ትውውቅ
አማኑኤልንም ሆነ እሴተ ማርያምን ሳነጋግር ከ14 እና ከ15 ዓመት ታዳጊ ሕፃናት ጋር እያወራሁ ያለሁ ሳይሆን ከብዙ ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ዘንድ ምክር ልቀበል የሄድኩ ያህል ነው የተሰማኝ። ምክንያቱም ባንድም ይሁን በሌላ ከእድሜያቸው ቀድመው የተጓዙ ናቸው። ብቻ በትካዜ እና በመሳቀቅ ውስጥ ሆነው ችግራቸውን ሲናገሩ ልብ ይነካል። ለካ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› ወይ ያስብላል።
እሴተ ማርያም ፀሀይ ትባላለች። የ15 ዓመት ታዳጊ ልጅ ናት። ተወልዳ ያደገችውና አሁንም በመኖር ላይ የምትገኘው አስኮ አዲስ ሰፈር ልዩ ስሙ ሙገር በሚባለው ሰፈር ውስጥ ሲሆን የምትኖረውም ከታናሽ ወንድሟ አማኑኤል ጋር ነው። እናትና አባታቸውን በሞት ተነጥቀዋል። ወላጅ እናታቸው ከሞተች ሦስት ዓመት ያለፈ ሲሆን አባታቸውን ካጡ ደግሞ ስድስት ወር ሆኗቸዋል።
እናታቸው ከመሞቷ በፊት ቢግ ቡዝ (Big buzz) በተባለ ድርጅት ውስጥ በፋይናንስ ማኔጅመንት ትሰራ ነበር። አባታቸው ደግሞ በሚሊኒየም አፓርትመንት በተባለ ድርጅት ውስጥ በዋና ስራ አስኪያጅነት ያገለግል ነበር።
ምኞት
እሴተ ማርያም የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ወንድሟ አማኑኤል ደግሞ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ራሷን በህክምና ሙያ ወይም ጥቁር ካባን የደረበች ጠበቃ ሆና ማየትን ትሻለች። “ለምን ሁለቱን “ሙያዎች መረጥሽ?” የእኔ ስለዚች ትንሽ ብላቴና ለማወቅ ያኮበኮበው ልቤ ገፋፍቶኝ የሰነዘርኩላት ጥያቄ ነበር።
“የአባቴን አሟሟት ሳስበው አሁንም ድረስ ያመኛል። እንቅልፌን መተኛት አልችልም። ክፍል ውስጥ ሆኜ እንኳን የማስበው እሱን ነው። በጣም በተጨነቅኩኝ ቁጥር ራሴን ያመኝና ይጥለኛል።” ትላለች እሴተማርያም የነገሮችን ውስብስብነት ስታስረዳ።
“ብዙ ጊዜ ስለሚያመኝ የትምህርት ቤታችን አስተዳደር ጠርቶ ይመክረኝ ነበር። አባቴ የሞተው የተሳሳተ መድሃኒት ተሰጥቶት ነበር። ነገር ግን በዚያን ሰዓት ማንም ሰው ስላልነበረ ነው እንጂ በህይወት ይኖር ነበር ብዬ አስባለሁ።
ለዚህም ዶክተር የመሆን ፍላጎትና አቅም ኖሮኝ እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን መፍትሄ ብሰጣቸው ደስ ባለኝ ይለኛል።ይህንን ማሳካት ካልቻልኩ ደግሞ ጠበቃ ሆኜ ፍትህ ላጡ ሰዎች ጥብቅና መቆም እፈልጋለሁ።” ትላለች።
አማኑኤል፤ የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና ተፈትኗል። እሱም ልክ እንደ እህቱ ሁሉ ከዓመታት በኋላ ራሱን ማየት የሚሻበት ስፍራ አለው። እናም ተመርቆ አርኪኦሎጂስት (Archeologist) ሆኖ መስራት ህልሙ ነው። ቢሆንም ግን “ቢሆንም ምኞቴን አሳካለሁ ወይ ብዬ ሳስብ እፈራለሁ::” ይላል ነገሮች እየከበዱ መምጣታቸውን ሲያስረዳ።
ህይወት ትናንትና ዛሬ!
እነዚህ ታዳጊዎች የድሮ ህይወታቸው ከአሁን ህይወታቸው ጋር ሲነፃፀር ብዙ ነገሮች እንዳልሆኑ ሆነዋል። “ቤተሰቦቻችን ህይወታቸው ከማለፉ በፊት እንደ እኛ ደስተኛ ቤተሰብ አለ ብለን አናምንም። የማይረሱ ተናፋቂ ቀናትን አሳልፈናል። ብዙ ሰዎች ቤታችን ይኖሩ ስለነበር በሰዎች ተከበን ነው ያደግነው። ያኔ ልጆችም ስለነበርን ቀናችንን በደስታ ከማሳለፍ ውጭ ስለ ጭንቀት ምንም አናውቅም ነበር።” የምትለው እሴተማርያም ናት።
የተወለድኩበት ቀን ወደዚህ ዓለም በመምጣቴ የምቆጭበትና የማማርርበት ቀን ነው። ምክንያቱ ደግሞ ከሶስት አመታት በፊት እናቴ ስትሞት ከልደት ቀኔ ሦስት ቀናት በኋላ ሲሆን አባቴ ደግሞ ከሳምንታት በፊት ነው።
እናት እና አባትን አጥቶ መኖር መግለፅ ከምችለው በላይ በጣም ከባድ ነው። የእኛ ህይወት ሳናስበው ነው እየከበደና እየጨለመ የመጣው። አብረውኝ የሚማሩት ተማሪዎች እናቴ እንዲህ አድርጋልኝ፣አባቴ ደግሞ እንዲህ አደረገልን ሲሉ ከልቤ የሚሰማኝ የመከፋት
ስሜት ነው። ይህ ስሜት ከትምህርት ቤት ጀምሮ ቤት ድረስ ይከተለኛል ስትል አሁን ያለውን አኗኗርና ስሜቷን ትናገራለች – ታዳጊዋ።
“ወላጆቻችን በህይወት እያሉ ዓለም ከዚህ የተለየ ገፅታ ነበራት። በደስታና በብዙ ተስፋ የተሞላች ነበረች። የምናውቀው ሳቅን ብቻ ነበር። የፈለግነውን ሳንበላ መሽቶ አይነጋም።
ከወላጆቻችን ሞት በኋላ ግን ነገሮች ተቀያየሩ። አሁን እንደ እኛ ብቸኛ ሰው ያለ አይመስለኝም። ስማችንን አቆላምጠው ይጠሩ የነበሩት ሁሉ ለወላጆቻችን ቀብር እንባቸውን በማዝራት ተሰናበቱን። አፈር ከለበሱ በኋላ እነሱም እኛም ተረሳን።” የሚለው ደግሞ ታዳጊው አማኑኤል ነው።
ስጋት
በአሁኑ ወቅት የታዳጊዎቹ ትልቁ ፈተና የመኖሪያ ቤታቸው ጉዳይ ነው። አባታቸው ከመታመሙ አንድ ወር በፊት የመኖሪያ ቤታቸውን አስይዞ ከባንክ አንድ ሚሊየን ብር ተበድሮ ነበር። በዚህ ብር ምን እንደተሰራ፤ ለምን ዓላማ እንደዋለ የሚያውቁት አንዳች ነገር የለም።
ከዚህም በተጨማሪ በአንድ ወር ውስጥ 600ሺ ብር የት እንደገባ ሳይታወቅ በባንክ አካውንቱ ውስጥ የተገኘው 400ሺ ብር ብቻ ነው። የዚህ እንቆቅልሽ ዛሬም ታዳጊዎቹ ላይ ጥያቄ ፈጥሯል። ለመሆኑ አባታችን በአንድ ወር ውስጥ ይህ ብር ምን ተሰራበት፤ ከአባታችን ሌላ ሚስጢሩን የሚያውቀው ማነው ሲሉ ጥያቄ ፈጥሮባቸዋል። በዚህ ሁሉ ሂደት ሕይወታቸው በጥያቄ የተሞላች ሆናለች።
“ገና ከልጅነታችን ጀምሮ መሬቱ ተገዝቶ ሲሠራ ያየነው ቤት በዛ ላይ አባታችን ሥራ ከመሄዱ በፊት ጠዋት ጠዋት ውሃ እያጠጣ እናታችን የሰው ፊት አይታ ብር ተበድራ የሰሩትን ቤት ሊሸጥ መሆኑን ማየት ይከብዳል::›› ይላሉ።
“የቤታችን ነገር በቀላሉ መከፈል የሚችል ነበር፣ምክንያቱም ስላልፈለጉ እንጂ የአባታችን ጓደኞችና ዘመዶች ሀብታሞች ናቸው። ነገር ግን ፈቃደኞች አይደሉም። ችግሮች መቅለልም መክበድም ይችላሉ::
የእኛ ችግር ቀላል ሆኖ ሳለ ግን እዳው ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ከባድ ሆኗል። እኔ በዚህ እድሜ ላስባቸው የማይገቡኝን ነገሮች ሁሉ አስቤያለሁ።›› የምትለው ነገሮች ሁሉ እንቆቅልሽ የሆኑባት የ15 ዓመት ታዳጊዋ እሴተ ማርያም ናት።
“በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ግን ፈጣሪ ከጎናችን መሆኑን የምናየው የእቁብ አንድ 147ሺ ብር በምህረት ሲተውልን ነበር። አባታችን ከመሞቱ በፊት ዕቁብ ይጥል ነበር። እቁቡን በልቶ ብር ሳይመልስ ስለሞተ እንድንከፍል በተደጋጋሚ እንጠየቅ ነበር። ጉዳዩ ወደ ክስም ሊሄድ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ቆይተው የእቁብ እዳውን እንደተዉልን ነገሩን።”
ይሁንና አሁንም ከመሳቀቅ አልተገላ ገልንም። “ድሮ ድሮ ጥሩ ቀናትን ብናሳልፍም ዛሬ ኑሯችን ሰቀቀን ሆኗል። በየቀኑ ቤቱን ሊገዙት የሚያዩት ሰዎች በመጡ ቁጥር እንጨነቃለን። እናት እና አባታችንን ያጣነው በሞት ቢሆንም አሁን ግን እዳ እኛን እንዳይ ለያየን ለመጥፎ ሕይወት እንዳይዳርገን እንሰጋለን።”
ተማፅኖ
“በእግዚአብሄር ዘንድ ዘላለም ቅፅበት ናት:: ለዚህ ቅፅበት ለሆነች ህይወት መልካም ነገርን አድርገን ብናልፍ በሰውም በእግዚአብሄርም ዘንድ ትልቅ ቦታ ይኖረዋል። እኔ የትኛውም እምነት መስጠትን እንደሚሰብክ አምናለሁ። ዛሬ ቤታችን ተሸጦ ጎዳና ላይ እንዳንወድቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ለጋስ እጆች ያስፈልጉናል።›› ስትል እሴተ ማርያም ትማፀናለች።
አማኑኤልም “እድሉን አግኝተን እግዚ አብሄርም ፈቅዶ ብድራችንን የሚከፍልንን ሰው እንፈልጋለን። በምድር ላይ መልካም የሰራ በሰማይ ይከፈለዋል እና እኛም ትብብር ያስፈልገናል። እኔና እህቴ ከመለያየትና የእናትና የአባቶቻችን ቅርስ ከማጣት ታደጉን።” ሲል የእህቱን ተማፅኖ ይጋራል።
ታዳጊዎቹ በክፉ ቀናት ያልተለዩዋቸውን ጥቂት ዘመድ ወገን ብሎም ያልረሱንን ጎረቤቶቻችንን እግዚአብሄር ይስጥልን ሲሉም ስለሆነው ያመሰግናሉ፤ ስለሚሆነውም ነገር ብዙ ተስፋ በማድረግ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
ዳግማዊት ግርማ