
ኢራን እና እስራኤል የዓለምን ቀልብ የተቆጣጠረ መጠነ ሰፊ ጦርነት ዉስጥ ከገቡ አንድ ሳምንት አስቆጥረዋል። ለብዙ ወራት በከፍተኛ ዉጥረት የቆየዉ የአገራቱ ግንኙነት ሰኔ 13 ቀን 2025 “ዘመቻ አምበሳው ተነሳ” በሚል መሪ ቃል እስራኤል ባደረገችዉ የአየር ጥቃት በይፋ ተለኮሰ። የኢራን የኒኩሊዬር ማብላያ ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠረዉ ጥቃት ግለቱን እያናረ የሰዉ ልጆችንም ስጋት እየተቆጣጠረ ባይጠበቄ አሰቃቂ ኩነቶች ቀጥሏል። ለእስራኤል ጥቃት አፀፋ ኢራን 150 የባለስቲክ ሚሳኤል እና ድሮኖችን በመጠቀም ከተሞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰች ሲሆን ሰሮካ ሆስፒታል ላይ የተፈፀመዉ ጥቃት ለመቶዎች መጎዳት መንስኤ እንደሆነ የተለያዩ የመገናኛ አዉታሮች ዘግበዋል።
ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ በሁለቱም ወገን ከ 800 በላይ ንፁሃን ሰዎች ተገድለዋል። ይህም ቀጠናዉን ብሎም ዓለምን ለከፍተኛ ስጋት እንደዳረገ መረጃዎች ያሳያሉ። በጉዳዩ ላይ በግልፅ አሜሪካ እና ሩስያ የገቡበት ሲሆን ሁለቱም በዲፕሎማሲ ይፈታ ቢሉም በተለይ አሜሪካ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን ስትጠቁም ሩስያ ይህን በመቃወም አስጠንቅቃለች ።
አዉሮፓዉያን ግጭቱ በዲፕሎማሲ እንዲፈታ ግፊት እያደረጉ ሲሆን ዓለም አቀፉ የሀይል ገበያ ደግሞ ሀርሙዝ የተሰኘዉ ቁልፉ የነዳጅ ዘይት ማመላለሻ መንገድ እንዳይዘጋ ትልቅ ስጋት ዉስጥ መዉደቁን ሮይተርስ የዜና ምንጭ አስታዉቋል። የግጭቱ ስፋት እና አጠቃላይ አካሄድ ዓለም ሶስተኛዉ ጦርነት እንዳይጀመር ስጋት ዉስጥ እየከተተዉ ይመስላል። ይህንን ጦርነት ከቀደሙት ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች አጀማመር ጋር የሚያመሳስሉት ማሳያዎች አሉ? መፍትሄ ለመስጠት የሚበጁ እድሎች ምንድን ናቸዉ? የተለያዩ መራጃዎችን እያጣቀስን የተነሳንበትን ርዕሰ ጉዳይ ቀጥለን እናብራራ።
አሁን ላይ እየተካሄደ ያለዉ የመካከለኛዉ ምስራቅ ትኩሳት ዓለምን ወደ ሶሰተኛዉ እልቂት ሊወስዳት ይችላል የሚያስብሉ ጉዳዮችን ተንታኞች በአራት ከፍለዉ ያስቀምጣሉ። የመጀመሪያዉ የተለያዩ ጎራዎች እና የእጅ አዙር ጦርነቶች በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ላይ የታዩ እና ለአጀማመሩም ትልቅ አበርክቶ የነበራቸዉ መሆናቸዉን ታሪክ ያስረዳል። ጦርነቶቹ ቅርፅ እንዲይዙ ያደረጋቸዉ ሀያላን አገራት ጎራ እየለዩ መሰለፋቸዉ ነበር። ሀያላኑ በጎራ ሲሰለፉ ከነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸዉ አገራትም እንዲሰለፉ ስለሚገደዱ መካረሮች ከቁጥጥር ዉጪ ሆነዉ ዓለም ሁለት ጊዜ የሰዉ ልጅን እልቂት አስተናግደዋል።
እስራኤል እና ኢራን በማካሄድ ላይ ያሉት ጦርነትም በተመሳሳይ ሀያላን ጎራቸዉን እያሳዩበት ይመስላል። The Economist ይዞት የወጣዉ መረጃ እንደሚያሳየዉ እስራኤል ከጅምሩ በአሜሪካ እየተደገፈች ሲሆን ከአቀማመጥ ቅርበት እና ጠቀሜታ አንፃር ደግሞ አብዛኞቹ የአዉሮፓ አገራት ለምሳሌ ጀርመን እና እንግሊዝ ከጎኗ እየተሰለፉ እንዳሉ የመረጃ ምንጩ ጨምሮ አስነብቧል። አብዛኞቹ የባህረ ሰላጤዉ አረብ አገራት እነ ሳዉዲ አረቢያ እና የተባበሩሩት አረብ ኤምሬትስም ከጎኗ እንደሆኑ ከመግለጫቸዉ መረዳት ይቻላል። በኢራን በኩል ሂዝቦላህ፣ እና ሃዉቲ ጦርነቱ ላይ በመሳተፍም ጭምር የተሰለፉ ሲሆን ሩስያ እና ቻይና በግልፅም በስዉርም አጋርነታቸዉን እያሳዩ መሆናቸዉን ሪፖርቶች በማሳየት ላይ ናቸዉ። ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ ሌሎች ተዋናዮችም ጎራቸዉን እየመረጡ የሚመጡ ስለሚሆን ሶስተኛዉ የሰዉ ልጅ እልቂት በቅርቡ ሊከሰት ይችላል።
ሁለተኛዉ ማሳያ ወታደራዊ ዝግጅት እና እሱን ተከትሎ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች ጦርነቱን ዓለምአቀፋዊ ይዘት ሊያላብሰዉ ይችላል። የመጀመሪያዉን የዓለም ጦርነት መነሻ ብንመለከት በዉጥረት ላይ የቆየዉን የአገራቱን ሁኔታ ያባባሰዉ የአርዱክ ፍራን ፈርዲናንድ በፅንፈኞች መገደል ሲሆን በዚህም ፖላንድ በ1918 ነፃ አገር ሆና እንድትወጣ መንስኤ ነበር። The International Institute Strategic Studies እንዳስቀመጠዉ እስራኤል እና ኢራን በወታደራዊ ብቃታቸዉ እና አቅማቸዉ ትልቅ ደረጃ አላቸዉ። ልዩነታቸዉ የቅርፅ እና የአላማ ብቻ ነዉ እንደ መረጃዉ።
አሁን ላይ ለእስራኤል እና ኢራን ግጭት እንደ አቀጣጣይ መንስኤ ተደርጎ በተለይ በእስራኤል በኩል የሚገለፀዉ የኢራን ኒኩሊዬር ጉዳይ ነዉ። የኢራን ኒኩሊዬር መታጠቅ ለህልዉናዬ አስጊ ስለሆነ እና አገሪቱ እያበለፀገችዉ ያለዉ ኒኩሊዬር ደግሞ በጣም አደገኛ መሆኑን መረጃ አለኝ ያለቸዉ እስራኤል ከ 60 እስከ 70 በመቶ የደረሰዉን ኒኩሊያር አስቆማለሁ፣ ካልሆነ ህልዉናዬ አደጋ ላይ ይወድቃል ስትል ብትቆይም ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ የአያቶላህን ስርኣት እናስወግዳለን ሲሉ ተደምጠዋል። ኢራን ያልተጠበቀ ጉዳት ሰሮካ ላይ ማድረሷን ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ካዝ ከዚህ በኋላ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ኮሚኒ በህይወት እንዲቆይ አንፈቅድለትም ማለታቸዉን ፍራንስ 24 ዘግቧል። ይህ አካሄድ በጎራ እየተከፈሉ ላሉ ሀያላን እንደ ማስጀመሪያ አመክንዮ በመሆን ወደ ሁሉን አቀፍ ግጭት ሊወስድ ይችላል።
ሶስተኛዉ ማሳያ የተራራቀ እና እርስ በርሱ ለያጠፋፋ የሚችል ርዕዮተ ዓለም ወይም “አይዲዮሎጂ” መኖሩ ነዉ ይላሉ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን። ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ትልቁ አባባሽ መንስኤ ፋሺዝም እና ዲሞክራሲን በተካረረ ልክ የሚያራምዱ ሀያላን መፈጠራቸዉ መሆኑን ታሪክ ያሳያል። በመካሄድ ላይ ያለዉ የእስራኤል እና ኢራን ጦርነት ላይም የየአገራቱ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ትልቁ ዘዋሪ እንደሆነ ተንታኞች ያስረዳሉ። እስራኤል ፓርላመንታሪ ዲሞክራሲን የምትከተል ሲሆን ኢራን ደግሞ እስላማዊ አብዮትን የምታራምድ እና የእስራኤልን ነፃ አገር የመሆን ሁኔታ ያልተቀበለች ናት። ይህም ማለት የአገራቱ ፖሊሲ እና እንቅስቃሴ የሚቃኘዉ በዚህ እሳቤ በመሆኑ ማንኛዉም ትርጓሜም በዚያዉ አግባብ ስለሚመነዘር ግጭቶች በተለያዬ ደረጃ ሲካሄዱ ቆይተዋል። የኢራን ኒኩሊዬር መታጠቅ የርዕዮተ ዓለሟን ለማሳካት ማስኬጃ ከሆነ የእስራኤል መርህ ይጣስ እና ቆይቶም ቢሆን ጦርነቶችን ማዋለዱ አይቀርም ይላሉ ተንታኞች። በሌላ በኩል የእስራኤል ርዕዮተ ዓለምም ለራሷ የሚመች አስተዳደር ለማምጣት እንድትሰራ ስለሚያስገድዳት የኢራንን አስተዳደር መዘወር ትፈልጋለች በማለት የሚሞግቱም አሉ።
አራተኛዉ ምልክት ሀያላን አገራት በሁለቱ ግጭት ጣልቃ መግባት መጀመራቸዉ ነዉ። በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች የታየዉ ተቀዳሚ መንስኤ ሀያላን አገራት እነ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ሩስያ፣ ፈረንሳይ እና የመሳሰሉት በተለያዬ አሰላለፍ መፋጠጣቸዉ እንደነበር ይታወቃል። እነዚህ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀያላን በመካሄድ ላይ ባለዉ የእስራኤል እና ኢራን ግጭት ዉስጥ እጃቸዉን እያስገቡ መሆናቸዉ የዓለምን ስጋት እየጨመረ ነዉ ይላል የ ዘ ኢንዲፐንደንት መረጃ።
የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሰኔ 19 ቀን 2025 እንደገለፁት በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ዉስጥ ኢራን የኒኩሊዬር ድርድሩን ማድረግ መቻል ወይም አለመቻሏን ካየን በኋላ ስለ ጦርነቱ መተባበር ጉዳይ አቋማችንን እናሳዉቃለን ማለታቸዉን BBC ዘግቧል። ፕሬዚዳንቱ ይህን የተናገሩት የኢራን ምክትል የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሜሪካ በጦርነቱ እጇን ካስገባች እንተላለቃለን በማለት ለBBC ከገለፁ ከ24 ሰኣታት በኋላ ነዉ ብሏል የዜና ምንጩ።
የአሜሪካ ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ ቀይ መስመር ያስባለንን ማሳያ እናንሳ። አሜሪካ በቀጥታ የምትሳተፍ ከሆነ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኢራን ጎን ሊቆሙ የሚችሉ ሀያላን በተለያየ ልክ እየታዩ ነዉ። ዘ ኢኮኖሚክ ታይምስ እንደዘገበዉ አሜሪካ በእስራኤል እና ኢራን ጦርነት እጇን እንዳታስገባ ሩስያ አስጠንቅቃለች። የሩስያ የዉጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ ማሪያ ዛሀሮቫ እንደገለፁት አሜሪካ በወታደራዊ መንገድ የምትገባበት ከሆነ ማንም ያልጠበቀዉ መጥፎ ነገር ይፈጠራል ብለዋል። ቻይናም እስራኤል የፈፀመችዉ ሉኣላዊነትን የተጋፋ በመሆኑ አወግዘዋለሁ ብላለች።
የአሜሪካ በእስራኤል በኩል መምጣት ለእስራኤል ትልቅ ጠቀሜታ አለዉ ይላሉ ከሜርት ቴሌቪዥን ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት የእስራኤል አምባሳደር የቼል ሌይተር። ይህንም ሲያብራሩ እስራኤል የኢራንን የኒኩሊዬር ማብላያ ከጥቅም ዉጪ ማድረግ ስለምትፈልግ ይህም ከ80 እስከ 90 ሜትር በጥልቅ የተቀበረ ፎርዶ የተሰኘ ኒኩሊዬር በመሆኑ ይሔን መምታት የሚችል ቦምብ ያላት ስለሆነ ነዉ ይላሉ። ጋዜጣ ፕላስ ያናገራቸዉ በቀጠናዉ የሶስተኛ ዲግሪያቸዉን እየሰሩ ያሉት ዳዊት መዝገበ ፀጋዬ እንደ ሌሎች ተንታኞች በዚህ አይስማሙም። የተባለዉ መሳሪያ አሜሪካ ቢኖራትም ይሄን ኒኩሊየር በቀላሉ መምታት አስቸጋሪ ነዉ። በተራራ ስር የተቀበረ በመሆኑ ተከታታይ ምት ይጠይቃል። በዚህ መካከል ደግሞ ኢራን አጋሮቿ በግልፅ ወደ ፊት ሊመጡ ስለሚችሉ ጦርነቱ ከቁጥጥር ዉጪ ሊሆን ይችላል በማለት ያብራራሉ።
ምንም እንኳን ተቀዳሚዉ የእስራኤል ስጋት ኒኩሊዬር ቢሆንም ኢራን እጅግ ዘመናዊ የባለስቲክ ሚሳኤሎችንም እንደታጠቀች መረጃዎች ያሳያሉ። አልጄዚራ እንደዘገበዉ ሀጂ ቃሰም የተሰኘ አዲስ የሚሳኤል ስሪት ባሳለፍነዉ እሁድ እለት ወደ እስራኤል የተወነጨፈ ሲሆን የእስራኤልን የአየር መቆጣጠሪያ መምታት እንደቻለ እና ከሌሎች ሚሳኤሎችም በላይ እጅግ ፈጣን ሆኖ መመዝገቡን ገልጿል።
ከላይ ባነሳነዉ አካሄድ የመካከለኛዉ ምስራቅን እጣፋንታ የሚወስኑ ሀይሎች እየተገለጡ ነዉ። ወደ ድርጊት ለመግባትም የአሜሪካን አካሄድ እየተጠባበቁ ይመስላል። ለሶስተኛዉ የዓለም ጦርነት ማስጀመሪያ የሆኑትን ማሳያዎች ለመቀልበስ አሁንም እድል አለ ይላሉ ዳዊት። ዘ ኢንዲፐንደንት ባወጣዉ ማብራሪያ አሁን ላይ ያሉት ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች፣ የተሻለ እና የነቃ ማህበረሰብ መኖሩ እና ፈጣን የመረጃ ልዉዉጦች ወደ ጦርነቱ እንዳንገባ ሊያደርጉ ይችላሉ በማለት ጥቆማዉን ያስቀምጣል። መሰልጠን በንግግር ማመን መሆኑን የሰለጠኑት የሚፈተኑበት ወሳኝ ጊዜ ነዉና መሰልጠናቸዉን እንዲያሳዩን እንመኛለን።
በመቅደስ ታዬ