
አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ‹ስካይትራክስ› የ2025 የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ሽልማትን ለስምንተኛ ጊዜ ማሸነፉ አየር መንገዱ ለሚያቀርበው አስተማማኝና ጥራት ያለው አገልግሎት የተሰጠ አንዱ ማረጋገጫ እንደሆነ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፣ ሽልማቱ አየር መንገዱ በመላው ዓለም ባሉ ደንበኞቹ ያተረፈውን ታማኝነት የሚያሳይ ነው።
‹‹በስካይትራክስ ምርጡ የአፍሪካ አየር መንገድ ተብለን በድጋሚ እውቅና በማግኘታችን ተደስተናል።ስኬቶቻችን የአየር መንገዱ መላ ቤተሰብ የጠንካራ ሥራ፣ የቁርጠኝነትና የሙያ ፍቅር ማረጋገጫዎች ናቸው።ዓለም አቀፍ ደረጃውን ለጠበቀ አገልግሎትና አፍሪካን ከሌላው ዓለም ጋር ለሚያገናኝ ትስስር ቁርጠኛ ሆነን እንቀጥላለን›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ በመሆኑ በአህጉሪቱ የአየር ትራንስፖርት ልማት ቁልፍ ተዋናይ ሆኖ እንደሚቀጥል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።አየር መንገዱ በዘመናዊ አሠራር፣ መዳረሻዎችን በማስፋት እና በዘላቂ የዲጂታል ሥርዓት በመታገዝ አዳዲስ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በማስቀመጥ እየተሠራ እንደሆነም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ መስፍን ገለፃ፣ አየር መንገዱ ጠንካራ የፋይናንስ አፈፃፀም አለው።በአሁኑ ወቅት በአምስት አህጉራት ከ160 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ መዳረሻዎች አሉት። እያደገ የመጣውን የተጓዦች ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የአየር ማረፊያ መሠረተ ልማቶችን እያዘመነ ይገኛል።በዚህም የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት 25 ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግድ ሆኗል። ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ በቢሾፍቱ ግዙፍአውሮፕላን ማረፊያ ለማስገንባት በዝግጅት ላይ ነው።
የ‹ፌርፋክስ አፍሪካ› ኩባንያ ሊቀ መንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው በ‹ኤክስ› ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ አየር መንገዱ ለስምንተኛ ተከታታይ ዓመት ሽልማቱን ማሸነፉ እንደ ሁልጊዜውም ሀገርንና ሕዝብን የሚያኮራ ተቋም መሆኑን እንደሚያመለክት ገልፀዋል።
የ100 ሀገራት ዜጎች የሆኑ 22 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ምርጡን አየር መንገድ ለመምረጥ ድምጽ መስጠታቸውን የጠቆሙት አቶ ዘመዴነህ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ተብሎ ለስምንተኛ ተከታታይ ዓመት መመረጡ የሚያኮራ እንደሆነ ገልጸዋል። የአየር መንገዱ ደንበኞች ያላቸውንታማኝነት እና ሠራተኞቹ ለድርጅቱ ዘላቂ ስኬት ያሳዩትን ትጋትም አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፓሪስ በተካሄደው የ2025 የዓለም የአየር መንገድ ሽልማት ከ‹‹አፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ›› በተጨማሪ ‹‹የአፍሪካ ምርጥ የቢዝነስ ክፍል››፣ ‹‹የአፍሪካ ምርጥ የኢኮኖሚ ክፍል››፣ ‹‹በቢዝነስ ክፍል ምርጥ ምግብ አገልግሎት ሰጪ›› ሽልማቶችንም አሸንፏል።“የአቪየሽን ዘርፍ ኦስካር” የሚባለው ዓመታዊው የዓለም የአየር መንገድ፣ ሽልማት በዓለም አቀፍ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በፈጠራና በደንበኞች ርካታ ዘርፎች የታዩ የላቁ አፈፃፀሞች እውቅና የሚያገኙበት ታላቅ መድረክ እንደሆነ ታውቋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም