
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም ምርቶች ላይ 50 በመቶ ታሪፍ ሊጥሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ አስተዳደራቸው ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያደረገው ውይይት ምንም ውጤት እያስገኘ አለመሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የሚተገበር የ50 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ አሜሪካ ውስጥ የተመረቱ የአውሮፓ ምርቶች ግን ታሪፍ እንደማይጣልባቸው ጠቁመዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት አሜሪካና የኅብረቱ አባል ሀገራት የሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ታሪፍ አልባ (ዜሮ ታሪፍ) እንዲሆን ምክረ ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ትራምፕ ግን በእዚህ እንደማይስማሙ ገልጸው፤ በሀገራቸውና በኅብረቱ መካከል የንግድ ድርድር እንዲካሄድ ቢያሳስቡም፤ የሁለቱ ወገኖች የንግድ ንግግር ለውጥ አለማሳየቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕን አበሳጭቶ የኅብረቱ አባል ሀገራት ወደ አሜሪካ በሚልኳቸው ሁሉም ምርቶች ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል። ፕሬዚዳንቱ የ50 በመቶው ታሪፍ እንዲዘገይ የሚያደርግ ቅድመ ሁኔታ እንዳላቸውም ፍንጭ ሰጥተዋል። ይህን ታሪፍ ሊያዘገየው የሚችለው የአውሮፓ ኩባንያዎች በአሜሪካ ውስጥ ትልቅ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ከተዘጋጁ ነው“ ብለዋል።
ይህ የትራምፕ ውሳኔ የአሜሪካ ሁነኛ አጋር የሆነው የአውሮፓ ኅብረት የአሜሪካ ዋና ተፎካካሪ ከሆነችው ቻይና የበለጠ የታሪፍ ሰለባ እንዲሆን ያደርገዋል። ትራምፕ ከቻይና ወደ አሜሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ 145 በመቶ ታሪፍ ጥለው የነበረ ቢሆንም፤ ይህን ታሪፍ ለ90 ቀናት ወደ 30 በመቶ ዝቅ አድርገውታል።
የትራምፕ የታሪፍ ውሳኔዎች ቻይናን ለማግለልና ከአሜሪካ ወዳጆች ጋር አዳዲስ የንግድ ውሎችን ለማሰር ያለሙ እንደሆኑ ቢናገሩም፤ የታሪፍ ማስፈራሪያዎቹ ከዓላማዎቻቸው በተፃራሪ የቆሙ በመሆናቸውና ኅብረቱ ቻይና ከተጣለባት የበለጠ ታሪፍ እንዲጣልባት ስለሚያደርግ የኅብረቱ አባል ሀገራት ከቻይናና ከሌሎች ሀገራት ጋር ትብብር እንዲፈጥሩና የትራምፕን የንግድ ፖሊሲ እንዲቃረኑ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ተንታኞች ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ ኅብረቱ ለትራምፕ የንግድ ውሳኔዎች ጠንካራ ስትራቴጂ የለውም ተብሎም እየተወቀሰ ነው።
27 አባላት ያሉት የአውሮፓ ኅብረት ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የታሪፍ ዛቻ ምላሽ ሰጥቷል። የኅብረቱ የንግድ ኃላፊ ማሮስ ሴፍኮቪች፣ የአውሮፓ ኅብረት ከአሜሪካ ጋር ያለውን የንግድ ግንኙነት በማስፈራራት ላይ የተመሠረተ መሆን እንደሌለበት አሳስበዋል። ኅብረቱ ከአሜሪካ ጋር ያለው የንግድ ስምምነት በአክብሮት ላይ እንዲመሠረት ቁርጠኛ ስለመሆኑም ተናግረዋል። ከአሜሪካ የንግድ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ “የአውሮፓ ኅብረት ለሁለቱም ወገኖች የሚሠራ ስምምነትን ለማረጋገጥ እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል። “የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ንግድ ግንኙነት ወደር የለሽ ነው። ይህም በጋራ መከባበር መመራት እንጂ በማስፈራሪያ ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም። ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን” ብለዋል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሐን ዋደፉል በበኩላቸው፤ ታሪፎቹ ማንንም እንደማይጠቅሙ ተናግረው፤ ይልቁንም በሁለቱም ወገኖች በኩል የገበያ ቀውስ እንደሚፈጥሩ አስጠንቅቀዋል። “በድርድሮቹ ስለምናምን መደራደራችንን እንቀጥላለን” ያሉት ሚኒስትሩ፤ የኅብረቱ ኮሚሽን የአውሮፓ ምርቶች በአሜሪካ ገበያ ቦታ እንዲኖራቸውና የአውሮፓን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት ሀገራቸው እንደምትደግፍ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለፈው መጋቢት መገባደጃ ላይ ይፋ ባደረጉትና በበርካታ ሀገራት ላይ ይተገበራል በተባለው የታሪፍ ውሳኔያቸው፤ በአውሮፓ ኅብረት ላይ የ20 በመቶ ታሪፍ ጥለው ነበር። ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንቱ “በርካታ ሀገራት ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ጥያቄ እያቀረቡ ስለሆነ ከ10 በመቶው የመነሻ የታሪፍ ምጣኔ ውጪ ያሉትን አብዛኞቹን ታሪፎች ለ90 ቀናት እንዲዘገዩ እናደርጋለን” በማለታቸው እንዲሁም አሜሪካ እና ቻይና አንዳቸው በሌላኛቸው ምርቶች ላይ የጣሉትን ታሪፍ ለ90 ቀናት በ115 በመቶ ዝቅ ለማድረግ መስማማታቸውን ተከትሎ የትራምፕ ታሪፍ ዛቻ ጋብ ብሎ ቆይቷል።
የአውሮፓ ኅብረት ከአሜሪካ ትልቅ የንግድ አጋሮች መካከል አንዱ ነው። ባለፈው ዓመት ኅብረቱ የ605 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጦችን ወደ አሜሪካ የላከ ሲሆን፤ 370 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ደግሞ ከአሜሪካ መግዛቱን የአሜሪካ መንግሥት መረጃዎች ያሳያሉ። ይህም አሜሪካ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በነበራት የንግድ ልውውጥ ከ235 ቢሊዮን ዶላር በላይ የንግድ ጉድለት እንዳጋጠማት ያሳያል። ትራምፕ ከኅብረቱና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለውን የአሜሪካ የንግድ ጉድለት “ግፍ” ሲሉ ጠርተውታል። ይህ የንግድ ጉድለት የመጣውም ከአሜሪካ ወደ ሌሎች ሀገራት የሚላኩ ምርቶች ከፍተኛ ታሪፍ ስለሚጣልባቸው እንደሆነ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ያምናሉ።
አዲሱ የትራምፕ የታሪፍ ማስፈራሪያ የኅብረቱና አሜሪካ ግንኙነት ያለበትን ሁኔታ የሚጠቁም እንደሆነም ተገልጿል። ትራምፕ ወደ ዋይት ሃውስ ከተመለሱ በኋላ ከጠንካራ የአሜሪካ አጋሮች መካከል አንዱ ስለሆነው አውሮፓ ኅብረት ተደጋጋሚ አሉታዊ አስተያየቶች መስጠታቸው ይታወሳል። ምክትላቸው ጀምስ ቫንስም ባለፈው የካቲት ወር በተካሄደው በ61ኛው የሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ (Munich Security Conference) ላይ ባደረጉት ንግግር አውሮፓን መወረፋቸው አይዘነጋም።
ብዙ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ላይ በያዙት አቋም ደስተኞች አይደሉም። መሪዎቹ ትራምፕ አውሮፓን ከጉዳዩ እያገለሉና ለሩሲያ እያደሉ እንደሆነ ያምናሉ። ትራምፕ ግን “እኔ ከማንም አላዳላሁም፤የቆምኩት ሰላምን ከሚወድ ሁሉ ጋር ነው” ብለው የአውሮፓውያኑን ቅሬታ ያጣጥላሉ።
የትራምፕ ነገር ያላማራቸው አንዳንድ የኅብረቱ መሪዎች አውሮፓ ከአሜሪካ ጥገኝነት መላቀቅ እንዳለበት ደጋግመው እየተናገሩ ነው። ለአብነት ያህልም ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሚወስዷቸው ርምጃዎች በእጅጉ መበሳጨታቸውን የሚናገሩት አዲሱ የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪኽ ሜትስ፣ ከአሜሪካ ጫና የተላቀቀ አውሮፓን መገንባት ከዋና ዋና እቅዶቻቸው መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል። የአሜሪካ መንግሥት የአውሮፓ መፃኢ እድል ግድ እንደማይሰጠው በግልጽ ማሳየቱንና አውሮፓ በፍጥነት የራሱ የሆነ መከላከያ ሳያስፈልገው እንደማይቀርም ተናግረዋል። “ከአሜሪካ በኩል ምን ዓይነት ውሳኔና ርምጃ እንደሚመጣ ብዥታ የለብኝም። ከአሜሪካም ከሩሲያም ከፍተኛ ጫና እየደረሰብን ነው” በማለት አውሮፓ ለምጣኔ ሀብቱም ሆነ ለጸጥታው ተባብሮ ከመቆም ውጪ ሁነኛ አጋር አለኝ ብሎ መዘናጋት እንደማያስፈልገው አበክረው ሲናገሩ ይደመጣሉ።
በሌላ በኩል ፕሬዚዳንቱ አይፎኖች (iPhones) አሜሪካ ውስጥ የማይመረቱ ከሆነ በአፕል ምርቶች (Apple) ላይ 25 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉም ተናግረዋል። ለአሜሪካ ገበያ የሚቀርቡ የአይፎን ምርቶች አሜሪካ እንጂ ህንድ ወይም ሌሎች ሀገሮች ውስጥ መመረት እንደሌለባቸው ለኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቲም ኩክ እንደነገሯቸው ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ቻይና ውስጥ ማምረቻ የነበረው አፕል ኩባንያ አሜሪካ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ መጣሏን ተከትሎ ማምረቻውን ወደ ህንድ ለማዞር ማቀዱን አስታውቆ ነበር። ኩባንያው ለአሜሪካ ገበያ ከሚያቀርባቸው ምርቶቹ ውስጥ 80 በመቶውን የሚያመርተው ቻይና ውስጥ ነው።
ኩባንያው የምርት ማዕከሉን ከቻይና ወደ ህንድ ለማዞር የወሰነው ከትራምፕ የታሪፍ ሰይፍ ለማምለጥ ነበር። ከእዚህ በተጨማሪም ኩባንያው ለሰው ሰራሽ አስውሎት ቴክኖሎጂ ልማት በአሜሪካ ምድር 500 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ማቀዱን ባለፈው የካቲት አስታውቆ ነበር። ይሁን እንጂ አፕል ትራምፕ “በአሜሪካ ላይ አደገኛ ቁማር ትቆምራለች” ብለው በተደጋጋሚ ከሚያብጠለጥሏት ከቻይና ለመራቅም ሆነ 500 ቢሊዮን ዶላር ለማፍሰስ መወሰኑ ለትራምፕ በቂ አልሆነም።
“መዝገበ ቃላት ውስጥ ካሉ ቃላት መካከል በጣም የምወደውና ደስ የሚያሰኘኝ ‘ታሪፍ (Tariff)’ የሚለው ቃል ነው” ብለው የተናገሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ የታሪፍ ጭማሪ የአሜሪካን አምራች ኢንዱስትሪ ለመጠበቅና ምርትን ለማሳደግ ይጠቅማል ብለው ያምናሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ግን፤ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በየጊዜው ይፋ የሚያደርጓቸው የታሪፍ ጭማሪዎች ለዋጋ ንረት፣ ለምጣኔ ሀብት መዳከምና ለዓለም አቀፍ የንግድ ጦርነት ያስከትላሉ። የታሪፍ ጭማሪው ለአሜሪካውያን ሸማቾች የምርቶች ዋጋ እንዲንር ያደርጋል፤ በሌሎች ሀገራትም የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ይፈጥራል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም