በ14 ማዞሪያ፤ 14 ጊዜ እስር
ወጣት ስንታየሁ በአዲስ አበባ ቀጨኔ አካባቢ 14 ማዞሪያ በሚባል አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው። 39 ዓመት ሞልቶታል። የቤተሰቦቹ ገቢ አነስተኛ ስለነበር የትምህርት ቤት ወጪ ለመሸፈንና ራሱን ለመቻል ሲል በአንድ ወቅት መንገድ ላይ ተሽከርካሪ ያጥብ ነበር። መንገድ ላይ ማጠብ ክልክል ስለሆነ ከፖሊሶች ጋር ድብብቆሽ ይጫወት ነበር።
ጀሪካን ሲወሰድበት፣ ውሃ ሲደፋበት ብዙ መከራ አይቷል። በፖሊስ ተይዞ 14 ጊዜ ታስሮ ተፈትቷል። ይህ ሂደት ሲደጋገም ምርር ይለዋል። መኪና ያጥብ የነበረውም ውሃ ከቦኖ እየቀዳ መሆኑ ደግሞ ድካሙን ጨምሮበታል።
አንድ ቀን ግን በሚኖርበት መንደር መኪና የሚያጥቡ ልጆች ውሃውን አንድ ጊዜ ብቻ ተጠቅመው ወደ መሬት ላይ ሲደፉት ይመለከታል። በዚህን ጊዜ አንድ ነገር ይታየዋል። መኪና እየታጠበ የሚፈሰውን ውሃ ቦይ ይዞ እንዲወርድ አድርጎ ጉድጓድ ቆፍሮ በዚያ ውስጥ እንዲጠራቀም አደረገው።
ከዚያም ውሃውን ከጉድጓድ ውስጥ እየቀዳ ይጠቀምበት ጀመር። ግን አሁንም የሚጠቀመው ውሃ ንጹህ ባለመሆኑ እንደፈለገው ደንበኞችን ማስደሰት አልቻለም። በተጨማሪም ከፖሊስ ጋር ያለው ግብግብ መቀጠሉ ስራውን ከባድ አደረገበት። ይህን እየሰራም እያለ ስለምን አዲስ ሥራ መጀመር፤ አዲስ አሰራር መከተል ለምን አልሞክርም ብሎ ከራሱ ጋር ይነጋገራል።
ከዚያም ከተወለደበት መንደር ወጣ ብሎ ሥራ ለመስራት ቦታ ማማረጥ ጀመረ። ከአዲሱ ገበያ ከፍ ብሎ ድልበር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ ቆሻሻ ከሚጠራቀምበት ሥፍራ ይሄድና ‹‹ይገርማል የመኪና እጥበት» ብሎ ብዙዎችን የሚያስገርም ሥራ ይጀምራል። በወቅቱ ሥራውን ሲጀምር 1ሺ500 ብር ብቻ ነበረው።
እርሱ ሥራ የጀመረበት አካባቢ ቀደም ሲል ቆሻሻ የሚጣልበትና ከዋናው መንገድ ወጣ ያለ ጫካ ስለነበር በርካታ ወንጀሎች ይካሄዱበት ነበር። ስንታየሁ ግን አካባቢውን ከቆሻሻም፤ ከወንጀልም አፀዳው። ሰፊ ቦታ ስለነበረው ተሽከርካሪዎች እንደልብ ለመቆምና ለማጠብ ስለሚመች ደንበኞቹ እየተበራከቱ መጡ። ሥራውንም በሚገባ አላመደው፤ ሌሎች ሰዎችንም እየቀጠረ ሥራውን እያሳደገ መጣ።
አዲስ ፈጠራ
ስንታየሁ ትምህርቱን ያቋረጠው ከ12ኛ ክፍል ቢሆንም፤ የፈጠራ ባለቤት ከመሆን አላገደውም። ቀደም ሲል በባልዲ ውሃ እየቀዳ ሲሠራ ቆሻሻ ውሃ ስለነበር በሥራው አይረካም፤ በዚህ ላይ እንደፈለገው ውሃ አያገኝም። አሁን በሚሰራበት አካባቢው ደግሞ ውሃ ባለመኖሩ ከሱሉልታና ሌሎች አካባቢዎች የጉድጓድና ወንዝ ውሃ በመጠቀም ነበር የእጥበት ሥራውን የሚያከናውነው።
ይሁንና ይህን ውሃ ደጋግሞ ለመጠቀም በቴክኖሎጂ መደገፍ እንዳለበት አመነ። በየቀኑ እየተፈላሰፈ የሚያስበውን ሁሉ በወረቀት እየሞነጫጨረ የራሱን ዲዛይን ሠራ። ውሃን በማጣራት ደጋግሞ የመጠቀም ፕሮጀክት ወደ ተግባር ቀየረው።
በፈጠራውም በመጀመሪያ በቦታ ከሌላ ስፍራ የመጣውን ውሃ ወደ ውሃ ማጠራቀሚያ ጋን “ታንከር” እንዲገለበጥ ይደረጋል። በመቀጠልም የኬሚስትሪ እና የፊዚክስ ህጎችን በመከተል ውሃ እንዲጣራ ይደረጋል። የተለያዩ ሂደቶችን ካለፈ በኋላ ውሃው ንጹህ ይሆንና ለእጥበት ዝግጁ ይሆናል።
አሁንም የፈጠራው ስራ አላበቃም። አንድ ተሽከርካሪ ከታጠበ በኋላ የሚባክን ውሃ የለም። መሬት ለመሬት ለፍሳሽ በሚመች መልኩ በተሰሩ መስመሮች ውስጥ ሄዶ የተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል። ከዚያም ዳግም የማጣራት ሂደት ውስጥ ይገባል። አንድ ተሽከርካሪ የታጠበት ውሃ በአማካይ 39 ጊዜ ደጋግሞ በማጣራት ጥቅም ይሰጣል። በዚህ ስፍራ በአማካይ በቀን 400 ተሽከርካሪዎች ይታጠባሉ።
በዚህ ሂደት ውስጥም በርካታ ሥራዎች የሚከናወኑ ሲሆን፤ ቆሻሻ ብሎ የሚወገድ ነገር የለም። ለአብነት መኪና ሲታጠብ ከላይ የሚንሳፈፉ የነዳጅ፤ ናፍጣ እና ጋዝ ብሎም ዘይቶች በቴክኖሎጂ ተለይተው በሌላ እቃ ይቀመጣሉ። በሊትርም ሦስት ብር ይሸጣል። ለከተማዋ የመጠጥ ውሃ የሚሆነውን አይጠቀምም። ምክያንቱ ደግሞ ማህበረሰቡ ውሃ እየተቸገረ ተጨማሪ ችግር መሆን አይፈልግም፤ ይልቁንም ጥቅም ላይ ያልዋሉትን ሁሉ ወደ ጥቅም እየቀየረ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣትና ሌሎችንም ማስተማር ይፈልጋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ
ስንታየሁ የቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን ሥራ በመፍጠርም ረገድ የሚስተካከለው የለም። እኔ አንድ እንጀራ ነው የምበላው፤ ሌሎችም ይህን የማግኘት መብት አለባቸው ብሎ ያስባል። ስንታየሁ እዚህ ቦታ ለመድረስ ስንት መከራ እንዳየሁ እኔና ፈጣሪ ነን የምናውቀው ይላል። አሁንም ቢሆን በበርካታ የቢሮክራሲ ውጥንቅጦች መቸገሩን ይናገራል።
ግን ነገሮች ለበጎ ስለሆኑ ሰዎች አንድ ቀን ዓላማዬን ሲረዱ እኔን ከመክሰስ ይልቅ ያግዙኝ ይሆናል ይላል። ስንታየሁ በተገፋ ቁጥር ጥንቃቄ፤ በገላመጡት ቁጥር ትህትናን በመማሩ ዛሬ ላይ ስለመደረሱ ይናገራል። በአሁኑ ወቅት ለ170 ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ለመንግስትም ተገቢውን ግብር እየከፈሉ አገራዊ ኃላፊነታቸውንም ይወጣሉ።
በርካቶችም በዚህ ስራ ሰርተው ትዳር መስርተዋል፤ ልጆችም ወልደዋል። የመንጃ ፈቃድ አውጥተው እራሳቸውን እንዲችሉና ለሌሎችም የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ራሳቸውን ችለው እንዲሠማሩ ይመክራል፤ ይደግፋል። በዚህ አካባቢ የሰዎች መብዛትንና የተሽከርካሪ ፍሰትን በመከተል በርካታ ሻይ ቡና የሚሸጡ ሰዎች በዝተዋል፤ አነስተና ካፌዎችና ሬስቶራንቶችም ተበራክተዋል።
ቀላል የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችና፣ ጌጣጌጦችን ብሎም መፍቻና ብሎኖችን የሚሸጡ በርካታ ወጣቶች በአካባቢው መደብ መደብ ሰርተው እንጀራቸውን እያበሰሉ ነው። በዚህ አካባቢ ግን ሁሉም በአንድ ነገር ይስማማሉ። ስንታየሁ በዚህ ጫካ ውስጥ የመኪና እጥበት መጀመሩ ለእነርሱም የገቢ ምንጭ ሆኗል።
ሽልማቶች
ስንታየሁ የሚሠራውን ሥራና ፈጠራ ብዙዎች በዓይናቸው አይተው፤ በእጃቸው ዳሰው መስክረውለታል። ከቀበሌ፣ ወረዳ፣ ክፍለ ከተማ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ድረስ ሽልማት ተጎናፅፏል። መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በሥራው ተደምመው እውቅና ሰጥተውታል፤ በሽልማት እጆች ዳሰውታል።
ትከሻውን መታ! መታ! እያደረጉ በርታ ብለውታል። ለአብነት ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹ወጣት የልማት ጀግና ጀግና›› ተብሎ ወርቅ ሜዳሊያ ተጎናጽፏል።
በከተማ እና ክፍለ ከተማ ምርጥ ስራ ፈጣሪና የፈጠራ ባለቤት ተብሎ ተሸልሟል። የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠሩ ሸልመውታል። አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ደግሞ የወሰደውን ብድር በወቅቱ በመመለስ እና ለታሰበው ዓላማ በማዋል የምስክር ወረቀት ሰጥቶታል።
ከዚህም ባሻገር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢና ጥበቃ ባለስልጣን ከአካባቢ ጋር ያለው ተዛምዶ ጤናማ ስለመሆኑና ጉዳት እንደማያደርስ መስክሮለታል። ከእነዚህም በተጨማሪ በርካታ ድርጅቶች በሥራ ፈጠራውና ወጣቶችን ለሥራ በማነሳሳት እውቅና ሰጥተውታል።
ማህበራዊ ሕይወት
ከሰዎች ጋር መግባባት የነገሮች ሁሉ መሰረት እንደሆነ ያምናል። በአሁኑ ወቅት የሁለት ልጆች አባት ነው። ለቤተሰብ መስጠት ያለበትን ሰዓት ይሰጣል። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በርካታ ሰዎች ተሽከርካሪዎች የሚያሳጥቡት ቅዳሜ እና እሁድ ስለሆነ ትርፍ ጊዜ ላይኖረው ይችላል።
ግን ደግሞ ማድረግ ያለበትን ነገር ከማድረግ አይገድበውም። ስንታየሁ አሁን የሥራ ዕድል ከተፈጠራላቸው ወጣቶች ሌላ ማህበራዊ ኃላፊነት እየተወጣ ነው። አብረውት ከሚሰሩ 170 ወጣቶች ውስጥ መንጃ ፈቃድ ማውጣት የሚፈልግ ካለ ግማሽ ክፍያውን እርሱ ይሸፍናል። ሌላ ቦታ መቀጠር የሚፈልግ ካለ ሥራ ይፈልግላቸዋል። በእርሱ እምነት ሰዎች የትም ይሁኑ የትም ሥራ ይስሩ እንጂ ጥቅሙ ለኢትዮጵያ ነው የሚል ፍልስፍና አለው።
በእርግጥ በርካቶች ከዚያ መሄድ አይፈልጉም። ምክንያቱም አንድ ሰው በቀን በአማካይ ከ300 እስከ 500 ብር ለማግኘት ምቹ አሠራር ዘርግቷል። ይህ ገቢም በወር ተሰልቶ ይከፈላቸዋል። ይሁንና ጠዋት እስከ ሁለት ሰዓት፤ ማታ ደግሞ ከ11 ሰዓት ተኩል እስከ ሌሊቱ 5 ሰዓት የሚሰሩት ደግሞ ከሚሰሩት 50 ከመቶ የመውሰድ መብት አላቸው።
ሠራተኞቹም በራሳቸው ስም የቁጣባ ደብተር ከፍተው ለነገ ሕይወታቸው መሻሻል እንዲቆጥቡ ስንታየሁ ያስገድዳቸዋል። በእነዚህ መሰል ምቹ ሁኔታዎች የተነሳ ድርጅቱን የሚለቁ የሉም። በተጨማሪም አምስት ዓመት የሰሩ ወጣቶች ልዩ ክፍያ አላቸው። በዚህ ስፍራም በርካቶች አኗኗራቸው ስለመሻሻሉ ይናገራሉ።
ካፒታል
ስንታየሁ እዚህም እዚያም እያለ ካጠራቀማት ገንዘብ ውጭ ምንም አልነበረውም። ሥራውን ሲጀምር ኪሱ ባዶ ነበር፤ ወኔው ግን ትልቅ። በእጁ ላይ ምራቅ እንትፍ! እንትፍ! ብሎ ከቆጠራት በ1ሺ500 ብር የጀመረው ሥራ ዛሬ ላይ ወደ ሚሊዮን አሳድጎታል። መብራት ሲጠፋ ለሥራ ይረዳው ዘንድ በ1ነጥብ7 ሚሊዮን ብር ሁለት ጀኔተሮችን ገዝቷል። አካባቢውን ለማሳመርና ለሥራ ምቹ ለማድረግ ብሎም ውሃውን ደጋግሞ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን ለመገጣጠምና አጠቃላይ ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን ለማጠናቀቅ 4ነጥብ3 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጓል።
በአጠቃላይ የራሱን ፈጠራ ሃሳብ የሆነውን ቴክኖሎጂ ወደ ተግባር ለመቀየር ስድስት ሚሊዮን ብር ኢንቨስት አድርጓል። በካፒታል ደረጃ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ብር አለው። ከዚህም ባሻገር ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም አንድ ሚሊዮን ብር ብድር ተበድሮ በአግባቡ ሰርቶ በወቅቱ መልሷል። አሁንም ለሥራው ይረዳው ዘንድ 1ነጥብ5 ሚሊዮን ብር ብድር ይጠብቃል።
ቀጣይ እቅዶች
ስንታየሁ በአንድ ሥራ እና በጥቂት ፈጠራ ብቻ መወሰን አይፈልግም። ሕይወቱን ሙሉ አዳዲስ ነገሮችን መስራት፤ አዳዲስ አስተሳሰቦችን ማፍለቅ ይፈልጋል፤ እያደረገውም ነው። አሁን በሥራ ላይ የሚጠቀመውን ቴክኖሎጂ እና እውቀት ለበርካታ ሰዎች እያጋራ ነው። በርካታ ሚሊዮን የሚፈስባቸው እቅዶችን ነድፏል። በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችም የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነው ማየት ይመኛል።
ለዚህም የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው። በዚሁ ላይ ግን የምርምር ሥራ የሚሠሩ ምሁራን፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተቋማትም በሙያ ቢያግዙት ፍላጎቱ ነው። እርሱም የሚችለውን እውቀት ሊያካፍል፤ ፈጠራውን ሊያሻሽል ብሎም አገራዊ ኃላፊነትን በሰፊው ለመወጣት በጽኑ ይመኛል።
በአሁኑ ወቅት 39 ጊዜ የሚጠራውን ውሃ በቀጣይ 100 ጊዜ በማጣራት ጥቅም ላይ ለማዋል ጥናቱ ተጠናቋል። በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ቢያንስ ለሶስት ሺ ወጣቶች ውሃን መልሶ መላልሶ በማጣራት መኪና እጥበት ላይ ለሚሰሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ጥናቱን አጠናቋል። በተለይም ደግሞ ውሃን በማጣራት ደጋግሞ በመጠቀም የውሃ እጥረት ለሚገጥማቸውና የመኪና እጥበት ለሚሰሩ ድርጅቶች ውሃ በቦቴ መኪና ለማቅረብ ጥናት ሰርቷል።
ይህም የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ የሚሻሙ ድርጅቶችን አሠራር ለማሻሻልና ከተማዋንም ከብክለት ለመታደግ በመወሰን የታቀደ ፕላን ነው። በገንዘብ ደረጃም እጅግ አዋጭና ሚሊዮን ብሮችን በአጭር ጊዜ የሚገኝበት መሆኑን ይናገራል። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ደግሞ የዶሮ ኩስ ላይ ሌሎች ግብዓቶችን ጨምሮ መኖ ለማዘጋጀት፣ ብሎም የበቆሎ ዘይትና ተረፈ ምርቶቹን የተለያዩ ጥቅሞች ላይ ለማዋል ጥናቱን አጠናቋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር