
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በውጤታማነቱ እንዳይቀጥል በርካታ ፈተናዎች እንደተጋረጡበት ባለሙያዎች ይጠቁማሉ። እነዚህ ፈተናዎች ከውስጥ አሠራር ጀምሮ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ አንድና ሁለት ብቻ አይደሉም። ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ባለፉት በርካታ ዓመታት ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየውና አሁንም ድረስ መፍትሄ ያላገኘው የተተኪ አትሌቶች ጉዳይ ነው።
የተተኪ አትሌቶች ጉዳይ ሲነሳ ለዓመታት ፈተና ሆኖ የዘለቀው የአትሌቶች እድሜ ማጭበርበር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። ይህ የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ እንደ አፍሪካም ፈተና ነው። በኢትዮጵያ ግን አሳሳቢ መሆኑን በቅርቡ በድሬዳዋ በተካሄደው ከ18 እና 20 ዓመት በታች ቻምፒዮና ላይ ታይቷል። ባለፉት በርካታ ዓመታትም በእድሜ ገደብ በሚካሄዱ መሰል ውድድሮች በተገቢው እድሜ የሚወዳደሩ ታዳጊና ወጣት አትሌቶች እድሜ ቀንሰው (“አጭበርብረው”) በሚወዳደሩ ታላላቆቻቸው እየተዋጡ እንደሀገር ተተኪ ለማጣታችን ትልቅ ምክንያት መሆናቸውን ብዙዎች ይስማማሉ። ይህ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብቻ ሳይሆን የዓለም አትሌቲክስም ከአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት (ዶፒንግ) ቀጥሎ በስፖርቱ የተደቀነ ትልቅ አደጋ ሆኖ የተቀመጠ ነው።
ለዚህ ችግር ሁነኛው መፍትሄ በህፃናት አትሌቲክስ (kids atheletics) ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ነው ብለው በርካታ ሀገራት እየሠሩበት ነው። ባለተሰጥኦ ህፃናት አትሌቶችን በትክክለኛው ሳይንሳዊ መንገድ ማሰልጠን የተተኪ አትሌቶችን ችግር ለመፍታት እና ዘላቂ ስኬትን ለማረጋገጥ ትክክለኛው መንገድ ነው።
በአትሌቲክሱ በተለይም በመካከለኛ፣ ረጅም ርቀትና ማራቶን የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በህፃናት አትሌቲክስ ላይ መሥራት ከጀመሩ ቆይተዋል። ውጤቱንም እያዩ ይገኛሉ። ለዚህ አንዱ ማሳያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የተለያዩ አትሌቶችን ሲያሰልፉ መታየታቸው ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ረገድ ዘግይቶም ቢሆን በህፃናት አትሌቲክስ ላይ መሥራት ጀምሯል። ፌዴሬሽኑ ካለፈው አራት ዓመት ወዲህ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በትግራይና አማራ ክልል አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ ህፃናት ላይ እየሠራ ይገኛል። በቅርቡ ወደ ሌሎች ክልሎችም የማስፋፋት ሃሳብ አለው።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስልጠና ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ኢንስትራክተር ሳሙኤል ብርሃኑ፣ “የወጣት አትሌቶች የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ ሁሌ ብናወራው የማያልቅ ትልቁ ጉድለታችን ነው። ለአትሌቲክሳችን በሚገባው ደረጃ አለማደግ፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት ወደ ኋላ እየጎተተን የሚገኝ ትልቅ ችግር ነው።” ይላሉ። ለዚህ አንዱ ማሳያም የሚያደርጉትም ድሬዳዋ በተካሄደው የወጣቶች ቻምፒዮና ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በእድሜ ተገቢ ያልሆኑ አትሌቶች መሳተፋቸውን ነው።
እንደ ኢንስትራክተር ሳሙኤል ገለፃ፣ የህፃናት /kids አትሌቲክስ በኢትዮጵያ ዘግይቶ ቢጀመርም በመላው ዓለም ከዕድሜ ጋር የተያያዘውን ችግር እየፈታ ይገኛል። ከዚያም በላይ ተሰጥኦን መሠረት ባደረገ ተገቢው ሙያ ለተገቢው ሰው ተብሎ በዓለም አትሌቲክስ በስፋት በትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነው። አሰልጣኞች ከዚያ ጀምሮ የሚያሰለጥኑበት፣ ደረጃና ሂደት ያለውም ነው። አንድ ሰው አትሌት መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ በየትኛው የውድድር አይነት ነው መሰልጠን ያለበት፣ በውርወራ ወይስ በዝላይ፣ በሩጫ በየትኛው ርቀት በሚባልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሚያስችል ትልቁ የአትሌቲክስ መሠረት ነው።
ኢትዮጵያ በህፃናት አትሌቲክስ ላይ ለመሥራት በብዙ ምክንያቶች ብትዘገይም ከአትሌቶች እድሜ ጋር በተያያዘ ያለውን ትልቁን ተግዳሮት ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተደረገበት መሆኑን ኢንስትራክተር ሳሙኤል ያብራራሉ።
“ካለፈው አራት ዓመት ጀምሮ ነው እየሠራንበት የምንገኘው፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁለት 1ኛ ደረጃና በመለስተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምረን ህፃናቱ ፕሮጀክቶችን መቀላቀል የሚችሉበት እድሜ ላይ በሚደርሱበት ወቅት ተሰጧቸው ተለይቶ ባላቸው አቅም መሠረት ባደረገ መልኩ ትክክለኛው ሥርዓት ውስጥ ተመልምለው ይገባሉ። ይህን ተሞክሮ እንደመነሻ በማድረግ ዘንድሮ በድሬዳዋ ከተማና በትግራይና አማራ ክልል እየሠራን ነው፣ በሌሎች ክልሎችም ይቀጥላል። በአማራ ክልል ደሴ ከተማ በሁለት ትምህርት ቤቶች ላይ በስልሳ ህፃናት፣ በትግራይም በሁለት ትምህርት ቤቶች በስልሳ ህፃናት ላይ፣ በድሬዳዋ ከተማም በተመሳሳይ። ሌላው የተሰጥኦ አካባቢ ተብሎ የተለየው ኦሮሚያ ክልል ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይሆን ዘግይቷል፣ በቅርቡ ግን በአምቦና ጊንጪ አካባቢ የግድ ይጀመራል።” በማለት ኢንስትራክተር ሳሙኤል የህፃናት አትሌቲክስ በኢትዮጵያ ያለበትን ሁኔታ ያብራራሉ።
ኢትዮጵያ የህፃናት አትሌቲክስን በመጀመር ረገድ ብትዘገይም ከተጀመረ በኋላ የታየው ተስፍ “ቀደም ተብሎ ታስቦበት ቢጀመር” የሚል ቁጭት እንደፈጠረባቸው ኢንስትራክተር ሳሙኤል ይናገራሉ።
“አዲስ ነገሮችን ለመቀበል እንቸገራለን፣ ይህ ደግሞ ወደ ኋላ አስቀርቶናል” የሚሉት ኢንስትራክተር ሳሙኤል፣ የህፃናት አትሌቲክስን እንደ አፍሪካ የሚመራና የሰለጠነ ሁለት ሰው ብቻ ነው ያለው ይላሉ። አንዱ ደግሞ እሳቸው ናቸው። በዚህ ዙሪያ ትምህርቱን የወሰዱትም ከ10 ዓመት በፊት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሌሎች ባለሙያዎችም እየተፈጠሩ ነው። እነ ኬንያ ከ15-16 ዓመት በፊት ጀምረው አሁን ላይ ፕሮጀክቶቻቸው በሙሉ ከእድሜ ጋር በተያያዘ ችግር የለባቸውም። ተሰጥኦን መሠረት ያደረጉ በርካታ አትሌቶችን በዚህ ሥርዓት ውስጥ እያሳለፉ ውጤታማ እየሆኑም ይገኛሉ።
ኢንስትራክተር ሳሙዔል እንደሚያብራሩት፣ እነዚህ ህፃናት ተሰጥኦን ማጎልበት ላይ በደንብ ተሠርቶባቸው ከ7-8 ዓመት ጀምሮ ሃያ ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ብቁና ውጤታማ ይሆናሉ። በስልጠናና ልምምድ ተገርተው ነው የሚያድጉት። በኢትዮጵያ ከምልመላና ተሰጥኦ ልየታ ጋር በተያያዘ ብዙ አከራካሪ ችግሮች አሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ፕሮጀክት ወይም በትምህርት ቤት ሮጦ አንደኛ ከወጣ ታዳጊ “ይሄ ጥሩ ነው” እያልን ነው የምንመለምለው፣ ይህ ታዳጊ ሌላ ቦታ ቢወዳደር አንደኛ ላይወጣ ይችላል፣ ተሰጥኦውም ላይሆን ይችላል። አንዳንዴ እኛ ጋር የምናያቸው አትሌቶች ምናልባት አትሌት ሳይሆን ሙዚቀኛ ወይም ሌላ መሆን የሚገባቸው ይሆናሉ። የህፃናት አትሌቲክስ ላይ መሥራት ይህንንና መሰል ችግሮችንም ይቀርፋል።
በዚህ ረገድ ሌሎች ሀገራት በህፃናት አትሌቲክስ ላይ ብዙ ሠርተውበታል። ግን አልረፈደም ብለን ተነስተናል። “አንዳንዴ ከሌላው ዓለም ጋር እኩል ለመራመድ ግድ የሚሆኑብን ነገሮች አሉ፣ አሁን እነ ኖርዌይ፣ አሜሪካ ወዘተ እየሄዱበት ያለው ነገር ለዚህ ማሳያ ነው። ፉክክሩ ከአፍሪካ ጋር ብቻ ሳይሆን እንደ ዓለም ነው፣ ወደዚህ ሥርዓት ካልገባን እንደቀድሞው ከተጓዝን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምናልባትም ከ10 ዓመት በኋላ ያለንን ሊነጥቁን ይችላሉ። አሁን በማራቶን ጭምር እየመጡብን ነው፣ በአጭር ርቀትና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ደግሞ እኛ የለንበትም፣ ስለዚህ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤታማነት አይኖርም ማለት ነው። የብዙዎቻችን እንጀራ፣ የሀገር ኩራት የሆነውና በዓለም ከፍ ያደረገን ትልቁ ስፖርታችን መገለጫችን ይህን ባለመሥራታችን አይጠፋም ብለን ራሳችንን አጀግነን የምንቀመጥበት ነገር የለም።” ይላሉ ኢንስትራክተር ሳሙኤል።
ኢንስትራክተር ሳሙኤል ቀጥለው ሲያብራሩ፣ አሁን የግድ ስለሆነ ተጀምሯል። በትውልድ ቅብብሎሽ ደግሞ ይዳብራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ይናገራሉ። የተጀመረውን የህፃናት አትሌቲክስ ትልቅ ደረጃ ለማድረስ ብዙ ሀብት ይፈልጋል። እርግጥ ነው አሁን ብዙ የተሟሉ ነገሮች የሉም። ግን ካለመጀመር መጀመሩ ይሻላል። እንደ ሀገር ብዙ ነገሮች ላይሟሉ ይችላሉ፣ በዚህ ተስፋ ከመቁረጥ ግን እየሠሩ መታገል ይሻላልም ብለዋል።
“የትኛው አሰልጣኝ ነው የሚያሰለጥናቸው፣ ከህፃናት ሥነልቦና፣ ሥነምግብ ወዘተ ጀምሮ ብዙ የተለየ ነገር ይፈልጋል። የስፖርት ትጥቅ ትልቁ ጉዳይ ነው፣ የዓለም አትሌቲክስ የሚደግፈን ውስን ነው፣ ስልጠና የሚሰጥበት ቁሳቁስ በራሱ የተለየ ነው፣ ይሄ ሁሉ ባልተሟላበት ሁኔታ ነው የምንሠራው፣ ግን ችግሮችን ብቻ እያየን ከተቀመጥን የሆነ ጊዜ ላይ ስፖርቱ መቆሙ አይቀርም፣ ስለዚህ እየሠራን ክፍተቶችን እያየን ሕዝብና መንግሥት እንዲያውቅ በማድረግ መቅረፍ ነው ያለብን። እነኬንያም ሲጀምሩ እንዲህ ነበር፣ ዛሬ ግን በእነዳንጎቴ ግሩፕና በሌሎች ትልልቅ ኩባንያዎች የህፃናት አትሌቲክሳቸው ስፖንሰር እስከመደረግ ደርሰዋል።” የሚሉት ኢንስትራክተር ሳሙኤል፣ እኛም የህፃናትን አትሌቲክስ አስፈላጊነት ተረድተን ተግተን ከሠራን እነሱ የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ የሚያግደን ነገር የለም ብለው ያምናሉ።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በድሬዳዋ የወጣቶች ቻምፒዮና በተካሄደበት ወቅት፣ የነገ ተተኪ አትሌቶች መፍለቂያ የሆነው የህፃናት አትሌቲክስ ውድድርን በማየቱ መደሰቱንና ነገ ውጤታማ ለመሆን ከተፈለገ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግሯል።
“እውነት ለመናገር ባየሁት የህፃናት አትሌቲክስ ሰልጣኞችና በውድድራቸው በጣም ደስ ብሎኛል፤ እኛ ሀገር በደንብ አልተሠራበትም እንጂ የአትሌቲክሱ ውጤታችን ቀጣይነትና ተከታታይነት እንዲኖረው ህፃናት ላይ በደንብ መሥራት ያስፈልጋል”በማለት የሚናገረው ስለሺ ፌዴሬሽኑ ይሄንን በማመንና ትኩረት በመስጠት የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉ ገልጿል።
በድሬዳዋ፣ በሐረር፣ በደሴና በመቐለ ከተማ የህፃናት አትሌቲክስ ስልጠናዎችን በፌዴሬሽኑ ሙያተኞች እየሠጠ መሆኑን ያስታወሰው ፕሬዘዳንቱ፣ ፌዴሬሽኑ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ያስረዳል። ህፃናቱ ከትልልቅ አትሌቶች ጋር እየተገናኙ ልምድ፣ ሞራል፣ ስልጠና እንዲያገኙ፣ ዕይታ ውስጥ እንዲገቡ ጥረት ማድረግም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ባይ ነው። “ጥሩ ጅማሮ ነው” ካለ በኋላ የነገ ተተኪዎች እሱን በመሠሉ ስመ-ጥርና ታላላቅ አትሌቶች መሸለማቸውን አስመልክቶ፣ “የነገ ተተኪዎችን መሸለም የተለየ የደስታ ስሜት አለው፤ ደስታው ደግሞ ለሁለታችንም ነው ለእነሱም፣ ለእኛም፤ የበለጠ እንዲነሳሱ እንዲጠነክሩም ትልቅ የሞራል ስንቅ ይሆናቸዋል፤ የልጅነት ጉጉታቸውና ስሜታቸው ገንፍሎ ወጥቶ የት ሄደን ነው የምንመዘገበው? ብለው ሲጠይቁ ስለተሸለሙ ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ሲያለቅሱ ማየት ልብ ይነካል” በማለት ተናግሯል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም