
ዛሬ ዓለም በጤናው ዘርፍ ዘርፈ ብዙ ለውጦች እያስመዘገበች ትገኛለች። በተለይም ሕክምናውን በቴክኖሎጂ ከመደገፍ አኳያ ሀገራት ውድድር ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል። ይህ ውድድር እስከ ተቋማትም ድረስ የዘለቀ ነው። ይህ ደግሞ በየሀገራቱ የሕክምና ቱሪዝሙ (ሜዲካል ቱሪዝሙ) በስፋት እንዲታይ ዕድል ሰጥቶታል። ለመሆኑ ይህ ዕድል ለሀገራት ምን ዓይነት ጠቀሜታ ሊሰጥ ይችላል፤ በእኛስ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ በምን ዓይነት መልኩ እየተሠራበት ይገኛል፤ አዳዲስ እየገቡ ያሉ ተቋማትስ ምን ዓይነት አቅም ይዘው እየመጡ ናቸው ካልን ብዙ መልስ የሚሰጡ ጉዳዮችን ማንሳት እንችላለን።
የቤተሳይዳ አሜሪካን የሜዲካል ፕላዛና ለሀገር ይዞት ስለመጣው የተሻለ ዕድል ብቻ ብናነሳ ከሜዲካል ቱሪዝሙ አንጻር በርካታ ፋይዳዎች ያሉት ነው። ስለ ሜዲካል ፕላዛው ከማውራታችን በፊት ግን እንደነዚህ አይነት ተቋማት ሀገር ውስጥ መገንባታቸውና ሥራ መጀመራቸው ምን ይፈይዳል፤ የሜዲካል ቱሪዝሙን ከማስፋት አንጻርስ ምን አይነት ጠቀሜታ አላቸውና መሰል ጉዳዮችን እንመልከት።
የሕክምና ቱሪዝም ሕክምናን ወይም የጤና እንክብካቤን ለመከታተል ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር የመጓዝ ልምድን የሚያቀዳጅ ነው። ይህ ክስተት ደግሞ ዛሬ ላይ በጣም ዝነኛ እየሆነ መጥቷል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በጣም ታዋቂ ጭምር እየሆነ ነው። በዚህም ሙሉ ጤነኛ የሆነ ሰው ሳይቀር ሙሉ ምርመራ ያስፈልገኛል ብሎ ካሰበ ሀገር አቋርጦ የተሻለ ሕክምና ለማግኘት ይጓዛል። በዚህም የተሻሉ ናቸው ተብለው የሚጠቀሱት ሀገራት ከሕክምና ቱሪዝሙ የተሻለ ገቢ ያገኛሉ። ይህ ደግሞ ለዜጎቻቸው የተሻለ የጤና አገልግሎት ከመስጠት ያለፈ ሥራ እንዲሠሩ የሚያግዛቸው ነው። ከዚያም ባሻገር በየጊዜው በሕክምና ዘርፉ ራሳቸውን እንዲያዘምኑም ይሆኑበታል።
የሕክምና ቱሪዝም እንዴት ሀገር ውስጥ ይስፋፋል፤ ምን አይነት ምቹ ሁኔታን ይፈልጋል? ከተባለ በርከት ያሉ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል። ነገር ግን በዚህ ዓምዳችን የተወሰኑትን ብቻ ዘርዝረን እንመለከታለን። የመጀመሪያ የምናየው ወጪ ቆጣቢነቱን ሲሆን፤ ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ ሆነው በትንሽ ወጪ በቅርብ ርቀት መድኃኒቶችን፣ የሕክምና ሂደቶችን፣ የቀዶ ጥገና እና የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን ማግኘት ሲችሉ የሚፈጠር ነው፡፡
ሌላው ጥሩ እንክብካቤና ጥራት ያለው ሕክምና ማግኘት መቻል ሲሆን፤ ብዙ የሕክምና ቱሪስቶች የሚያገኟቸው የጤና እንክብካቤ ተቋማት ከፍተኛ ጥራት ያላቸው እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። ዘመናዊ የሕክምና ሥርዓቶችን የተከተሉ እንዲሆኑም ይሻሉ። ብዙ የሠለጠኑ የሕክምና ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎችን ማፍራት ወይም የላቀ ቴክኖሎጂ ማግኘቱ ጥሩ ምቾት ይሰጣቸዋልም። ስለዚህ እንደ ሀገር ተመራጭ የሕክምና ቱሪዝም ሀገር ለመሆን ይህንን ማሟላት የግድ ይላል።
የሕክምና ቱሪዝሙን እንዲጨምር የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ቀላልና ተደራሽ የመሆኑ ምስጢር ነው። አንዳንድ የሕክምና ሂደቶች በጣም ረጅም የጥበቃ ጊዜ ሊኖራቸው ይችላል። ወይም ደግሞ ሕክምናዎቹ በሚፈለገው መልኩ የሚገኝባቸው በተወሰኑ ሀገሮች ብቻ ሊሆን ይችላሉ። ስለዚህም ሕክምና ፈላጊዎች ቀለል ወደአለው ቦታና ተደራሽ ወደሆነበት ሀገር ያመራሉ። ሕክምናው በበለጠ ፍጥነት ወይም በብቃት የሚያገኙበትን ሀገር ምርጫቸው ያደርጋሉ።
ልዩ ሕክምናዎችን ማድረግ እንዲሁ የሕክምና ቱሪዝሙን ከሚያስፋፉ መንገዶች አንዱ ነው። አንዳንድ የሕክምና ሂደቶች ወይም ሕክምናዎች በአንዳንድ ሀገሮች ተለይተው ሊሰጡ ይችላሉ። በሌሎች ውስጥ ቢገኙም እነዚህ ታካሚዎች ልዩ እንክብካቤን ይፈልጋሉና ልዩ ሕክምናውን ከልዩ እንክብካቤው ጋር አጣምረው የሚሰጡ ሀገራትን ይመርጣሉ። በተጨማሪም በልዩ ሕክምናቸው ሁልጊዜ የማይገኙትን የሚሰጡትንም መርጠው ይሄዳሉ። ስለሆነም ይህንን አገልግሎት በልዩነት መስጠት ቱሪዝሙን ለማስፋት ከፍተኛ ፋይዳ አለው።
ሌላው የጤና እንክብካቤን ከቦታና ባህል ቱሪዝሙ ጋር ማስተሳሰር ነው። ለታካሚዎች ሕክምናቸውን ከጉዞ ጋር በማጣመር ዘና የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ይሻሉ። መድረሻቸውን እንደየቦታው ባህል፣ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ወይም የመዝናኛ ዕድሎችን በመምረጥ ጭምር ማድረግን ይፈልጋሉ። ይህም ለሰዎች ጤናማ አካባቢን ይሰጣል። እናም ሕክምና ከዚህ አንጻርም ታይቶ ምርጫ ይደረጋል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ተመራጭ እንደሆነች ማንም አይክደውም፡፡
ማንኛውም የሕክምና ቱሪዝም የጉዞ ሎጂስቲክስን እንደ መጓጓዣ፣ ማረፊያ፣ የቪዛ ፍቃድ እና የቋንቋ እንቅፋቶችን ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት። ከዚህ አንጻርም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አሠራር የተሻለ እንደሆነ ይገለጻል። ምክንያቱም ምርጥ የሆነ ዓለማቀፋዊ ብራንድ የተሰጠው አየር መንገድ አለ። ማረፊያንም በተመለከተ በተለይም በአዲስ አበባ እጅግ ቅንጡ የሆኑ ሆቴሎች እየተገነቡ እና የተገነቡም እንዳሉ ማንም የሚረዳው ጉዳይ ነው።
ሌላው የሕክምና ቱሪዝምን ያስፋፋል ተብሎ የሚታሰበው ጉዳይ የሕክምና ክትትል ነው። በውጭ ሀገር የሚደረግ ሕክምና ሙሉ በሙሉ ተደራሽ በሚሆንበት ጊዜ ታካሚዎች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ክትትል ወይም የሕክምና አማካሪዎች ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህም ከሐኪሞች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ወይም የጤና አጠባበቅን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የግድ በሀገር ቤት ወይም በቤት ውስጥ ሆነው ክትትል የሚያደርጉበት ሁኔታ መፍጠር የግድ ይላል። ስለዚህም ይህ አገልግሎት ካለ ሀገራት ተመራጭ እንዲሆኑ ዕድል ይሰጣቸዋል። በአጠቃላይ ኢንሹራንስና ሕግን ጨምሮ ሀገራትም ሆኑ ተቋማት በአግባቡ ተጠቅመውባቸው የሚሠሩ ከሆነ የሕክምና ቱሪዝሙ የማይሰፋበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም።
ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ ምን ይመስላል ከተባለ የኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ ኢንዱስትሪ ባለፉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ እጅግ የላቀ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሎ መውሰድ ይቻላል። ምክንያቱም ለሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ሆና ብቅ እንድትል የሚያደርጓትን በርካታ ሥራዎችን አከናውናለች፤ እያከናወነችም ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የጤና አጠባበቅ መሠረተ ልማቷን በማሻሻልም የተሻሉ ተቋማት እንዲፈጠሩ እያደረገች ስለመሆኑም ማሳያው በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የቤተ ሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ ነው። ሆስፒታሉ የሀገሪቱን የሕክምና አገልግሎት ለማዘመንና የተሻለ ጥራት ያላቸው አገልግሎቶችን ለመስጠት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚሠራ ሲሆን፤ ከሀገር አልፎ ዓለማቀፋዊ ተቀባይነት እንዲኖረው ተደርጎ የተዋቀረ ስለመሆኑ በምረቃው ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ ተናግረዋል።
ይዘዋቸው የመጡት አገልግሎቶች ከቴክኖሎጂ አንጻርም የሀገር ውስጥ ተገልጋዮችን ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ ጭምር የሕክምናው ቱሪዝም መስሕብ ስለመሆናቸውም አንስተዋል። እያደገ የመጣውን የጤና አጠባበቅ አገልግሎት፣ የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ታካሚዎችን ፍላጎት ማሟላት እንዲቻልም የሚያደርግ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
ቤተሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ ከሀገር አልፎ አፍሪካ ላይ ጭምር የማይገኙ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችለውን ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያ ይዞ የመጣ እንደሆነ የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ በኢትዮጵያ ያለውን የጤና እንክብካቤ ተቋማት ወይም ልዩ የሕክምና አገልግሎቶች ላይ ተደጋጋሚ መቆራረጦችን ከማስቀረቱ ባለፈ ዜጎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላል። ከዚያም በላይ ደግሞ እነዚህ አገልግሎቶችን ሽተው የሚመጡ ታካሚዎችን ከጎረቤት ሀገሮች ጭምር ለመሳብ ይረዳልም ብለዋል፡፡
መንግሥት ለዜጎቹ ጤና በእጅጉ ይጨነቃልና የሜዲካል ቱሪዝም ለማስፋፋት በሚያደርገው ጥረት ለሚሳተፉ እንደ ቤተሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ አይነት የግል አልሚዎችን በእጅጉ ይፈልጋል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ሜዲካል ፕላዛው ለሚሠራቸው ቀጣይ የማስፋፊያ ሥራዎች ከተማ አስተዳደሩ ከጎኑ እንደሚቆም አስረድተዋል። አክለውም የእንደነዚህ ዓይነት ተቋማት መስፋፋት እንደ ሀገር ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንዳለውና የውጪ ምንዛሪን በሀገር ውስጥ ማስቀረት እንደሚያስችል አብራርተዋል።
ንፁሕ ከባቢን በመፍጠርም ጤናማ ማኅበረሰብ እንዲኖር ከማድረግ አንጻር እንደነዚህ ዓይነት ሆስፒታሎች መኖር ሚናው የማይተካ ስለመሆኑ ገልጸው፤ ከጤናው ባሻገር አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ተስማሚና ዓለም አቀፍ ተፈላጊነት እንዲኖራት የሚያደርግ ነው። የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በመዲናዋ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የላቀ አገልገሎት መስጠት የሚያስችሉ የቱሪዝም፣ የጤናና የመንገድ ልማቶች እየተከናወኑ መሆኑንም ያሳያል። በተለይም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥ ነው ሲሉም አድናቆታቸውን ቸረዋል፡፡
በአፍሪካ የመጀመሪያው የልብ ሕክምና መሣሪያ የተገጠመለት፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአጥንት መመርመሪያ መሣሪያ የያዘው ሜዲካል ፕላዛው፤ በኢትዮጵያ የላቀ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ለሜዲካል ቱሪዝም የጎላ አበርክቶ ያለው ነው። ከዚያም ባሻገር አዲስ አበባን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ራዕይ ከማሳካት አንጻር ትልቅ አስተዋፅዖ የሚያደርግ እንደሆነም በመድረኩ ላይ አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ይህ ተቋም በዚህ መገንባቱና ሥራ መጀመሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እንደ ሀገር የሚያመጣ ነው። ለአብነት የዜጎችን ጤና ያሻሽላል፤ የተገጠሙለት ቴክኖሎጂዎች ዘመኑን የዋጁ በመሆናቸው አሁን በከፍተኛ ደረጃ እየተከሰቱ ያሉ ሕመሞችን ከመቀነስ አኳያ የማይተካ ሚናም ይጫወታል። በተለይም ከልብ ሕመም ጋር ተያይዞ እሠራበታለሁ ብሎ ይዞ የቀረበው ዘመናዊ መሣሪያ ለብዙኃኑ ጤና መፍትሔ የሚሰጥ ነው።
አዲስ አበባ ከተማን ፅዱና ለሕክምና ምቹ የሆነች ከተማ ከማድረግም አንጻር ተቋሙ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል። ከዚያም ጎን ለጎን በተላላፊ በሽታዎች ዜጎች እንዳይጠቁ ያስችላል። ስለሆነም እንደነዚህ ዓይነት ተቋማትን በማስፋት ለዜጎቻችን የተሻለ የሕክምና አማራጮችን ማመቻቸት የከተማችን ዋና ጉዳይ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
ሆስፒታሉን በኢትዮጵያ ውስጥ እንድንጀምርና እንድንሠራ ያደረገን ነገር ሀገሪቱ በብዙ መልኩ ምቹ አማራጭ ያላት በመሆኗ ነው። በዚህም ሆስፒታሉ በልዩ ክትትልና ድጋፍ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ ገንብተንና መሟላት ያለባቸውን የሕክምና ቁሳቁስ አሟልተን ለምረቃ አብቅተነዋል ያሉት ደግሞ የቤተሳይዳ አሜሪካን ሜዲካል ፕላዛ ችፍ ኦፊሰር ሚስተር ማርክ ናቸው።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ሜዲካል ፕላዛው በሕክምና ዘርፍ ዓለም የደረሰበትን የጤና አገልገሎት ለመስጠት የተዘጋጀ ነው። በኢትዮጵያ ደረጃ በቴሌ ሜዲስን፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በርቀት ሕክምና ዘመናዊና የሚለካ ሕክምና መስጠት የሚችልም ነው። ከዚህ አንጻርም ዜጎች በብዙ መልኩ የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ ይሆናሉ።
የሜዲካል ፕላዛው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አየለ ተሾመ እንደሚሉት ደግሞ፤ ይህ ተቋም የሕክምና ቱሪዝሙን ከማስፋት አንጻር፤ ዜጎቻችንንም ቢሆን ከተጨማሪ በሽታ ይታደጋቸዋል። የገጠማቸው ችግርም በአግባቡ መፍትሔ እንዲያገኝ ያስችላቸዋል። ለተጨማሪ ሕክምና ከሀገር ወጥተው የሚንከራተቱ ዜጎችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው በተሻለ አንክብካቤ እንዲታከሙ ይረዳቸዋል። በተለይም የልብ ሕመም መሣሪያው የብዙዎችን ችግር እንደሚፈታ ተስፋ የተጣለበት ነው።
ሜዲካል ፕላዛው ከዚያም ባሻገር ሌሎች ጥቅሞችም ያሉት እንደሆነ የሚናገሩት ሥራ አስፈጻሚው፤ አቅሙ ያላቸው ሰዎች ወደ ትልልቆቹና በቴክኖሎጂው የታገዙ ሆስፒታሎች ሲያመሩ የሕክምና መጨናነቁን ይቀንሳሉ። የሐኪሞችን ጫናም ያቀላሉ። ስለዚህም በተለይ የመንግሥት ሆስፒታሎች አካባቢ ያለውን ወረፋ ቀንሶ በተሻለ ጊዜ የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። እንዴት ቢባል በሽታን ለማከም ከምንም በላይ ቴክኖሎጂው ከፍተኛ ፋይዳ አለውና ሜዲካል ፕላዛው ይህንን ከማሟላት አንጻር የተሻለ ነው።
ሜዲካል ፕላዛው ከንጽሕና አንጻር እንኳን ቢጠቀስ ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ ባክቴሪያን የማስወገድ አገልግሎት የሚሰጥበት ዘመናዊ መሣሪያ የተገጠመለት ነው። ቀዶ ሕክምና ሳያስፈልግ ሕመሞችን ለማወቅ የሚያስችሉ መሣሪያዎችም በበቂ ሁኔታ ያሉት ነው። መብራትም ሆነ ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችም የሚከናወኑት በቴክኖሎጂ አማካኝነት ነው። ስለሆነም እንደ ሀገር ጠቀሜታው የጎላ ነው ሲሉ ይዞት ስለመጣው መልካም ዕድል ያብራራሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም