ለዘመናት የንግድ ማዕከል ሆና ቆይታለች። ከመሃል አገር፣ ከአፍሪካ ቀንድ እና ከአረብ አገራት ጋር በንግድ መንገዶች ስትገናኝ ከቀሪው ዓለም ጋር ደግሞ በቀይ ባህር ወደቦች አማካኝነት እንደምትገናኝ ይነገርለታል – ሐረር ። ህዝቡ እርስ በርሱ ከሚበላላው የዱር እንስሳ (ጅብ) ጋር ሳይቀር ተግባብቶ የሚኖርባት ከተማ ናት፡፡ እኛም በዚሁ የፍቅር ከተማ ተገኝተን በፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ስር በሚገኘው ፕሮጀክት እየተደረገ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ ተጠቃሚዎችን አነጋግረናል።
በሀረር ከተማ በአቦከር ወረዳው ነዋሪ ከሆኑት እና በኤጀንሲው ድጋፍ ከሚደረግላቸው ግለሰቦች መካከል ወይዘሮ አለሚቱ አመነ አንዷ ናቸው፡፡ ወይዘሮዋ ዕድሜያቸው ከ70 ከዓመት በላይ ሲሆን፤ በሴፍቲኔቱም የቀጥታ ተጠቃሚ ናቸው። ከወሎ እንደመጡ የሚናገሩት ወይዘሮ አለሚቱ፤ በዕድሜ እና በጤና ችግር አልጋ ላይ እስከዋሉበት ጊዜ ድረስ በግል የንግድ ሥራ ይተዳደሩ ነበር፡፡ ነገር ግን የእድሜው ጫና ተጨምሮ ካለባቸው የዓይን ህመም ጋር እንደ ቀድሞ የንግድ ሥራቸውን ማጧጧፍ አልቻሉም፡፡
ወይዘሮ አለሚቱ አንድ ሴት ልጅ አለቻቸው። እሷም በአንድ መስሪያ ቤት የጽዳት ሰራተኛ ነች። የምታገኘው ገቢ ቤተሰብን መግቦ እናቷን ለማሳካምና ለመጦር የሚያስችል አይደለም፡፡ በመሆኑም ሳይወዱ በግዳቸው እድላቸውን እያማረሩ ችግርን መግፋት የግድ ሆኖባቸዋል። ያም ሆኑ ዛሬ ተስፋቸውን የሚያለመልም የምስራች አግኝተዋል። በፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ችግረኞችን በሴፍቲኔት የመደገፍ ፕሮግራሙን ነድፎ ወደ ሥራ ሲገባ እሳቸውም የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል ።በሴፍቲ ኔት ፕሮግራም በቀጥታ የሚታቀፉ ችግረኞች በህብረተሰቡ ምርጫ ሲመለመሉ ወይዘሮ አለሚቱም ዕድሉን ካገኙት ሰዎች መካከል አንዷ ሆነዋል፡፡
ወይዘሮ አለሚቱ በሴፍትኔት በመታቀፋቸው ለቀለብ የሚሆን ገቢ እና ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎችም ይደረግላቸዋል። ነገር ግን ከኤጀንሲው የሚያገኙት ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ ከሌሎች በሚያገኙት ድጋፍ ጭምር በደስታ እየኖሮ እንደሆነ ይናገራሉ። ተጥዬ እንዳልቀር አድርጎኛል፤ ተስፋ ሰጥቶኛልም ይላሉ ስለድጋፉ ሲናገሩ።
ልክ እንደ ወይዘሮ አለሚቱ አመነ በዚሁ ፕሮግራም ታቅፈው በኑሮአቸው ለውጥ ካመጡ ሰዎች መካከል ወይዘሮ ዘርፌ አየነው ሌላኛዋ ናቸው፡፡ ቀድሞ የቤት እመቤት እና የሁለት ልጆች እናት እንደሆኑ የሚናገሩት ወይዘሮ ዘርፌ፤ ባለቤታቸው የቀን ሥራ በመስራት የሚያመጡትን በመጠበቅ ቤተሰባቸው እንደሚተዳደር ገልጸዋል፡፡ ይህ ፕሮግራም ከመጣ በኋላ ግን የቤተሰባቸው ህይወት እንደተለወጠ እና ልጆቻቸውንም ትምህርት ቤት መላክ እንደቻሉ ይናገራሉ።
በአቦከር ወረዳ የሴፍቲኔት ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ሀይማኖት የሺጥላ በበኩላቸው፤ ወረዳው ስር የሰደደ ድህነት ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚገኙበት ሲሆን፤ ጥቂት የማይባሉ ነዋሪዎችም ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡ እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ካሉበት የድህነት ህይወት ለማውጣት መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው መረባረብ አለበት።
አሁን በትንሹም ቢሆን ድጋፉ እየተደረገ እንደሆነ የሚናገሩት አስተባባሪዋ፤ ቀጣይ ብዙ መሰራት ያለባቸውና ከችግሩ መውጣት የሚገባቸው ነዋሪዎች ስላሉ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ያሉ አካላት ሊደርሱላቸው እንደሚገባ አንስተዋል። ኤጀንሲው በያዘው ፕሮግራም አራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎችን በምግብ ዋስትና ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2011
አብርሃም ተወልደ