የተወለደው ክብረ መንግስት ሲሆን ያደገው አርሲ ነገሌ ነው። አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው እዛው አርሲ ነገሌ ነው። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በአካውንቲንግ ኤንድ ፋይናንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ተምሯል።
በአድቬንቲስት ኮሌጅ፥ ኩየራ አፍሪካ ቤዛ፥ ሪፍት ባሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመምህርነት ያገለገለባቸው ተቋማት ናቸው። ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የሆነው የዛሬው የዘመን እንግዳችን በፕሮቴስታንት ቤተ እምነት ውስጥ በመልካም ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ ወጣት አገልጋይ ዋነኛው ነው።
በተለይም ደግሞ መልካም ወጣት በሚል ስያሜ ከአገሪቱ የተለየዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ ወጣቶችን በትክክለኛ መንገድ በማነፅና በማሰልጠን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ አንቱታን አሰጥቶታል።
በቅርቡ ደግሞ በተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ አነቃቂ ንግግሮችን በማድረግ እውቅናውን ከቤተዕምነቱ አልፎ አገር አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በር ከፍቶለታል። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርበዋለን።
አዲስ ዘመን፡- በመጀመሪያ ምንም እንኳን የሃይማኖት መሪ እንደመሆንህ አንቱ መባል ቢገባህም ወጣት በመሆን አንተ እያልኩ ውይይታችንን እንድንቀጥል ፍቀድልኝ?
አገልጋይ ዮናታን፡- በደስታ!
አዲስ ዘመን፡- በተማርክበት የአካውንቲንግ የሙያ ዘርፍ ለምን አልቀጠልክም?
አገልጋይ ዮናታን፡- እያንዳንዱ ሰው ወደ እዚህ አለም ሲመጣ የተፈጠረበት ዓላማ አለው ብዬ አምናለሁ። ከዛ አንፃር ይመስለኛል አሁን ያለሁበት አገልግሎት የተጠራሁበት እውነት ነው በሚል አስተሳሰብ የተማርኩበትን ሙያ ወደ ጉን ለመተው የወደድኩት። የልጅነቴ መሻት የነበረውም አስተማሪ መሆን ፤ አገር መምራት ፥ ትውልድን ለመልካም ነገር መቀስቀስ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- እናም አሁን የልጅነት መሻትህ ከስኬት ደርሷል ትላለህ?
አገልጋይ ዮናታን፡– በደንብ! መቼም አሁን ያለሁበት ነገር መጨረሻ ነው ባልልም እግዚአብሄር ብዙ እየረዳኝ እንደተሳካልኝ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች ዮናታን በአገሩ ጉዳይ ላይ ወግ አጥባቂ የሚባል ሰው ነው ይሉሃል፤ እውነት ነው?
አገልጋይ ዮናታን፡- በትክክል፤ አገሬን እወዳለሁ፤ ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ብዙ ትርጉም አለው። እኛ የራሳችንን ነገር ብዙ አናደንቅም፤ አንወድም እንጂ በጣም የሚደንቁ እሴቶች ያሉን ማህበረሰቦች ነን።
ይህንን የምለው ለማለት ብቻ አይደለም። ዛሬ የሰለጠኑ የሚባሉት አገሮች የተቸገሩበት ነገር እኛ ጋር ከስልጣኔ በፊት የነበረ ነው። ደግሞም እኔ በኢትዮጵያዊነት ድርና ማግ ውስጥ ያደግሁት በመሆኔ ነው መልዕክቶቼና ትምህርቶቼም ውስጥ አገሬ ኢትዮጵያ የአገሬ ልጆች የሚል ነገር የማይጠፋው።
አዲስ ዘመን፡- ሌሎች የመንፈሳዊ ትምህርት አገልጋዮች ስለአገር ጉዳይ መናገርና መስበክ ፖለቲከኛ እንደመሆን ይቆጥሩታል፤ አንተ ግን ከዚያ አስተሳሰብ ወጥተህ እንድታስብና እንድትናገር መሰረት የጣለልህ ምንድን ነው?
አገልጋይ ዮናታን፡- ጥሩ ጥያቄ ነው የጠየቅሽኝ፤ አንዳንዴ ሰዎች ሃይማኖተኛ አይደለህም ወይ? ለምንድን ነው ስለፖለቲካ፥ ስለአገር የምታወራው ይሉኛል። እኔ ሃይማኖተኛ ብሆንም የቀበሌ መታወቂያ ረስተዋል። እኔ የቀበሌ መታወቂያ ያለኝ፤ ኢትዮጵያዊ የሆንኩ፥ ልጅና ትዳር ያለኝ ሰው ነኝ።
ስለዚህ በእኩልነት፥ በሰብአዊነት፥ በፍትህ፥ በሰላም፥ ተቻችሎና ተከባብሮ፥ መልካም እሴትን አስቀጥሎ በመኖር ውስጥ «አንተ ዝም በልና እኛ እንወስንልህ፤ እኛ ብቻ እናውራልህ» ማለት በዚህ ዘመን የማይጠበቅ የማንነት ክስረት ነው ብዬ ነው የማምነው። ስለዚህ እኔ የሃይማት ሰው ብሆንም ግን የቀበሌ
መታወቂያ አለኝ። ከዚህ አንፃር ያደግሁበት ቤተሰብ እየነገረኝ ያደግሁት ሌላውን ስለመውደድ፥ ስለኢትዮጵያ ትልቅነት፥ አገር ማለት የኛ ሰፈር ብቻ ሳይሆን እጅግ ትልቅ እንደሆነ ነው። የሚገርምሽ የኢትዮጵያ ሰራዊት በጄነራል ፊት ሰላምታ እየሰጠ እንደሚያልፍ ትልቅ ትንሽ ሊቅ ደቂቅ ፥ ባለስልጣን ሃብታም እያሳለፈች ሳታልፍ የኖረች አገር ነች።
ኢትዮጵያን በጥሩ ሁኔታ ቤተሰቦቼ በእኔ አምዕሮ ስለዋታል፤ ፈጥረዋታል ብዬ አስባለሁ። በነገራችን ላይ አይሁዳዊ እኮ አገር አለው!። አገሩን በጣም ነው የሚወደው። ክርስቶስም ሲመጣ ለአይሁዶች አይደል? እንግዲህ ክርስቶስ አይሁዳዊ ሆኖ መጥቶ አገር ካለው ኢትዮጵያዊ እንዴት አገር አይኖረውም?።
እንዴት መንፈሳዊ ብቻ ይሆናል?። ደግሞም እኩልነት፥ ሰላም፥ አንድነት፥ ፍቅር በዋነኛነት ማስተማር ያለብን በሃይማኖት ውስጥ ያለን ሰዎች ነን። ምክንያቱም ሞራል በአብዛኛው የሚቀዳው ከሃይማኖት በመሆኑ ነው። በጥቅሉ ግን ለእኔ አሁን ላለሁበት ሁኔታ መሰረት የጣለልኝ ያደግሁበት ማህበረሰብ ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች አንተን ሲገልፁህ ልክ እንደ ሰይፍ በሁሉ በኩል የተሳለ አእምሮ ያለው ሰው ነው ይሉሃል። አንተ ነኝ ትላለህ?
አገልጋይ ዮናታን፡- በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክ ስጦታ ነው ብዬ ነው የማስበው። እኔ በዚያን ያህል መጠን ጥሩ ነገር አለኝ ብዬ አልልም። ምክንያቱም ትንሽ ነገር ይዤ ነው የምፍጨረጨረው። ከዚያ በተረፈ ግን አነባለሁ። በአብዛኛው በኢትዮጵያውያን የተፃፉ መፃሃፍቶችን ነው የማነበው። በዋናነት ግን ኢትዮጵያዊና የሃበሻ አፈር ሽታ ያላቸውን መፅሃፍ ነው የምመርጠው።
በነገራችን ላይ ህይወት ሁለንተናዊ ነች። ህይወት ልብስ ብቻ አይደለችም። ብር ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ትበያለሽ እንጂ እየበላሽ አትውይም። ምግብ የቱንም ያህል አስፈላጊ ቢሆን አትውይበትም። ማንኛውም ሰው በሁለንተናዊ አቅጣጫ ማደግ አለበት ብዬ ነው የማምነው።
ለምሳሌ አሁን ያለው ትውልድ ችግሩ አላማና ራዕይ ማጣት እንጂ ገንዘብ ማጣት አይደለም። ጥበብ የሚባለው «ክሪቲካል ቲንኪንግ» ነው። መንፈሳዊነትንም ነው የሚያሳየው። ስለዚህ የመልዕክቶቼ ይዘት ሁሉንም የሚዳስሱበት ምክንያት አንድ ሰው ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ማደግ አለበት ብዬ ስለማምን ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንተ የምታያቸውን አገራዊ ህፀፆች ደፍረህ በመንቀስና በመናገር ትታወቃለህ፤ በተለይ ደግሞ በቢራ ማስታወቂያ ላይ የሚዲያ ተቋማት የሚያደርጉትን ጥንቃቄ በሚመለከት ደፍረህ ማሳሰቢያ መሰል ደብዳቤ እስከመላክ የደረስክበት አጋጣሚ አለ። ምን አይነት ምላሽ አገኘህ?
አገልጋይ ዮናታን፡- እኔ አገሬን ይጠቅማል፤ ትውልዱን ይጠቅማል ብዬ በማምነው ነገር ሁሉ ወደ ኋላ አልልም። በቅርቡ ለምሳሌ ኳስ ሜዳዎቻችን የብሄር ሜዳ ከመሆን ይከልከሉልን ብዬ ፅፌያለሁ። በነገራችን ላይ ጎል የሚያገባ ብሄር የለም፤ የሚያገባ አገር እንጂ።
በቢራ ላይ ለመፃፍ ያነሳሰኝ የአንድ ጓደኛዬ የአራት ዓመት ህፃን ልጅ ነው። ይህ ልጅ አንድ ቀን አባቱን « አባባ ቢራ ይጠጣል እንዴ?» ብሎ ጠየቀው። አባትም « አይጠጣም» አለው። ልጁም ቀጠል አደረገና «እኔ ግን ሽልማት ስላለው እጠጣለሁ» አለው። ስለዚህ አንድ የአራት አመት ልጅ ሽልማት አለው ብሎ ካመነ ሌላው ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ተፅእኖ ሳስብ ደነገጥኩ።
ስለዚህ ቴሌቪዥን ምን እየሰራ ነው የሚል ጥያቄ ራሴን ጠየቅኩ። እግዚአብሄር ይስጣቸውና እነሱም በፃፍኩት ደብዳቤ መሰረት ቶሎ ብለው ወደ ተግባር ገብተዋል። ይህም ለእኔ ተስፋ ሰጪ ነው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያዊ ይቆያል እንጂ ነገር ይረዳል። ቢራ ለአገር ከሚጠቅመው ይልቅ የሚያመጣውን ጉዳት ማሰቡ በራሱ በቂ ነው። ከዚያ አንፃር የመለሱት ምላሽ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን፡- አክቲቪስቶች ላይም የሰላ ትችት ስትሰነዝር ትደመጣለህ። ይህ አቋምህ ከምን የመነጨ ነው?
አገልጋይ ዮናታን፡- አክቲቪስቶች ላይ ያለኝ አመለካከት ሁሉም መጥፎ ናቸው የሚል አይደለም። ምክንያቱም ጨዋና አገራቸውን የሚወዱ፤ ሃሳባቸውን በጨዋነት የሚገልጡ፤ ዋጋ የከፈሉ በመኖራቸው ነው። የዚያኑ ያህል ደግሞ የጥላቻና የጥፋት ተልዕኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አክቲቪስቶች አሉ።
በእኛ አገር ፖለቲካ ሃሳብ ፖሊሲ መሆኑ ቀርቶ ዘር ሆኗል። አንድ ነገር ትክክል ነው ለማለት ሃሳቡ ሳይሆን የሚመረመረው ሰውየው ዘሩ ከማነው የሚለው ሆኗል። ሃሳቡ ይመጥናል፤ አይመጥንም አይደለም የሚባለው። ስለዚህ የከረረውንና ዘር ላይ መሰረት ያደረገውን የፖለቲካ አመለካከት የጥላቻ የመከፋፈል ሀሳብ የሚያራምዱ ፖለቲከኞች አሉ። የእኔን ቤት ለመገንባት ያንቺን ቤት ማፍረስ፥ የእኔን ክብር ላንቺ ውርደት መግዛት መፈለግ መንፍሳዊነትም፥እውቀትና ስልጣኔም አይደለም።
ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አክቲቪስቶች ከተወሰኑት በስተቀር አብዛኞቹ ስራ ቢፈለግላቸውና ከስደተኞች በላይ እነሱን ቢያቋቁማቸው ጥሩ ነው ባይ ነኝ። እኔ እንዳውም ማይክሮ ዌቭ አይክቲቪስት ናቸው ብዬ አስባለሁ። ማይክሮ ዌቭ አገልግሎቱ የቀዘቀዘ አሙቆ ማቅረብ ነው። በየትኛውም ዘመን የትኛውም የአገር መሪ የራሱ ደካማ ጠንካራ ጎን አለው።
ኢትዮጵያ በባለፉት 27 ዓመታት ኢህአዴግ በመራበት ዘመን መልካም ስራ አልተሰራም ማለት አይደለም። መንገድ፥ ትምህርት ቤትና ሌሎችንም መሰረተ ልማቶች ተሰርቷል። ሀገር ላይ ግን አልተሰራም። በእልህ ተከራካሪ ትውልድ እንጂ በልቡ የተሸነፈ፤ የሌላውን ሃሳብ የሚያዳምጥ ዜጋ ላይ አልተሰራም። ግድቡን ከመገደባቸው በፊት ይህንን የጥላቻ ማዕበል ነበር መገደብ የነበረባቸው። ባልተሰራ ጭንቅላት የተሰራ ቤት ይፈርሳል።
ዛሬ በነጮቹ አገር ብሄርተኛ የሚለው ሃሳብ ፅዩፍና የተጠላ ነው። ፈረንጆቹ 60ዓመታት በፊት የናቁትና የጣሉትን የብሄርተኝነት ሃሳብ ነው እኛ እንደ ስልጣኔ የምናራግበው። ከዚህ አንፃር እኛ ጋር ያለው ነገር ወቅቱን የጠበቀ አይደለም። ልክ ነው በምኒሊክ ዘመን የተሰራ ስህተት ሊኖር ይችላል። ደግሞ የሰሩት ደግነትም አለ። መንግስቱ ሃይለማርያም መሃይምነትን በማስወገድ ለሃገሬ ያደረገውን አስተዋፅኦ ለምንድን ነው የሚካደው?።
እኔ አንድ ነገር ልነግርሽ እፈልጋለሁ። ዘረኝነት ትናንት የተበሉትን የፖለቲካ ካርታ ዛሬ የወጣቶችን ህይወት አስይዘው የሚጫወቱ የከሰሩ የፖለቲካ ቁማርተኞች ጫወታ ነው። እኔ የምረዳው ይመኙት የነበረውን በተለይ በ1960ዎቹ የነበሩ፥ ዩኒቨርሲቲ ቀምሰናል፥ የነ ሶቅራጥስን መፅሃፍ አንብበናል፤ የእነ እስታሊንን ትምህርት ተምረናል፤ ብለው የነበሩ በታሪክ አጋጣሚ በጓድ መንግስቱ ሃይለማርያም ምክንያት ስልጣኑ ያመለጣቸው እና ሲቆጩ የኖሩ ሰዎች አሉ።
በመሰረቱ ኢህአዴግ ለዚህ ሁሉ ውዥንብርና ውድቀት ምክንያት የሆነው ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? ራሱን የሚያነፃፅረው የዛሬ 40 እና 50 ዓመት ከነበሩትና ከቆሙት ሃይለስላሴ ጋር ነው። የዛሬ 27 ዓመታት ከቆመው ደርግ ጋር ነው። ሲጀምር ራሱ የዛሬ 27 ዓመታት ዩኒቨርሲቲ ሶስት ነበር ብሎ ነው የሚጀምረው።
ከቆመ መንግስት ጋር እንዴት ራስሽን ታወዳድሪያለሽ?። ለምን ከኬኒያና ከደቡብ አፍሪካ መንግስት ጋር ራሳቸውን አያወዳድሩም?። ሩዋንዳ ሆነው ለምን ራሳቸውን አይገመግሙም?። ስለዚህ ሰው ሲሸነፍ ወደ ጎንና ወደፊት ማየቱን አቁሞ ወደ ኋላ ይሄዳል።
የተሸነፉና የከሰሩ አክቲቪስቶች ሁሌ የሚያጣቅሱት ከትናንት ነው። ከዚህ አንፃር ሁሉም ማለት ባይቻልም ለእኩልነት ለፍትህ ለነፃነት የታገሉ እጅግ በጣም የማከብራቸው አክቲቪስቶች አሉ። የዚያኑ ያህል ደግሞ በስመ አክቲቪስትነት የተሰገሰጉና አገር በማፍረስ እራሳቸውን ያደራጁ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች በአጭር አማርኛ ምን ብለህ ትገልጣቸዋለህ ካልሽኝ ትናንት የተበሉትን ካርታ ዛሬ የእናቶችን ጉልበትና የእናቶችን አንጀት አስይዘው ለማስመለስ የሚጫወቱ፥ የከሸፉ ፖለቲካ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ቤተዕምነቶች የመብዛታቸውን ያህል ወጣቱን ሰብስበው መያዝ ያልቻሉበት ምክንያት ምንድን ነው?
አገልጋይ ዮናታን፡- እውነት ለመናገር የቤተክርስቲያን መብዛት ከበዛው ሺሻ ቤት፥ ከበዛው ጫት ቤት አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ስታንዳርድ የሚጠየቅባቸው ብዙ ፈቃዶች አሉ። ስታንዳርድ የማይጠየቅባቸው ነገሮች ቢኖሩ ጫት ቤትና ሺሻ ቤት ናቸው።
ስለዚህ እኔ ከህዝብ ቁጥራችን አንፃር ቤተ እምነቶች በዝተዋል ብዬ አላስብም። ብዛት እድገት ነው ወይ? ብለሽ ከጠየቅሽኝ መልሴ እንደሁኔታው ይወሰናል የሚል ይሆናል። ግን ጥራት ወሳኝ ነው፤ ከሚል መነሻ የሚፈለግባቸውን አገልግሎት ወጣቶች ላይ አልሰሩም። የሚገርምሽ ከእኛ በላይ በወጣቱ ላይ ብዙ ዋጋ የከፈሉና የደከሙ በወጣት ላይ የሚሰሩ የሚዲያ ሽፋን አላገኙም። እሱን ሳልናገር ማለፍ አልፈልግም።
በሌላ በኩል ግን ይህንን ጉዳይ ጉዳያቸው አድርገው የሚሰሩ ተቋማት መጠን የብዛታቸውን ያህል አይደሉም በሚለው ሃሳብ እስማማለሁ። ዋናው የሚታየኝ ችግር ግን አገልግሎቱ ከአዳራሽ መውጣት እና ተደራሽ መሆን አለመቻሉ ነው። በእርግጥ በተለያዩ ምክንያቶች ቤተክርስቲያናት ሊከፈቱ ይችላሉ።
የእኛ አገር ሴቶች «እህል ከሆነ ይጠፋል፤ ልጅ ከሆነ ይገፋል» እንደሚሉት ሁሉ እኔ የቤተክርስቲያናት መብዛት አያሳስበኝም። ሁኔታዎችና ፖሊሲው ባይመቸውም እውነተኛ ለትውልድ የተከፈለ ሸክምና ራዕይ ከሆነ አመታትን ያቋርጣል፤ ። ለእንጀራ ብቻ የተከፈተ ከሆነ ግን በምቹ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳን ሊጠፋ ይችላል። ስለዚህ እንደዚህ ቢታሰብ ጥሩ ነው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በፕሮቴስታንት እምነት ስር ያሉ የሚዲያ ተቋማት የግለሰቦችን መልካም ፍቃድ ሳያገኙ የሰዎችን ስነልቦና የሚጎዳ ዝግጅት እንደሚያቀርቡ ይነገራል። አንተም ሚዲያ ካላቸው የዕምነቱ መሪዎች አንዱ እንደመሆንህ ከሱስ ለሚላቀቁት ወጣቶች ስነልቦና ምን ያህል ጥንቃቄ ታደርጋለህ?
አገልጋይ ዮናታን፡- እንደምታውቂው ከጥቂት አመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ሚዲያ እንደ መንግስት አንድ ሚዲያ ነበር። በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥ የተጀመሩት ሚዲያዎች ሚዲያን የሚመጥን ቁመና አስተሳሰብ ልምድና እውቀት ሳይኖረን ድንገት በእንቅስቃሴዎች ብዛት ነው እጃችን የገባው።
ጋሪው ከፈረሱ እንደሚባለው አይነት የኤዲቶሪያል ፖሊሲ ሳናዘጋጅ ነው ዘርፉን የተቀላቀልነው። እነዚህ ነገሮች አሁን ሰከን እያሉ ነው። ብዙዎቹ ራሳቸውን ወደ ማየት እየሄዱ ነው። እንዳልሽው ግን ድንገት ሲገባ እውቀትና ልምድ ሳይኖር ሲቀር ክፍተቶች መፈጠራቸው አይቀርም።
እኛን በተመለከተ እንዳውም ብዙዎችን ወደ ሚዲያ ለጆሮ በሚመች ሁኔታ እየመጠንን እና ወላጆችን ሊያነቃ በሚችል መልኩ ነው ለማቅረብ የምንሞክረው። ይህም የሚሆነው እነሱ ራሳቸው ሲፈለጉ ብቻ ነው። እንዳውም አንዳንዶቹ አይሆንም ስንላቸው «እኔ 600 ልጅ ይሆናል ያበላሸሁት የኔ ሚዲያ ላይ መውጣት እነዚያን ሰዎች ነው የሚመልሰው » ብለው ይሟገቱናል።
ስለዚህ በፕሮቴስታን ሚዲያዎች አካባቢ ያሉ ውዥንብሮች አይቀጥሉም። የማይቀጥሉት ደግሞ ከህግም አግባብ፤ ከልምድም አንፃር እየተማሩ ይሄዳሉ። ለዚህ ደግሞ አብነት የሚሆኑን በ1950ዎቹ በአሜሪካ ከ60 በላይ የፕሮቴስታንት እምነት ሚዲያዎች ተከፍተው የነበረ ቢሆንም አመታት የተሻገሩት ሶስት ብቻ ናቸው።
ስለዚህ ሚዲያ በባህሪው ምክንያት ይፈልጋል። የሚኖርለት ዓላማ ይፈልጋል። ፋይናስ አያኖረውም። ስለዚህ አሁን መታሰብ ያለበት ለምንድን የምንጠቀምበት? እንዴት ነው መጠቀም ያለብን? የሚለውን ነው። አሁን ራሳችንን ወደ ማየት ሰከን ወደ ማለት እየመጣን ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኞቹ ቤተ እምነቶች የወጣቱ ሞራል መላሸቅና አለመረጋጋትና መከፋፈል ተቋማቱ መስራት በሚገባቸው ልክ የአስተሳሰብ ቀረፃው ላይ ባለመስራታቸው እንደሆነ ይነሳል። በዚህ ላይ የአንተ እምነት ምንድን ነው።
አገልጋይ ዮናታን፡- እንዳው ደግ ነገር በባህሪው ጮሆ አይሰማም እንጂ በኦርቶዶክስም፤ በሙስሊሙም ሆነ በፕሮቴስታንት ዕምነት እጅግ ጨዋ የሆነው ሰው ይበዛል። እምነቱን አክባሪና አገር ወዳድ የሆነው ህዝብ ይጨምራል። እንዳልኩሽ ግን ችግሩ ከመጥፎ ነገር ከጥሩ ነገር ይልቅ ጆሮ የመያዝ፥ የመሰማት ባህሪ አለው። ከዚያ አንፃር የሃይማኖት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ስራ አልሰሩም ማለት አይቻልም።
ግን የሚጠበቅባቸውንና ከቴክኖሎጂ፥ ከማህበራዊ ሚዲያው አንፃር ኢሞራላዊ ሆኖ እያደገ ባለው አዲሱ ትውልድ ላይ ቤተእምነቶች የሚጠበቅባቸውን ያህል አልሰሩም። ለምሳሌ አንገቱ የተቆረጠ ሰው ስለፀጉሩ አይጮህም።
ምክንያቱም አንዴ በመለያየቱ ማለት ነው። ስለዚህ አንድ ሰው የመፅሃፍ ቅዱስ አማኝ ከሆነ ስለዘሩ፥ ስለግል ጥቅሙ፥ ስለግል ክብሩ አይደለም የሚጮኸው። ምክንያቱም ቀድሞውኑ ከዚያ አስተሳሰብ በመለያየቱ ነው።
በተጨማሪም የሚጠበቅብንን ካለመስራት አንፃር ብቻ ሳይሆን በሽታው ወደ ቤተእምነቶቻችን በሌላ አንፃር ገብቷል። ውጭ የምናየው ዘረኝነት፥ ብሄርተኝነት፥ መገፋፋትና ጥላቸው ወደ ቤተክርስቲያንም ገብቷል። ይህ የሆነው ደግሞ ቤተክርስቲያን በሯን ስለከፈተች ነው።
ይሄ እንግዲህ በትጋትና በጥንካሬ በመስራት ማስወገድ ያለብን ነገር ይመስለኛል። ቤተክርስቲያን ሰላም ከሆነች አገር ደህና ትሆናለች በሚል እምነት በተለይ በወጣቱ ላይ ትኩረት መስጠት ይገባናል። የእኛ ትልቁ ክፍተት የነበረው ወንጌል ላይ አለመስራት ሳይሆን ወጣቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ አለመስራት ነው።
በየቤተክርስቲያኑ ለወጣቱ የሚሰጠው ጊዜ በጣም አነስተኛ ነው። ይህም በመሆኑ ነው በቀላሉ ለአሉታዊ ነገር ክፍት የሚሆነው። ከዚያ አንፃር መዘናጋታችን፥ በህብረትና በአንድነት አለመቆማችን ተደማምረው ያመጡት ችግር ነው።
አዲስ ዘመን፡- በተመሳሳይ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚስተዋለው ግጭትና መፈናቀል ወጣቱ ላይ ጣት ይቀሰርበታል፤ ለዚህ ደግሞ ትውልዱን በስነምግባር አንፆ ማሳደግ ያለመቻሉ እንደሆነ ይነሳል። ይህ ምን ያህል አሳማኝ ነው ?
አገልጋይ ዮናታን፡- ሙሉ ለሙሉ ከስነምግባር ጉድለት ነው ብዬ አላስብም። ምክንያቱም በየዘመናቱ አብዮቶች ነበሩ። ከህግ ማክበር የሚቀድመው የፍላጎት መሟላት ነው። ይህንን በቀላሉ ለማስረዳት አውሮፓ ስትሄጂ አብዛኞቹ ህግ ያከብራሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ መሰረታዊ ፍላጎታቸው ተሟልቶላቸዋል። በዚህ አቅጣጫ አንዳንድ ምሁራኖች እንደሚሉት ሰው ህግ ወደማክበር የሚመጣው መሰረታዊ ፍላጎቱ ሲሟሉለት ነው ብዬ አምናለሁ።
ስለዚህ አሁን በየቦታው የሚነሳው ሁከትና ብጥብጥ ስርዓት አልበኝነት የወለደው አይደለም። መሰረታዊ ፍላጎት የፈጠረው እንጂ። አንድ በዲግሪ የተመረቀ ልጅ ስራ ሲያጣና ሰፈሩ ሄዶ ካልተማሩ ጓደኞቹ ጋር ቁጭ የሚልበት አገር ውስጥ እኮ ነው ያለነው። ለምሳሌ እኔ የማውቀው አንድ ጂኦሎጂ ተመርቆ መስቀል አደባባይ ላይ ጎዳና ወጥቶ የሚተኛ ልጅ አለ። ስለዚህ እንዲህ ያሉ የፍላጎት አለመሟላት የሚወልደው ቁጣ በቀላሉ ወደ ስርዓት አልበኝነት የመምጣት ዝንባሌ አለው ብዬ አምናለሁ።
በእርግጥ እኛ ከሌላው አለም ሁሉ ሌሎችን በማክበር በመፍራት የምንኖር የመልካም ማህበረሰብ ባለቤት ነን። እንዲያውም እንደ ፍላጎታችን ያለመሟላቱ የስነ ምግባር እጦት አልታየብንም። ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ በታዩ በብዙ መልኩ መንግስት እየደጎማቸው በከፍተኛ ሁኔታ በዝርፊያ ተደራጅተው የሚኖሩ ሰዎች አሉ።
እኔ በእኛ አገር የተከሰተው ነገር አንድም መሰረታዊ ፍላጎት ካለመሟላቱ የተነሳ የሚፈጠረው ተስፋ መቁረጥ እና ጨለምተኝነት፥ ራስን የበታች አድርጎ መቁጠር ይህን ተከትሎም ወደ ሱሰኝነት የመግባት ምክንያት ይሆናል። ሲቀጥል ደግሞ ባለፈው 27 ዓመታት መንግስት ያዋጣኛል ብሎ ሲከተለው የነበረው የማህበረሰብ አደረጃጀት ፖሊሲ ወቅቱን የመጠነ አልነበረም።
ይህንንም በምሳሌ ብጠቅስልሽ መፅሃፍ ቅዱስ ኢሳያስ አራት ላይ « ሰይፋቸውን ለማጭድነት፥ ጦራቸውን ለማረሻነት ይቀጠቅጣሉ፤ ከእንግዲህ በኋላ ሰይፍን አይማሩም» ይላል። ስለዚህ አንድ ሰው መሳሪያውን የሚቀይረው ትምህርቱን ሲቀይር ነው። ትምህርቱን ካልቀየርሽለት መሳሪያውን አይቀይርም።
ትናንትና የያዙትን ጦር ለምንድነው ማጭድ ያደረጉት? ብለሽ ብትጠይቂ ትናንትና የያዙት ትምህርት ነው። የተሰጠን ትምህርት ከፋፋይ ነበር። ከእኛ ሰፈር፤ ከእኛ ጎጥ ከእኛ አለም ውጭ ሌላ አለም የለም የሚል ነው። በእኛ ጉዳት ለሌላው ሰው መኖር ምክንያት እንደሆነ ነው እየተነገረን የኖርነው።
ስለዚህ አሁን የሚታየው አለመረጋጋትና ግጭት የትምህርቱ ውጤት ነው ብዬ ነው የማስበው። ስለዚህ ሁለት ነገር ነው የሚታየኝ፣ አንዱ መሰረታዊ ፍላጎቶች አለመሟላትና ወቅቱን ያልጠበቀ ትምህርት መሰጠቱ ነው። ለምሳሌ እስታሊን በዚያኛው ክፍለ ዘመን ብሄርን የተረጎመበት መንገድ አለም ፈትሾት ውድቅ አድርጎታል። ፈረንጆቹ እንኳን ፈትሸውት ውድቅ አድርገውታል።
ስለዚህ ይህ እኛ ስንመራበት የነበረው ፖሊሲ ራሱን ከጊዜው ጋር ማጣጣም አልቻለም። ከዚህም ጋር ተያይዞ ለምሳሌ ውጭ ያሉት ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ሃሳብ የሚሰጡት ራሳቸው በዜግነት ፖለቲካ ውስጥ እየኖሩ ሌላውን አስካሪ በሆነና ሊያግባባ በማይችል ሃሳብ ነው የሚጠምዱት። ስለዚህ የትምህርት መዛባትና የፍላጎት ማጣት ይመስለኛል አሁን ያለውን ግጭት የወለዱት።
አዲስ ዘመን፡- እግረ መንገድህን አሁን ያለውን የለውጡን ሂደት እንዴት እንደምታየው ግለፅልን?
አገልጋይ ዮናታን፡- እኔ አሁን ያለውን የለውጥ ሂደት የማየው እንደ አረገዘች ሴት ነው። አንዲት ሴት ስታረግዝ እግሯ፥ እጇ፥ ፊቷ ያብጣል፤ አካሄዷ ይለወጣል፤ ትናንት ትወደው የነበረውን ዛሬ መጥላት ትጀምራለች፤ ወደ ላይ ወደ ላይ ይላታል፤ ያቅለሸልሻታል። ልክ እንደዛ አገሬም አሁን አዲስ ተስፋ አዲስ ህይወት ፀንሳለች፤ ስለዚህ እዚያም እዚህም ያለው ሰው ያቅለሸልሸዋል፤ ትናንት ይወደው የነበረውን ጠልቶታል።
ከዚህ አንፃር ፅንስ ተጠልቶ ወይም የማለዳ ህመም ተጠልቶ ፅንስ መቋረጥ አለበት አይባልም። ከዚህ ጋር ስታስተያይው ደግሞ ልጅ የሚወለደው ከደም ጋር ነው። እኛ አቅፈን የሳምነው ህፃን ልጅ ነርሷ አጽድታ የሰጠችን ነው። የትኛውም ህፃን ልጅ እንደተወለደ ቢሰጥሽ አትስሚውም።
እንግዲህ ልጅ ሲወለድ የጠላው ያንቀዋል፤ የወደደው ያጥበዋል። ልክ እንደዛ ነው ይሄ ለውጥ ከችግሮች ያልወጣው። የመጣው ለውጥ የተወሰኑ ችግሮች ስላሉበት እንነቀው አንድ አማራጭ ነው፤ እንጠበውና እናሳድገውም ሌላው አማራጭ ነው። ስለዚህ እኔ ለውጡን ከነችግሩ ከሚቀበሉት መካከል ነኝ። እውነቱን ብነግርሽ ላለፉት 27 ዓመታት ራሴን እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየቆጠርኩ ነው የኖርኩት።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ስትል ምን ማለት ነው? በግልህስ የደረሰብህ ነገር አለ?
አገልጋይ የኖታን፡- አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተምሬ ሳበቃ በተማርኩት ትምህርት ወደአደኩበት አገር ስመለስ ስራ መስራት አልቻልኩም። ጥሩ ውጤት እያለኝ፤ የተሻለ አቅም እያለኝ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ይቀጠሩ የነበሩት የኢህአዴግ አባል የነበሩ ብቻ ነበሩ። የፖለቲካ አባል ካልሆንሽ እንዲሁም እዛ ካለው ብሄር የመጣሽ ካልሆንሽ አትቀጠሪም። ወላጆቼ ግን ግብር የከፈሉት ለዚያ ከተማ ነው።
የኖሩት እዚያ ከተማ ነው። ሌላ ከተማ አናውቅም። በስመ ሌላ ብሄር ነው አድሎ ሲደረግብኝ የነበረው። ለዚያም ነው ራሴን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ስቆጥር የነበረው። አሁን ላይ ግን ያንን ድርጊት የማስበው በብስጭት በቁጣ ሳይሆን ውስጡ ያለውን እውነት ተናግሮ በማሳመን ጥሩ የሆነ የዲሞክራሲ የነፃነት የእድገት ሽታ እንዲሸትሽ ምክንያት እንደሆነ አድርጌ ነው። ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሲናገር እኔ የምሰማው ተፈጥሯዊ (ያልተቀባባ ) የሆነ ነገር ነው። ለዚህም ነው የምወደው።
እኔ አሁን ይህች አገር ያለችበት ሁኔታ በሚበልጥ ተስፋ እንጂ የጨለመ ነገር ውስጥ እንዳለች አድርጌ አይደለም። ጉዳዩ የጠሉት ሊያንቁት፤ የወደዱት ሊያጥቡት፥ እየተሯሯጡ መሆኑ እንጂ። ይህንን ደግሞ ከህፃን ልጅ ውልደት ጋር አገናኘዋለሁ። መፃሃፉ «ስለልጇ መከራዋን ትረሳዋለች» እንደሚል ስለሚመጣው የተሻለ ተስፋ አሁን ያለውን መከራ ምንም እንዳይደለ መቁጠር ነው የምፈልገው።
ስለዚህ ለውጡ በቆንጆ ሁኔታ እየሄደ ነው ብዬ አምናለሁ። ደግሞም ለውጥ በአንድ ጀንበር አይመጣም፤ ጊዜና ትብብር ይፈልጋል። የዚህችን አገር ለውጥ ከፐዝል ጋር ላገናኝልሽ፤ ዝብርቅርቅ ያለ ፐዝል ቦታ ቦታውን ፈልገሽ ለመደርደር አንደኛ ትኩረት፣ ሁለተኛ ጊዜ፣ ሶስተኛ አዕምሮሽ ከእጅሽ ጋር መንቀሳቀስ ይፈልጋል። ልክ እንደዛ ሁሉ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የተዘበራረቀ የሚመስል ነገር በጊዜው ውብ እንደሚሆን አልጠራጠርም።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች የብሄርተኝነቱ ችግር እየጦዘ የመጣው ከለውጡ በኋላ እንደሆነ ያነሳሉ። አንተ በዚህ ላይ ምን ትላለህ?
አገልጋይ ዮናታን፡- እኔ በዚህ ሃሳብ አልስማማም። እውነት ለመናገር የደርግም ሆነ የሃይለስላሴ መንግስት የነበረው ችግር ብሄርተኝነት አይደለም። ብሄርተኝነት የሚለው ሃሳብ ኢህአዴግ በዋነኝነት አገሪቱን ለማስተዳደር የተጠቀመበት መንገድ ነው። አሁን እድል ሲያገኝ ፈነዳ እንጂ በዚህ አስተሳሰብ መሰራት ከጀመረ የአንድ ወጣት እድሜ ያህል ፈጅቶበታል። ለእኔ አሁን ያለው ብሄርተኝነትና እሳተ ጎመራ አንድ ናቸው።
እሳተ ጎመራ እንዴት እንደሚፈጠር በምትመለከችበት ጊዜ ከላይ ያለው የመሬት አካል ታች ያለውን ይጫነዋል፤ እታች ሙቀት አለ፥ ሃይል አለ፥ መተንፈስ ይፈልጋል። እድል አግኝቶ የወጣ ቀንም ሁሉንም ነገር ድርምስምስ ነው የሚያደርገው። ላለፉት 27 ዓመታት ከላይ ያለው አካል በመሳሪያ አቅም በእያንዳንዱ ውስጥ የከተተውን አይነት ስሜት አፍኖት ነው የቆየው።
ለውጡ እኮ ያፈነውን ክዳን አወጣው እንጂ ግለቱ፥ ጥላቸው፥ መገፋፋቱ ተቦክቶ የተጋገረው ባለፉት 27 አመታት ነው። እንዳውም ክዳኑን ማንሳቱ ጥሩ ነው ባይ ነኝ። ድንገት አንድ ቀን ሁሌ ውስጤ እየተፍገመገመ ቀን ጠብቆ ከሚወጣ አሁን መተንፈሱ ተመራጭ ነው።
ከዚያ ይልቅም ያዋጣል፤ አያዋጣም፤ ያስኬዳል፤ አያስኬድም ብለው እንዲፈትሹት የአሁኑ ትውልድ ምክንያት እየሆነ ይመስለኛል። ይህንን ጉዳይ በምሳሌ ላስረዳሽ፤ አንድ ሰው ሰፈር ውስጥ ሲገባ ሲወጣ የሚጮሁ እንቁራሪቶች ነበሩ። እናም አንድ ቀን ለስራ ሲወጣ አንድ ሆቴል እንቁራሪት የሚያቀርብልኝ የሚል ማስታወቂያ ያወጣል።
እኔ አቀርባለሁ ብዙ እንቁራሪት አለኝ ብሎ ሲሄድ እንደጠበቀው ብዙ እንቁራሪት አላገኘም፤ አራት ብቻ ነበር የነበሩት። እንቁራሪት በባህሪው አራት ሆኖ ጩኸቱ የአራት መቶ ነው። እጅግ ብዙ እንቁራሪት ያለ ነው የሚመስለው። አሁን እዚህም እዚያም የሚጮኸው ነገር ብዙ ሊመስለን ይችላል።
ነገር ግን ከሚጮኸው የማይጮኸው ይበዛል። ከዚያ ይልቅም ሰክኖ ሁሉንም ነገር በፍቅር ማድረግ የሚፈልገው አካል ብዙ ነው። ስለዚህ እንደ አጠቃላይ እኔ አሁን የሚጮኸው አካል ከለውጡ በኋላ ነው የበዛው ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡- ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በየቤተ እምነቱ የነበረውን መቃቃርና አለመግባባት ችግር ለመፍታት መስራታቸው ምንም እንኳን መልካም ቢሆንም ህገመንግስቱ ያስቀመጠውን ቀይ መስመር አልፈዋል እያሉ የሚወቅሷቸው ሰዎች አሉ። ልክነው ብለህ ታምናለህ?
አገልጋይ ዮናታን፡- ከዚህ በፊት መንግስት ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ ሳይገባ የቆየበት ዘመን ካለ ብታስታውሺኝ ደስ ይለኛል?። መንግስት 27 ዓመታት የኖረው የት ነው። መንግስትና ሃይማኖት አይገናኙም፤ መንግስት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ አይገባም፤ አሁን ቀይ መስመሩን አልፏል ካሉ እኔ እንዳውም የሚገባኝ አሁን ነው ድንበሩን የጠበቀው። ልዩነታቸው አንዱ ጉዳይ ላይ ነው።
ከዚህ ለውጥ በፊት የነበረው መንግስት ሃይማኖት ውስጥ ሲገባ ጭምብል ለብሶ፤ ካድሬ መልምሎ ቄስና ፓስተር ሾሞ ነው። አሁን ያለው መንግስት ደግሞ በአደባባይ አገራችሁን ውደዱ ማለቱ ነው ለውጡ። መቼ ነበር ኢህአዴግ እግሩ ከሃይማኖት ቤት ወጥቶ የሚያውቀው? እዛ ሆኖ አይደለም አገር ሲያተራምስ ህዝብና ህዝብን ሲያጣላ የነበረው!። ስለዚህ ለእኔ ልዩነታቸው በግልፅና በድብቅ መሆኑ ነው።
በነገራችን ላይ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ማለት እኮ ሃገር ነች። ኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ቅኔ፥ ጥበብ፥ ትምህርት ድርና ማግ እንደተሰራች ነው የሚሰማኝ። አሁን ዶክተር አብይ ድንበራቸውን አልፈዋል የሚለው አባባል እኔ አይገባኝም። አየሽ! እኛ ብዙ ጊዜ የለመድነው በውሸት በለበጣ ማስመሰልን ነው።
የሙስሊም ወንድሞቻችን ጥያቄ የነበረው ከመሃላችን እጃችሁን አስወጡልን እኛ ራሳችንን ራሳችን እንመራለን የሚል አልነበር እንዴ?። ማን ነበር ለሙስሊሙ ህብረተሰብ መሪ ይመርጥለት የነበረው? አሁን መንግስት እጁን ሰብስቦ እያለና ሙስሊሙ ራሱን በራሱ የሚመስለውን ሲመርጥ ነው እጁን አስገባ የሚባለው? ይህችን ይህችን እንኳ ተያት!።
ለዚህ አንድ ምሳሌ ልንገርሽ፤ አንድ ትልቅ ባለስልጣን የአእምሮ ህሙማን ማዕከል ለማየት ጉብኝት ይወስዱታል። እናም እዛ ሲደርስ በጣም ብዙ እብዶችን ቢኖሩም ጠባቂው ግን አንድ ሰው መሆኑን ያያል። ይህንን ጊዜ ልክ አይደላችሁም እንዴት ይህንን ሁሉ እብድ በአንድ ሰው ታስጠብቃላችሁ ችግር ቢፈጥሩስ? ይላል። የዚያን ጊዜ የሚያስጎበኛቸው ሰው «እብድ በባህሪው ስለማይተባበር አይተናኮልም፤ ደግሞም ያበዱት ስለማይተባበሩ ነው» የሚል ምላሽ ይሰጣቸዋል።
አሁን እየተባለ ያለው እንተባበር ነው። ለእኔ አለመተባበር እብደት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያደረጉ ያሉት ነገር ኦርቶዶክስ አገር መሆንዋን፥ ሙስሊም ወንድሞቻችን ሃብት መሆናቸውን፥ ፕሮቴስታንቱም ጋር ብዙ አቅም መኖሩን በመገንዘብ ይህንን በጋራ ተጠቅመን ጥላቻንና አለመተማመን አስወግደን እንቀጥል ማለታቸው እኔ ከአንድ የአገር መሪ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብዬ ነው የምወስደው። ይህን ለሚሉ ሰዎች መቼ ነበር ኢህአዴግ እጁን ከሃይማኖት ተቋማት አስወጥቶ የሚያውቀው? የሚለውን ጥያቄ ግን እንዳትረሽብኝ!።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፕሮቴስታንት አማኞች ጋር ባደረጉት የውይይት መድረክ ላይ ተሳትፈህ ነበር?
አገልጋይ ዮናታን፡- አልተሳተፍኩም፤ እኔ በዛ ሰዓት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ውይይት እያደረኩ ነበር። እኔ ባልሳተፍም ግን የወንጌላውያን አማኞችን ሰብስበው ማናገራቸው በጣም መልካም ነው የሚል እምነት አለኝ። ቪዲዮንም እንዳየሁት ራሳችንን እንድናይ ምክረ ሃሳብ የተነሳበት መድረክ እንደነበር ለመገንዘብ ችያለው። በተለይም የወንጌል አማኞች አንድና ወጥ የሆነ የሚመራን ተቋም ያለመኖሩ ህብረት እንዳይኖረን አድርጓል።
ሰፍቶ ወደሚወጣ የአገር በረከት መለወጥ የሚችሉበትንም መንገድ ይቀይሳል ብዬ አምናለሁ። በመካከላችን የነበረው መከፋፋልና መለያየት እንደነገርኩሽ እብደት ነው። ይህንን ከመፍታት አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠበቅባቸውን እንደሰሩ አስባለሁ። ከዚህ በኋላ የሚቀረው የሃይማኖት መሪዎቹ ተግባር ነው። ከእኛ የሚጠበቀው ይህንን መልዕክት ተቀብሎ በመልካም ጎዳና መሄድ መቻል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ስለምንድን ነበር የተወያየኸው? የሄድክበትንስ አላማ አሳክተሃል?
አገልጋይ ዮናታን፡- በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በመልካም ወጣት ስልጠና ዙሪያ ነው ምክክር ያደረግነው። ስልጠናው መልካም አመለካከት ስብዕና ግንባታ ብቻ ሳይሆን ከዛ አልፎ እንዴት ወደ መሬት ማምጣት እንደሚቻል በስፋት ተወያይተናል። እኛ አሁን በመላው አገሪቷ የሚመጡ 30ሺ ወጣቶችን ነው የምናስተምረው።
ይህ ደግሞ በ105 ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ 30ሺ ማስተማር ማለት ምንም ማለት አይደለም። እንዴት አድርገን ልናበዛው፤ ልናሰፋው እንደምንችል ምክክር አድርገናል። በተለይም ከተለያዩ ክልሎች ወደ መልካም ወጣት ማዕከል ከሚመጣ ይልቅ ማዕከሉ ራሱ ወደ ወጣቱ የሚሄድበት አግባብ መዘርጋት ይገባል።
ከዚያም አልፎ በምስራቅ አፍሪካ እንገነባለን ብለን ለምናስበው አንድ ትልቅ የወጣት ማዕከል ግንባታ 1ቢሊዮን 200ሚሊዮን ብር ይፈልጋል። በዚህ ዙሪያ ከቦታ ዝግጅት፥ ከተለያዩ ስትራቴጂካዊ ነገሮች አንፃር መክረናል። መንግስትም ደግሞ አስፈላጊ የሆነ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቶልናል። እርሳቸው ቃል ከመግባት ባለፈም በየቢሮው የሚያጋጥሙን ቢሮክራሲዎች እንዲፈቱ ከማድረግ አኳያም የበኩላቸውን ክትትል እንደሚያደርጉ ነው የነገሩን።
አዲስ ዘመን፡- ለአንተ አንድ ወጣት መልካም ነው ለመባል ምን ምን መስፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅበታል?
አገልጋይ ዮናታን፡- እንግዲህ መልካም ወጣት ማለት ለእኔ አገሩንና ቤተሰቡን የሚወድ፤ እኔ ከማለት ይልቅ እኛ ማለት የሚቀናው፤ በመልካም ስነምግባር ማህበራዊነት የሚስማማው፤ ስደትን አማራጩ ያላደረገ፤ ከወደቀ ድንጋይ ውስጥ መልዓክ የሚታየው፤ ከትናንቱ ስህተቱ ቀለም ተውሶ ዛሬና ነገውን ለመፃፍ የማይፈልግ፤ ወደ ህልሙ ለመምጣት መሮጥ ቢያቅተው የሚራመድ፤ መራመድ ቢያቅተው የሚያዘግም፥ ማዝገም ቢያቅተው የሚንፏቀቅ እንጂ መቆምን አማራጩ ያላደረገ ወጣት ነው መልካም የምለው።
ለነገሩ መልካም ወጣት ብዬ ለመስራት ስነሳም ይህንን ታሳቢ አድርጌ ነው። እንግዲህ አይተሽ ከሆነ ወድቃለች ከሚሏት ኢትዮጵያ ወጥተው አድጋለች በሚሏት አሜሪካ የወደቀ ህይወት የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ነገር ግን ወድቃለች በሚሏት ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅን ህይወት መኖር የሚችሉ ዜጋን ማፍራት ነው የልቤ ሃሳብና የፕሮግራሙ አጀንዳ።
አዲስ ዘመን፡- አንተ የምታስተምራቸውን ወጣቶች በዚህ መንገድ በመቅረፅ ረገድ ውጤታማ ነኝ ብለህ ታምናለህ?
አገልጋይ ዮናታን፡- አዎ በደንብ፤ ይህንን ስልም ለምሳሌ ካስተማርኳቸው በኋላ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ የነበሩ፥ ከአገር ለመውጣት ይመኙ የነበሩ፥ በሱስ ውስጥ የነበሩ፥ በብዙ ግራ መጋባት ውስጥ የነበሩ እንደገና ተስፋቸው ታድሶ፤ ሌላው ይቅርና ወደ ትምህርታቸው የተመለሱ አሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለውጥ የማንነት ለውጥ ነው። የኢኮኖሚና የአገር ለውጥ አይደለም።
ስለዚህ ከጨለምተኛ አስተሳሰብ ወጥተው ሌላውን አቃፊ፥ በቀላሉ ተግባቢና ወዳጅ፥ የችግር ሳይሆን የመፍትሄ አካል መሆን የሚስማማቸው እንዲሆኑ ነው የማስተምራቸው። ለዚህ ደግሞ እየሰራሁ ስለመሆኔ ወላጆቻቸው ናቸው የሚመሰክሩልኝ። በተጨማሪም እኔ ባለሁበት ቤተ እምነት ብቻ ሳይሆን በሌላውም ቤተ ዕምነት ያሉ ሰዎች እየሰራሁት ስላለሁ ስራ መልካምነት ይመሰክሩልኛል።
አዲስ ዘመን፡- መልካም ወጣት ብለህ የወጣቶች አዕምሮ ቀረፃ ላይ እየሰራ ያለኸው ስራ ምን ያህል ውጤታማ እየሆነ ነው?
አገልጋይ ዮናታን፡- በመልካም ወጣት እንግዲህ ወደ 11ሺ ወጣቶችን ነው ያስተማርኩት፤ አምና 20ሺ ወጣቶችን ያስተማርኩ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ 30ሺ ወጣቶችን ለማስተማር ነው የታሰበው። በድምሩ በሶስት ዓመታት ውስጥ 60ሺ ወጣቶችን በአካል እያስተማርን ነው ያለነው። እንዳልኩሽ ለውጥ በአንድ ጀንበር የሚመጣ ጉዳይ አይደለም። አንድ ሰው እንዲለወጥ ቤተሰቡ፥ ማህበረሰቡ፥ ትምህርት ቤቱ እንደዚሁም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተሳትፎ ይፈልጋል።
ከዚህ አንፃር ስልጠናው በተሟላ መልኩ ባይሆንም እንኳ ይበል የሚያሰኝ ነው። በነበሩት ሁኔታዎችም ከግባችን አንፃር ስለሆነ ስኬታችንን የምንለካው። በዚህ አመት እያንዳንዱ መልካም ወጣት በዚህ አመት የሚፈርመው የቃል ኪዳን ሰነድ አለ። እዛ ላይ የመጀመሪያው የቃል ኪዳን ነጥብ «ማህበራዊ ሚዲያን ተጠቅሜ ቤተሰቤን፤ ቤተክርስቲያኔን ሃገሬን አላፈርስም» የሚል ነው።
ሁለተኛው «ለእኔ ለጥቅሜ ስል በእንደዚህ አይነት ወቅቱን ባልመጠነ ቡድን ውስጥ በመደራጀት ሌላውን ቡድን አላጠፋም። ተናዳፊ የሆነ አካሄድን አልከተልም» የሚል ነው። ከውጤታማነት አንፃር ባለፉት ሁለት ዓመታት ያደረግነው በጣም ጥሩ የሚባል ነው። ምንም እንኳን ለስድስት ቀናት ወጣቶቹን የምናሳድርበት ቦታ የመሳሰሉት ተግዳሮቶች ቢኖሩብንም እግዚአብሄርም ረድቶናል በርካታ ወጣቶችን መለወጥ ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- በስድስት ቀናት ቆይታ ወጣቱ ይለወጣል ተብሎ ይታመናል ?
አገልጋይ የኖታን፡- አይ ለውጡ ይጀምራል ነው የሚባለው!። እኔ አሁን የማከክ፥ የመቀስቀስ ስራ ነው የምሰራው። ተነሳሽነቱ ከወጣቱ ካለ፤ ቤተሰብና ጓደኞቹ የሚተባበሩ ከሆነ ልጁ መልካም የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም። ለነገሩ እኮ አንድ ወጣት ለመበላሸት ስድስት ዓመት ነው የፈጀበት እኔ እንዴት በስድስት ቀን ውስጥ እቀይረዋለው?። እኔ የማምነው ለውጥ የማያቋርጥ መሆኑን ነው።
የመጀመሪያው የእኛ ስራ ቢያንስ ካለበት ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም፤ የገባበትን ሁኔታ እንዲጠላ ማድረግ ነው ። አሁን ከሱሱ ጋር እየኖረ፥ ሱሱን እያንቆለጳጳሰ መኖሩን እንዳይቀጥል ማድረግ ነው። ከሰው በላይ ለመሆን ቅመው፤ ከሰው በታች ይሆናሉ፤ ከዚያም ከሰውነት ሙሉ ለሙሉ ይጠፋሉ። ከዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዲወጡ ባደረግነው ጥረት ደግሞ ተሳክቶልናል።
ይህ የሆነው እንግዲህ በአካል ነው። ወደ ሚዲያ ስትመጪ የኛን ማህበራዊ ሚዲያ ወደ 16 ሚሊዮን ወጣቶች ተከታትለውታል። በመላው አለም ያሉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያኖች ይከታተሉታል። ስለዚህ በአካል ጉትገታ ከተደረገበት ይልቅ በሚዲያ ተፅእኖ የተፈጠረበት ይበዛል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በተለይ በሀሽሽ ሱስ የተጠመዱ ወጣቶችን ከሱስ ለማላቀቅ በምታደርገው ጥረት ከአዛዋዋሪዎችና ህገወጦች የደረሰብህ ጥቃት የለም?
አገልጋይ ዮናታን፡- ብዙ አለ! አንዳንዱ ሚስጥር የምታገኚ ይመስለዋል። ስለዚህ ሚስጥር እንዳታወጪ ያስጠነቅቅሻል። ዛቻውም ብዙ ነው። በነገራችን ላይ ብዙ ግጭቶች የሚነሱት ከጥቅም ግጭት ጋር ተያይዞ ነው። እምነት ቤት ውስጥ የሃይማኖት መልክ በመያዝም ይሁን በቀጥታ የሚደርሱብን ማስፈራሪያዎች አሉ። በነገራችን ላይ እኛ አገር እኮ አደንዛዥ እፅ የሚሸጠው ፊት ለፊት ነው።
እኔ በባህሪዬ በጣም ቀለል ያለ አኗኗርን የሚመርጥ ነኝ። በቆሎ እሸትም እየበላው በየመንገዱ እሄዳለሁ። ስለዚህ ለጥቃት አድርሾቹ እኔን ለማግኘት በጣም ቀላል ነው። እኔን ለማግኘት ምንም የተወሳሰበ ፍለጋ አያስፈልገውም። ከዚህ አንፃር የሚፈራ አላገኙም እንጂ በስልክም በአካልም ማስፈራሪያና ዛቻ የሚያደርጉ ሰዎች አጋጥመውኛል።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህን ግለሰቦች ለህግ አሳልፈህ ለመስጠት ሞክረሃል? አገልጋይ ዮናታን፡- እስካሁን ይህንን አላደረግሁም። «የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው» የሚለውን የጌታ የእየሱስን መርህ ስለምከተል ያን ያህል ገፍቼ መሄድ አልፈለግኩም። ደግሞም የኔ ዋና ትኩረት ልጁ መለወጡን እንጂ ከኋላ ያለውን ታሪክ የመንግስት ወይም የፍትህ አካላት ጉዳይ ነው። በነገራችን ላይ የሀሽሽ ሽያጩም ሆነ ዝውውሩ ከመንግስት ብዙ ተሰውሮ ነው የሚደረገው የሚል እምነት የለኝም። ሺሻ ቤቶች እኮ ሊታሸጉ ሲሉ ቀድመው «ልንመጣ ነው» የሚሉት እኮ እራሳቸው ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ችግር ይህንን ያህል ከተስፋፋ ምንአይነት አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ትላለህ?
አገልጋይ ዮናታን፡- በዚህ ዙሪያ ብዙ ስራ መሰራት አለበት ብዬ አምናለሁ። በተለይ ያሉ ህጎችና አዋጆች አካል እንዲኖረው ማድረግ ይገባል። የሚወሰዱት እርምጃዎችም የአንድ ሰሞን መሆን የለበትም። ዛሬ የኔ ልጅ እዚህ ነገር ውስጥ ባይገባም የጎረቤቴ ልጅ እስካለ ድረስ ግን እዚህ ነገር ውስጥ ላለመክተቱ ምንም ማረጋገጫ የለውም።
ከዚህ አንፃር የምናገኘውን ገንዘብ ብቻ አይደለም ማሰብ የሚገባን። የምናጣውንም ትውልድ ከግምት ውስጥ ማስገባት ይገባናል። ሻሸመኔ እኮ አስፋልት ላይ ነው የእፅ ዝውውሩ የሚካሄደው። ይህንን ጉዳይ አገሩን የሚወድ የመንግስት አካል ቁርጥ ያለና የማያዳግም ስራ መስራት አለበት ብዬ አስባለው።
አዲስ ዘመን፡- ማዕከሉን ለመገንባት በዋናነት ተግዳሮት የሆነብህ ጉዳይ ምንድን ነው?
አገልጋይ ዮናታን፡- መልካም ወጣት ለመሳተፍ አንድ ወጣት ልጅ አንድ ሺ ብር ያዋጣል፤ ይህ ማለት ስድስት ቀን ይቆያል፤ ምሳና ራት ይበላል፥ ቲሸርት፥ ሞጁልና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን ያገኛል።
ይህ ማለት ከሚያወጣው ገንዘብ በቂ ነው ማለት አይደለም። ግን የኛን ሸክም ከመካፈል አንፃር የኛ አጋር አካላት፣ ሌሎች ቤተሰቦች ናቸው ድጋፍ እያደረጉ ያሉት። ወደፊት ማንም ሰው ምንም አይነት ክፍያ ሳይከፍል ቢማር ደስ ይለኛል። አሁን ግን ያለው ጫና ብዙ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አገልጋይ ዮናታን የዛሬው የዘመን እንግዳ በመሆን ከእኛ ጋር ቆይታ በማድረግህ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ።
አገልጋይ ዮናታን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 22/2011
ማህሌት አብዱል