ለእሷ የገጠሩ ህይወት ሁሌም ቢሆን መልካም ነበር። እሸቱን ከጓሮ፣ ወተቱን ከጓዳ፣ ዳቦውን ከማጀት እንዳሻት ለማግኘት ከልካይ አልነበራትም። ወላጆቿ በግብርና የሚኖሩ አርሶበሌ ናቸው። በረከትን በታደለው ኑሯቸው ልጆች ወልደውና ስመው በሰላም አሳድገዋል።
ማንጠግቦሽም ሆነች ሌሎች ልጆች በሳር ጎጇቸው ተሰባስበው ፍቅርን ሲጋሩ ኖረዋል። ከነዚህ መሀል መማር የቻሉት ከተማ ውለው ይመለሳሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ከቀዬ መንደራቸው ሳይርቁ ከብቶችን ሲያግዱ ይውላሉ። ማንጠግቦሽ ህይወቷ በነዚህ መንገዶች መሀል ሲቃኝ ቆይቷል። ትምህርቱንም ቤት ተቀምጦ መዋሉንም ታውቃዋለች።
የነ ማንጠግቦሽ ቤተሰቦች ልክ እንደሌሎች ሁሉ በከተማ የሚኖሩ ዘመዶች አሏቸው። በአካባቢው ደግሞ ከተሜ ለሚባሉቱ ልዩ ግምት ይሰጣል። በተለይ የአዲስ አበባ ሰዎች ከሆኑ የግምቱ መጠን በእጥፍ ጨምሮ በላቀ አድናቆት ይወራላቸዋል። በእነሱ ዘንድ አዲስ አበቤዎች እንደስማቸው ሁሌም አዲስ እንደሆኑ ነው። መኖሪያቸው፣ ኑሯቸውና ማንነታቸው በተለየ ሥዕል ተቀርጿል።
በዚህ አካባቢ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ ብቅ የሚሉ ከተሜዎች ልብስና ንግግራቸው የተለየ ነው። ለስጦታ የሚያመጧቸው ዕቃዎችም በተቀባዮቻቸው ዘንድ እንደ ብርቅ ይታያሉ። አንዳንዴ ደግሞ ድንገት መጥተው ሰዎችን ይዘው ይሄዳሉ። ከሚሄዱት ውስጥ ልጆች ካሉበት ደግሞ ትርጉሙ የተለየ ነው። በዓመቱ ተመልሰው ሲመጡ በአካል አድገው፣ በዕውቀት ጎልብተውና አምሮባቸው ስለሚሆን ሌሎችን ለማጓጓት ጭምር ምክንያት ይሆናል።
ማንጠግቦሽ ባሳለፈችው ዕድሜ እንዲህ አይነቱን እውነት ስታየው ኖራለች። ብዙ የምታውቃቸው እኩዮችዋ ከዘመዶቻቸው ሄደው ተለውጠው መምጣታቸውን አትረሳም። እሷም ብትሆን እንደእነሱ ከተማ ገብታ በከተመኛ ብታወራ አትጠላም። የተሻለ ለብሳና ተጫውታም «ዘመናዊ» ብትባል ደስታዋ ነው። እንደ ብዙዎቹም ተምራና ተመርቃ ስሟ ገናና ቢሆን ትወዳለች።
የልጅነት አዕምሮዋ ከተማን እንዳሰበ የሚውለው ታዳጊ የሚሄዱትን እየሸኘች፣ ተመልሰው የሚመጡትንም በአድናቆት እያስተዋለች ዓመታትን ቆጠረች። ማንጠግቦሽ ወላጆችዋን ብትወድም ከተማ ዘልቆ መኖርን በእጅጉ ተመኘች። በትምህርቷ በርትታና፣ በእውቀት ደረጃዋ ልቃም ታናናሾችዋን ስታስከትል እየታያት ውስጧን አበረታች። ማንጠግቦሽ እያደር ከተማ የመኖር ፍላጎቷ ጨመረ።
አንድ ቀን ረፋዱን አንዲት የከተሜ እንግዳ ወደነ ማንጠግቦሽ ጎጆ ብቅ አለች። ሰላምታዋን አስቀድማ እግሯ ከመግባቱም መምጣቷን ያዩ ቤተሰቦች «ቤት ለእንግዳ» ሲሉ በፈገግታ ተቀበሏት። ህጻናት ልጆቻቸው ደግሞ መድረሷን እንዳዩ በደስታ እየዘለሉ ተጠመጠሙባት። የያዘችውን ተቀብለው ወደውስጥ እንደዘለቀች ቤቱ በተለየ ደባብ ተዋጠ።
ወደገጠር የዘለቀችው ድንገቴዋ እንግዳ አዲስ አበባ የምትኖረው የነማንጠግቦሽ አክስት ነበረች። የእሷ ድንገት መምጣት በተለይም ለልጆቹ የተለየ ደስታን ፈጥሮ አመሸ። የገዛችላቸውን ልብሶችና ሌሎች ስጦታዎችን እንዳዩም ጊዜው ለእነሱ የተለየ ሆኖ ቆየ ።
ውሎ ሲያድር የቤተሰብ ጨዋታው ቀስ እያለ ደራ። ለጥቂት ቀናት የመጣችው እንግዳ ተመልሳ ከመሄዷ በፊትም ለዘመዶችዋ አንድ ጥያቄ አቀረበች። ከልጆቹ መሀል ማንጠግቦሽን አዲስ አበባ ወስዳ ብታስተምርና ብታሳድጋት እንደምትወድ ገልጻም ፈቃዳቸውን ጠየቀች።
ማንጠግቦሽ ይህን ስትሰማ ልቧ ለመሄድ ተነሳ። ከልጅነቷ ጀምሮ የምትመኘውን የከተማ ኑሮና የምትጓጓለትን የትምህርት ጉዳይ ልታሳካው መሆኑን አስባም አስቀድማ ተስማማች። ወላጆችዋ ከመንገዷ ሊያስቀሯት አልተቻላቸውም። የምትሄደው ከአክስቷ ቤት መሆኑ ደግሞ ሀሳባቸውን እንዲጥሉ አድርጓቸዋል።
ከቀናት በአንዱ ቀን እንግዳዋ ማንጠግቦሽን አስከትላ አዲስ አበባ ገባች። ታዳጊዋም አገሯን ጎንደርን በትዝታ እያሰበች ቀዬዋን ተሰናብታ የከተሜን ህይወት ጀመረች። ውሎ አድሮ ልብሷን ቀይራ አካባቢውን መምሰል የያዘችው ታዳጊ ቤተሰቦችዋን እንደናፈቀች ወራትን ቆጠረች።
ለማንጠግቦሽ የአክስቷ ቤትና ህይወት አስቀድማ እንደሳለችው ሆኖ አልተገኘም። እሷ በፈለገችው ጊዜ ትምህርት ቤት ገብታ መማር ያለመቻሏ ደግሞ ሁሌም እያሳሰበ ያስከፋት ጀምሯል። አዲስ አበባ ሰፊና ምርጫው ብዙ መሆኑን የምታውቀው ወጣት ካለችበት ወጥታ ወደ ሌላ ለመሄድ መካሪ የሚያሻት አልሆነም።
እሷን መሰሎች ሰው ቤት ተቀጥረው ገንዘብ ሲይዙና ኑሯቸውን ሲቀይሩ አይታለች። በየዓመቱ ሀገራቸው እየሄዱም ዘመዶቻቸውን ጠይቀው እንደሚመለሱ ታውቃለች። ሁኔታዎች ባሰበችው መንገድ ያልሄዱላት ማንጠግቦሽ ግን በድንገት ከአክስቷ ለመራቅ ወስና ከቤት ወጣች። በሰራተኝነት ተቀጥራ ለመስራትም በደመወዝ ተስማምታ ተቀጠረች።
አሁን አዲስ አበባና ማንጠግቦሽ ባዕዶች አይደሉም። ከተማው እሷን፣ እሷም ከተማውን በደንብ ለይተዋል። በዕድሜ እያደገችና በውበት እያማረች የመጣችው ወጣት ወር ጠብቃ በሚከፈላት ደመወዝ ራሷን ችላለች። የከተማውን መውጫና መግቢያ ማወቋም ከብዙዎች ጋር አግባብቷታል። አሁን በልጅነቷ እንደምታውቀው እውነት ወደ ገጠር ትዘልቃለች። ቤቶችዋን አይታ ለአገሬውም ታይታ ትመለሳለች።
ማንጠግቦሽ ውበቷ ጨምሮ ወጣትነትን ስትላበስም የብዙዎችን አይን መሳብ ችላለች። ይህ አይነቱ የኑሮና የአካል ለውጥ ደግሞ ገጠር ለምታውቃቸውና እሷንም ለሚያውቋት ሁሉ መልካም የሚባል ነው። እሷ ከተሜ መሆኗን ለማሳየት እነሱም መለወጧን አይተው ለማድነቅ ጥሩ አጋጣሚ ይሆንላታል። እሷም ብትሆን በአለባበስና በአነጋገሯ መለወጧን ታውቀዋለች።
ማንጠግቦሽ የልጅነት ህልምና ትውስታዋን በራሷ ላይ በማየቷ ደስተኛ ነች። ሰርቶ በማግኘት ራስን ማቆም እንደሚቻልም ገብቷታል። አሁንም ግን የሰው ቤት ስራዋ ለትምህርቷ መንገድ አልከፈተም። እስከዛሬ ተቀጥራ ከሰራችባቸው ቤቶች አብዛኞቹ እሷን ለማስተማር የፈቀዱ አልነበሩም። በዚሁ ሰበብም ስራውን ስትለቅና በብዙ አሰሪዎች ቤት ስትገባና ስትወጣ ቆይታለች።
ዓመታትን በሰው ቤት ስራተኝነት የገፋቸው ወጣት ጥቂት ቆይታ ከአንድ ውሳኔ ደረሰች። ከነበረችበት ስራ ለቃም በአንድ ሆቴል አስተናጋጅ ለመሆን ተቀጠረች። ይህ አይነቱ ለውጥ ለጊዜው ጥሩ ሆኖ አገኘችው። ጥቂት ቆይታ ግን ለቤት ኪራይና ለሌሎች ወጪዎችዋ ተጨማሪ ገቢ እንደሚያሻት ገባት። ለዚህም ቢሆን መፍትሄ አላጣችም። ከሁለት ጓደኞችዋ ጋር ቤት ተከራይታ በጋራ መኖር ጀመረች።
ማንጠግቦሽ የወጣትነት ዕድሜዋ ራሷን ከመቻሏ ጋር ተዳምሮ ነጻነት ሰጥቷታል። በየጊዜው ከአዲስ አበባ ጎንደር እየተመላለሰች ዘመዶችዋን መጠየቅም ልምድ አድርጋለች። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ከአንድ ወጣት ጋር አግባብቶ በፍቅር አላምዷታል። ፍቅረኛዋን ያገኘችው ወደ አገር ቤት ለመሄድ በጉዞ ላይ በነበረችበት አጋጣሚ ነበር።
በጨዋታ የጀመረው መግባባት ቀስ እያለ ወደ ፍቅር ሲለወጥ ሁለቱም አብሮ ለመሆን ፈቅደው ቆይተዋል። የወጣትነት ዕድሜያቸው ፍላጎታቸውን የፈጠነ ቢያደርገው ደግሞ ከጋብቻ የቀደመ ግንኙነትን ደጋግመዋል። ወጣቷ በህይወቷ ላይ ያከለችውን ለውጥ እያጣጠመችው ነው። ከፍቅር ጓደኛዋ ጋር የጀመረችው የፍቅር ግንኙነት እንደጅማሬው እንደሚዘልቅም እምነቷ ሆኗል።
ትናንት አልፎ ዛሬን መተካት ይዟል። የማንጠግቦሽ የአዲስ አበባ ኑሮና የህይወት ትግልም እንደነበረው ቀጥሏል። አሁን ከፍቅረኛዋ ጋር የነበራት የቀደመ ግንኙነት እየቀዘቀዘ መምጣቱን አውቃለች። ለዚህ ምልክቱ ደግሞ በየጊዜው ያለመገናኘታቸው እውነታ ሆኗል። እሷ ከዛሬ ነገ ሁኔታው በነበረው ይቀጥላል የሚል ሀሳብ ነበራት። በእሱ በኩል ግን ዳግም አብሮነቱን የሚፈልግ አይመስልም።
አንድ ቀን ማንጠግቦሽ ህመም ቢጤ ተሰማት። ይህ ችግር ደግሞ ከቀናት በፊትም አብሯት እንደነበር ታስታውሳለች። አለፍ እያለ ሲደጋግማት ግን ጤንነቷን ማረጋገጥ ፈልጋ ወደ አንድ ክሊኒክ ጎራ አለች። ሀኪሙ ከአንዳንድ ጥያቄዎች በኋላ ሙሉ ምርመራ እንድታደርግ በሚል ወደ ላብራቶሪ ላካት።
የታዘዘላትን ይዛ ወደሚመለከተው ያመራችው ታካሚ ከደቂቃዎች በኋላ የምርመራውን ውጤት ይዛ ተመለሰች። ወረቀቱን ለሀኪሟ አቀብላም የምትባለውን ጠበቀች። ሀኪሙ ውጤቱን ደጋግሞ ካስተዋለ በኋላ ፊቱ በፈገግታ እንደተሞላ እውነታውን ነገራት። የማንጠግቦሽ ምርመራ የሶስት ወራት ጽንስ በሆዷ መኖሩን አመላካች ሆኗል።
አስደንጋጭና ድንገተኛ የሚባል ምላሽ ለጆሮዋ የደረሰው ወጣት የሰማችውን እውነት እንደመርዶ ተቀብላ ከክሊኒኩ ወጣች። ይህ ለእሷ ክፉ የሚባል አጋጣሚ ነው። በህይወቷ መንገድም ያጋጥመኛል ብላ አሰባው አታውቅም። የሆነውን ሁሉ በድንገት የሰማችው ወጣት በለቅሶና በትካዜ ቀናትን ቆጠረች። ሚስጥሯን ለራሷ ብቻ አድርጋም ለመፍትሄው ተሯሯጠች።
የጊዜው መጨመርና የጽንሱ መግፋት ያሰበችውን ለማድረግ እድል አልሰጣትም። ለመፍትሄውና ጉዳዩን ለማዋየት ደጋግማ የደወለችለት ፍቅረኛዋም ሊያገኛት እንደማይፈልግ ተረድታለች። የስራዋ እረፍት የለሽነትና የሁኔታዎች አለመቅናት ቢያስጨንቃትም ላጋጠማት እርግዝና መፍትሄ ለማግኘት የቻለችውን ሁሉ ሞክራለች። ሙከራዋ ግን ቀን ከመጨመር የዘለለ ስኬት አልነበረውም።
አሁን ማንጠግቦሽ ከማትፈልገውና ካልጠበቀችው የህይወት መስመር ላይ ቆማለች። በድንገት የልጅ እናት እንደምትሆን ሲገባት ደግሞ ትካዜዋ ብስጭትን አክሎ መድረሻ ያሳጣታል። ብቸኝነቷ፣ ሚስጥር ጠባቂነቷና ዝምተኝነቷም ሳታስበው ባይተዋር እያደረጋት ነው። እንደ ፍላጎቷ ቢሆን እንደ ወግና ባህሉ ተድራና ተኩላ ብትወጣ ትመርጥ ነበር። አሁን ግን ይህ ምኞት ጉም እንደ መዝገን ከንቱ ሆኖባታል።
ሆዷ እየገፋ እርግዝናዋ እየጨመረ ሲሄድ የመውለጃ ጊዜዋ መድረሱ ገበቷታል። አሁን ባለችበት እውነት ግን እሷን የሚያርስ ወገንና ለልጇ አባት ሆኖ የሚቆም አባወራ ከጎኗ የለም። ይህን ደጋግማ ስታስብ ደግሞ ንዴትና ብስጭት፣ እልህና ፀፀት እየተፈራረቁ ያስጨንቋታል።
ጥቅምት 15 ቀን 2003 ዓ.ም
ገና ከማለዳው ህመምና ቁርጠት ሲሰማት አርፍዷል።ያዝ ለቀቅ እያደረገ ሲያንገላታት የቆየው ስሜት ለእሷ አዲስ ቢሆንም ምጥ እንደሆነ አውቀዋለች። ጊዜው ገፍቶ ምጡ ሳይፋፋም ወደ ህክምና መድረስ አለባት። እሷን ደግፎና አጅቦ ለሀኪም የሚያደርሳት የቅርብ ሰው የለም። እርግዝናዋን በሚስጥር መያዟና ሆዷ በጥርጣሬ አለመታየቱ እስከዛሬ ያለ ጥያቄ እንድትራመድ ረድቷታል።
ማንጠግቦሽ አሁንም ብቻዋን መሄድ እንዳለባት ወስናለች። ለዘጠኝ ወራት የያዘችውን ሚስጥር ለማንም መንገር እንደማይኖርባት ካሰበችበት ቆይታለች። በጤና ጣቢያው ደርሳ ካርድ ስታወጣና ወደ ማዋለጃ ክፍሉ ስትሄድ ማንም ከጎኗ አልነበረም። የቅርብ ተጠሪና አጋር እንደሌላት ያወቁት የጤና ባለሙያዎች በተለየ ቅርበትና ሀዘኔታ ወላዷን እየተንከባከቧት ነው።
የምጡ ስቃይ ቀላል አልነበረም። ያለፈችበትን ጭንቀትና የቆየችበትን ህመም ለሌሎች ማስረዳት በእጅጉ ይከብዳል። እናት ለመሆን ደግሞ ይህን ፈታኝ የምጥ ሰዓት በትግል ማለፍ የግድ ይላል።ይህ ጊዜ በህይወትና ሞት መሃል ሆኖ በእጅጉ የሚፈተኑበት ነው። ራስን ለመተካት ወልዶ፣ ለመሳም መንገዱ አጭርና ቀላል አይደለም። ማንጠግቦሽ በዚህ ሁሉ አስጨናቂ የስቃይ ስሜት ውስጥ አልፋ በሰላም ተገላገለች። ከደቂቃዎች በኋላም አዋላጆቹ ወንድ ልጅ መውለዷን በማብሰር ህጻኑን አምጥተው አስታቀፏት።
አሁን ወላዷ ከምጥ ስቃይዋ አርፋ ልጇን ታቅፋለች። መውለዷን ያወቁ አንዳንዶችም «እንኳን ደስ አለሽ» እያሏት ነው። ሚጢጢው እንግዳ ከእናቱ ደረት አርፎ በአፉ ጡቶቿን ይፈልጋል።ትንንሽ እጆቹ፣ለስላሳው አካሉና ድፍት ያለው ፀጉሩ ማራኪ ነው።በወጉ የማይሰማው ድምጹ የለቅሶ ቅላጼ አለው።
ማንጠግቦሽ አልጋ ይዛ ጥቂት እንዳረፈች ከጤና ጣቢያው ልትወጣ ግድ አለ ።ይህ ይሆን ዘንድም የልጇና የአራሷ ጤንነት መልካም መሆኑ ተረጋግጧል። ነርሶች ይህን እውነት በነገሯት ጊዜ ግን ወላዷ አይኖችዋ በዕንባ ተሞሉ። ዛሬ ለመውጣት አቅም እንዳጣችና አብሯት የሚቆይ ዘመድ ወዳጅ እንደሌላት ስትነግራቸው በሀዘኔታ እንድታድር ፈቀዱላት።
የምሽት ተረኞች ስለሷ ሰምተው ተጨነቁ። ወገን እንደሌላት ተረድተውም የምትጠጣውን አጥሚትና የምትመገበውን ምግብ አሰርተው አመጡላት። ጉዳዩን የሰሙ አንዳንዶችም የአቅማቸውን በማድረግ «እንኳን ማርያም ማረችሽ» ሲሉ ካለችበት ደርሰው ጎበኟት። ነገ በኔን የተረዱ ብዙዎችም ቀረብ እያሉ የአቅማቸውን ረዷት።
ይሁንታውን ያገኘችው አራስ በተዘጋጀላት የማደሪያ ክፍል አረፍ አለች። እፎይታ ተሰምቷትም ልጇን እያጠባች ጥቂት አሸለበች። በእንቅልፏ መሀል ግን ስለህይወቷ ታስባለች። መጪውን እድሏን፣የወደፊት ዕቅድና ዓላማዋን እየሳለችም አብዝታ ትጨነቃለች። የዘጠኝ ወራት ሚስጥሯን ተገላግላለች። ከዚህ በኋላ የሚሆነውን አታውቅም።
ሌሊት አስር ሰአት ከሰላሳ
ድንገት ከእንቅልፏ የባነነችው ማንጠግቦሽ ወደ መጸዳጃ መሄድ ፈልጋለች። ውሎዋን በምጥ ስቃይ ብታልፍም አሁን ላይ ሰውነቷ እየበረታ ነው። እንደምንም ተነስታ መንገድ የጀመረችው እናት መውጫው ላይ ስትደርስ ልጇን መለስ ብላ አየችው። ህጻኑ አይኖቹን ገጥሞ እንደተኛ ነው። ያረፈችበት ክፍል ብቸኛ በመሆኑ ለማንም ልጇን «አደራ» ማለት አላስፈለጋትም።
ያሰበችበት ደርሳ እንደተመለሰች ህጻኑን ዳግም አስተዋለችው። በጨርቅ ተጠቅልሎ ተኝቷል። ጨቅላነቱ ያሳዝናል። በእጅ ለመንካት ያሳሳል። በሙሉ አይን ለማየት ያጓጓል። አሁን ልጁ እያለቀሰ አይደለም። እንዲህ መሆኑ ለእናቲቱ የተመቻት ይመስላል። ከቆመችበት አለፍ ብላ ወደተኛበት አልጋ አመራች። በዕንቅልፍ መሸነፉን አስተውላም ዙሪያ ገባውን ቃኘች። በአእምሮዋ ብዙ ሀሳብ ተመላለሰ። ትሯሱን አንስታ ቀረበችው። እጆቿን በትንሽዬው ፊቱ ላይ አጥብቃ አሳረፈች። ጥቂትም ጠበቀችው።
አሁን መንጋቱን ለማብሰር ወፎች መንጫጫት ጀምረዋል። ከቆይታዎች በኋላ ትላንት የወጡት ባለሙያዎች ተራውን ከምሽቱ አዳሪዎች ይረከባሉ። በዚህ ሰዓት ደግሞ ህሙማንን በመጎብኘት አዳራቸውን መጠየቅ ልምድ አድርገዋል።
ከነበሩት ነርሶች መሀል አንደኛዋ ወላዷን አስታውሳ ወደተኛችበት ክፍል አመራች። እግሯ በስፍራው እንደደረሰ የሰማችው ወሬ ግን በእጅጉ አስደነገጣት። ትናንት ጤንነቱን አረጋግጣ ደህንነቱን የመሰከረችለት ህጻን በድንገት መሞቱን አምና መቀበል አልቻለችም። ይህ ጥርጣሬዋም ህጻኑን ለምርመራ አድርሶ በፖሊስ ማስረጃዎች እንዲመረመርና በህክምና እንዲታይ አፋጥኗል።
የፖሊስ ምርመራ
ከጤና ጣቢያው መረጃ የደረሰው ፖሊስ በስፍራው ተገኝቶ የህጻኑን አስከሬን ተረከበ። በወቅቱ ሟቹ ህጻን ፊትና ደረቱ ጠቁሮና በእጅጉ በልዞ ነበር። ሁኔታው ከጥርጣሬ ያደረሰው ፖሊስ አግባብ ባለው አካል አስመርምሮ ድርጊቱ በሰው እጅi መፈጸሙን አረጋገጠ። የህጻኑን እናት በህግ ጥላ ስር አውሎም በተገቢው ጥያቄ ቃሏን ተቀበለ። ማንጠግቦሽ በፍቅረኛዋ መካዷና ህጻኑን ለማሳደግ አቅም ማጣቷ የወለደችውን አፍና ለመግደል እንዳነሳሳት ተናገረች።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ኔ 22/2011
መልካምሥራ አፈወርቅ