የምዕራብ ጎጃሟ ቡሬ ከተማ በዕድሜ የሚመስሉትን ሁሉ እንደ አካባቢው ባህልና ወግ አሳድጋለች። ከእነዚህ መሀል መማር የሚሹት ለተሻለ ዕውቀት ከመንደራቸው ርቀው ሄደዋል። መሥራትና መለወጥ የሚፈልጉትም እንጀራን ፍለጋ ከቀዬያቸው ወጥተዋል። ይህ እውነት ደግሞ እስከዛሬ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ሆኖ ባለበት መንገድ ቀጥሏል።
ቡሬ ተወልዶ ያደገው ሀይሉ መንገሻም እንደ እኩያ ባልንጀሮቹ ትምህርት ቤት ገብቶ መማር የጀመረው በለጋነት ዕድሜው ነበር። ወላጆቹ መልካም ስም እንዳላቸው አንዳንድ ልጆች በዕውቀት እንዲበለጽግ ይሹ ነበር። የተማረ የተመራመረ ሆኖም ወደፊት ስማቸውን በበጎ እንዲያስጠራ ሲመኙ ኖረዋል።
የቤተሰቦቹ ለትምህርት ማተኮር ከግብርናው ይልቅ ለዕውቀቱ እንዲያጋድል ዕድል ሰጠው። ከየዕለቱ የጉልበት ሥራ ርቆም ከደብተሩ የሙጥኝ ማለትን ለመደ። ሲነገረው እንዳደገው ስለ ጠንካራዎቹ የአገሩ ልጆች ስኬት እያሰበም ለአመርቂ ውጤት ሌት ተቀን በረታ። ይሄን ጅምሩን ያዩ አንዳንዶች ጥረቱን አይተው የነገውን ፍሬያማነት ተነበዩ። ወላጆቹ እንደሚያስቡት ለሀገር የሚያኮራ መሆኑን አምነው አወደሱት፤ አበረቱት።
ሀይሉ፣ በትምህርቱ በርትቶ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ቀጠለ። አስረኛ ላይ ሲደርስም ለብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና ተቀመጠ። የቤተሰቦቹ ፍላጎት በአመርቂ ውጤት ከስኬት ላይ መድረስ ነበር። እሱም ቢሆን በትምህርቱ ይበልጥ ልቆ አሸናፊ መሆን ምኞቱ ሆኖ ቆይቷል። ጊዜው ደርሶ የፈተና ውጤት ሲመጣ ግን የታሰበው ሁሉ ከንቱ መሆኑ ታወቀ።
ሀይሉ ከስኬት ይደርሰበታል የተባለው ትምህርት ውጤት አልባ ሆኗል። ይህ ክፉ አጋጣሚ ደግሞ ለቤተሰቦቹና ለእሱ ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆኑ አልቀረም። ውሎ አድሮ ከእሱ ጋር ለፈተና የተቀመጡና መልካም ውጤት ያገኙ ጓደኞቹ ካሰቡት ደረሱ። ሀይሉ ግን በወቅቱ ትምህርቱን ለመቀጠል የሚያስችል ዕድል አልነበረውም።
ከቀናት በኋላ አዲስ ዓመትን የተቀበለው ወጣት ቀጣዩን ጊዜ ያለምንም ቁምነገር ሊያሳልፍ ግድ ሆነ። ትምህርቱ እንደታሰበው ሆኖ ያለመሳካቱም መንደር ውስጥ ከመዋል የዘለለ ምርጫ አልሰጠውም። ተስፋ የለሽ መንገድን መጓዘ የጀመረው ሀይሉ ነገሮች ሁሉ ያለመሳካታቸውን ሲያውቅ መላ በሚለው ሃሳብ ከራሱ ጋር መከረ። የምክሩ ጫፍም አዲስ አበባ የመጓዝ ውሳኔ ላይ አደረሰው።
ሀይሉ ድንገቴው ሃሳቡ ያመጣለት መላ ፈጥኖ ተሳካለት። በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ገብቶም የሸገር ልጅ መሆን ቻለ። ራሱን ለማስተዳደር የመረጠው የዘበኝነት ሥራ ደግሞ እያደር ከብዙዎች አግባባው። አሁን ውሎ በሚያድርበት የጥበቃ ሥራ በቂ ገንዘብ ይዟል። ከተማውን ተላምዶም መውጫና መግቢያውን ለይቷል።
ሥራውን አጠንክሮ የተሻለ ገቢ ማግኘት ሲጀምር አዕምሮው በሌላ ጉዳይ መወጠር ያዘ። ያሰበው ዕቅድ በአግባቡ ከተሳካለት ለከተማ ህይወቱ የሚበጅ ጥሩ ገንዘብ ሊይዝ ይችላል። በላብና በወዝ እንዲሁም በጉልበቱ ድካም ከሚያገኘው በላይም ይሄኛው አማራጭ የሚልቅ ሆኖ ታይቶታል።
ሀይሉ ጥቂት ጊዜያትን በአዲስ አበባ እንደቆየ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። ድንገት ተነስቶ የመሄዱ አጋጣሚም ሲያስብበት ለከረመው ጉዳይ በቂ የሚባል ምላሽ ሰጠው። አገር ቤት ከራርሞ ወደነበረበት ሲመለስ ደግሞ እጆቹ ባዷቸውን አልነበሩም። ውስጡም ቢሆን ከወትሮው ይበልጥ ተስፋ ሰንቆ ነበር። ለዚህ ፈጣን ለውጥ ምክንያት የሆነው ደግሞ በሄደበት ስፍራ የፈጸመው ህገ ወጥ የመሳሪያ ሽያጭና ዝውውር ነበር።
ሀይሉ አዲስ አበባ ተመልሶ ከገባ ወዲህ የኪሱን ገንዘብ ቋጥሮ በህገወጥ መንገድ የያዘውን ብሬታ ሽጉጥ ሸሽጎ አስቀመጠ። ይህን ከማድረጉ አስቀድሞ የሽጉጡን መሥራት በወጉ አረጋግጧል። ጭር ካለ ጫካ ገብቶም የጎረሰውን ጥይት እንዴት እንደሚተፋው በጆሮው ሰምቶ በዓይኖቹም አረጋግጧል። ይህን ካደረገ በኋላም ልበ ሙሉነት ሲሰማው ቆይቷል።
የአዲስ አበባ ህይወትና የሀይሉ ኑሮ ዛሬም በትናንቱ መንገድ ቀጥሏል። እሱ መሳሪያውን በእጁ አስገብቶ ሸሽጎ ቢያስቀምጥም፤ ዛሬም ከዘበኝነት ህይወት አልተላቀቀም። ይህ መሆኑ ደግሞ ዘወትር እያስከፋ ያነጫንጨዋል። የኑሮ ውድነትና በወጉ ራስን ያለመቻል እውነትም በሃሳብ ወንዝ አሻግሮ ይመልሰዋል። ሁሌም ቢሆን በጥበቃ ደመወዝ የልቡ አለመድረስ በትካዜ አውሎ ያስመሸዋል።
አንድ ቀን ሀይሉ ወጣ ባለበት አጋጣሚ ከማስታወቂያ ግርግዳ አንድ ነገር ተለጥፎ አየ። ጽሑፉን በአንድ ትንፋሽ አንብቦ እንደጨረሰም ለውሳኔው በእጅጉ ፈጠነ። አሁን ዓይኖቹ እያሳዩት ያለው እውነት ለእሱ የኑሮ ለውጥ አንድ ዕርምጃ እንደሚሆን አምኗል። ማስታወቂያው እሱን መሰል ወጣቶች ለፖሊስነት ሙያ የሚመለምል በመሆኑ መስፈርቱን እንደሚያሟላ እርግጠኛ ሆኗል።
ጊዜ ያልፈጀው ወጣት፣ ያሉትን መረጃዎች በወጉ አሰናድቶ ለሚመለከተው አካል አቀረበ። መስፈርቱ የሚጠይቀውን መመዘኛ አሟልቶም ለፖሊስነት ሙያ ተመለመለ። እንዲህ በሆነ ጊዜም ወጣቱ ራሱን ሊችል እንደሆነ አስቦ ከልቡ ተደሰተ። ወደ ማሰልጠኛው ሲጓዝም በሙሉ ልብና በተለየ ስሜት ሆነ።
ሀይሉ በጦላይ የውትድርና ማሰልጠኛ ስልጠናውን ጀመረ። በወራት ቆይታውም በቂ የሚባል የወንጀል መከላከል ልምድን አዳበረ። ብቁ ወታደር ለመሆን ቴኳንዶ ተማረ። ራስን ለመከላከል፣ አድማ ለመበተንና ችግሮችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ሙከራዎችን ሁሉ በተግባር አገኛቸው። እነዚህ ፈታኝ የሚባሉ የስልጠና መንገዶች ለእሱ የተለዩ ችሎታዎች ሆነው አብረውት ዘለቁ።
ወታደራዊ ስልጠናው በስኬት እንዳበቃ ሀይሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሆኖ ተቀጠረ። አለባበሱ ተቀይሮም በወታደራዊ አቋም ታየ። ትናንት በሰዎች ደጃፍ የቆመው ማንነቱ ዛሬ ሀገርና ወገንን በንቃት የመጠበቅ ዓላማ ላይ ተመስርቷል። ውሎ አዳሩ በካምፕ ውስጥ ቢሆንም፤ የትናንትናውን የዘበኝነት ታሪክ በመፋቁ ተደስቷል። አሁን ከፖሊስ ሀይሉ የተረከበውን ሙያዊ ግዴታ የሚወጣበት ጊዜ ነው። ይህን ዕውን ለማድረግም ባንዲራ ይዞ ቃልኪዳን የገባለት ሙያው ሊያስገድደው ግድ ሆኗል።
ፖሊሱ ሀይሉ ከስሙ ፊት «ኮንስታብል» የሚለው መጠሪያ ታክሎ መጠራት ጀመረ። አሁን አምና አብሮት የነበረ የበታችነት ስሜት አልተከተለውም። ዘንድሮ ቁርጠኛ ፖሊስ ሆኖ አገሩን ሊያገለግል ተዘጋጅቷል። የፖሊስነት ሙያ ራስን ከመቻል ባለፈ ኃላፊነቱ ከባድ ነው። ሰላምና ደህንነትን የማስጠበቅ ግዴታውም ከሌሎች ወገኖች ይበልጥ በሙያው ትከሻ ላይ ሊወድቅ ግድ ይላል። ኮንስታብል ሀይሉም ይህን እውነታ ጠንቅቆ ያውቀዋል።
ሀይሉ በሙያው ተሰማርቶ ፖሊስ መባል ከጀመረ ወራት ተቆጠሩ። በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከመሰሎቹ ጋር እየተዘዋወረ ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅም የየዕለት ግዴታው ሆነ። ይህ አጋጣሚ ግን እንደ መጀመሪያዎቹ ወራት የሚያስደስተው አልሆነም። ውስጡ በማንነቱ ቢኮራም ወር ደርሶ ደመወዝ ሲቀበል ግን ይከፋና ይነጫነጭ ጀመር።
ልፋቱን ከወር ደመወዙ ጋር የመዘነው ሀይሉ፣ ውጤቱ ከድካሙ አልመጥን ቢለው በትካዜ ውሎ ማደርን ለመደ። ከዘበኝነት ሥራው ርቆ ፖሊስ መባሉም ከእርካታ ጥግ አላደርስ አለው። ይህኔ ፈጥኖ መለወጥ የሚሻው ማንነቱ በተስፋ መቁረጥ ተናወጠ። ይህ ስሜት ሲደጋገም ደግሞ ውስጡ በሌላ ሃሳብ ተሞልቶ ለመፍትሔው ቀዳዳዎችን አበጀ።
ሀይሉ ቀድሞ ከአገር ቤት ያመጣው ህገወጥ መሳሪያ በእጁ ይገኛል። ይህን ጥሪቱን በደህና ዋጋ ቢሸጠው ደግሞ ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደሚያገኝበት እርግጠኛ ነው። ይህን ከማድረጉ በፊት ግን ተመልሶ ወደ አገሩ መግባት ፈልጓል። ወደስፍራው ለመሄድ የፈለገው ደግሞ አዲስ ዓመትን በማሳበብ ነበር። ለዚህ ቆይታውም ሰፋ ያለ ጊዜ ያስፈልገዋል። የፍላጎቱን አድርሶ ባሰበው ጊዜ ለመመለስ ግን አሳማኝ ምክንያት ሊፈልግ ግድ ነው። ይህን ካላደረገ አለቆቹ በቂ ፈቃድ አይሰጡትም።
ሀይሉ ሀገሩ ቆይቶ የሚመለስበትን ምክንያት ሲያወጣና ሲያወርድ ሰነበተ። አንድ ቀን ግን አዕምሮው በአንድ ሃሳብ ላይ አተኮረ። ከዚህ ሃሳብ ጋር ፈጥኖ ለመስማማትም የፈጠነ ሆነ። ያቀደውን በምን መልኩ ማሳመን እንደሚኖርበት ሲያቅድ ቅንጣት ታህል አልተቸገረም።
የቅርብ አለቃው ዘንድ ገብቶ አንገቱን ደፍቶ ሲቀርብ ዓይኖቹ በዕንባ ተሞልተውና ፊቱ በኀዘን ድባብ ተሸፍኖ ነበር። ሲቃ እያነቀው ታላቅ እህቱ በድንገት መሞቷን ሲናገርም ለሰሙት ሁሉ የሚያስደነግጥና ኀዘን ብሎ ፈቃድ የወሰደው በህይወት ባለችው እህቱ ስም ነበር። እንቁጣጣሽን በደስታ ሲዝናና ያሳለፈው ወጣት፣ ለኀዘን በሚል የወሰደው ፈቃድ እንዳለቀ ወደ መስሪያ ቤቱ ተመለሰ። ይህ ከሆነ ከጥቂት ቀናት በኋላ ዳግም አለቃው ዘንድ ቀርቦ የዓመት ፈቃዱን ጠየቀ።
የሀይሉ አለቃ ማመልከቻውን ሲያዩ ጥያቄውን ለመመለስ አልፈቀዱም። ለምክን ያታቸው በቂ የሆነ ምላሽ አስቀምጠው ሥራውን እንዲቀጥል ነገሩት። ይህን የሰማው ሀይሉ ሲበሳጭ ዋለ። እሱ እንዳሰበው ሆኖ ፈቃዱን ያለማግኘቱም በእጅጉ አናደደው። ይህን ስሜቱን የሚያረግብበትን ሲያስብ ደግሞ እግሮቹ ወደ አንድ አረቄ ቤት አራመዱት።
ጨርቆስ ሰፈር ሲዝናና ባመሸበት አረቄ ቤት ሲጠጣና ሲረብሽ አደረ። የድርጊቱን መላ ማጣት ያስተዋሉ አንዳንዶችም ሲታዘቡት ቆዩ። ማንነቱን ያወቁ ብዙዎችም ፖሊስ ሆኖ ባልተገባ ስፍራ በመገኘቱ አጥብቀው ኮነኑት። ይህ አስነዋሪ ድርጊት በመረጃ በመረጋገጡ የሥራ ክፍሉ በምክርና በማስጠንቀቂያ ሲያሳስበው ቆየ። በእሱ ላይ ግን እያደር ስነምግባር ይሉት መልካም ባህርይ ጠፋ። ስሙ በጎ ባልሆኑ ድርጊቶች መነሳቱም እንደተለመደ ቀጠለ።
አሁን ሀይሉ የተሰማራበት የሙያ ግዴታው እየሰለቸው መጥቷል። በወር የሚያገኘው ደመወዝ በቂ ያለመሆኑም ዘወትር ያበሳጨው ይዟል። በሥራው አጋጣሚ በተለያዩ ስፍራዎች ቢዘዋወርም በኑሮው ላይ ለውጥ ማምጣት አልቻለም። ዘወትር የግል መሳሪያውን እንደያዘ አርቆ ያስባል። ወገቡ ላይ የተሰደረውን ምስጢር እየነካካም ለመፍትሔው እያወጣ ያወርዳል።
መስከረም 12 ቀን 2003 ዓ.ም
ሀይሉ በዚህ ቀን እንደተለመደው ሲተክዝና ሲጨናነቅ ውሏል። የራሱን መሳሪያ ይዞ የወጣው ገና በማለዳው ቢሆንም፤ ከሸክም ሌላ የተረፈው ነገር አልነበረም። ሁሌም መሳሪያውን በያዘ ቁጥር የሚያስበው ጉዳይ ከሃሳብ ያለመዝለሉ ያስገርመዋል። ዛሬ ግን ያገኘውን አጋጣሚ ሊያልፍ እንደማይገባ ውስጡ ሹክ እያለው ነው።
መርካቶ ራጉኤል አቅራቢያ ከሚገኘው አንድ ሕንፃ ስር ተቀምጦ ወጪ ወራጁን የሚቃኘው ሀይሉ፣ አዕምሮው አርቆ ማሰብ ይዟል። ዛሬ አንድ ነገር ሳይፈጽም መመለስ እንዳማይኖርበት ደግሞ ገና ከቤቱ ሲወጣ ወስኖ ነበር። አሁን የተቀመጠበት ስፍራ ለአቢሲኒያ ባንክ የቀረበ መሆኑ ወደ ባንኩ የሚገቡና ከባንኩ የሚወጡ ሰዎችን አጥርቶ ለማየት ያመቸዋል።
በርካቶች በዚህ መንገድ ተመላልሰው በባንኩ እየገቡ ወጥተዋል። ጥቂቶቹ በመኪና፣ ገሚሶቹ በእግራቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ከሌሎች ጋር ሆነው በባንኩ ሲመላለሱ መዋላቸውን ታዝቧል። ከእነዚህ መሀል ግን ዓይኖቹን የሳበችው አንዲት ሴት ብቻ ሆናለች። ወጣቷ በአንድ እጇ ፌስታል ቢጤ ይዛ ወደ ባንኩ ስትገባ በትኩረት ቃኝቷል። ጥቂት ቆይታም ከባንኩ ስትወጣ ዓይኖቹ በትክክል አረጋግጠዋል።
አሁን ሀይሉ ከወትሮው ይበልጥ እየነቃ ነው። የአካባቢው ጭርታና የወጣቷ መዘናጋት ደግሞ ዕቅዱን እንዳሰበው እንደሚያሳከለት ተማምኗል። ይህን ሲያስብ ቃል የገባለት ሙያው ውል አለው። ሀገርና ወገኑን ደህንነታቸውን ከሚያሰናክል ስጋት ለመመከትና የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ የእሱ ፖሊስነት ደጀን እንደሚሆን ጠንቅቆ ያውቃል። ይህ እውነታ ውል ይበለው እንጂ አሁን እሱን በማሰብ ጊዜ ማጥፋት አልፈለገም።
ሀይሉ ከተቀመጠበት ሆኖ አካባቢውን በድጋሚ ቃኘው። ላሰበው ዕቅዱ እምብዛም የሚያሰጋ ሆኖ አልታየውም። ወጣቷ ከባንኩ ወጥታ ታክሲ ለመያዝ ከአስፓልቱ ጫፍ ቆማለች። ቀረብ በሎ አስተዋላት። በእጇ የያዘችው ቦርሳ ሞላ ብሏል። የሚያልፍ መስሎ ብሬታ ሽጉጡን አወጣ። ክፉኛ ደንግጣ እየተንቀጠቀጠች አየችው። ይሄኔ በሽጉጡ ሰደፍ የቀኝ ሽንጧ ላይ መቶ ከመሬት ጣላት። እስክትጮህ አልጠበቀም። በእጇ ያለውን ቦርሳ መንትፎ ወደ አሜሪካን ግቢ በሚወስደው መንገድ ቁልቁል ተፈተለከ።
ጥቂት ቆይታ ወጣቷ መጮህ ጀመረች። በስፍራው የነበሩና ሁኔታውን ያስታወሉ መንታፊውን ሊይዙ በሮጠበት ተከተሉት። ሌሎች ደግሞ በደረሰባት ምት ጉንጯ ተሰንጥቆ እየደማች ያለችውን ተጎጂ ከወደቀቸበት ሊያነሱ ፈጠኑ። ወዲያው ወጣቱ ፖሊስ በፖሊስች ተይዞ ብቅ አለ። ቦርሳውን ወርውሮታል ብሬታ ሽጉጡ ግን እጁ ላይ ይታያል።
ወጣቷ መንገደኛ እሱ እንዳሰባት ብዙ ገንዘብ ልታወጣ የገባች ደንበኛ አይደለችም። የባንኩ ሠራተኛ በመሆኗ ለሥራ የተዘጋጀ ቼክ አሠርታ ወደ ሌላ ባንክ እያመራች ነበር። በቦርሳዋም ዣንጥላና ጥቂት ገንዘብ ብቻ ይዛ ነበር።
የፖሊስ ምርመራ
ያልታመነውን ታማኝ እጅ ከፍንጅ ይዞ መመርመር የጀመረው ፖሊስ የሆነውን ሁሉ ከስፍራው ደርሶ በማስረጃዎች አረጋግጧል። የተሰጠውን የህዝብ አደራ በመዘንጋት በውንብድና ወንጀል ተሰማርቶ መገኘቱንም በበቂ መረጃዎች አደራጅቷል። የውግ ቁጥሩ 1704765 ብሬታ ሽጉጥ ከመሰል አምስት ጥይቶች ጋር ለመንግሥት ገቢ ሆኗል። በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 219/03 የተደራጀው ክስ በረዳት ሳጂን አንዋር ጀማል ተጣርቶም ክሱ ለዐቃቤ ህግ ተላልፏል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011
መልካምስራ አፈወርቅ