ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው ለረጅም ዓመታት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምሥራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ገነት ኤልያስ የቅኔ መምህር በመሆን በርካታ ሊቃውንትን ስላፈሩትና በቅርቡ ከዚህ ዓለም ስለተለዩት መምህር በላይ ፍላቴና ቅኔዎቻቸው ነው። ሥራዎቻቸውን ያሰባሰብኩት ለሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ እንዲሆነኝ የቅኔ መረጃ በመስክ ሥራ ሳሰባስብ በነበረበት 2006 ዓ .ም ላይ ነው። በተጠቀሰው ዓመተ ምሕረት ወደ ደብረ ገነት ቅዱስ ኤልያስ ቅኔ ቤት ሳመራ የመምህር በላይ ፍላቴ እድሜያቸው 81 ነበር።
የቅኔ ሊቁ መምህር በላይ ቅኔ የተማሩት ከመምህር ያሬድ ዘመንግሥቶ፤ ከአለቃ ተጠምቆ ዘደብረ ማርቆስ፤ ከመምህር ጌቴ ገሞራ ዘአዴት መድኃኔ ዓለም፤ ከመምህር ገብረ ሥላሴ ክንፉ ዘደብረ ኤልያስ ነው። የቅኔ መንገዳቸው ሰምና ወርቅ ሲሆን እርሳቸው ከአሰባሰቧቸው 20 ሥራዎቻቸው ውስጥ ሦስት ጉባኤ ቃናዎች ለቅምሻ ያህል እንደሚከተለው ከፍቺና ከትንታኔ ጋር ቀርበዋል።
1. ግእዝ ጉባኤ ቃና
መርድአ ባቢሎን ነድ እንተ ይሄሉ በራማ፤ ኀበ ቤተ ቅኔ አተወ እምድኅረ ፈጸመ ዜማ።
ሰም (ፍች)፡- ራማ በተባለው ቦታ በድካም የሚኖረው የባቢሎን እሳት ተማሪ የዜማ ትምህርቱን ጨርሶ ወደ ቅኔ ቤት ገባ።
ወርቅ (ምሥጢር)፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ቀኖና መሠረት አንድ ተማሪ የዜማ ትምህርቱን ተምሮ ሲጨርስ ወደ ቅኔ ቤት ይገባል። በዚህ ዓይነት አንድ ወቅት የደብረ ኤልያስን ዜማ ቤት እሳት ፈጀው። ሰነባብቶ ደግሞ የቅኔ ቤቱን እሳት በላው። ይህ ታሪክ የሰምና ወርቅ ቅኔ መነሻ ሆኗል።
መምህር በላይ ይህንን ምክንያት አድርገው በሁለቱ ጉባኤዎች ላይ የዘረፉት ነው። በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተጻፈው እሳት በባቢሎን ሰውን አቃጥሏል። ናቡከደነጾር እነ አናንያ አዛርያ፤ ሚሳኤልን ለጣኦት ስገዱ ብሎ አንሰግድም ስላሉት ከእሳት ላይ እንደጣላቸው ያሳያል። ይህ የሰም ምሳሌ ነው። ተማሪና እሳት ምሳሌዎች ናቸው። ተማሪ ሰም፤ ነድ ወርቅ ናቸው። የቅኔ ባለቤቶች ነድና መርድእ ናቸው።
2. ጉባኤ ቃና
መና ተጋድሎ ይበልእ ለባሕቲቱ ወልደ ኢየሉጣ ቅድስት፤ ዓይነ ዓይነ እንዘ ይሬኢ ቀኖት።
ሰም (ፍች)፡-፡- የኢየሉጣ ልጅ ቂርቆስ የብቻውን መጋደል እንጀራን ይበላል። ጓደኛው ቀኖት (ችንካር) ዓይን ዓይን እያየ እርሱ እንጀራ ችንካርን ብቻውን ይበላል ማለት ነው። አንድ ሰው ጓደኛው ዓይን ዓይን እያየው እንጀራ ለብቻው ይበላል ይባላል። በሀገራችን ባህልና እምነት መሠረት አንድ ሰው አጠገቡ ሌላ ሰው ቁጭ ብሎ ለብቻው የሚበላ ከሆነ እምነትና ሥነ ምግባር የጎደለው ከሰው ልጅ ባሕርይም የወጣና የእንስሳት ጠባይ እንዳለው ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ለዚህም ነው በሀገራችን «ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል» የሚል ተረት የሚነገረው። የተገኘውንና ቤት ያፈራውን አንድ ላይ ተካፍሎ መብላት ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የተቀደሰና የተባረከ ባህላችን ነው።
ነገርን ነገር ያነሣዋል እንዲሉ በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት በሩሲያ ፌደሬሽን፤ በቫሮኔዥ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የተወሰንን ኢትዮጵያውያን በትምህርት ላይ እያለን አንድ ጓደኛችን የፈረንጅ ባህል (በተለይም የጀርመኖችን) እከተላለሁ ብሎ ምግብ እየሠራ ለብቻው መመገብ ጀመረ። እንደሚታወቀው በጀርመንም ሆነ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች አንድ አባት ምግብ ሠርቶ እየበላ ባለቤቱ፤ ልጁ ወይም ጓደኛው ቢመጡበት «እንብላ» ብሎ አይጋብዛቸውም። በዚህም በእኛና በፈረንጅ ባህል መኻከል ከፍተኛ የሆነ የባህል ተቃርኖ ያለመሆኑን ለመረዳት እንችላለን፡ ምክንያቱም በፈረንጅ አገር ሁሉም ሰው ተቀርጾ የሚያድገው ቅድሚያ ለራስ በሚለው ሥነ ልቡናና ፍልስፍና ስለሆነ ነው። በሩሲያ ባህል ግን ልክ እንደ አበሻ አብሮ መብላትና መጠጣት የተለመደ ነው። ለብቻው የሚበላ ሰው ይወገዛል።
የፈረንጅ ባህል ተከታይ ነኝ ወደሚለው ኢትዮጵያዊው ጓደኛችን መኖሪያ ክፍል ሩሲያዊቱ የሴት ጓደኛውም ሆነች እኛ ወገኖቹ በአጋጣሚ ስንሄድ ምግብ በመሥራት ወይንም በመብላት ላይ ከሆነ «ይቅርታ ያዘጋጀሁት ለእኔ ብቻ ነው» ብሎ ምግቡን ሰው እያየው ግጥም አድርጎ ይበላና ሻይ ቡናውንም ለብቻው ይጠጣ ነበር። እኔም አንድ ቀን ለሥራ ጉዳይ ወደ መኖሪያ ክፍሉ ጎራ እንዳልኩ እንቁላል በሥጋ ጠብሶ ሊበላ ሲል ደርሼበት ነበር።
እርሱም «ይቅርታ ወንድሜ ! ሻዩም፤ ምግቡም የተዘጋጀው ለእኔ ብቻ ስለሆነ በልቼና ጠጥቼ እስክጨርስ ድረስ ጠብቀኝ » ብሎና አጠገቡ ቁጭ ብየ ለብቻው ግጥም አድርጎ በላ። ዓይን ዓይን እያየሁት ከበላ በኋላ አነጋገረኝ። እናም በዚህ ጠባዩ በቫሮኔዥ የኢትዮጵያ ተማሪዎች አያ ብቻ በሌንና ስም አይጠሬን «አባ ዥቦ » እያሉ ይጠሩት ጀመር። መምህር በላይ ፍላቴ የተቀኙት ቅኔም ያስታወሰኝ ይህንኑ የባህላችንን ጉዳይ ነው።
ወርቅ (ምሥጢር)፡- የኢየሉጣ ልጅ ቂርቆስ ጓደኛው ቀኖት (ችንካር) ዓይን ዓይን እያየው የብቻውን መጋደል እንጀራን ይበላል ማለት አይሁድ የቂርቆስን ዓይኑንና ጀሮውን እንደቸነከሩት (እንደወጉት) ያመለ ክታል።
3. ግእዝ ጉባኤ ቃና
እምኵሉ ይትሌዓል ጉባኤ ቃና ድንግለ ሙሴ ክብርኪ።
ላዕለ ዘጌዴዎን ፀምር እስመ ይጼዋዕ ስመኪ። ይህ ቅኔ መምህር በላይ ለእኔ በቅኔ ቤት ስሜ አባ ጌዴዎን ያበረከቱት ነው።
ሰም (ፍች)፡- የኢያሱ ድንግል ጉባኤ ቃና ከሁሉ ሰው ይልቅ ክብርሽ በጣም ከፍ ያለ ነው። በጌዴዎን ግምጃ ላይ ስምሽ ይጠራልና።
ወርቅ (ምሥጢር)፡- የአንዳንድ ሰው ወይንም የቅዱሳን ስም በሐውልት፤ በመጽሐፍ፤ በግድግዳ ሥዕል፤ በዋሻ ውስጥ ጽሑፍ፤ በእንጨት፤ በሸክላ ወይንም በጨርቅ ላይ ሊጻፍና ሊቀረፅ ይችላል። ወይም የድንግል ማርያም ስም በበትር፤ በደመና፤ በምርሻ፤ በዕፀዋት፤ በእሳት፤ በግምጃ… ተመስሎ ሊጠራ ይች ላል። በዚህ ረገድ እመቤታችን ድንግል ማርያም የጌዴዎን ግምጃ ተብላ ትጠራለች። ይህ ታሪክ በሰም ረገድ የቀረበ ሲሆን ወርቁ ወይንም ምሥጢሩ ጉባኤ ቃና በአባ ጌዴዎን እየተጠናች ስለሆነ ክብር አገኘች ማለት ነው።
አንድ ነገር ተረስቶና ተዘንግቶ ኖሮ ትኩረት ሲያገኝ ዛሬማ ቀን ወጣለት፤ ትኩረት ተሰጠው ተብሎ አድናቆት ይቸረዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)