ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ቀደም ሲል “በብሔራዊ ቴአትር”ተደርጎ በነበረው “መፍትሄው ኢትዮጵያዊነት ነው “ በሚለው ርዕሰ-ነገር ሥር ያቀረብኩት ንግግሬ መልካም ግብረ መልስ አገኘ መሰለኝ፤ በጽሑፍ በዚሁ ዓምድ ላይ ወጣ። ከዚያም በኋላ በተነጋገርነው መሰረት ዓምዱን የሚመጥኑ ጽሁፎች እያዘጋጀን ለመላክ የምንችልበት ሁኔታ መኖሩን በማወቃችን ይህን ጽሁፍ በማቅረብ፣ አሃዱ ብያለሁ።
የዛሬው ጽሑፌ ትኩረትም በሉት፣ መሪ ሃሳብ በፍቅር ለሰላም፣ ለኢትዮጵያ መቆም የሚል ፅንሰ-ሐሳብ ያለው እንዲሆን ወጥኜ እንዲህ አዘጋጀሁት። ከፍቅርና ሰላምስ የበለጠ ምን ነገር አለን?
አንዳንዶች ከሰላም ፍቅር ይቅደም ሲሉ ሌሎች ደግሞ ለፍቅር ሰላም ይቅደም ይላሉ። ይሁን እንጂ ፍቅር የሌለበት ሰላም ተወጥሮ ሊፈነዳ የተቃረበ ጦርነት ነውና፤ ለተዋጣ ሰላም ፍቅር መሰረት መሆኑን ግን ብዙዎች ይስማሙበታል።
ፍቅር ልባም ያደርጋል፤ ልባም ሰው ደግሞ ላፈቀረው ነገር ቢሞት እንጂ፤ አይገድልም። ለሰላምም ሁል ጊዜ ዘብ ይቆማል። የሰላምንም ዋጋ ያለፈበት ይረዳዋል። በፍቅር ኃይል የተለወጡ ነገሮች እድሜ ዘላቂ መሆኑን ህይወት አሳይታናለች፤ ክንውኖቹም የተሳኩ ይሆን ዘንድ የሰላም መኖር እንደ ዋስትና ነው፤ የሚጠቀሰው። በእርግጥ ነውም ማለት እንችላለን።
የጽሁፌ ዓላማ፣ ታሪክ መዘከር አይደለም ማጣቀስ እንጂ። መዘከር ካለበት ግን መዘከር የተገባ መሆኑን ማጤንም ተገቢ ነው።
ኢትዮጵያ ሐገራችንን በዚህ ፈታኝ ወቅት እጅግ የሚያስፈልጋት ሌላ ምንም ሳይሆን ፍቅርና ሰላም ነው። የፍቅር ማእከል የሆነው ይቅርታ የማያክመው ነገር ደግሞ የለም፤ የታከመው ፀብ በጽናት እንዲዘልቅ በፍቅር ላይ የተመሰረተውን ሰላም አጥብቆ መያዝ ይገባል።
ጽሑፌን፣ ሁለት ስንኝ ባላት በሩሲያዊው የሌርሞንቶቭ ግጥም ማሟሸት ፈልጋለሁ። (እርሱ) ለሩሲያ ቢላትም እኔ ለሐገሬ ኢትዮጵያ አውየዋለሁ።
“ኢትዮጵያ ሃገሬ ኢትዮጵያ እማማ፤ ደሃም ሐብታምም ነሽ፤ ኃያልም ደካማ!!” ይላል ግጥሙ…
ድህነቷ በተቀናጀ ሁኔታ ያልታረሰው ምድሯና ማዕድኗ እና በሌላ በኩል ድህነቱን እንደጽድቅ መንገድ የሚቆጥር ህዝብ ያላት ሀገር መሆኗ ሲሆን፣ ሐብታምነቷ ደግሞ ድሃ ናት ብሎ የከዳትና የተዋት ህዝብ የሌላት እንዲያውም ክፉ ሲገጥማት ከማያርፈው ማህፀኗ የሚወለዱ የማይተኙ፣ ብርቱ ልጆች የምታፈራ፣ የጀግኖች ባለጸጋ የሆነች፣ ለሰላምና ደህንነቷ ህቅታቸውን እንደ ዋዛ ለመስጠት የማያመነቱ ጎበዛዝት እናት መሆኗ ነው፤ ሀብታምና ኃያል የሚያደርጋት።
ከብሉይ እስከ አዲስ ኪዳን፣ ከቁርዓን እስከ ሐዲሳት መጻህፍት፣ እናም ዋቄፈታ ድረስ ህዝቧ የእምነት ማህተም ያሳረፈባት፤ የቀደመውን ሳትጥል አዲሱን ለመቀበል እጆቿን የዘረጋች፣ አቃፊ ማህደር ናት፤ ኢትዮጵያ!!
ኢትዮጵያ፣ ሰራዊት በአዛዡ ፊት ሰላምታ እየሰጠ እንደሚያልፍ፣ ሣታልፍ ሁሉን የምታሳልፍ ኩሩ ሐገር ናት። ሰዎች ስለፈለጉ ብቻ ሳይሆን እርሷ ያካበተችው የረዥም ዘመን ታሪክ ያኮራት እውቅ ሃገርም ናት።
በሞታቸው ተወራርደውባህር የሚያቋርጡ ስደተኞች ብቻ ሳይሆን ከነመከራዋ አብረዋት ለመኖርና ለመሞት የቆረጡ የአዕላፍ አፍቃሪዎ ቿም እናት ናት፤ ኢትዮጵያ!!
ድንጋዮቿ በማዕድናት የከበሩ፣ አፈሯ ሰብል አብቃይ፤ አየሯ ጤና አፍሪ፣ ህዝቦቿ ምንጊዜም ታሪክ ሰሪ የሆኑባት ምድር ናት፤ ሐገራችን።
በጉልበቷ ታምና ገፍታ ሳይሆን ተገፍታ፤ በማንአለብኝነት ታብያ ሳይሆን ተከፍታ፣ ስትከላከል የወራሪዎቿን ቅስም የሰበረች፤ ግን ተማራኪዎቿን የተንከባከበች ፈሪሐ -እግዚአብሔር ያለው ህዝብ ምድር ናት፤ ኢትዮጵያ!!
ቤትን መልካምና ጥፉ የሚያደርገው የቤቱ ነዋሪ ነው፤ ኗሪው ላጠፋው ጥፋት ቤት አይወቀስም፤ ሐገርም እንዲሁ ናት፤ ከብልጽግናዋ ይልቅ ለድህነቷ ከእድገቷ ይልቅ ለጉስቁልናዋ ያደረግነውን ራዕይ አልባ ጉዞ ማቆም ካልቻልን ሐገራችንን ከህመሟ ማዳንም ሆነ ማገገም ያስቸግረናል፤ ለዚህ መድኃኒቱ ራዕያችንም በፍቅር የታሸ መሆን ይገባዋል።
ፍቅር እንደምንናገረው የማይቀልል ስንኖረው ተግባቦት የሚጠይቅ መሰረቱ በይቅር ባይነት የመስዋዕትነት ኣምድ ላይ የቆመ የችግር መፍትሔ ነው።
ስለዚህም ነው “ሐገሬ ምን አደረገችልኝ” ሳይሆን “ምን አደረግንላት” ብለን መጠየቅ ያለብን። እኛ የእጆቻችን ፍሬዎች፤ የልባችን ሐሳብ ውጤቶች ነን። ዜጎቿ ሰላም ወዳድ የሆኑላት ሐገር አማራጯ መፍረስ ሳይሆን መታነጽ፣ መደህየት ሳይሆን መበልጸግ፣ ነው። ዕጣ ፈንታዋ ተቸግሮ ማስቸገር ሳይሆን በሰላም ውዴታ የሄዱ የሚመለሱባት፤ የጠፉ የሚገኙባት ሐገር ነው፤ የምትሆነው።
አንድ ጸሐፊ ቀደም ሲል እንደገለጸው፣ ግን ጦርነት ሶስት ነገሮችን ይጠይቃል።
አንደኛ ወርቅ
ሁለተኛ ወርቅ
ሶስተኛ ወርቅ ነው። እነዚህ ሁሉ ለቅድመ ጦርነት ምልመላና ፕሮጋንዳው፣ በጦርነቱ መሐል ያለው ለመከላከያ የምታወጣው ወጭና የድህረ ጦርነቱ የግንባታ ወጭ ነው።
የሚያሳዝነው ነገር፤ የምንዋጋው ከፍለንና ለመውደምም እንዲሁ አድርገን ነው፤ በዚህ ላይ ከምንከፍለው ነገር ውዱና ዋናው የሰው ልጅ ህይወት ግብር ነው።
በሌላ በኩል፣ ሰላም ግን የሚያፈርሰው ነገር የለም። የሚፈርስ እንኳን ቢኖር ለማሳመር ነው፤ ለመለወጥ የምናፈርሰው የልማድ ማንነትን ነው። ያንን አፍርሰን መገንባት ስንጀምር ግን ከሰላሙ የሚቀዳው ውበትና ብርሃን ምድሪቱን ከማለምለሙ ሌላ ህዝቦቿን ከፍቅር ጠበል የሚያስጎነጭ ይሆናል። ከቶም የሰላም መጥፎ የለውምና።
ኢትዮጵያ፣
ዘመናትን፣ የተሻገረው ባህሏ ከውጭ ጠላት የሚመጣውን ጥቃት፣ በጋራ መመከት ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የውስጥ ሰላሟን የሚያደፈርሰውን የመገፋፋት ጥላቻ በመነጋገርና በመወያየት ችግርን የማስወገጃ የፍቅር ባህል ግን ገና አልዳበርንም።
እንዲያውም “ችግርን በችግር “ የማጥፋት ዝንባሌያችን በደማችን ሰርጾ ያለ እስኪመስል፣ “ሃበሻ አርጩሜ ያስፈልገዋል”…”ሐበሻ ካልሸነቆጡት አይነቃም”እና “ “ሐበሻን መታገስ ብጉንጅን መዳበስ” እና የመሳሰሉትን አሉታዊ ሃሳቦችን በገዛ አንደበታችን ላይ ተነቅሰን እንዞራለን።
በኩራትም እንናገረዋለን፤ ከላይ እንዳያችሁት በሁሉም አባባሎች ውስጥ አለንጋ፣ ቁንጥጫና ህመም አለበት። ለዚህ የዋህና ክፉ ቀን በመጣ ቁጥር ደሙን እየገበረ ሉዓላዊነቷን ማስከበር የማይሰለቸውን ህዝብ “መገረፍ አለበት” የሚሉት ዘባቾች አንተ ምን አዋጣህ ቢባሉ የሚያሳዩት አንዳች ነገር እንኳ የላቸውም።
ለፍርድና ውግዘት ግን ፈጣኖች ናቸው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ከሚሰጡት ይልቅ የሚወስዱት ከሚሰሩት ይልቅ የሚያወሩት የሚበልጥና ፍቅርና ርህራሄ ያልፈጠረባቸው ናቸው።
ራሳቸውን ኮንነው ራሳችንን እንድንኮንን ከሚያደርጉብን ኮናኝ ባህል እኛም ወጥተን ያለ ፈራጅነት ሐሳብ የምንወያይበት፣ ያለ ቁስል መነካካት የምናወጋበት የእርቅና የምህረት ጉባኤን በየአውዳችን ማድረግ አለብን። ደግሞም እንችላለን!
እውነቱን በመነጋገርና ምስክርነቱን ለታሪክ በማኖር በዚህ የኋላ የመለያየት ጨለማ ላይ የምናደርገውን ትርክት ዘግተን በወደፊት አንድነታችን ላይ የፍቅር ብርሃንን ማወጅ አለብን።
ኢትዮጵያን ከራሳቸው በላይ በማግዘፍ ባዶ እጃቸውን ዱር ቤቴ ብለው በኃይላቸው በተመኩ ወራሪዎች ላይ በከፈቱት የመከላከል ውጊያ አለኝታነታቸውን ያስመሰከሩላት አበውን፣ ማንነት ለማዘከር ይኼ ዓምድ ዓላማውም ትልሙም አይደለም።
ከሁሉም የኢትዮጵያውያን ነገዶች፣ እምነት አራማጆችና የሐገሪቱ ክፍሎች ደሙን ያልገበረ ዜጋ የለም፤ ሁሉም እንደ አንድ ሰው ተዋግተዋል፤ እንድ አንድ ሰው ተሰውተዋል።
በሌላ በኩል ራሳቸውን ከኢትዮጵያ በላይ ያደረጉና ከወራሪው ጠላት የተባበሩ አልጠፉም፤ እነርሱ ግን ባህርን በጭልፋ የመጥቀስ ያህል ናቸው፤ እጅግ ጥቂት። ለጊዜው ጣሊያን በሠጣቸው ሹምባሻነትና ሙንጣዝነት. “የሹም “ ቀሚስ ለብሰውና በአድርባይነት አጥር ታጥረው ታይተው ነበር።
ያኔ ነው ታዲያ፡-
“ጣሊያን ይሄድና ሶልዲውም ያልቅና፣
ያስተዛዝበናል ይኼ ቀን ያልፍና !!” (የህዝብ ግጥም ) የተባለው።
ኢትጵያን የጠላቶቿ ግፍና ጫና አላሰጠማትም፤ በከዷት ልጆቿም እብሪት አልተሰናከለችም፤ ሆዳቸው በበለጠባቸው ከንቱዎች ማቃለል ከንቱ ሆና እንዳልቀረችም ታሪክ መዝግቦታል።
እዚህ ጋ፣ አንዲት ምሳሌ የሆኑኝን አበው ታሪክ ለአብነት ማንሳት እወዳለሁ ‹- አቡነ ጴጥሮስን ከጣሊያን ጋር ሊያግባቡ ከመጡት ሸምጋዮች መካከል አንዱ የወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያረክ፣ አቡነ አብረሐም፤ “የወጣ ፀሐያችን የነገሰ ንጉሳችን ነው፤ አሁን ገናናውን የጣሊያንን መንግሥት ማገልገል የመጣን ዝናብ ማሳለፍ ነው “ እንዳሏቸውና፣ አቡነ ጴጥሮስ ግን “በኢትዮጵያ ጸሐይ ስር ንጉስ መሆን ያለበት የኢትዮጵያ ልጅ አይመስልዎትም? ካልሆነ ግን በእስራኤል ያልዘለቀ ቄሳር በኢትዮጵያም እንዲዘልቅ አልስማማም “ ሲሉ እንደመለሱ ተሰምቷል።
አቡነ አብረሐምን ዛሬ የሚያስታውሳቸው የለም፤ አቡነ ጴጥሮስን ግን ይኸው ሁሌ በኩራት እናወሳቸዋለን። እንደ ጴጥሮስ ያሉ ባላቸው የሐገር ፍቅር ብቻ ሳይተኩሱ “ገዳዮች”፣ ራሳቸውን እንደጧፍ ያነደዱ አፍቃሬ ሀገርና አፍቃሬ እውነት ዜጎች፣ በዚያ መገናኛ ብዙሃኑ ባልነገሱበት ዘመን ልበ ብርሃኖች፣ አላጣችም፤ ዛሬም፣ ቢሆን ሃገሬ በዚህ ትውልድ ውስጥ አሳቢ የፍቅር ልጆች አታጣም።
ሀገር እኮ ልጆች የኮለኮሏት የእንቧይ ካብ አይደለችም፤ ዜጎች በተለያዩ ዘመናት በጋራ ጉዳይ ተባብረውና በድንበሯ ላይ ተነባብረው የሰሯት ድንቅ ምድር ናት፤ በተለይ ኢትዮጵያ።
አንዳንዶች መብቴ ተሸርሽሮና ተነጥቆ ከምኖር ኢትዮጵያ ለምን “አትለያይም” ሲሉ ይደመጣሉ። ሃገራችን ከልዩ ልዩ ኩባንያ የተሰራ ዕቃ የተገጣጠመችና በብሎን የታሰረች ማንም የሚከረክሳት የፋብሪካ ውጤት አይደለችም።
የእነዚህ ሰዎች ነገረ ሥራ እንግዳ የሚሆንብኝም በዚህ መሰል ንግግራቸው ነው፤ “አባወራው” በባለገ ቤተሰብ ይበተን፤ በ”አንድ ፊጋ ከብት” የተነሳ በረቱ ይፍረስ የሚሉ ናቸው።
መከሰስ ካለበት አባወራው፤ ገለል መደረግም ካለበት ፊጋው በሬ እንጂ ቤቱና በረቱ መሆን የለበትም፤ ብዬ በጽኑ አምናለሁ። በረቱና ቤቱ እንዲፈርስ መፍቀድ ማለት ካፒቴኑን ለመግደል መርከቧን ማስጠም፣ አባወራው ስለባለገ ቤቱን ማቃጠል ማለት ነው።
ሐገሬ የተቸገረን ለመርዳት ዘር መስፈርት ያልሆነባት፤
የሞተን ለመቅበር ዘር መስፈርት ያልሆነባት፤
ለታሰረ ዋስ ለመሆን ዘር መስፈርት ያልነበረባት፣
የከሰረን አትራፊ ለማድረግ የሚረባረቡባትን …. ሃገሬን ምን ቡዳ እንደበላት የሚነግረኝ እፈልጋለሁ። ምናልባት ያሠራት ገርጋሪ ሰይጣን ቢሆን የአምላክን ስም ጠርቶ ማውገዝና ማውጣት ባልገደደን ። አእምሯዊ ሤራና ሥጋዊ ተንኮል ሆነና አስቸገረ እንጂ።
ነገር በምሳሌ ሲሆን ይቀላልና አንድ ምሳሌ ላክልላችሁ። በአንድ የአእምሮ ህሙማን ሆስፒታል ውስጥ በርካታ ህሙማኑ የሚጠበቁት በአንድ ሰው ብቻ መሆኑን ያየ ሰው፤ አንተ ሰው እነዚህን ሁሉ ሰዎች ለብቻህ ጠብቀህ እንዴት ትችላለህ፣ አያስቸግሩህም? ሲል ይጠይቀዋል።
አያስቸግሩኝም፤ ምክንያቱም የአእምሮ ህሙማን በመሰረቱ አይተባበሩም፤ ጥፋት ያለ ትብብር አይሆንምና ሲል መልሶለታል። እኛስ ብዬ መልስ ያጣሁለት ነገር ይህ ነው፤ አብደናል ወይ? በድህነት ላይ መተባበር፤ መበልፀጉ እንኳን ቀርቶ ለሰላም መተሳሰር እንዴት ያቅተናል።
ግን ይህ ሁሉ ሆኗል ተብሎም በሐገር ተስፋ አይቆረጥም፤ ከላይ ያልኩትን እደግመዋለሁ፤ ሐገራችን ኢትዮጵያ፣ ሰራዊት በአዛዡ ፊት ሰላምታ እየሰጠ እንደሚያልፍ፣ ሣታልፍ ሁሉን የምታሳልፍ ኩሩ እናት ናት።
አንዳንዶች በራሳቸው የስልጣን ዘመን በሥልጣን ካርታ የተበሉትን ቁማር በወጣቱ ዘመን፣ በወጣቱ ዕድሜ፣ በእናታችው አንጀት አስይዘው ለማስመለስ የሚቆምሩ የጥላቻ ፖለቲከኞች ናቸውና፤ ጆሯችሁን አትስጡ።
የቀሚሷ ጥለት በማንም ጥበብ የማይተካ የኩራታችን ምንጭ የሆነች ብዙ ሐገሮች እንደ ሐገር ከመጠራታቸው በፊት ጀምሮ ስም ያላት እናት ሀገር ነው፤ ያለችን። ማንም ያሻውን ልብወለድ እየተረከ ወጣቶችን ልብ እንዲሰርቅ እድል ፈንታ መስጠት አይገባም። የወጣቶቻችን ልብ ከተሰረቀም ለፍቅር ብቻና ከእርሱም ለሚመነጨው የመተባበርና የመተጋገዝ የይቅር ባይነት ጉዳይ ብቻ ይሰረቅ። ከተሰረቀም ለሃገራችን ትንሳኤና ለህዝቦቿ ሰላምና ክብር ለመስራት የተሰረቀ ይሁን !!
ለጭካኔና ውዝግብ ከቶውንም እጆቻችሁንም ልባችሁንም አታንሱ። ጭካኔ የፍርሃት የበኩር ልጅ ናት፤ ፈሪ ሰው የሚያሸንፍበት አላማ ስለሌለው ዓላማውን ለማስፈጸም ዱላ ቆርጦ ቅን ለሆኑ ልጆች ይሰጣል።
ነገረኛ ወትሮውንም ዳር ቆሞ ያፋጃል እንጂ፣ የሁከቱ ተዋናይ አይሆንም። ኢትዮጵያ ዛሬ እንደ እሳት የሚፈጃትንና የሚያፋጃትን ሳይሆን አባርዶና አረጋግቶ፣ የሚያሰክናትን ነው፤ የምትፈልገው። ስለዚህ በተቻለ መጠን ለጸብ የታገሳችሁ፣ ለፍቅር የጀገናችሁ ሁኑ።
ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ በአንድ ወቅት፡-
“በዚህች ቅጹብ ዕድሜ በዚህች አጭር ህይወት፣
በፍቅር ባንኖር በፍቅር እንሙት።”
እንዳለው ልባም ሰው ለፍቅርና ሰላም ይሞታል እንጂ፣ በሰላም ስም፤ በመብት ስም ያገር ሰላም አያደፈርስም፤ እኛ ግን ለዚህ መሰረቱ የሆነውን ፍቅር አጥብቀን ከያዝን የማንወጣው አቀበት የማናልፈው ማዕበል አይኖርም።
በመጨረሻም፤ ፍቅር ያጸደለባት ሰላም የሰፈነባት ሃገር እንድትኖር ወጣቶቿ ከምንጊዜውም በላይ መስራት አለባቸው፣ አለብን ብዬ አምናለሁና፤ ለፍቅር በጋራ እንነሳ፤ ፍቅር ከውስጥ እንጂ ከውጭ አይመጣምና ከልባችን በመተሳሰብ እንተጋገዝ።
የማይታበየው ፍቅር በትህትናና በትዕግስት፤ በይቅር ባይነትና በኃላፊነት ስሜት እንድንሰራ ግድ የሚለን ዘመን ላይ አድርሶናል። ለኢትዮጰያ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ሌላ ለውድቀቷም ሆነ ለልማቷ የሚወቀስም ሆነ የሚወደስ ማንም የለም። በህይወት ሳለን አለኝታነታችንን ማሳየት ይገባናል።
በመጨረሻም መጨረሻ ሰሞነኛውን የሀገሬን ሁኔታ ያጤነ ሰው፣ ለዚህች ሐገር የሚበጃት እሳት ሳይሆን ውሃ፣ ግጭት ሳይሆን መረጋጋት፤ ጦር ማንሳት ሳይሆን ጦር ማውረድ (ሰላም )፤ ጥላቻ ሳይሆን ፍቅር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው፣ “የኃጥአን ቃል ደምን ለማፍሰስ ትሸምቃለች፤ የቅኖች አፍ ግን ይታደጋቸዋል(ምሳ 12፡6)“ ነውና፤ ሰላምና ፍቅርን በህይወታችን ላይ ማወጅ በራሱ ለሀገርና ለህዝብ በረከት ስለሆነ ሁላችንም በፍቅር ለሰላም ዘብ እንቁም።
የምንፈራውና የምናከብረው ነገር ቢኖር እንኳን ቅዱስ እግዚአብሔርን ብቻ ይሁን እንጂ፤ በወቅቱ የተነሳውን አስፈሪ ሁኔታ ወይም አስቸጋሪውን ሰውና ወገንም መሆን የለበትም። የፈራነው ነገር እርሱ ይነግስብናል፤ የጠላነው ነገር እርሱ ይወርሰናልና።
ስለዚህ ሁኔታዎች የፈጠሩትን ፍርሃት ማሸነፍ የምንችለው በክፋት ፊት በድፍረት ቆመን የፍርሃቱን ምንጭ ስንገልጥ ነው። ያኔም አስፈሪውን ወገን በወዳጅነት ማርከን ፍርሃቱን በመተው በሰላም የመኖሪያ ድባብ እንፈጥራለን። ጥላቻ በፍቅር ፊት ፀብም በሰላም ፊት ብርቱ አቅም የላቸውምና።
እግዚአብሔር፣ ኢትዮጵያንና ህዝቧን በሰላምና በፍቅር ይባርክ!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011