
አዲስ አበባ፡– በኦሮሚያ ክልል በ2017 ዓ.ም አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በችግኝ ተከላው የሚሳተፉ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
የክልሉ የደን ልማት እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ከተማ አብዲሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለማከናወን ከ15 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለማሳተፍ የንቅናቄ ዝግጅቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በንቅናቄው የተፈጥሮ ሀብትን በማልማት በመንከባከብ እና በመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የተለያዩ ግንዛቤ ሰጪ ሥልጠናዎች ከክልል እስከ ቀበሌ ለባለሙያው እና ለማኅበረሰቡ ተሰጥተዋል፡፡
ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በችግኝ ለመሸፈን መለየቱን ጠቅሰው፤ 500ሺህ ሄክታር መሬት በጂፒኤስ በመለየት ችግኝ የሚተከልባቸው ጉድጓዶች በጥራት እና በብዛት መዘጋጀታቸውን፤ ችግኞቹ የደን ሽፋንን ለመጨመር የሚያስችሉ፣ የመኖ አገልግሎት የሚሰጡ፣ የፍራፍሬ ችግኞች እና የአካባቢ ውበት የሚያለብሱ እንዲሁም የቀርከሓ ችግኞችንና መሰል ችግኞች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሶንቆሌ ተራራ በርካታ የክልሉ አመራሮችና ነዋሪዎች በተገኙበት ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም የችግኝ ተከላው መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
32 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች ወደ ሥራ መሰማራታቸውን ጠቅሰው፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና አካባቢያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በማዘጋጀት እንዲሁም ከሚተከሉበት ቦታ እና አፈር ጋር ተስማሚነታቸውን ታሳቢ በማድረግ ዝግጅቱ ሲከናወን መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በተለያዩ ዞኖች ከ15 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎች በተከላው የሚሳተፉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
5 ቢሊዮን ችግኞች በአረንጓዴ ዐሻራው መርሐ ግብር በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ለመትከል መታቀዱን ገልፀው፤ በተፋሰሶች ውስጥ የአፈርና የውኃ ጥበቃ የተሠራባቸው ቦታዎች ላይ፣ የተራቆቱ ተራራዎች፣ ወንዝ እና መንገድ ዳር፣ እርሻ ማሳ ውስጥ፣ አጥር ዳር እና ለመዋቢያ የተመረጡ ቦታዎች ላይ ይተከላሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮ ሀብትን ማልማት እና መንከባከብ እንዲሁም በአግባቡ መጠቀም ከተፈጥሮ ጋር መታረቅ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያስችል በመጥቀስ፤ ሁሉም ዜጋ ችግኝ በመትከል ድርሻውን መወጣት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም