አገልግሎቱ የቁጥጥር ሥራዎች ላይ በትኩረት እንዲሠራ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

አዲስ አበባ፡የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ገቢ ከማግኘት ባሻገር ወጣቱ ትውልድ እንዳይበላሽ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራዎችን በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። በ11 ወራት ከስፖርት ውድድር የሎተሪ ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱም ተመላክቷል።

ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት መሥሪያ ቤት ከ2013 ዓ.ም እስከ 2016 ግማሽ ዓመት የፈቃድ አሰጣጥ እና የቁጥጥር ክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ከትናንት በስቲያ ውይይት አድርጓል።

በወቅቱ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ አራሬ ሞሲሳ እንዳስታወቁት፤ ስፖርታዊ የሎተሪ ውድድሮች ለሀገር ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ቢሆንም፤ ከገንዘብ በላይ ሀገር ተረካቢው ትውልድ እንዳይበላሽ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

አገልግሎቱ ፀረ ሙስና፤ ዋና አዲተር እና በራሱ አቅም የሠራቸውን ጥናቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሠራ አሁን እያገኘ ካለው ገቢ የበለጠ ማግኘት እንደሚችል ያመለከቱት ምክትል ሰብሳቢዋ፤ ሥራውን ሲሠራ የወጣቱን ትውልድ ጤናማ የሕይወት ጉዞ ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ከትውልድ የሚበልጥ ምንም ነገር ስለሌለ፤ አንድ ግለሰብ ወደ አገልግሎቱ መጥቶ ፈቃድ ሲያወጣ፤ ፈቃድ የሚያወጣው ግለሰብ የሚጠየቀውን ገንዘብ ከየት ነው ያመጣው ወይስ ሌላ ሰው ከጀርባ ሆኖ እያሠራው ነው የሚለውን ማጣራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

በአገልግሎቱ መዋቅር ፈቃድ የሚሰጠው እና ቁጥጥር የሚያደርገው አካል በአንድ ዳይሬክቶሬት የሚመራ በመሆኑ፤ የውድድር ቤቶች አስፈላጊውን   መስፈርት ሳያሟሉ ሲቀር የመደበቅ ሁኔታ ሊኖር ይችላል፤ አገልግሎቱ በክዋኔ ኦዲት የቁጥጥር ሥራው ደካማ ሆኖ የታየው ከዚህ አንጻር ሊሆን ስለሚችል፤ ሁለቱን ዘርፎች መለያየት እንደሚስፈልግ ጠቁመዋል።

ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት ለገቢዎች ሚኒስቴር የተሰጠ ቢሆንም፤ ደንቦች ወጥተው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን እስከሚወስድ ድረስ በተቀመጠው አዋጅ መሠረት የሎተሪ አገልግሎቱ ፈቃድ እየሰጠ ይገኛል። ይህ መመሪያዎችን ለማሻሻል፤ አሠራሮችን ለማዘመን ማነቆ እየሆነ ስለሆነ፤ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ፤ ፕላን ሚኒስቴር እና ፍትሕ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን እስከ መስከረም 28 ቀን 2018 ዓ.ም ችግሩን ፈትተው እንዲቀርቡ አሳስበዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው እንዳስታወቁት፤ አገልግሎቱ ኦዲት የተደረገው በሦስት የትኩረት አቅጣጫዎች እና በ30 መመዘኛዎች ነው።

የትኩረት አቅጣጫዎቹ አንደኛ ከፈቃድ አስጣጥ እና ከገቢ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ፤ ሁለተኛ ፈቃድ የተሰጣቸው የአገልግሎት ዕድል ሎተሪ ቤቶች የወጡ ደንቦችን ስለመተግበራቸው መከታተል እና ሦስተኛ የዕድል ሎተሪዎች የሚያመጡትን ዘርፈ ብዙ ጫና ለመቀነስ የተሠሩ ሥራዎች በተመለከተ ነው ብለዋል።

ከፈቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ አገልግሎቱ በ30 ደቂቃ ፈቃድ እንሰጣለን ቢልም፤ በተለይ ከክልሎች ጋር ተይይዞ እስከ ስድስት ዓመት የሚወስድበት ሁኔታ አለ። ይህን ችግር ለመፍታት በየአካባቢው ቅርንጫፍ መክፈት ሳያስፈልግ በቴክኖሎጂ መሥራት የሚቻልበትን መንገድ መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤዛ ግርማ በበኩላቸው፤ የዘንድሮ በጀት ዓመት ሲጀመር ፈቃድ ያላደሱትን፤ በትክክል ገንዘብ የማይከፍሉትን በማጥራት ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል። በዚህም እንደ ሀገር የነበሩ የስፖርት ውድድር ሎቶሪ ቤቶች ከ174 ወደ 94 መውረዳቸውን አስታውቀዋል።

ይህም የተደረገው ለመንግሥት ትክክለኛ ገቢ የሚከፍሉ የስፖርት ቤቶችን ይዞ ለመቀጠል በማሰብ መሆኑን በመግለጽ፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት 11 ወራት ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ገቢ ማግባቱንም አስታውቀዋል።

በዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You