዋ ደግሞ መርዝ ይዛ ሊያጠቁኝ ሲሞክሩ በአካባቢው ሰዎች በመኖራቸውና እኔም ነገሩን ቀድሜ በመረዳቴ ለማምለጥ ችያለሁ። ዶክተር አረጋዊ በታሰሩበት ዕለትም አጎና ሲኒማ ሜዳው ላይ ሻይ ቤት ሳለሁ አምስት ሰዎች መጥተው አስፈራርተውኛል። ሰዎቹ «ከዶክተር አረጋዊ ጋር የምታደርጋቸው ተቃውሞዎች በጣም መጥፎ ስለሆነ ተጠንቀቅ!» ብለውኛል። ከሚገርምሽ ወደ ቀብር፣ ኀዘንና ሰርግ ቢኖርብኝም እንኳ በእግሬ መሄድ አልችልም፤ ምክንያቱም እዚያ ሲመጣ እንደ እባብ ቀጥቅጡት የሚል ትዕዛዝ በመተላለፉ ነው። አሁንም ቢሆን ይዝቱብኛል፣ ይገድሉኛል ወይም ያስገድሉኛል ብዬ ከነስማቸው ዘርዝሬ ለሚመለከተው የፍትህ አካል ሁሉ ያሳወቅኳቸው ሰዎች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኞቹ የህወሓት አመራሮች የትግራይ ሕዝብና ህወሓት አይነጣጠሉም ሲሉ ይደመጣሉ፤ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
አቶ ምዑዝ፡- ለእኔ የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። ደግሞ አብዛኛው የኢትዮጵያ ታሪክ ያለው ትግራይ ውስጥ ነው። ትግራይ እኮ እነ አፄ ዮሐንስ፣ እነ ራስ አሉላ፣ እነ ንግስት ማክዳ (ሳባ)፣ እነ ቅዱስ ያሬድ፣ እነ አጼ ካሌብ፣ እነ አቶ መለስ ዜናዊ ያፈራች ናት። እነዚህ ሰዎች የታገሉትና ያስተዳድሩ የነበሩት ለትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ አንድነት ጭምር ነው። የተዋጉትም ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ነበር። ከዚህ አንፃር ህወሓት ተዋግቶ ሥልጣን ከያዘና ለ27 ዓመታት አገሪቱን ካስተዳደረ በኋላ አሁን ደግሞ ጊዜ ደርሶ ሥልጣኑን ሲለቅ የክልሉን ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ለመነጠል ጥረት ማድረግ አለበት ብዬ አላምንም።
ከዶክተር አብይ መምጣት ጋር ተያይዞ ትግራይ የከተሙት የህወሓት አመራሮች ሕዝቡን እንዲጨቆንና የእነርሱ ጠባቂ እንዲሆን ነው እያደረጉት ያሉት። በእኔ እምነት የትግራይ ሕዝብና ህወሓት አንድ አይደሉም፤ በኢትዮጵያዊነቱ ያምናል። የትግራይ ሕዝብ ከሌሎቹ ብሔሮች ጋር ተጋብቶ ተዋልዷል። ከኢትዮጵያ ተለይቶ መኖር አይችልም። አሁንም ቢሆን የትግራይ ሕዝብ ተገድዶ እንጂ በፍላጎቱ የህወሓት አጎብዳጅ መሆን አይችልም። ይህ ሁኔታ በትንሽ ቀናት ይለወጣል የሚል እምነት አለኝ። በአሁኑ ወቅትም የለውጥ ጅማሬዎች አሉ፤ ፓርቲዎችም እየበዙ ነው። እርግጥ ነው እነርሱን ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት አለ። ግን በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይችልም። ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ እንደሌላው ሕዝብ ዴሞክራሲና ነፃነት ማግኘት አለበት ብዬ ነው የምከራከረው።
አዲስ ዘመን፡- በእነ ዶክተር አረጋዊ ላይ የተፈፀመው እንግልት በክልሉ ዴሞክራሲና በሃሳብ የመናገር ነፃነትን ከመገደብ አኳያ ምን ዓይነት አሉታዊ ሚና ይኖረዋል?
አቶ ምዑዝ፡- በነገራችን ላይ ሰሞኑን በነዶክተር አረጋዊ ላይ የተፈፀመው ድርጊት ከሕዝቡ ባህል ውጪ ነው። በትግራይ አስከሬን ትልቅ ክብር ይሰጠዋል። አይደለም ድብደባና እንግልት ፍፁም በሆነ ፀጥታና መረጋጋት ነው አስከሬን እንዲሸኝ የሚፈቀደው። በሌላ በኩል ዶክተር አረጋዊ የህወሓት ነባር አመራርና ታጋይ የነበሩ ሰው በመሆናቸው ልክ እንደሌላው ታጋይ ክብር እንጂ ዱላ አልነበረም የሚገባቸው። ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ነው። አሁን እኮ እነርሱን የተቃወመ ወይም ያልደገፋቸው ሰው አገር መግባት አይችልም። ለኀዘን እርሙን ማውጣት፣ ለሰርግ መታደም አይችልም። ያለበለዚያ ከእነርሱ ጋር ማጨብጨብ አለበት። እነሱ “እሺና አዎ” የሚላቸውን ነው የሚፈልጉት። በቅርቡ እንደምታውቂው እንደ እኔ ፊት ለፊት የሚናገሩ ሰዎች ቤት እየተመረጠ እንዲፈርስ ተደርጓል። ይህ ደግሞ አያዋጣቸውም። አንድ ቀን ሕዝቡ ገንፍሎ ሲወጣ እነርሱ ምን እንደሚደርስባቸው ይታወቃል። የሚያዋጣቸው ሰው የፈለገውን እንዲያስብና እንዲናገር መፍቀድ ነው። ደግሞም ሰውን አስገድደሽ ማኖር የምትችይው ለተወሰነ ጊዜ ነው። መጥፎ ነገር ሰርተሽ ሕዝቡ ይቀበለኛል ማለት ሞኝነት ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በትግራይ ክልል ሕዝባዊ በዓላት ላይ የፌዴራል መንግሥቱንና ዶክተር አብይን የሚነቅፉ መፈክሮች መስማት እየተዘወተረ መጥቷል። አንዳንድ ሰዎች ይህ ሁኔታ ሕዝቡን ከሌላው ሕዝብ ጋር ያቃርናል የሚል ስጋት አላቸው። እርስዎስ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ምዑዝ፡- ትክክል ነው!። በመሰረቱ ይህንን የሚለው ሕዝቡ አይደለም። የተደራጁ አካላት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ነው መንግሥትን የሚቃወሙት። አብዛኞቹም ይህንን በሉ ተብለው በጽሑፍ ተቀብለው ነው የሚወጡት። በቀብሩ ላይም እንደሰማሁት ከየከተማውና አውራጃው 50 ካድሬዎች ተውጣጥተው መጥተው የዚህን ዓይነት አላስፈላጊ ተግባር የፈፀሙት። የመጡትም ይህንን ለማድረግ እንጂ ለቀብር አይደለም። በነገራችን ላይ እኔም ሆንኩ ዶክተር አረጋዊ ልክ እንደሌላው ካድሬ ሁሉ በትውልድ ስፍራችን የመኖር፥ የመሄድ እኩል መብት አለን። አንተ ተቃዋሚ ስለሆንን መሬታችንን አትረግጥም ማለት ማንም አይችልም። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይህንን መብታችንን ነፍገውናል። ሌላው ይቅርና እንኳን በትግራይ መቐለ ይቅርና እዚህ ባለሁበት ቦታም ገፍፈውኛል። በቀብሩ ዕለት እነዛ ከእያንዳንዱ ወረዳ የተውጣጡት 50 ሰዎች ከተማዋን ሲያናውጡት ነው ያደሩት። ሕዝቡ እያለቀሰ ባለበት ወቅት እንዲህ መባሉ ትክክል አይደለም። ትግራይ ምን ሆነች በሚል በጣም ኀዘን ተሰምቶኛል።
አዲስ ዘመን፡- የትግራይ ሆነ የሌሎች ክልሎች የመገናኛ ብዙኃን ሕዝብን ከሕዝብ የሚጋጩ መልዕክቶች እያስተላለፉ በመሆኑ የተሰጣቸው ነፃነት መገደብ አለበት የሚሉም ሰዎች አሉ። የእርሶ እምነት ምንድን ነው?
አቶ ምዑዝ፡- እንዳልሽው በአሁኑ ወቅት ያሉ ሚዲያዎች እገሌ መጣብህ በማለት አንዱን በአንዱ ላይ በማነሳሳት ሥራ ላይ ተጠምደዋል። የትግራይና የአማራ ክልል ሚዲያዎች ኢትዮጵያን ቁልቁል የሚደፋ አሉታዊ መረጃ ነው የሚያስተላልፉት። በጣም የማዝነው ደግሞ ምሁራን ነን ባዮችን ነው። እነዚህ ሰዎች ትክክለኛ የሕዝብ ተቆርቋሪ ሆነው ሳይሆን የፓርቲ ቅጥረኛ ስለሆኑ ነው እንዲህ ዓይነት መረጃ የሚያሰራጩት። የኢትዮጵያ መንግሥት ሊቆጣጠራቸው አልቻለም። ጦር አሰልጥነዋል፣ ሚሊሻ አሰልጥነዋል። ጡረታ የወጡ ጀነራሎች እያሰለጠኑ ናቸው። መጣብህ ስለሚባልም የትግራይ ሕዝብ ባላወቀው ሃጢያት እየተጨነቀ ነው ያለው። የመጨረሻውን ችግር የሚፈጥሩት ሚዲያዎች በመሆናቸው መንግሥት ሚዲያን መቆጣጠር አለበት። በተጨማሪም ሕዝቡን ለጦርነት የሚያነሳሱ ዘፋኞችንም አንድ ሊላቸው ይገባል። በሌላ በኩልም ልዩ ኃይል የሚባለው የፖሊስ አካል ሥርዓት ማስያዝ ይጠበቅበታል። በነገራችን ላይ ሕገመንግሥቱ ያስቀመጠው ክልሎች ልዩ ኃይል የሚባለው ፖሊስ እንደሚመለምሉና እንዲያደራጁ እንጂ መትረየስ እንዲ ያስታጥቁ አልፈቀደላቸውም። በዚህ መልኩ ነው ብዙ ቦታ ችግር እየደረሰ ያለው። ስለዚህ ሚዲያ፣ ምሁራንና ልዩ ኃይል የሚባሉት የኢትዮጵያንና የትግራይን ሕዝብ የሚያጣሉ በጣም ችግር እየፈጠሩ እንደሆኑ ግልፅ ነው። ይህንን ሁሉንም ብዙኃን መገናኛዎችን መንግሥት ተቆጣጥሮ ሥርዓት ማስያዝ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የትግራይ ክልል አመራሮች በተለያዩ አካባቢዎች መፈናቀሎች ቢኖሩም በትግራይ ሕዝብ ያልተፈናቀለው መልካም አስተዳደር ስላለ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። መፈናቀሉም የመጣው ከዶክተር አብይ መምጣት ጋር ተያይዞ እንደሆነ ያነሳሉ። በእርግጥ በትግራይ መፈናቀል የለም? የተባለውስ ነገር ተጨባጭነት አለው ብለው ያምናሉ?
አቶ ምዑዝ፡- በመጀመሪያ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀለው የትግራይ ሕዝብ ነው። አሁንም ከ100 ሺ በላይ የትግራይ ተወላጆች ተፈናቅለው ይገኛሉ። እነዚህ ተፈናቃዮች ሌሎቹ አካባቢዎች እንደተደረገው መመለስ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። በዚህ አጋጣሚ የአማራን ሕዝብ በጣም ላመሰግን እወዳለሁ። ምክንያቱም የትግራይ ተወላጆች ሲፈናቀሉ የአማራ ሕዝብ ካሉበት ድረስ በመሄድ ንብረታቸውን ወስደው አስረክበዋቸዋል። ወርቅ ቤት የነበራቸው ወርቆቻቸውን መልሰውላቸዋል። የሚገርምሽ ዘርተው የነበሩትንም እህላቸውን አጭደው ሳይቀር ነው ወስደው ያስረከቧቸው። ይህ ደግሞ የኖረ ኢትዮጵያዊ እሴት ነው።
በቅርቡም እንደሰማሁት 20 እና 30 ተሽከርካሪዎች ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከኅብረተሰቡ ተውጣጥተው በመሄድ እባካችሁ ወደ አገራችሁ ወደ አማራ አገር ተመለሱ ብለዋቸዋል። በሌላ በኩል ግን በትግራይ የተደረገው ሴራና የተደረገው እንዳይመለሱ ነበር። መፈናቀሉ የተከሰተው ከዶክተር አብይ መምጣት ጋር ተያይዞ እንደሆነም አላምንም፤ አልቀበለውም። ምክንያቱም ይህ መፈናቀል የጀመረው 2009 ዓ.ም ነበር። ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን የመጡት ደግሞ መጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ነው። ስለዚህ ይህ ሃሳብ በየብሔሩ የተለኮሰ ነው ብዬ የማምነው።
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም ይህች አገር በጎሳ በጎጥ ትከፋፈላለች፣ ትለያያለች ይሉ ነበር። አሁን እየሆነ ያለው በዶክተር አብይ የተጠነሰሰ አይደለም። ዶክተር አብይ ከመጡ በኋላ እንደውም ስለሰላም ነው የዘመሩት። እርሳቸው ባይመጡ ኖሮ ሕዝብ ይባላ ነበር። በዚህ መልኩ ዶክተር አብይ ያመጡት መፈናቀል የለም። “ምን መደረግ አለበት?” ካልሺኝ ጠንከር ያለ እርምጃ መወሰድ አለበት ነው መልሴ። ሕዝቡ ወደ አንድነት መመለስ አለበት። መፈናቀል አሁን የመጣ አይደለም ቀደም ብሎ የተጀመረ ነው። ዴሞክራሲ በትግራይ የለም። ስለሌለ እኮ ነው ሰዎች የተደበደቡት። ትግራይ ጋዜጣም መጽሔትም አይገባም። ህዝቡ ዴሞክራሲ ያመጡት እነሱ ናቸው። ግን ታፍኖ ነው ያለው። አሁን ደግሞ መቐለ ላይ የከተማዋ የህወሓት አመራሮች ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተቀራርበው መስራት አለባቸው። ዶክተር አረጋዊን፣ ዓረናንና እኛን ኑ እስቲ ማለት ነበረባቸው። ልዩነታችን ላይና በቅሬታዎቻችን ዙሪያ ያሉን ነገር የለም። ሁላችንም እናልፋለን ግን ምን ዓይነት ትግራይና ኢትዮጵያ ትፈጠር የሚል ነው አቋማችን።
አዲስ ዘመን፡- ህወሓት ለዴሞክራሲ ነው የታገልኩት፣ ደምም የፈሰሰው የሚል ሃሳብ አለው። እና መርሆው አሁን ካሉኝ ጋር አይጣረስም?
አቶ ምዑዝ፤ ትክክል ነው። ይጣረሳል። በፈሰሰው ደም ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ መጥቷል። ከደርግ የተሻለ ነገር ታይቷል።
አጼ ምኒልክም ለኢትዮጵያ ብዙ ነገር ሰርተዋል። ስልክ፣ ባቡር አስገብተዋል፣ አገር ጠብቀዋል። ጃንሆይም ብዙ መልካም ነገሮችን ሰርተዋል። የአፍሪካ ህብረት እንዲመሰረት አድርገዋል። ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም ጥፋቱ እንዳለ ሆኖ ሰርቷል። አቶ መለስም ለአገሩ ጥቂት የማይባሉ መልካም አስተዋፅኦዎችን አበርክቷል። ከዚህ አንፃር ህወሓት የተነሳበትን አላማ ለማስፈፀም ያደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው። ግን አሁን ያለው ሁኔታ ከዚህ አቋሙ የሚንሸራተት ነው የሚመስለው።
አዲስ ዘመን፡- የዓረና አባል የሆነ ሰው መቐለ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ ምክክር ላይ ሲናገር አንዳንድ የህወሓት አመራሮች በጭብጨባ ለማቋረጥ ሙከራ አድርገዋል። ይህ አንድ ለዴሞክራሲ ቆሜያለሁ ከሚል ፓርቲ አመራሮች እንዲያውም መስራቾች ይጠበቃል? ሃሳብን በውይይት መፍታት ሲቻል ለማቋረጥና ተጽእኖ ለመፍጠር የተደረገውን ነገር እንዴት ያዩታል ?
አቶ ምዑዝ፡- ትክክል ነሽ! ዴሞክራሲ የለም ብዬሻለሁ። እንዲያውም ትላልቅ ሰዎች ነበሩ ሲያጨበጭቡ የነበረው። በእውነት ይህ ተግባር የማይገባ ነው። እነዚህ ሰዎች ትላልቅ ሰዎች የሚባሉ ናቸው። ወደ ቤተክርስቲያን፣ መስኪድ ነው መሄድ ያለባቸው። በእዚህ ዕድሜያቸው እኮ የተጣላውን ሰው ማስታረቅ ነበር የሚጠበቅባቸው እንጂ እንደዚህ ዓይነት ጭብጨባ ማድረግ ከእነሱ የሚገባ አልነበረም፤ ወንጀልም ነው። የአረና አባል ሲናገር በጭብጨባ ማቋረጣቸው እኮ ዴሞክራሲ አለመኖሩን ነው የሚያሳየው። በነገራችን ይህ አጋጣሚ በመገናኛ ብዙኃን ስለተላለፈ እንጂ ሌላ ቦታም እንደዛ ነው የሚደረገው። ይህንን ጉዳይ የፌዴራል መንግሥት እንዴት እንደሚመለከተው አላውቅም።
እኔ የማውቀው የትግራይ ሕዝብ ውሃ ስጠኝ ስትለው ማር የሚያቀርብ ነው። ለሰንደቅ ዓላማው ሟችና የዋህ ሕዝብ ነው። ይህንን ጉዳይ በተቃወምኩበት ጊዜ የተረፈኝ ነገር ባንዳ መባልን ነው። እኔም በትግራይ ነፃነት እንዲወጣ፣ ሰው እንዳይበደል፣ መንገድ እንዳይዘጋ ነው የታገልኩት። ሌሎች በተናገሩት ሰላማዊ የትግራይ ሕዝብ አሁንም በ70ዎቹ እንደነበረው ዓይነት ተገንጣይ እየተባለ ነው። አሽከርካሪዎች ትግራዋይ በመሆናቸው ችግር እየደረሰባቸው ነው። እየተጎዳ ያለው እንጀራ ፍለጋ ቤተሰቡን ለማስተዳደር የመጣ ነው እንጂ እነርሱ አይደሉም። ማንም ሰው በትግራይ ተወላጅነት ብቻ መለየት የለበትም፤ እንዲህ የሚያደርጉ ማቆም አለባቸው። ትግራዋይ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መከበር አለበት። መታወቂያ ብቻ ሳይሆን የተሽከርካሪ ሰሌዳም «ኢት» ቢባል ሁሉም ሰው ሌላው ብሔር ችግር እንዳይደርስበት የሚከላከል ይሆናል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ሕዝቡ ግን የትግራይን መገንጠል ይፈልጋል ብለው ያምናሉ? እንበለውና ትግራይ ብትገነጠል ተጎጂ የሚሆነው ማነው?
አቶ ምዑዝ፡- በመሰረቱ ትግራይ አትገነጠልም። በምንም መንገድ አይታሰብም። ሕዝቡ፣ ጦሩ፣ ታጋዮችም፣ ካድሬውም ይህንን አያስቡትም። የተከበሩ ዶክተር ደብረጽዮንን አከብራቸዋለሁ። ትግራይ ከገቡ በኋላ ብዙ ለውጦች አድርገዋል። በየቀበሌው፣ በየገበሬ ማህበሩ ሕዝቡን ይበዘብዙ የነበሩትን በመቀየር ለውጥ አምጥተዋል። ማዳበሪያ በግዳጅ ይገዛ የነበረውን ቀይረዋል። እርሳቸው እንዲህ ያደርጋሉ ብዬ አላምንም። ደግሞም ከሌሎች አገሮች ለመገናኘት የሚያስችል ወደብ መኖር አለበት። ከኤርትራ ጋርም አልተስማሙም። በመሆኑም አያስኬድም፣ አያስቡትም። ትግራይ ብትገነጠል ተጎጂ የሚሆነው የትግራይ ሕዝብ ነው። በእኔ እምነት ይህንን የሚያስቡት በ1960ዎቹ የነበሩ ሰዎች እንጂ አዲሱ ትውልድ አይደለም። ስለዚህ ትግራይ በምንም መልኩ ትገነጠላለች ተብሎ አይታሰብም።
አዲስ ዘመን፡- ከዴሞክራሲ ጋር ተያይዞ በህወሓት ሕግ እየተጣሰ ነው ይከበር እየተባለ በተለያየ ጊዜ መግለጫ ይሰጣል፣ ፌዴራል መንግሥቱ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠርም ጥረት ይደረጋል። በተዘዋዋሪ መንገድ ሕገ መንግሥትን ያለማክበር ሁኔታ አለ። በፍርድ ቤት በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ተከሳሾችን ሸሽጎ የመያዝ ሁኔታ ይስተዋላል ይህ እንዴት ያዩታል?
አቶ ምዑዝ፡- ሕገመንግሥት በየትኛውም ክልል መከበር አለበት። ይህ ማለት ግን በሕገመንግሥቱ ላይ እኔም የማልስማማባቸው ድንጋጌዎች አሉ። በተለይም የራስን ዕድል በእራስ መወሰን እከመገንጠል የሚለው፣ የፖሊስ ኃይል ማደራጀት የሚለውና ነፃ ገበያ የሚለው አንቀፅ መውጣት እንዳለበት አምናለሁ። በአማራና በትግራይ ክልል መካከል በተፈጠረው ፖለቲካዊ ውጥረት እኮ ሕዝቡ በገበያ እየተቸገረ ነው። አዲስ አበባ ጤፍ 3 ሺ 600 መቶ እየተሸጠ ያለው። ይህንን የኑሮ ውድነት ያመጣው ደግሞ በአገሪቱ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት መኖሩ ነው።
በሕገ መንግሥቱ ሊሻሻሉና ሊከበሩ የሚገባቸው ነገሮች አሉ። ምሁራኖችም ይህንን ይደግፉታል። ሕገ መንግሥቱ ይከበር ሲባል ራስም ማክበር ይገባል። በፌዴራል ፍርድ ቤት የሚፈለግ ተጠርጣሪ አስቀምጦ ሕግ ይከበር ማለት አይቻልም። ሕገ መንግሥቱ የሃሳብ ነፃነት፣ የመደራጀት፣ የሰብአዊ መብት መጠበቅን ደንግጓል። ዶክተር አረጋዊ ለቀብር በተገኙበት ወቅት ድንጋይ ተወርውሮባቸዋል። ይህ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ድርጊት ነው። የእርሳቸው ደጋፊዎች ወይም ሹፌራቸው ተወስደው የተፈጸመባቸው ወንጀል ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጻረር ነው። እርሳቸውን ማሰር ተገቢ አይደለም። ስለዚህ በትግራይ ሕገ መንግሥቱ እየሰራ አይደለም። የሚነገረውና የሚተገበረው የተለያየ ነው። ሕገ መንግሥቱ በመጀመሪያ መከበር የነበረበት በትግራይ ክልል ነው። ግን እነርሱ እያከበሩ አይደለም፡ አንዳንድ የሚሸፋፈኑ ነገሮች ስላሉ ነው እንጂ ሕገ መንግሥቱ መከበር የነበረበት በእነርሱ ነው። በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች፣ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ መጠየቅ አለበት ብዬ አምናለሁ። ካልሆነ ሕዝቡ ያጉረመርማል። አቶ ጌታቸው አሰፋ ብቻ ሳይሆኑ ሕዝብን ያሰቃዩ፣ የደበደቡ፣ የነጠሉ ተጠርጣሪዎች አሉ። በመሆኑም በአገር አቀፍም ሕግ መከበር አለበት።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ጉዳይ በተለይ የፌዴራል መንግሥቱ ፈርቷል እየተባለ ይታማል? በዚህ ረገድ ከፌዴራል መንግሥት ምን ይጠበቃል ብለው ያምናሉ?
አቶ ምዑዝ፡- በመሰረቱ የፌዴራል መንግሥቱ እያሳየ ያለው ትዕግስት መለሳለስ ነው ብዬ አላምንም። መቐለ ላይ የከተሙ የህወሓት አመራሮች ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተቀራርበው መስራት አለባቸው። መለሳለስ ሳይሆን አስተዋይነት ነው ብዬ አስባለሁ። ዶክተር አብይን እንደ ቆራጥና አስተዋይ መሪ ነው የማያቸው። ወጣት መሪ ናቸው። ደርግ መግደል ስላበዛ ነው የተደመሰሰው። የጠላውን ያለ ማስረጃ ይገድል ነበር። ሰላማዊ ሰውንም ገድሎ ይፎክር ስለነበር እንጂ ከትግራይ ከደደቢት ተነስተው አያሸንፉትም ነበር። ትዕግስቱ አሁን የበቃ ይመስለኛል። መፍራት ሳይሆን ማስተዋል ነው የሚመስለኝ። ከእንግዲህ ግን በእዚህ መልኩ የሚቀጥል አይመስለኝም። ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ እንዲሁም ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ አቶ እዘዝ ዋሴና አቶ ምግባሩ ከበደ ህልፈትን ተከትሎ በእስኪሪብቶ ብቻ ሳይሆን ሌላውንም ማድረግ እንችላለን ብለው ስለተናገሩ ፍርሃት ነው ብዬ አልወስደውም።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት መቐለ ላይ ለከተሙት የህወሓት አመራሮች የሚያስተላልፉት መልዕክት አለዎት?
አቶ ምዑዝ፡- እነዚህ ሰዎች ከዩኒቨርሲቲ ወጥተው ወይም ከትምህርታቸው ተለይተው ትግል ገብተው የታገሉ ናቸው። ኢህአዴጎች ናቸው። አብዛኞቹ ጥሩ ዕውቀት ያላቸው አሉ። ግን ይህንን ወደ መጥፎ እየተቀየረ ነው። የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያውያን የተለየ አይደለም። እንገነጥላለን እየተባለ የሚነሳው ሃሳብ መቆም አለበት። ደግሞም እነዚህ መቐለ ላይ የከተሞ የህወሓት አመራሮች ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተቀራርበው መስራት አለባቸው። እረፍት መውሰድም ይገባቸዋል። አገርን በመለወጥ ብዙ ሰርተዋል። የበደሉትን በይቅርታ በማለፍ አማካሪ ሆነው ቢቀጥሉ ይበጃቸዋል። ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ቢታረቁ ይሻላቸዋል። ከአማራ ሕዝብ ጋር ጦርነት ቢከፈት የሚሞተው ደሃው ነው። እነርሱም ችግር ላይ ይወድቃሉ።
በተጨማሪም ዶክተር አብይ ኤርትራ ገብተው እርቅ አውርደዋል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የወረደውን ሰላም ማየት አለባቸው። እነርሱም ወደ ሽምግልና ቢሄዱና ሰላም ቢሰፍን ጥሩ ነው። ለእኛ ጦርነት አይጠቅመንም። ሰብአዊ መብት ይከበር የምንለውንም ቀርበው ቢያነጋግሩን ጥሩ ነው። ለነገሩ እኔ ከእነርሱ የምፈልገው ነገር የለኝም። መፍትሄው በንግግር የሚፈታ ቢሆን ይሻላል። ወደ ኢትዮጵያዊነታቸው መመለስ አለባቸው። እነዚህ ሰዎች የተቃወማቸውን ከማባረር የትግራይ ሕዝብን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲያስተዳድሩ እጠይቃቸዋለሁ። ዶክተር አብይም ሰሞኑን በምክር ቤት እንደተናገሩት ይፈጽማሉ ብዬ አምናለሁ። እኔም ቃለምልልስ እንዳልሰጥ የሚፈጸም ማሳቀቅ መቆም አለበት። የአማራና የትግራይ ሕዝቦች የተጋቡና የተዋለዱ ናቸው። በመሆኑም ጦርነት መግጠም አይገባቸውም። ሁለቱን ህዝቦች ለመለያየት የሚደረገውም ነገር መቆም አለበት። በማህበራዊ ድረ ገጽ የሚያጣሉ መረጃዎች ማስተላለፍ ሊቆም ይገባል። ያልሆነ ወሬ መወራት የለበትም። ሁላችንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ማገዝ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- ለቃለምልልሱ በአ ንባቢዎች ስም አመሰግናለሁ
አቶ ምዑዝ፡- እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 29/2011