የመጽሐፉ ስም፡- ጦቢያ
ደራሲ፡- አፈወርቅ ገብረኢየሱስ
የህትመት ዘመን፡- 1900 ዓ.ም
የገጽ ብዛት፡- 80
ዋጋ፡- 100 ብር
የሥነ ጽሑፍ ሰዎች በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም የመጀመሪያዋና በራስ ቋንቋ የተጻፈች ረጅም ልቦለድ መጽሐፍ እንደሆነች ነው የሚናገሩት። መጽሐፏ ዘንድሮ 111ኛ ዓመቷ ነው። ይች መጽሐፍ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ልቦለድ መሆኗን የስነ ጽሑፍ ሰዎች ባይነግሩን እንኳን ራሷ መጽሐፏም ትናገራለች። የዚህች መጽሐፍ አተራረክ በ1950ዎቹና 1960ዎቹ እንደነበሩት የረጃጅም ልቦለድ መጽሐፎች አይነት አይደለም። እነዚህ ዘመናት በብዛት ረጃጅም ልቦለዶች የተጻፉባቸው ናቸው። አተራረካቸውም ከጦቢያ በእጅጉ ይለያል።
የጦቢያ አተራረክ በተረታዊ አነጋገር ስልት ነው። ተረት ሲነገር ‹‹ጦጣ እና ዝንጀሮ ነበሩ…›› በሚል አገላለጽ ነው። ፍሰቱም በቀጥታ ጉዳዩን መናገር ነው። ሴራ፣ ምልሰት… የሚባሉት የልቦለድ አላባውያን እምብዛም አይታዩበትም።
ጦቢያ ልቦለድም ልክ እንደዚያ ነው። ውስብስብ ገለጻ አያበዛም፤ ወይም ታሪኩን በምልሰት አይደግምም። መጽሐፏ ምዕራፍ የላትም፤ ታሪኩ ይጀመራል፤ ሲያልቅ ያልቃል። ምናልባትም ይህ መጽሐፍ ፊልም ይሁን ቢባል ዘጋቢ ፊልም ሊመስል ይችላል።
ከ1950ዎቹ በኋላ የተጻፉ ልቦለዶች ግን የስነ ጽሑፍ አላባውያን የሚባሉትን ይዘው ነው። እዚህ ላይ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በአንድ የስነ ጽሑፍ መድረክ ላይ የሰማሁትን ልናገር። ክርክሩ ሥነ ጽሑፍ በሥነ ጽሑፍ ህግ ይታሰራል አይታሰርም የሚል ነበር።፡ ልቦለድ ህግ አለው የሚሉቱ እንደ ሴራ፣ መቼት፣ ምልሰት፣ ታሪክ… የመሳሰሉትን የልቦለድ አላባውያን እየዘረዘሩ እነዚህን ማሟላት አለበት አሉ። ተከራካሪዎቻቸው ደግሞ፤ እነዚህ ህጎች ከመውጣታቸው በፊት ልቦለድ ተጽፏል አሉ፤ ምሳሌም ጦቢያን ገለፁ።
ያም ሆነ ይህ ዛሬም ቢሆን ልቦለድ ሁሉንም የልቦለድ አላባውያን የማሟላት ግዴታ የለበትም የሚለው የስነ ጽሑፍ ሰዎችን ያስማማል። የሚጻፈውም የግድ አላባውያኑን ማሟላት አለብኝ ብሎ ሳይሆን የግድ የጽሑፉ ታሪክ ያስገባቸዋል፤ ምናልባትም ሁሉም አለባውያን ላይሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ የትኛውም ልቦለድ ታሪክ አለው፣ መቼት አለው፣ ገጸ ባህሪያት አለው። ሴራም ደካማ ሊሆን ይችላል እንጂ ሴራ አለው። ጦቢያም ሴራ አላት።
ጦቢያ የመጀመሪያዋ ረጅም ልቦለድ መሆኗን የሚነግረን ሌላው ባህሪዋ ደግሞ የገጽ ብዛቷ ነው። በእርግጥ መጽሐፏ ከ1900 ጀምሮ በተለያየ ቅርጽ ስትታተም ስለነበር የገጿ ብዛት ይቀያየራል፤ ሆኖም ግን በ90 እና በ80 መካከል ነው። ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ባላት ቅርጽ ግን 80 ገጽ ብቻ ናት፤ ለዚያውም የቃላት መፍቻዎችን ጨምሮ። ዋናው ይዘት የሚያልቀው ገጽ 71 ላይ ነው። ከመቶ ገጽ በታች የሆነ መጽሐፍ ብዙም አላየንም፤ ስለዚህ ይሄም የመጀመሪያ መሆኗን ያመላክተናል። ዋጋ ወቅቱን ተከትሎ ስለሚሄድ ማሳያ ሊሆን አይችልም።
ሌላው የመጽሐፏ ልዩ ባህሪ እና አሁንም የመጀመሪያ መሆኗን የሚያመላክተን የተጻፈችበት ቋንቋ ነው። የተጻፈችው በአማርኛ ቋንቋ ነው፤ ግን በዚህ ዘመን ያለ ትውልድ ለማንበብ ይቸገራል። ለዚያውም እኮ በየህትመቷ መጠነኛ ማሻሻል እየተደረገባት ነው። አሳታሚዎቹ በመግቢያው ላይ እንደሚናገሩት ማሻሻያ የሚደረገው በጣም መጠነኛ ነው። ታሪካዊ ይዘቷን መልቀቅ የለባትም ብለው በማሰብ ነው። ለዚህም ነው መጽሐፏ ብዙ እንግዳ ቃላት ያሏት፤ እነዚያ ቃላት ግን አማርኛ ናቸው።
በነገራችን ላይ ደራሲው አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ለአማርኛ ቋንቋ መበልጸግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በአማርኛ ቋንቋ ልቦለዶች እንዲጻፉ መንገድ አሳይተዋል። እዚህ ላይ ግን አንድ ነገራቸው ይጠቀስ። የግዕዝ ቋንቋ ከአማርኛ ቋንቋ መላቀቅ አለበት ብለው የሚከራከሩ ናቸው። ግዕዝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ ያገልግል፤ ካልቻለ ይቅር እንጂ ከአማርኛ ጋር መደበላለቅ የለበትም የሚል አቋም አላቸው።
መጽሐፏ የምትጠቀማቸው ቃላት የንግግር ቃላት ናቸው፤ ለዚያውም በገጠር አካባቢ የሚነገሩ ቃላት። ገጠር ውስጥ የሚነገሩ ቃላት ትክክለኛ የአማርኛ ቃላት ናቸው የሚሉ የስነ ጽሑፍ ምሁራንም አሉ። ለምሳሌ ‹‹ጽሑፍ›› የሚባል የአማርኛ ቃል የለም›› ነው የሚሉት። በአማርኛ አጻጻፍ ‹‹ጥሑፍ›› መባሉ ነው እንግዲህ! ይሄ ደግሞ በጽሑፍ ውስጥ ያልተለመደ ስለሆነ ብናገኘውም በስህተት የተባለ ነው የሚመስለን፤ ወይም ግልጽ ትርጉም ላይሰጠን ይችላል። ‹‹ጸ እና ፀ›› ለግዕዝ ቃላት የሚያገለግሉ ሲሆኑ በአማርኛ ‹‹ጠ›› ነው የሚተካቸው።
ከመጽሐፏ አንዳንድ ማሳያዎችን እንኳን ብንወስድ ‹‹አገር›› እንጂ ‹‹ሀገር›› አትልም። ‹‹ሀገር›› የግዕዝ አጻጻፍ ነው፤ በጽሑፍ ውስጥ የምናገኘውም ይሄው ሲሆን በገጠር አካባቢ ግን ‹‹አገር›› እያሉ ነው የሚጠቀሙት። መጽሐፏ በ‹‹ከ›› ቦታ ‹‹ተ››ን ትጠቀማለች። ይሄም የገጠር አካባቢ አገላለጽ ነው። ‹‹ከጓደኛዬ ጋር›› ለማለት ‹‹ተጓደኛዬ›› ጋር ተብሎ ይገለጻል።
መጽሐፏ የመጀመሪያ ልቦለድ ለመሆኗ አሁንም ሌላ ማሳያ እንመልከት።
የሥነ ጽሑፍም ሆነ የፖለቲካ ታሪካችን መነሻው ሃይማኖታዊ ነው። ጦቢያ ልቦለድ መጽሐፍም ታሪኳ ሃይማኖታዊ ነው። ይሄውም ደራሲው በዘመናቸው ያስተዋሉትን መጻፋቸው ነው። የልቦለድ መጽሐፉ ታሪክ በከፊል እንዲህ ነው።
መቼቱ ክርስትና መስፋፋት በጀመረባት ጥንታዊት ኢትዮጵያ ላይ ነው። በወቅቱም በአገሪቱ ተከታታይ ጦርነት ቀስቅሷል። ታሪኩ በአንድ ክርስቲያን ቤተሰብ፤ በተለይም በአባትየውና በመንትያ ልጆቹ (ዋህድ እና ጦቢያ) ዙሪያ ያጠነጥናል። ዋህድ ወንድ ልጁ ሲሆን ጦቢያ ሴት ልጁ ናት፤ 16 ዓመታቸው ነው።
አባትየው በወቅቱ በነበረው አገዛዝ ለባርነት ይሸጣል። ከተሸጠበትም አንድ ቸር ነጋዴ ማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍሎ ነጻ ያወጣዋል። የዚህን ነጋዴ ውለታ ለመክፈል ቆርጦ የተነሳው ልጁ ዋህድ ብዙ ይንከራተታል፤ ስቃይና መከራ ይደርስበታል፤ ሳይሳካለትም እሱም ከባርነት ይወድቃል።
አንድ ዓመት ካለፈ በኋላ አባት ልጁን ዋህድን ፍለጋ ከሴት ልጁ ጦቢያ ጋር ተነሳ፤ ለደህንነቷ ሲባልም እንደ ወንድ አለበሳት። እንደ ወንድ የታጠቀችውን ጦቢያን አስከትሎ የጠፋውን ልጅ ፍለጋ ከመንገድ ገባ። እነርሱም ከባርነት እጅ ወደቁ። ዳሩ ግን አሳዳሪያቸው ንጉሥ በክብር አስተናግዶ፤ ከጠፋው ዋህድና ከነጋዴው ጋር ያገናኛቸዋል።
በልብወለዱ መጨረሻም የጦቢያ እውነተኛ ማንነት ይገለጣል። ንጉሡና አጃቢዎቹም ክርስትናን ይቀበላሉ። ንጉሡ ጦቢያን፣ ዋህድም የንጉሡን አንዲት ዘመድ ያገባል።
የመጽሐፉ አጠቃላይ ጭብጥ ግብረገብነትን ማስተማር ነው። ዋህድ አባቱን ወርቅ ከፍሎ ያስፈታለትን ነጋዴ ለማግኘትና ለማመስገን ነው ያ ሁሉ ስቃይና መከራ የደረሰበት።
መጽሐፏ የገጠር አካባቢ የንግግር ቃላትን ብትጠቀምም አንዳንድ ቦታ ላይ ደግሞ የጽሑፍ ቋንቋና ከተማ አካባቢ የሚነገረውን ትጠቀማለች። እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር መጠርጠር እንችላለን። ምናልባት አሳታሚዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲቀባበሏት በለመዱት አጻጻፍ የመሄድ ችግር ሊያጋጥም ይችላል።
በመጽሐፏ መግቢያ ላይ ከተነገረው መልዕክት አንዱ ይሄ ነው።
‹‹በዚች መጽሐፍ ውስጥ በአሁ ዘመን ደብዘዝ ብለው የሚታዩ አንዳንድ ቃላት ደራሲዋ በአዘጋጁት ጊዜ የነበረውን ስሜት እንዳይቀንሱ በማለት ለንባብ እንዲስማሙ ተስተካክለው እንዳሉ ተጽፈዋል››
‹‹በአሁ ዘመን›› የሚለው ‹‹በአሁኑ ዘመን›› ለማለት መሆኑ ግልጽ ስለሆነ የአንድ ሆሄን ስህተት እንደ ስህተት መቁጠር አያስኬድም። ‹‹ደራሲዋ›› የተባለበት ምክንያት ግን ግልጽ አይደለም፤ ወይም ስህተት ነው። ደራሲው አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ወንድ ናቸው።
ይህን ሀሳብ የወሰድኩት የጎላ ስህተት ሆኖ አይደለም፤ ይልቁንም በቅብብሎሽ ሂደት ውስጥ እንዲህ አይነት ስህተቶች እንደሚያጋጥሙ ለማሳየት ነው። ወይም ሌላ የተባለበት ምክንያት ካለ ግልጽ ማድረግ ነው። አንድ መጽሐፍ ማሻሻያ ሲደረግበት እንዲህ አይነት ስህተት ያጋጥማል። ከዘመናት በኋላ እኮ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ‹‹ወንድ ናቸው ሴት›› የሚል ውዝግብም ሊፈጠር ይችላል።
እዚህ ላይ አንድ የትርጉም መምህራችን የነገረንን ገጠመኝ ልናገር (መጽሐፉን አላስታውስም)። አንድ ተወዳጅ መጽሐፍ በተለያዩ ቋንቋዎች ለብዙ ጊዜ ይታተማል። በዚህ ቅብብሎሽ ውስጥ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ገጸ ባህሪው ዶክተር ሆኖ ተገኝቷል። ምንም እንኳን ጦቢያ ላይ ይህ ያጋጠመን በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ ብቻ ቢሆንም አንድ ቋንቋ በመቶ ዓመት ውስጥ ብዙ ለውጥ ይኖረዋል።
ጦቢያ ታሪካችን ናት። በራስ ቋንቋ መኩራትን አሳይታናለች። በተለይም ረጅም ልቦለድ መጻፍ ቆሟል በሚባልበት በዚህ ዘመን ጦቢያ ቅርሳችንም ናት። አሁን ዘመኑ የወግ እና የአጫጭር ልቦለዶች ሆኗል፤ ከዚህ አለፍ ሲልም አጫጭር ልቦለድ ራሱ እየቀረ ነው። ይህ እንዳይሆን መለስ ብለን የስነ ጽሑፍ ታሪኮቻችንን ልንመለከት ይገባል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011
ዋለልኝ አየለ