መሠረተ ሃሳብ
በታላቁ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰ በጣም የምወደው አንድ አባባል አለ። «ሁሉም ነገር በአግባቡ ይሁን» ይላል። ይህ በሁሉም ቦታ ሊጠቅም የሚችል፤ ምስጢሩን አውቀው ከተገለገሉበት ወርቃማ የሕይወት መርህ ሆኖ ሊመራ የሚችል ድንቅ ቃል ነው። ምክንያቱም ማንኛውም ነገር የቱንም ያህል አስፈላጊና ጠቃሚ ቢሆን እንኳን በአግባቡ ካልሆነ የሚጠበቀውን ጥቅም ላይሰጥ ይችላል።
እንዲያውም ጥቅሙ ወደ ጉዳት ሊቀየርና የጥፋት ምንጭ ሊሆን ይችላል። ማር እጅግ ጣፋጭ እጅግም ጠቃሚ እንደሆነ ይታወቃል። ጣፈጠን ብለን ከመጠን ያለፈ ብንመገበው ግን ለጉዳት ልንዳረግ እንችላለን። በአንጻሩ በልኩና በአግባቡ ሲሆን በገዳይነቱ የምናውቀው መርዝ መድኃኒት ሆኖ ፈውስን ሲለግስ እናስተውላለን።
ከዚህ የምንማረው ታላቅ ቁም ነገር አንድ ነገር ጠቃሚ ወይም ጎጂ ሊሆን የሚችለው በይዘቱ አስፈላጊነት ሳይሆን በአግባቡ በመጠቀምና ባለመጠቀም ነው። ለዚህም ነው «ሁሉም ነገር በአግባቡ ይሁን» የሚለው ቃል ትክክልና ስህተት፣ ጠቃሚና ጎጂ፣ ክፉና በጎ የሚባሉ ኅልዮቶች የሚለዩበትን ምስጢር ጠቅልሎ የያዘ የሕይወት መመሪያ ነው ያልኩት።
አቅምን ያላገናዘበ ትምህርት
አሁን ላጋራችሁ ስለፈለኩት ወደ ዛሬ ትዝብቴ ልመልሳችሁ። ትምህርት፡- አዎ ከፈጣሪ በታች ፈጣሪ ስለሆነው የትምህርት ጉዳይ። «ትምህርት የዕድገት መሠረት ነው»፤ «ትምህርት የለውጥ መሣሪያ ነው» ወዘተ… ስለ ትምህርት ጥቅም ብዙ ብዙ ተብሏል። ለእኔ ግን ትምህርት ከዚህም በላይ ነው፤ ምናልባት ጆን ድዌይ የተባለው አሜሪካዊ የትምህርት ፈላስፋ የተናገረው በመጠኑም ቢሆን ከእኔ ሃሳብ ጋር ይስማማል።
«ትምህርት ለሕይወት የሚደረግ ዝግጅት አይደለም፤ ራሱ ሕይወት ነው» ነበር ያለው የትምህርት ፍልስፍና ሊቁ። በእርግጥም ትምህርት ሕይወት ነው፤ እየወደቁ እየተነሱ የሚያልፉበት፣ ክፉውን ከበጎው የሚለዩበት፣ ሁሉን የሚማሩበት፣ የተሻለውን የሚመርጡበት፤ የበለጠውን የሚይዙበት ኑረት ነው።
ጥያቄው ግን በትክክል ትምህርት ሕይወት የሚሆነው መቼ ነው? የሚለው ይሆናል። በአግባቡ ሲሆን! እርግጥ ነው ትምህርት ሕይወት ነው፤ የለውጥ መሣሪያ ነው፤ የችግር መፍቻ ቁልፍ ነው፣ የብልፅግና ምንጭ ነው፤ ግን በአግባቡ ከሆነ ብቻ። በእኛ አገር በአዲስ አበባ በተለይም በአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የታዘብኩት የትምህርት አሰጣጥ ግን «ሁሉም ነገር በአግባቡ ይሁን» የሚለውን ይህንን ወርቃማ የሕይወት ሕግ የሚቃረን ነው። ምክንያቱ ደግሞ የተማሪዎችን የዕድገት ደረጃ መሠረት ያላደረገ፣ ከልጆቹ አዕምሯዊና ሥነ ልቦናዊ ዕድገት ጋር ያልተመጣጠነ፣ በአጠቃላይ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ትምህርት ሲሰጥ በዓይኔ በማየቴና በመታዘቤ ነው። ጥቂት ማሳያዎችን ላቅርብ።
ማንበብ የማይችሉ አርታኢያን
አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምር የቅርብ ጓደኛ አለኝ። ብዙውን ጊዜ የሳምንቷን የመጨረሻ የእረፍት ቀናችንን እሁድን በአንደኛችን ቤት ሆነን አብረን እናሳልፋልን። አንድ ቀን ታዲያ እንደተለመደው ወደ ጓደኛዬ ቤት ጎራ ብዬ አንዳንድ ነገሮችን እያነሳን እየተጨዋወትን ነው።
የበፊቱን ለቅቆ አዲስ ትምህርት ቤት ውስጥ መቀጠሩን ነግሮኝ ስለነበር መቼም ባለፉት ዓመታት የአገራችን የኑሮ ውድነትም እንደ ኢኮኖሚያችን የማያቋርጥ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ በመሆኑ ሥራ ከማግኘት እኩል የሚያስጨንቀን የክፍያው ነገር ነውና «አዲሱ ትምህርት ቤት ታዲያ እንዴት ይዞሃል፤ አሪፍ ይከፍልሃል?» ስል ጠየኩት። እርሱም «ክፍያው እንኳን ከዚያኛው ትንሽ ይሻላል፤ ግን እዚህም ሌላ የሚያስጠላ ነገር አለ፣ ደስተኛ አይደለሁም» በማለት የኀዘን ቅላጼ ባለው ድምፅ መለሰልኝ።
እኔም ሁኔታው የፈጠረብኝን የኀዘንና የመከፋት ስሜት እንደምንም ያዝ አድርጌ ፊቱን ትኩር ብዬ እየተመለከትኩ «ደመወዙ የተሻለ ከሆነ ደስተኛ ያልሆንከው ለምንድነው፤ ሌላ የሚያስጠላ ነገር ምን ገጠመህ?» ስለው ከኋላው ወዳለው ጠረጴዛ ዞረና አራት የሚሆኑ የ«ኤ4» መጠን ያላቸው ትልልቅ ሞጁል መሳይ መጽሐፍቶችን አንስቶ ሰጠኝ።
መጽሐፍቱን ተቀብዬ በጉጉት ማገላበጥ ጀመርኩ። ሁሉም የአራተኛ ክፍል ማስተማሪያዎች ናቸው። በያንዳንዱ ሞጁል ላይ የተጻፈው የትምህርት ዓይነት ስም እንደ ወረደ አንደኛው «ኢንግሊሽ»፣ ሁለተኛው «ስፖክን»፣ ሦስተኛው «ሪዲንግ ስኪል» አራተኛው ደግሞ «ጀኔራል ሳይንስ» ይላል። እኔ ራሴ የተመረቅኩበት የትምህርት ዘርፍ እንግሊዝኛ ቋንቋ በመሆኑ ትኩረቴን እንግሊዝኛ ሞጁሎቹ ላይ አድርጌ ምልከታዬን ቀጠልኩ።
«ኢንግሊሽ» የሚለውን ሞጁል አንስቼ የመጀመሪያውን ገፅ ገልበጥ አድርጌ ማውጫውን ስመለከት በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ «ፕሩፍ ሪዲንግ» የሚል ርዕስ ሳይ ክው ብዬ ደነገጥኩ። ራሴን ማመን ስላቃተኝ በፍጥነት ሞጁሉን ዘጋሁትና እንደገና ጀርባውን አፍጥጬ ሳይ መጽሐፉ እውነትም ለአራተኛ ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጀ ነው። አሁን አዲስ ሥራ በጀመረበት ትምህርት ቤት ውስጥ ጓደኛዬን ያላስደሰተው ነገር ምን እንደሆነ ገባኝ። ቀና ብዬ ጓደኛዬን በግርምት ተመለከትኩትና «እውነት ይሄን ለአራተኛ ክፍል ተማሪዎች ነው የምታስተምሯቸው?» በማለት ስጠይቀው «እኔንስ ያሳዘነኝና እዚህ መምጣቴን ያስጠላኝ ነገር ምን ሆነና፤ አየኸው አይደል የሚሰራውን ጉድ» አለኝ።
«እኔ ራሴ ፕሩፍ ሪዲንግ የሚባል ነገር አስራ ሁለተኛ ክፍል ላይም አልተማርኩም፤ እዚህ ግን ማንበብና መጻፍ እንኳን በደንብ ያልለመዱ የአራተኛ ክፍል ጨቅላ ሕፃናት ያለ አቅማችሁ ተማሩ ተብለው ሲጨነቁ ይውላሉ። ባክህ ገና የተወሰነ ብር ይጨመርልኛል ብዬ ህሊናዬን አልጎዳም፤ እዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ መስራት አልፈልግም፣ ልለቀው ነው»በማለት የተከፋበትን ምክንያት አጫወተኝ።
መምህሩ ትምህርት ቤቱን ለመልቀቅ መወሰኑ የሚያስመሰግነው ተግባር ነው። በመሆኑም እዚያ አስተማሪ መሆን የሚጎዳው ትውልድን ብቻ ሳይሆን ትውልድን የመቅረጽ ኃላፊነት የተጣለበትን መምህሩንም ጭምር የህሊና ባለዕዳ የሚያደርግ ነው። ምክንያቱም የአራተኛ ክፍል ጨቅላ ሕፃናትን «ፕሩፍ ሪዲንግ» የሚያስተምር ትምህርት ቤት እንደ እውነታው ከሆነ «የውድቀት ቤት» እንጂ «የዕውቀት ቤት» ሊሆን አይችልም። የትምህርትና የዕድገት ሥነ ልቦና ሳይንስ ባስቀመጠው መለኪያ መሠረት አራተኛ ክፍል ማለት ልጆች የፊደላትን ቅርጽ በደንብ የሚለዩበትና የመጀመሪያውን የንባብ ደረጃ የቃል በቃል ንባብ የሚለማመዱበት የክፍል ደረጃ ነው።
«ፕሩፍ ሪዲንግ» ማለት ደግሞ በአንጻሩ የንባብ የመጨረሻው ደረጃ ሲሆን ከፍተኛ የአዕምሮ ብስለትንና የማሰብ ችሎታን የሚጠይቅ ለአዋቂዎችም ሳይቀር የሚከብድ ክህሎት ነው። እኔው ራሴ ተምሬ የተመረቅኩት በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ሲሆን፤ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ «ፕሩፍ ሪዲንግ» የሚባል ነገር እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት መጽሐፍ ተዘጋጅቶለት ልማረው ይቅርና ስሙን እንኳን ሰምቼው አላውቅም።
ፕሩፍ ሪዲንግ የተማርኩት ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ ያውም ዘግይቶ በመጨረሻው ዓመት ላይ ነው። ይህም ተማሪዎች ፕሩፍ ሪዲንግ መማር ያለባቸው በየትኛው የዕድሜ ክልልና የአዕምሮ ዕድገት ደረጃ መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ ነው።
በእርግጥም ትምህርቱ ቃላትን ገጣጥሞ ከመጥራት በስቀር የሚያነቡትን ጽሑፍ ትርጉም እንኳን መረዳት ለማይችሉት የአራተኛ ክፍል ያልበሰሉ ሕፃናት ለአዋቂዎችም ሳይቀር የሚከብድ መሆኑን ኮርሱን በወሰድኩበት ወቅት አረጋግጫለሁ። በነገራችን ላይ ሕፃናት በዚህ ዕድሜያቸው የድምጽ ንባብ (Loud reading) ካልሆነ በቀር የጽሑፍን መልዕክት አንብቦ ለመረዳት የሚደረግ የጥሞና ንባብ (Comprehension skill) ለማድረግ የአዕምሮ የዕድገት ደረጃቸው የማይፈቅድላቸው መሆኑን ለመረዳት ትምህርት ቤት ገብቶ መማር አያስፈልግም፤ በተፈጥሮ የተገኘ የልቦና ዕውቀት ብቻ ይበቃል።
እናትና አባቶቻችን ትምህርት ቤት ሊያስገቡን ሲፈልጉ በጭንቅላታችን አልፈን በእጃችን ተቃራኒ ጆሯችንን መንካት አለመንካታችን እና ዕድሜያችን ለትምህርት መድረስ አለመድረሱን የሚያረጋግጡት እኮ ያለ ዕድሜ የሚሰጥ ትምህርት ለልጆቻቸው ጎጂ መሆኑን ትምህርት ቤት ገብተው ተምረው ስላወቁት አይደለም። ሰው ሆኖ መፈጠር ያጎናጸፋቸውን የማሰብ ችሎታና ተፈጥሯዊ አመክንዮ በመጠቀም ነው።
ፕሩፍሪዲንግ በእጅጉ አስተዋይነትንና ጥንቃቄን የሚፈልግ የንባብ ዓይነት ነው። ለአብነትም “kill him not, leave him” በሚለው ለቅጣት አስፈጻሚ ፖሊስ የተጻፈ የእንግሊዝኛ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ኮማ የምትባለውን ሥርዓተ ነጥብ “not” ከሚለው ቃል በፊት ተሳስቶ ቢያስቀምጣት እንደማንኛውም ስህተት በይቅርታ ወይም በእርማት የሚታለፍ አይደለም፣ በመሳሳታችን ምክንያት ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት አጥፍተናልና! ከፕሩፍ ሪዲንግ ጋር ተደጋግሞ የሚነሳ ሌላም አንድ የአገራችን እውነተኛ ታሪክ አለ።
«የቀድሞው ንጉሠ ነገሥትና እቴጌይቱ በአንድ በዓል ላይ ይገኛሉ። በማግስቱ ጋዜጣ ላይ የንጉሡና የንግሥቲቱ ፎቶ ግራፍ በመጀመሪያ ገጽ ላይ ይወጣል። የስዕሉ የግርጌ ጽሑፍ «ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትና ግርማዊት እቴጌ በተኙበት የበዓሉ ሥነ ሥርዓት ተፈጸመ» የሚል ሆኖ ይገኛል። በ “ተ” እና በ “ኘ” መካከል መግባት የነበረበት “ገ” በቦታው አልነበረም።
ነገሩ እውነት ሆኖ ጋዜጣው በጊዜው በሕዝብ ዘንድ የተሰራጨ ከሆነ፤ ይህን የመሰለውን ግድፈት ሳይመረምር እንዲወጣ ያደረገ የጋዜጣ አራሚና አዘጋጅ ሊደርስበት የሚችለውን ተግሳፅና ቁጣ መገመቱ አዳጋች አይሆንም።» (መኮንን ተካ «የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት ጽሑፎች መሠረታዊ መርሆዎችና እሳቤዎች (1976)»ን ጠቅሶ አማረ ማሞ እንደጻፈው)።
«ፕሩፍሪዲንግ» በአቻ የአማርኛ ትርጓሜው «የአርትዖት ንባብ» ከንባብ ክህሎትነትም በላይ ከፍተኛ ኃላፊነትን የሚጠይቅና ከባድ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሙያዊ የትምህርት መስክ መሆኑን መረዳት ይቻላል። ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የቋንቋ ጥናትን መርጠው ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ለእንደ እኔ ዓይነት ተማሪዎች ኮርሱ የሚሰጠው በመመረቂያችን ዓመት የመጨረሻው ሴሚስተር ላይ መሆኑም ይህንኑ ሃቅ ያጠናክራል።
እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ቀይ ስህተቶችን የማረምና በእነዚህ ስህተቶች ምክንያት የሚፈጠሩ አደጋዎችን የማስቀረት ክህሎትን ነው እንደ ተራ ነገር «ፕሩፍ ሪዲንግ» ተብሎ የአራተኛ ክፍል ሕፃናት የሚማሩት። ታዲያ እግዜር ያሳያችሁ ማንበብ በደንብ የማይችል አንድ የአራተኛ ክፍል ጨቅላ ሕፃን በምን ተዓምር ነው ከማንኛውም ዓይነት ስህተት በፀዳ መንገድ ማንበብን እንዲማር የሚደረገው? በየትኛው አመክንዮስ ነው ማንበብ በደንብ የማይችል አንድ ሕፃን የንባብ ስህተት አራሚ የሚሆነው? ታዲያ ማንበብ የማይችሉ አራሚዎች እያፈራን አይደለም ትላላችሁ? ይህንን ዓይነቱን ነው እንግዲህ የቱንም ያህል ከፍተኛ ጥቅም ያለውም ቢሆን በአግባቡ ካልሆነ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው ማለት!
አንድ ሆኖ አራት ምስል ካሳየህ መስታወትህ ጤናማ አይደለምሌላው በግል ትምህርት ቤቶች ትምህርት አሰጣጥ ያስተዋልኩት ትውልድን የሚያሳስት ጠቃሚ መሳይ ጎጂ፣ አሳቢ መሳይ አሳሳቢ አካሄድ አንድን የትምህርት ዓይነት ከአራት ቆራርጠው ተማሪውን የሚያሰላቹበትና የሚያደናግሩበት ሥርዓት ነው። ከላይ በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩላችሁ በተለይም ከአንድ እስከ አራት ባለው የታችኛው አንደኛ ደረጃ ትምህርት አንዱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት «ኢንግሊሽ»፣ «ስፖክን» «ሪዲንግ ስኪል» እና «ራይቲንግ» ተብሎ ፋይዳው ምን እንደሆነ በማይታወቅ መልኩ ተቆራርጦና በአራት ተባዝቶ ይሰጣል። እያንዳንዱ አላስፈላጊ ክፋይ ካሪኩለም ተቀርጾለት፣ መጽሐፍ ተዘጋጅቶለት አንዱን ትምህርት አራት ጊዜ ያስተምሯቸዋል። በመሠረቱ ስፖክን፣ ሊስኒንግ፣ ሪዲንግና ራይቲንግ የማይነጣጠሉ የአንድ ቋንቋ መሠረታዊ ክህሎቶች ናቸው። እንግሊዝኛም ይሁን አማርኛ ፈረንሳይኛም ይሁን ኦሮምኛ የቋንቋ ትምህርት መሠረታዊ ዓላምም እነዚህ አራት ክህሎቶች በበቂ ሁኔታ እንዲዳብሩና ጥቅም ላይ መዋል በሚገባቸው ልክ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማስቻል ነው።
«ስፔሻላይዜሽን» ነው እንዳይሉን እንኳን የሚያስተምሯቸው ሕፃናትን ነው። በእርግጥ አንድ ተማሪ ከአንድ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ተምሮ ቋንቋውን በደንብ ካወቀው በኋላ በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ይህንኑ ቋንቋ ማጥናት ከፈለገ እያንዳንዱን ክህሎት የበለጠ ለማሳደግ ሪዲንግ፣ ራይቲንግ ወዘተ… ለየብቻ በጥልቀት ተዘጋጅተው በኮርስ ደረጃ ሊማራቸው ይችላል እንጂ ሪዲንግ፣ ስፖክን ምናምን ተብሎ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ስፔሻላይዜሽን የለም። ታዲያ የግል ትምህርት ቤቶቻችን ከየትኛው የትምህርት ፍልስፍና አግኝተውት ነው የማይለያየውን አለያተው አንዱን ቋንቋ አራት አድርገው የሚያስተምሩት።
እናም ሕፃናቱን በዚህ ዓይነት መንገድ ማስተማር ልክ ማንበብ እንደማይችለው አራሚ ዓይነት እንግሊዝኛ ቋንቋ የማይችል የ«ራይቲንግ ስፔሻሊስት» ማለትም ቋንቋውን የማይችል ጸሐፊ ሊፈጥሩልን ካልሆነ በስተቀር ጥቅሙ አልታየኝም። እውነቴን እኮ ነው፤ «ኢንግሊሽ» እና «ራይቲንግ» ተብሎ አንድን ትምህርት በሁለት መጽሐፍ የተማረ ልጅ እኮ «እስኪ በእንግሊዝኛ ጻፍ ስትለው» በራይቲንግ ነው እንጂ በእንግሊዝኛ መጻፍ አልችልም ሊል ይችላል። አንድ መስታወት አራት ምስል የሚያሳይ ከሆነ የተሰነጣጠቀና ችግር ያለበት እንደሆነ ሁሉ የእናንተም የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ በአንድ ትምህርት አራት ዓይነት የማይገናኝ «ዕውቀት» የሚፈጥር ከሆነ ጤናማ አይደለም።
ሌላ ሸክም
ከሰባት እስከ አስራ አንድ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ ሕፃን በሳይንስ ትምህርት አማካኝነት ማወቅ የሚገባው መሠረታዊ ነገር አለ። ለምሳሌ ሕፃናቱ በዚህ ዕድሜያቸው የአምስቱን የስሜት ህዋሳት ስምና ተግባር ማወቅ ይገባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም ስለ ዋና ዋና ውጫዊ የሰውነት ክፍሎችና አገልግሎታቸው ዕድሜያቸውን በሚመጥን መልኩ መሠረታዊ ዕውቀት እንዲኖራቸው ይደረጋል። ሕፃናቱ መሠረታዊ የግልና የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅን እንዲማሩና እንዲለማመዱ ማድረግም በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች የተዘጋጀው የሳይንስ ትምህርት ማካተት የሚገባው ጠቃሚ ይዘት ነው።
ይሁን እንጂ በግል ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚሰጠው የሳይንስ ትምህርት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ በመሆኑ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ሊያገኙት የሚገባውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር ጥቅምና መብት የሚያሳጣ ከመሆኑም በአሻገር ይዘቱም ፍጹም ከሕፃናቱ አቅም በላይ ነው።
በዚህም «ጀኔራል ሳይንስ» በሚባለው የትምህርት ዓይነት የአራተኛ ክፍል ሕፃናት ልጆች ስለ ሥርዓተ ነርቭ ይማራሉ (ይማራሉ ሳይሆን ይጫናሉ ቢባል ይቀላል)። ለመግቢያ ያህል ስለ ሥርዓተ ነርቭ ፍንጭ የሚሆን ጥቂት ትምህርት የተማርኩት አስረኛ ክፍል ላይ መሆኑን በሚገባ አስታውሳለሁ፣ ከሥነ ሕይወት ትምህርት ይዘቶች መካከል ብዙዎቻችን የሚከብደንም ይኼው የሥርዓተ ነርቭ ክፍል እንደነበርም አልረሳውም።
የሥርዓተ ነርቭ ሳይንስ በስፔሻሊቲ ደረጃ ለሚያጠኑት የህክምና ባለሙያዎች እንኳን ጽንሰ ሃሳቡ ውስብስብና አስቸጋሪ በመሆኑ ለመረዳት ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ መሆኑ ይነገርለታል። ታዲያ ይሄን ሳይንስ ለእነዚህ ሕፃናት ማስተማር ዕውን ብስለት ወይስ ድፍረት? ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት የሚወጠር ነገር እንኳን ይበጠሳል። የሕፃናቱ አዕምሮ መሸከም የማይችለውን ከአቅም በላይ የሆነ ነገር መጫንስ ምን ለመፍጠር ታስቦ ነው፤ ዕውቀት ወይስ ጭንቀት?
ደዌን ለመፈወስ፣ ጤናን ለመመለስ ሕይወትን ለማዳን የሚወሰድ መድኃኒት እንኳን በህመምተኛው ዕድሜና አቅም ተለክቶ የሚሰጥ ነው። ከተገቢው መጠን ካለፈም መድኃኒቱ በማዳን ፈንታ መርዝ ሆኖ ይገድላል። ትምህርትም እንዲሁ ነው፤ ዕድሜን፣ የአዕምሮ የዕድገት ደረጃንና የመማር አቅምን ባገናዘበ መንገድ የማይሰጥ ከሆነ የዕውቀት መንገድ መሆኑ ቀርቶ የውድቀት መንስኤ ይሆናል።
መቋጫ ሃሳብ
የግል ትምህርት ቤቶቻችን ሆይ (የግሎቻችንዬ አቆላምጬ ስጠራችሁ ነው) ከሌላው የበለጠ ያወቃችሁና የተለየ ነገር የፈጠራችሁ መስሏችሁ እየተጠቀማችሁበት ያለው የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ዓላማውን ስቷል። በዚህ መንገድ የሚሰጠው ትምህርት ችግር ፈጣሪ እንጂ በፍጹም ችግር ፈች ሊሆን አይችልም። ዕድሜን፣ አዕምሯዊና ሥነ ልቦናዊ የዕድገት ደረጃንና አቅምን ያላገናዘበ ፍጹም ከአቅም በላይ የሆነ ትምህርት ሊፈጥር የሚችለው ከአቅም በታች የሆነ ትውልድን ነው።
ጠቃሚ መሳይ ጎጂ፣ አስተማሪ መሳይ የተሳሳተ መንገድ እየተከተላችሁ፣ እናንተ ተደናግራችሁ ግራ የገባው ትውልድ ፈጥራችሁ የታሪክ ባለዕዳ ከመሆናችሁ በፊት ቆም በሉና አስቡበት። እንዲህ ዓይነት ትውልድ ደግሞ አገር የምትረከበው እንጂ እርሱ አገርን ሊረከብ የማይችል በመሆኑ ምግባራችሁ ትውልድንና አገርን የሚጠቅም ይሆን ዘንድ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓታችሁ በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ዓለም አቀፍ መስፈርቱንና ሳይንሱን የተከተለ፣ አገባቡን የጠበቀ ይሁን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 26/2011
ይበል ካሳ