የተወለዱት ጅማ ዞን ውስጥ ሰጠማ ወረዳ በ1945 ዓም ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ኢሉባቡር በደሌ ከተማ ራስ ተሰማ ናደው ትምህርት ቤት የተማሩ ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ነው የተከታተሉት። በህግና በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፎች ሁለት ዲፕሎማዎችን መያዝ ችለዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲት በፊዚክስ ትምህርት ገብተው ለሁለት ዓመት ከተማሩ በኋላ ግን በአገሪቱ በተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ለማቋረጥ ተገደዋል። ከዚያም ወደ ዩክሬን በመሄድ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።
በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርጎ የቆዩት እኚሁ ግለሰብ በተለይም ከ1987 እስከ 1997 ዓ.ም በግል ተወዳድረው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ ገዢውን ፓርቲ በመሞገትና በመተቸት ይታወቃሉ። በ1997 ዓ.ም ደግሞ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲን ተቀላቅለዋል።
በአዲስ አበባ ወረዳ 7 (አውቶቡስ ተራ አካባቢ) ተወዳድረው በማሸነፍ የፓርላማ ወንበር አግኝተዋል። ነገር ግን በወቅቱ በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ የተነሳ ፓርላማውን አልተቀላቀሉም። ከዚያ ይልቅ የቅንጅት አመራሮች ሲታሠሩ እሣቸውም ታስረዋል። በፍርድ ቤት ተከራክረውም በነፃ ተሠናብተዋል።
በ2000 ዓ.ም መጨረሻ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ግን ከፖለቲካው መድረክ ጠፍተው ከርመዋል። የዛሬው የዘመን እንግዳችን አቶ በድሩ አደም እስከዛሬ የት ነበሩ? ለምንስ ጠፉ? አሁን ስላለው የፖለቲካ ስንክ ሳር የሚሉን አላቸው። ከእንግዳችን ጋር የነበረንን ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርበዋለን።
አዲስ ዘመን፡- ለበርካታ ዓመታት ጠፍተው የቆዩበት ምክንያት ምን ነበር?
አቶ በድሩ፡- በነበረው ስርዓት ምክንያት ነው የጠፋሁት። በነበረው መንግሥት በጣም ተጎድቻለሁ። በዚያ ምክንያት ዴሞክራሲ ይመጣል ብዬ ብዙ ታግያለሁ። ነገር ግን በዚያ ሰበብ ብዙ እንግልትም ደርሶብኛል። ከዚያ በፊት ሃሳብን በነፃነት በዛም፤ አነሰም መግለጽ እንችል ነበር። ወደ ኋላ የመጣው ምርጫ ሳይሆን ቅርጫ ነው።
ዴሞክራሲውም ዘቀጠ። በወቅቱ ቅንጅት ውስጥ በነበረኝ ተሳትፎ ምክንያት ብዙ በደል በእኔም ሆነ በቤተሰቦቼ ላይ ደርሶብናል። ስለዚህ ፍትህ እስኪመጣ፤ የዴሞክራሲ አየር እስኪነፍስ ድረስ ህይወቴን ማቆየት ስለሚያስፈልግ ነው ዞር ያልኩት። ዞር ብልም ግን ክትትሉ አልቀረልኝም ነበር። በየደረስኩበት ያሳድዱኝ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ከነበሩ የቅንጅት አባላት መካከል እርሶ ምን የተለየ ወንጀል ስለሠሩ ነበር የተለየ ክትትል ሲደረግቦት የነበረው?
አቶ በድሉ፡- እውነቱን ለመናገር እኔ ወንጀል ሠርቼም አላውቅም፤ ወንጀል መሥራትም አልፈልግም። በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ሠርቻለሁ፤ የተለያዩ አገራትንም ዞሬ ተመልክቻለሁ ግን አንዱ ምክንያታቸው 1997 ዓ.ም ምርጫ ላይ መሳተፌ ትልቅ ግጭት ውስጥ ገባን። እኔ ሳላስበው ግን ደግሞ ፈጣሪ ምላሴ ላይ አድርጎ የተናገርኩት ነገር በተለየ ሁኔታ ትርጉም ተሰጥቶት ትልቅ ዘመቻ ተደረገብኝ።
በእኔ ብቻ ላይ ሳይሆን በልጆቼና በባለቤቴ ላይ ጭምር ነው። እውነቱን ለመናገር የነበረው ፖለቲካ በጣም የዘቀጠና የወረደ ከመሆኑ የተነሳ ከልጆቼ እናት ጋር ለመፈታት የበቃነው በፖለቲካው ተጽዕኖ ምክንያት ነው። ቤተሰብ መሃል ገብቶ እስከማፍረስና ማጣላት ድረስ የተደረሰበት ሁኔታ ነበር።
ሌላው ቀርቶ ስንፋታ የተመደበው ዳኛ ፀያፍ ሥራ ነው የፈፀመው። ፍቺም ያደረግነው በፖለቲካ ባለስልጣናት ተፅእኖ ነው። ከሁሉ የሚያሳዝነኝ ግንቦት 27 ቀን ዳኛ ለቤተሰብ ጉባኤ እንዲታይ ጉዳያችን ታዞና ለሰኔ 14 ቀን ቀጠሮ ሰጥቶ ሳለ በቤተሰብ ሳንሸማገል በቀጠሮው ዕለት ያለምንም ክርክር ፍቺው መፈፀሙን የሚገልጽ ደብዳቤ በመዝገብ ቤት በኩል እንዲደርሰን መደረጉ ነው።
ደብዳቤውም ከግንቦት 27 ጀምሮ ፍቺው መፈፀሙን ነው የሚገልጸው። ይህ የሆነው ህጋዊ አካሄዱን በጣሰ መልኩ ነው። ይህ ትክክል አይደለም ብዬ ስቃወም ሰኔ 14 ላይ ፍቺ መፈፀሙን የሚያመላክት ደብዳቤ ደረሰኝ። ሁለቱም በእጄ ይገኛል። ይህም ፖለቲካው ምን ያህል የተጨማለቀ እንደሆነ ያሳያል።
እንግዲህ እስከዚህ ደረጃ ነው ተጽዕኖ ሲያደርስብኝ የነበረው። እንዲህ ዓይነት አሳፋሪና ቤተሰብን አራት ልጆችን ከወላጆቻቸው ለመነጠል ይህን ያህል የሚደረግበት አገር ውስጥ ነው ያለነው። በሄድኩበት ሁሉ በተሽከርካሪ ይከታተሉኝ ነበር። ይህም አልበቃ ብሏቸው ህዳር 16/ 2010ዓ.ም ወደ መስኪድ ለመሄድ ከጠዋቱ 11 ሰዓት አካባቢ ከቤቴ ስወጣ አስፓልት ዳር ቆሞ የሚጠብቅ ሰው ነበር።
ሲከታተለኝ ቆይቶ ትራኮን ሕንፃ ጋር ሲደርስ ጠፋ። በኋላ ትንሽ ከፍ እንዳልኩ ጣፋጭ ኬክ ቤት ሳልደርስ አራት የሰለጠኑ የሚመስሉ ሰዎች ከኋላዬ መጥተው አነቁኝና ጣሉኝ። ከዚያ ከ1 ሰዓት 45 ደቂቃ በኋላ ወንዝ ውስጥ ያለ ድንጋይ ላይ ነው ተጥዬ ራሴን ያገኘሁት።
ደብዳቢዎቹ በወቅቱ ሞቷል ብለው ነው ጥለውኝ የሄዱት፤ ምንም አላስቀሩልኝም ነበር። የነበረኝን ማስረጃ ብጣሽ ወረቀትና ሳንቲም ሳይቀር ነው ዘርፈውኝ የሄዱት። ስለዚህ ህይወቴንም ፈጣሪ ነው ያቆየልኝ ብዬ ነው የማምነው። በዚያ ምክንያት ምንም ማድረግ አልቻለኩም። በወቅቱ መደበቁ አስፈላጊም ነበር፤ ተደብቄም ግን አላመለጥኩም።
አዲስ ዘመን፡- በድብደባው ምክንያት ዘላቂ የሆነ የአካል ጉዳት ደርሶቦታል?
አቶ በድሩ፡- አዎ! እሰከአሁን ድረስ ጉሮሮዬ ላይ በደረሰብኝ ድብደባ በደንብ መናገር አልችልም፤ ህመሙም አሁንም ድረስ አለ፤ ሙሉ ጤናዬም አልተመለሰም።
አዲስ ዘመን፡- ለምን ያህል ዓመታት ነው ተደብቀው የቆዩት? በቤተሰቦቾት ላይ የደረሰ ጫና ካለ ይንገሩን?
አቶ በድሩ፡- ለ13 ዓመታት ነው። እንላድልሽው ከእኔ አልፎ ቤተሰቦቼ ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድሩባቸው ነበር። በተለይ የበኩር ልጄ እንደእኔ ግልጽ ስለምትናገር ብዙ ጫና ደርሶባት ነበር። በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የህግ ተማሪ ስለነበረች አባቴ የደረሰውን የዴሞክራሲ ጫፍ አደርሳለሁ ብላ ስትናገር አሰሯት፤ ገረፏት። ከፍተኛ ስቃይ አደረሱባት። በዚህ ምክንያት ትምህርቷን ከአራተኛ ዓመት አቋርጣ ነበር። አሁን ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተወዳደራ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝታ እየተማረች ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በምን ሁኔታ ነው እየኖሩ ያሉት? ወደ ፖለቲካውስ የመምጣት እቅድ የለዎትም?
አቶ በድሩ፡- እንግዲህ በአሁኑ ወቅት የምኖረው በጡረታዬ ነው። ለልጆቼም ጡረታ ይቆረጣል። አንዳንድ ቦታ ላይ በማማከር ገንዘብ ለማግኘት እሞክራለሁ። ብቻ ፈጣሪ ይመስገን ባለኝ ህይወት ደስተኛ ነኝ። ወደ ፖለቲካውም የመመለሱ ጉዳይ ፍትህ ከመጣ የማይቀር ነው። ቅርጫ ሳይሆን ምርጫ ከመጣ ህይወቴ እስካለ ድረስ መመለስ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለደረሰቦት ጉዳት በ1997 ዓ.ም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተናገሩት ንግግር ምክንያት እንደሆነ ይገለፃል፤ ምን ያህል እውነት ነው? እስቲ በወቅቱ የተናገሩትን ንግግር ያስታውሱን?
አቶ በድሩ፡- የተናገርኩት ንግግር ወንጀል አልነበረም። ይህም በመሆኑ ነው በወቅቱ ይቅርታ ጠይቅ ስባል አልጠይቅም ያልኩት። ፍርድ ቤቱም ይህንን አረጋግጦልኝ ነበር። ቢበዛ ከአምስት ወር በላይ ሊያስቀጣ እንደማይችል ተገልፆ በነፃ ነው የተለቀቅሁት። በመሰረቱ በመስቀል አደባባይ ላይ የተናገርኩት በአጋጣሚ ነው።
በወቅቱ ፅሑፍ እንዳቀርብ የታዘዝኩት ሦስት አርስቶች ላይ ሲሆን አንደኛው የውጭ ግንኙነት ላይ ነበር። በዚያ ርዕስ ዶክተር ብርሃኑና ዶክተር ያዕቆብ በወቅቱ ከአቶ ስዩም መስፍን ጋር ሲከራከሩ ዶክተር ብርሃኑ አንድ ነገር ተሳስቶ ተናገረ። ያም ምንድን ነው ዶክተር ብርሃኑ ‹‹ብዙሃኑ ደቡብ ሱዳን እያለ የምትሞዳሞዱት ከሰሜን ሱዳን ጋር ነው›› ብሎ ተናገራቸው።
ያን ጊዜ አቶ ስዩም «ይኸውላችሁ ኢንተርሞዮች ከጎረቤት ጋር ሊያጣሉን ተዘጋጅተዋል» ብሎ ተጠቀሙበት። ዶክተር ያዕቆብም ከድጡ ወደ ማጡ ሆነና «ኢትዮጵያ በሙሰሊሙ ዓለም ስትከበብ ዝም ብላችሁ ታያላችሁ» ብሎ ተናገረ። ያን ጊዜ አቶ ስዩም «አሁንም ተመልከቱ እንግዲህ ከዓለም አገራት ጋር ሊያጋጩን ነው» ሲሉ ጥሩ አድርገው ተጠቀሙበት። እናም ለዚያ የመልስ ምት የሚሆን የውጭ ጉዳይ ፖሊስ እንዳቀርብ ነበር የታዘዝኩት።
ሌላው ጉዳይ በፆታና በሃይማኖት ጉዳይ ላይ ነው ፅሑፍ እንዳቀርብ የተነገረኝ። እውነቱን ለመናገር እንደ ኢህአዴግ ሙስሊሙን የተጫነ
ወይም የበደለ የለም። ይህንን ስልም ያለ ምክንያት አይደለም፤ አፄ ዮሐንስ በአንድ ቀን በሺዎቸ የሚቆጠሩ ወለዮዎችን ጨርሰዋል። ግን ኢትዮጵያዊነቱን አልካዱም። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግን ሙስሊሙ ሳውዲ ሲሄድ ሊሴ ፓሴ (የይለፍ ወረቀት) እንዲያወጣ አዘዋል። የይለፍ ወረቀት የሚሰጠው አገር ለሌላቸው ስደተኞች መንግሥት ለሌቸው ነው እንጂ ለዜጋ አይሰጥም።
እንግሊዝ አገር የይልፍ ወረቀት የሚሰጡት መጤዎችን ለመፈረጅ ታሳቢ ተደርጎ ነው። በእኔ እምነት ሙስሊሙም በዚህ መልኩ ነው የተፈረጀው። ለነገሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ተከራክሪያለሁ።
ደግሞም በወቅቱ የነበሩ ሚዲያዎች ላይ ቀርቤ አቋሜን በተከታታይ ገልጫለሁ። የሚገርመው ክርስቲያኑ ወደ እየሩሳሌም የሚሄደው በፓስፖርት ነው። ይህም አሠራር ሙስሊሙን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ወይም አገር የለሽ ህዝብ ከማድረግ ነው የሚቆጠረው። ከ12 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያዊያን በሊሴ ፓሴ እንዳይገቡ ተከልክለዋል።
እናም እነዚህን ጉዳዮች ለማቅረብ ወደ መስቀል አደባባይ በምንሄድበት ጊዜ ከሰላማዊ ሰልፈኛው ያልተነናነሰ እና እንደ ችቦ የታጨቀ ወታደር ተሰልፏል። እንደአጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ኃይለኛ ዝናብም መጣ። ይሄ ወታደር ተሳስቶ አንድ ጥይት ቢተኩስ ህዝቡ በመረጋገጥ ያልቃል የሚል ስጋት ያዘን።
በወቅቱ ኢንጅነር ሃይሉ (ነፍሳቸውን ይማርና) ዝናቡም ስለመጣና ሁኔታው አስጊ በመሆኑ ንግግሩን ባናደርግ የሚል ሃሳብ ያመጣሉ። ከንግግሩ ይልቅም መፈክር አሰምተን ሰልፈኛን መሸኘት እንዳለብን ወሰንን። በዚያ መሰረትም እኔ መፈክር በማሰማበት ጊዜ ምላሴ ላይ ምን እንዳመጣ አላውቅም የዛሬ ዓመት አንድ በፈጣሪ ሁለተኛ በእናንተ ጡንቻ ትግሬ ወደ ነበረበት ይመለሳል ነው ያልኩት።
አዲስ ዘመን፡- ምን ማለቶት ነበር?
አቶ በድሩ፡- ገጠሬው ወደ ነበረበት ይመለሳል፤ እኛ እናሸንፋለን ማለት ነው። የተናገርኩት ይኸው ብቻ ነው። ነፃ የወጣሁትም የተናገርኩት ወንጀል አለመሆኑ ተረጋግጦ ነው። ለምሳሌ አንቺ ሸዋ ነበርሽ ወደ ሸዋ ትመለሻለሽ፤ ብልሽ ወንጀል አይደለም። ለነገሩ እንደ አተረጓጓምሽ ነው።
ለዚህች ቃል ግን ብዙ ትርጉም ተሰጠው። በእርግጥ የፈጣሪ ቃልም ነው የምለው ለዚህ ነው። አቶ ገብሩ አስራት ፅፈዋል። ትንቢቱ እንደተፈፀም ነው ብዙዎች እየተናገሩ ያሉት። ተመስገን ደሳለኝም «አፈገር በጊሻራ» የሚል ርዕስ ሰጥቶት በፍትህ ጋዜጣ ላይ አውጥቷል። ብዙዎቹም ፅፈውበታል።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ንግግርዎ አይጸጽትዎትም?
አቶ በድሩ፡- ኸረ እኔ አልፀፀትም፤ እንደዛሬ መሆኑን ባውቅም የባሳም እናገር ነበር። ምክንያቱም ትክክል እንደተናገርኩ ነው የማምነው። ምንም የሚያፀፅተኝ ነገር የለም። ትክክል ነው የተናገርኩት። ምክንያቱም ይቅርታ አድርጊልኝና ተላላኪ ትግሬ እኮ ነበር ሚኒስትሩን የሚያዘው። ይህ መሆኑን አልቀበለውም ነበር። መመለሳቸውም ጥሩ ነው። አገርን በጋራ እናስተዳደር። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘና እኩልነት ካለ ማለት ነው።
የዘረኝነት ፖሊሲን አልቀበልም። የዘር ፥ የሃይማኖት እኩልነት በሌለበትና የአንድ ብሄር የበላይነት የተጠበቀበት ስርዓት ስለነበር በእርግጥ ተቃውሞ ነበረኝ። በየቦታውም ገልጫለሁ። ሌላም ጊዜ እናንተ ተከዜን ትሻገሩ ሴይጣን ነው የሚለክፋችሁ ብያቸዋለው። በዚህ ንግግሬም አስረውኝ ነበር። ስለዚህ ደፍሬ በምናገራቸው ነገሮች አምኜ ስለሆነ ምንም አልፀፀትም።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የምክር ቤት አባል በነበሩበት ወቅት በምክር ቤቱ የነበረው የመናገር ነፃነትና ድባብ ምን ይመስል ነበር? አሁን ካለው ጋርም ያነፃፅሩልኝ?
አቶ በድሩ፡- አሁን ፈጣሪ ይመስገን ይባላል። ምክንያቱም የኢህአዴግ አባላት ራሳቸው አፍ አውጥተው መናገር የቻሉበት ጊዜ በመድረሳቸው ማለት ነው። በዚያን ሰዓት መተንፈስ የለም፤ አብዛኛው አድርባይና ፈሪ ነበር። እኔ በወቅቱ ያለኝ ዕድል ራሴን አዘጋጅቶ መግባት ብቻ ነበር።
546 የኢህአዴግ አባላት ባሉበት ምክር ቤት አፋቸውን የሚዘጋልኝን ስትራቴጂ ቀይሼ ነበር የምሄደው። ይህንን ማድረግ ካልቻልኩ ማሸነፍ አልችልም። ድምፅ ባላገኝ ቢያንስ ድምፅ አሳጣለሁ። ይህም ማለት እውነትን መካድ ስለማይችሉ እኔን ባይደግፉኝም ዝምታ ይመርጣሉ። ስለዚህ የማቀርበው ሃሳብ በሙሉ መቶ በመቶ በመረጃና ማስረጃ የተደገፈ ነው። እኔ ይህንን እንደሥራ ነበር የምቆጥረው።
የሚገርምሽ ከኢህአዴግ አባላት ጋር ውጪ እንስማማለን፤ ምክርቤት ውስጥ ሲሆን ግን ትንፋሻቸው ይጠፋል። በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ አባላት አንዳንድ ነገር ሲናገሩ ስሰማ ለእኛ ሳይሆን ለእነሱም ነፃነት መጥቷል ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ቀደም ድምፃቸው ታፍኖ ነበር። መናገር አይችሉም።
ስለዚህ የዛሬው ፓርላማና የቀድሞው በጣም ልዩነት አለው። እውነት እያለና አፍጥጦ የሚክዱ ነበሩ። በተለይ አቶ አስመላሽን በጣም አዝንበታለሁ። ጭንቅላት እንዳለው ባልክድም ነገር ግን እውነታውን ይክዳል። እንዲነገርም አይፈልግም። እውነታው ሲነገር ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ይበሳጭ ነበር። ሌሎቹ እንኳን አድርባዮች ነበሩ። ሌላው ይቅርና ለቤተሰቦቻቸው እንኳ የማያስቡ ሰዎች ነበሩ።
በሃገር ጉዳይ ለሚነሳ ጉዳይ ከመደገፍ ይልቅ የሚፃረሩ ነበሩ። ሞራልሽን የሚነካ ነገር ነው። እንዲያውም አንድ ጊዜ አንድ የዳውሮ ተወካይ የተናገረው ንግግር ህሊና ካለው ሰው የማይጠበቅ ነው። በእርግጥ አምነውበት አይደለም። ልወደድ ብለው፤ ለመሾም፥ ውጭ አገር ለመሄድ፥ አበል ለማግኘት ሲሉ ነው አድርባይ የሚሆኑት። እናም ብዙዎቹ በጣም የሚያሳዝኑ ናቸው። የዛሬዎቹ ግን በብዙ መልኩ የተሻሉ ናቸው። ለነገሩ እንኳን እነሱ እኛም ነፃ ወጥተናል።
አዲስ ዘመን፡- በምክር ቤት የኢህአዴግ ሹመኞችን ለመርታት ሲሉ መረጃ እስከ መግዛት ድረስ ጥረት ያደርጉ እንደነበር ሰምቻለሁ። ይህ ምን ያህል እውነት ነው? ከየትስ ነበር የሚገዙት?
አቶ በድሩ፡- ያልሽው እውነት ነው፤ እኔ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስም ነግሬዋለሁ። ከአንተ ቢሮ መረጃ ገዝቼለሁ፤ ማስረጃ አግኝቻለሁ ብዬ ነግሬው ነበር። በተለይ በጣም የማረልሳው አንድ ወቅት ላይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የወሰነው ውሳኔ አንድ ግለሰብ እያወጣ በራሱ መንገድ እያሻሻለ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚልክ መረጃ አገኘሁ።
ያኔ የመድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ የነበረ ግለሰብ በእንስሳትና በሰው መድሃኒት ላይ አንድ የአዋጅ ማሻሻያ ሲቀርብ በአንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 16 ላይ የሰውን መድሃኒት መድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ፥ የእንስሳትን መድሃኒት የግብርና ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ የእንስሳት ሃኪሞች እንዲያስተዳድሩ የሚገልፅ ሰፋ ያለ አንቀፆች ነበሩ።
ግለሰቡ ጤና ጥበቃን ወክሎ ይህንን አዋጅ ወስዶ ለግብርና ሚኒስቴር የተሰጠውን ኃላፊነት ለመድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን እንደሆነ አድርጎ ይፅፋል። እንግዲህ ልብ አድርጊ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወሰነው ቃለጉባኤ ነው በራሱ መንገድ የቀየረው። ይህ ሲሆን ማንም አላየውም።
ሁሉም ፈርሞ ለምክር ቤት ይላካል። ይህም አዋጅ ተባዝቶ ሲታደለን ሆኖ ተብሎ የተፈጠረውን ክፍተት አስተዋልኩ። እናም ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔን አውቀው ስለነበር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔን ኮፒ በገንዘብ ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ገዛሁኝ። ያንን ይዤ ገባሁ። ፓርላማ ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ ተደረገ።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ለአንተ ወዳጅ ሆነው የሚቀርቡት ግለሰቦች የምክር ቤት ውሳኔን ሰርቀው ለእነሱ በሚበጃቸው መልኩ የሚያዘጋጁ በመሆኑ ዝም ብለህ አጠገብህ ያሉትን ሰዎች በሙሉ አትመን አልኩት። በዘር ብቻ አስበው ዘመዶችን ብታምን ችግር ያመጣብሃል ብዬ መክሬዋለው።
በዚህ መልኩ ከስድስት ጊዜ በላይ ከመንግሥት ተቋማት መረጃ ገዝቼ በምክር ቤት አቅርቤያለሁ። ከሰባት ሺ በላይ ዶክመንቶች አሉኝ። እነዚያን በሙሉ መረጃዎች ለማጣራት ቢቻል በሰዎቹ፤ ካልተቻለ በሥራ አስኪያጁ፥ ካልሆነም በገንዝብ እገዛለሁ። በዚህም ሞራሌን መትተው ከመመለሳቸው በፊት ተዘጋጅቼ ብሄድ የእነሱን አንደበት አስሬ አንደበተ ርዕቱ ሆኜ እንድወጣ አግዞኛል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ለእውነት ተሟጋች ባህሪዎ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ወደአልሆነ ንትርክ ውስጥ ገብተው ያውቃሉ፤ ወይስ ሃሳብዎትን በቀና መንገድ ለመቀበል ይጥሩ ነበር?
አቶ ብድሩ፡- ይቅርታ አድርጊልኝና አቶ መለስን በዚህ በኩል አደንቀዋለሁ! ምንም እንኳ በርካታ ችግሮች ቢኖርበትም የተሻለ አስተሳሰብ አለው፤ ችግሩ ግን ለመልካም ነገር አላዋለውም። በእርግጥ መጀመሪያ አካባቢ ለረጅም ጊዜ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ በነበሩት በአቶ ደሳለኝ አለሙ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተጣልተን ነበር። እኚህ ሰው በርካታ ስህተቶችን የሠሩ ግለሰብ ነበሩ። በነገራችን ላይ እኔ ወደ ታች ያሉትን መቆርቆዝ አልወድም። ምክንያቱም ደሃን ብትነኪው ትርጉም የለውም።
የላይኛው ከተስተካከለ የታችኛው ይስተካከላል የሚል እምነት ስላለኝ ከላይኞቹ ጋር ነው የምጣለው። አቶ ደሳለኝ የአዜብ አባት ቤት ነው ያደጉት። ስለዚህ ቤተ መንግሥትም ሆነ ፓርላማ ለመግባት የተለየ መታወቂያ ነበራቸው። ዳኞችንም እንደፈለጋቸው ነበር የሚሾሙትና የሚሽሩት። አንድ ወቅት ላይ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ምንጣፍ ከወንድማቸው ሱቅ እንዲገዛ አደረጉ። በተጨማሪም ሹፌር ብለው የቀጠሩትም ሰው ቤተሰባቸው ነው። ይህ ሹፌር መኪና ሲያጋጭ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ገንዘብ መኪናው እንዲሠራ አደረጉ።
እነዚህንና ሌሎችምንም ኢኮኖሚያዊ ስህተቶችን ለምክር ቤቱ አቀረብኩ። ያን ጊዜ አቶ መለስ ጣልቃ ገብተው «ክቡር አፈ ጉባኤ እዚህ ተቀምጠው መካኒሳ ላይ ሰማይና ምድር ይገናኛል የሚሉ ሰዎችን የምትቀጡበት መሳሪያ የላችሁም ወይ?» ብለው ጠየቁ። አፈጉባኤው አቶ ዳዊትም ዝም አሉ። ይህን ጊዜ ደግሜ እጅ አወጣሁ፤ አቶ ዳዊት ደግሞ መልካም ሰው ስለነበሩ ፈቀዱልኝና እኔ የእሳቸውን ያህል ባልማርም ብዬ ጀመርኩ፤ በነገራችን ላይ በሾኬ (በአሽሙር) ስመታው ነው እንጂ ስገባው ነው እንጂ እኔም ሁለተኛ ዲግሪ አለኝ። እናም እኔ የሳቸውን ያህል ባልማርም እዚህ ተቀምጬ መካኒሳ ላይ ምድርና ሰማይ ይገናኛሉ አልልም አልኩ። ነገር ግን እኔ የምጫወተው በማስረጃ ነውና ከፈለጉ ማስረጃውን ልላክላችሁ ይፈቀድልኝ አልኩ።
ከስብሰባ ስወጣ መረጃውን አንጣ ተብዬ ሰጠኋቸው፤ ከዚያ በኋላ እኔና አቶ መለስ ተከባበርን። ከዚያ ጀምሮ በእውነት ነው የምለው ያነሳሁትን ጥያቄ በጣም አስቸጋሪና ወሳኝ የሆነ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ያቀረብኩትን መረጃ ተንተርሶ ምርመራ እንዲካሄድ ያድርግና ዕርምጃ ይወስድ ነበር። በእርግጥ ከእሱ ተምረው ሌሎችም እንደሱ ያደርጉ ነበር። ሌላው ይቅርና ቤተመንግሥት ግብዣ ቀርበን እያለ ያስጠራኝ ነበር። ከዚያም እዚያ ከማቅረብህ በፊት እስቲ ቀድመህ ንገረኝ ይለኝ ነበር። የማቀርበው መረጃ በእውነት ላይ የተመሰረተ ስለሆነና እውነትን መጋፋጥ ስለማይችል ሳይወድ በግዱ ይቀበለኝ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ከሌሎች የምክር ቤት አባላት የሚለዩት የመጡትን አካባቢ ችግር ብቻ ያለማንሳትዎ ነው። ይህ ልምድ ከምን የመነጨ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ በድሩ፡- እውነቱን ለመናገር ሰውም መረጃ የሚጠቁመኝ ማንነቴን ሳይሆን በእኔነቴ ሙሉ እምነት ኖሮት ነው። ጋምቤላ ሲታሰር ከጋምቤላ መረጃ ይመጣልኛል። መቀሌ ሲታሰር ከመቀሌ መረጃ ይመጣልኛል። እኔም እሄዳለው። በነገራችን ላይ እንትጮ ከሚባል አገር ሙስሊም ሴት ተማሪዎች «ሻርፕ ለብሰን ትምህርት ቤት መሄድ ተከልክለናል» የሚል መረጃ ደረሰኝና እዚያ ድረስ ሄጄ ያለውን ሁኔታ ካጣራሁ በኋላ ለትግራይ ክልል ዐቃቢ ህግ አቀረብኩ።
እኔ ለሚዲያ ከማቅረቤ ወይም ለምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት የዜጎች መብት ልታከብሩ ይገባል አልኳቸው። የለም ሻሽ ማሰር ክልክል ነው ከተባለም በአዋጅ ይደንገግ አልኳቸው። በእውነት ዐቃቢ ህጉ እግዚአብሄር ይስጠውና ወዲያውኑ ዕርምጃ ወስዶ ነገሩ ተስተካከለ። እስር ቤት ድረስ ሄጄም ጠያቂ መስዬ መረጃ የምሰበስብበት ጊዜ ነበር። በእርግጥ ፈጣሪ ይመስገንና በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ወይ ይፈታሉ ወይ ደግሞ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።
ሌላ ለምሳሌ ብጠቅስልሽ የፈረሰው ከርቼሌ ውስጥ 27 የሐረርጌ ልጆች እዚህ ዘጠኝ ዓመት ያለምንም ፍርድ እንደ ቆሻሻ መጣላቸውን ሰምቼ እንደ ጠያቂ ሆኜ ገብቼ ሙሉ መረጃቸውን ሰበሰብኩ። ከዚያም ለምክር ቤት አቅርቤ ወዲያው እንዲፈቱ ተደረገ። እናም የእኔ ፍላጎት ፍትህ ሰፍኖ ፤ ዴሞክራሲ በተግባር ላይ ውሎ ማየት ነው። ዋናው ቁምነገር ዴሞክራሲ ላንቺ ጎሎ ለእኔ ብቻ ቢሰፍን ፋይዳ የለውም።
ለኮንሶ የተከለከለ ለኦሮሞ ቢፈቀድ ፋይዳ የለውም። ዴሞክራሲ አለ ከተባለ ለሁሉም እኩል መኖር ነው መሆን ያለበት። ፍላጎቴ ያ ስለሆነ ነው ከሰባት ሺህ በላይ አቤቱታዎች ወደ እኔ የመጡት። ጊዜዬንም፥ ጉልበቴንና ገንዘቤንም በዚያ ላይ ሳውለው ከፍተኛ ደስታ ነው የሚሰማኝ። ደግነቱ ልጆቼም ያንን በማየት ደስተኛ ስለነበሩ ትልቅ ብርታት ይሰጡኝ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በምክር ቤቱ በነበርዎ ቆይታ ስኬታማ ነበርኩ ብለው ያስባሉ?
አቶ በድሩ፡- በእውነት ለእኔ በወቅቱ የነበረው የተስፋ ዳቦ ዛሬ የመንፈስ ኩራት ሆኖልኝ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ቤተሰቦቼን አስቸግሬያለሁ ለእኔ ግን የመንፈስ ኩራቱ ድንበር የዘለለ ነው። ዛሬ እጅግ በጣም ደስ የሚለኝ ይሄ ነው። ምክንያቱም ምክር ቤት ውስጥ በነበረኝ ቆይታ አንቀላፍቼ አይደለም የወጣሁት። ደመወዝ በልቼ አይደለም የወጣሁት። ይልቁንስ የልጆቼን ዳቦ መግዣ
አጥቼበት ግን ደግሞ የዘላለም እርካታ አግኝቼበት ነው የወጣሁት። ለእነሱም ደስታ ፈጥሬ፥ በተለይ በትምህርት ቤት የእኔ ልጆች መሆናቸውን ሲያውቁ በነፃ ያሳትማሩልኝ አሉ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የቅንጅት አባል እንደ መሆኖ በ1997 ዓ.ም ምርጫ ጋር ተያይዞ ቅንጅት አዲስ አበባን አለመረከቡ ትክክል ነበር ብለው ያምናሉ?
አቶ በድሩ፡- እውነቱን ለመናገር ሁላችን የቅንጅት አመራሮች ወንጀለኞች ነን።
አዲስ ዘመን፡- እንዴት?
አቶ በድሩ፡- አዎ ወንጀለኞች ነን፤ በዓለም ድንቅ የሆነ ዕድል አግኝተን ነበር። አዲስ አበባ ላይ ከ138 የምክርቤት አባላት 137ቱን አሸንፈናል። እንዲያውም አንዱንም ያላሸነፍነው ሰው ስለሌለን ብቻ ነው። በምክር ቤት ደረጃ 23ቱንም የአዲስ አበባ መቀመጫ አሸንፈናል። የአማራ ክልል ምክር ቤትን ማቋቋም በሚያስችል መልኩ አሸንፈን ነበር። መጨረሻ ላይ ሄደን አንዳንድ ቦታ ላይ መቆጣጠር አለመቻላችን ዕድሉ ከእጃችን አምልጧል።
በምርጫው ላይ የነበረንን ጥብቅ ክትትል ያህል በቆጠራ ላይ አልነበረንም። ብዙዎቹ ከአዲስ አበባ ወጥተው ሁኔታውን ለመከታተል ፈቃደኞች አልነበሩም። ሁሉም በሬዲዮና በቴሌቪዥን መጮህ ነበር የሚፈልገው። በነገራችን ላይ የህዝብ ተወካይ የሚሆን ሰው ገጠር ወርዶ ከህዝብ ጋር መደብ ላይ ተኝቶ ማደር ህዝቡን መስሎ መኖር ይጠበቅበት ነበር። ቁንጫ ካለም ከቁንጫው ጋር ተለማምዶ ለቁንጫው መፍትሔ መፈለግ ነው የሚጠበቅበት እንጂ ከላይ ተቆልሎ አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው በቴሌቪዥንና ሬዲዮ የሚያወሩ ሰዎች እውነተኛ ዴሞክራቶች አይደሉም። የስልጣን ጥመኞች ናቸው። ትልቁ የቅንጅት ችግር ይሄ ነበር። ወደ ህዝቡ መውረድ አይፈልጉም። እሱ ሽሮ ሲበላ አብሮ ሽሮ በልቶ መኖር አለበት።
ሌላው ኢህአዴግ በሠራው ወንጀል ህዝቡ ከድቶታል፤ ቅንጅት ያንን የከዳ ህዝብ ነድቶ ማምጣት ነበረበት። በእርግጥም ነድቶ ማምጣት ችሎ ነበር። እንደ አዲስ አበባ በክልል ደረጃ አሸንፈን ነበር። ነገር ግን ባለመውጣታችን የምርጫው ውጤት ተቀየረ። በነገራችን ላይ የምርጫ ውጤት የሚሰረቀው በምርጫ ላይ ሳይሆን በቆጠራ ላይ ነው። በእርግጥ አንዳንድ ቦታ ላይ ሊሰረቅ ይችላል። ለምሳሌ እኔ በ1987 ዓ.ም ስወዳደር ዋንጌኒ በምትባል ቦታ ላይ ምርጫ ሲካሄድ የእኔ ምልክት ማጭድ ነበር።
እናም ገበሬው እንዳለ ማጭድ ይዞ ነው የመጣው። በወቅቱ አንድ ካድሬ ምርጫ በሚደረግበት ጎጆ ውስጥ ገብቶ የሚመርጡ ሰዎችን እያሳሰተ ኢህአዴግን እንዲመርጡ ያስገድድ ነበር። ግን መራጩ እሱ በላበት ሁሉ አንገባም እያሉ አሸፈረኝ ብለው ሳይመርጡ ወጡ። መረጃው ደረሰንና በፈረስና በሞተር ሳይክል በመሄድ ያንን ካድሬ ከጎጆው እንዲወጣ ተደረገ። የቅንጅት ወቅት ላይም በተመሳሳይ ችግር ነበር። ሲቆጠር እንውጣ ብላቸውም የሚሰማኝ ግን አላገኘሁም። በቻልኩት መጠን ለመከተታል ሞክሬ ነበር፤ በውቅቱ ብዙ ስርቆት ሲፈጸም ለማየት ችያለሁ ከነማስረጃው አግኝቻለሁ።
ከዚያ በኋላም አዲስ አበባን የመሰለ ኢህአዴግን ሊዘርር የሚችል ስልጣን አግኝተን ሳንገባ ቀረን። በእርግጥ እኔ መግባት ፈልጌ ነበር። ምክንያቱም አዲስ አበባን ማሸነፍ ኢትዮጵያን ከማሸነፍ የበለጠ ትርጉም አለው። የፌዴራል መንግሥቱ መቀመጫ በመሆኑ ማለት ነው። እሷን ከስሩ እንደ ምንጣፍ ጎትተሽ ከወሰድሽው የፌዴራል መንግሥቱ በአንቺ ግዛት ላይ ነው የሚኖረው። እናም በአንዳንድ ለማስፈራራት በቀረቡ ሃሳቦች ተመርተው ሳንገባ ቀረን። ይሄ ስህተቱ የእኛ ነው።
ከዚያ የበለጠ እድል የለም። እሱ ብቻ አይደለም የፖለቲካ ስትራቴጂ ላይም ትልቅ ድክመት ነበረ። ህዝቡን እንግባ አንግባ ብለን እንጠይቅ አሉ። እንዴት እንዲህ ይባላል። እኔ ፕሮግራሜን አስተዋውቄ ህዝቡ ከመረጠኝ በኋላ እንዴት ልግባ አልግባ ብዬ እጠይቃለሁ? አይጠየቅም! እኔ በተወዳደሩበት የምርጫ ጣቢያ ሁለት ሺ ድምፅ ኢህአዴግ ሲያገኝ እኔ 36ሺ800 ነው ያገኘሁት።
ይህ ሁሉ ሰው መርጦኝ ሳለ በትንሽ አደራሽ ውስጥ ህዝብ ጠርቼ እንዴት አዲስ አበባ ልግባ አልግባ ብዬ እጠይቃለሁ? አላደርግም አልኩ፤ ይሄ የፖለቲካ ድኩማንነት ነው። አላድርግም አልኳቸው። ከዚያ በኋላ በጣም ደስ የማይሉ ነገሮች ተፈጠሩ። በሬ ሆይ ሳሩን ዓይተህ ገደሉን ሳታይ ይባል ነበርና ያንን ስልጣን ብቻ ዓይተው እንጂ ገደሉን ባለማያታቸው ትልቅ ስህተት ነው የተሠራው። አንገባም ማለታችን ትልቅ ስህተት ነው የሠራነው። ይህም ከፍተኛ ዋጋ ነው ያስከፈለን።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ አንዳንድ የቅንጅት አመራሮች ኢህአዴግ አዲስ አበባን ለማስረከብ ፈቃደኛ ስላልነበር እንደሆነ ነው የሚገልጹት?
አቶ በድሩ፡- ይቅርታ አድርጊልኝና እኔ ሽበት አውጥቻለው፤ ከዚህ በኋላ ቀንድ አላበቅልም፤ ያልሆነውን ሆነ የምልበት ምንም ምክንያት የለኝም። እውነታው አዲስ አበባን ተረከቡን ተብለን ነበር። እኛ ግን ለመረከብ ፈቃደኞች አልነበርንም። በመጀመሪያ ራስ አምባ ሆቴል ላይ ባደረግነው ስብሰባ የአዲስ አበባ ከንቲባ እንዲሆን ዶክተር ብርሃኑ ነጋን መረጥነው፤ ምክትል ደግሞ ዶክተር አድማሱን አደረግን።
በኋላም ለቀበሌ ሰው ይመልመል ተብሎ ምልመላው ሲካሄድ በዘረኝነት የተሞላ አሠራር ነበረ የተከተሉት። አዲስ አበባን ለመረከብ ማፈግፈግ ተጀመረ። ምክር ቤት ለመግባትም በማንገራገራችን ክስ ቀረበብን ፣ ግን የእኛ አባላት በፍትህ ስርዓቱ እምነት እንደሌላቸው ነው የገለጹት።
በነገራችን ላይ ወደ ምርጫ የገባነው ባለው ህገመንግሥትና የፍትህ ስርዓት ለመዳኘት አምነን ነበር። አለበለዚያ ጫካ መግባት ነበር የሚገባን። ከተቀበልን በኋላ ማጣጣል አይገባንም ነበር። የሚያሳዝንሽ ደግሞ ይሄ ድርጊት የሚፈፀመው ባልተማሩ ሰዎች አይደለም። በተማሩና ብቃት ባላቸው ሰዎች ነው። እርስ በርስ እንደገና መባላት ነው የተያዘው። አንዱ አንዱን ገልብጦ ለመግባት መሞከር ሁኔታም ነበር። በአጠቃላይ ለመረከብ ዝግጁ አልነበርንም።
የወቅቱን ሁኔታ ሳስበው የምንሠራውንም የምናውቅ አይመስለኝም። ህዝቡ አምኖብን ሲመርጠን ያንን ምርጫ ተቀብለን መግባት ሲገባን አንገባም ማለት ትክክል አልነበረም። እኔ ሁኔታው ስላላማረኝ ቅንጅት አመራሩን ይመርጣል ሲባል አልተገኘሁም። እውነቱን ለመናገር በፕሮፌሰር፣በብርሃኑና በልደቱ መካከል የተከሰተው ጠብ ምክንያት የሆኑ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል። ግን መናገር አልፈልግም። በመጀመሪያም ጥፋቱ የተፈጠረው ልደቱ ማንነቱን እያወቁ ማስገባታቸው ነው።
ከገባ በኋላ እሱን ማውገዝ አይገባም። ለማውገዝስ ምንድን ነው መሰረታችን? አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል የሚያደርገው መፍጨርጨር ከፍተኛ ነበር። ይህ ሁሉ ስላስጠላኝ ነው በስብሰባው ያልተገኘሁት። የሚገርመው በሌለሁበት ነው የቅንጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ አድርገው የመረጡኝ። ሌላው ደግሞ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ አልነበረችም። በተንኮል በመሰሪነትነው የቅንጅት ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት አደረጓት። ምርጫ ላይ አልነበረችም። ምርጫ ተጭበርብሯል ሲባል ከመጡት 32 ዳኞች መካከል ነበረች።
አዲስ ዘመን፡- ወይዘሪት ብርቱን አልነበረችም ሲሉ ምን ማለቶ ነው?
አቶ በድሩ፡- በምርጫ ወቅት ድርጅት ውስጥ አልነበረችም።
አዲስ ዘመን፡- አልተወዳደረችም?
አቶ በድሩ፡- በ1997 ዓ.ም ምርጫ አልተወዳ ደረችም፤ የተወዳደረችው በግል በ1992 ምርጫ ነው። የመጣችው የምርጫውን መጭበርበር ለማጣራት ነበር፤ ግን በመጀመሪያ ቀስተ ዳመና ገባች፣ከዚያ የቅንጅት አባል አደረጓት። እውነት ለመናገር ብርቱካን የተሾመችበት ቦታ የሚገባት አልማዝ የምትባል አንዲት ሐቀኛ የጎንደር ልጅ ናት። እናም ትልቅ ድክመቶች ነበሩ። በአጠቃላይ ቅንጅት የራሱ ጥፋት ነው በራሱ ነው የወደቀው።
አዲስ ዘመን፡- ከምርጫው በኋላ ከታሰሩት የቅንጅት አባላት እርሶ አንዱ ነበሩ?
አቶ በድሩ፡– አዎ ታስሬያለሁ፤ ግን የተፈታሁት እንደሌሎቹ ይቅርታ ጠይቄ አይደለም። በእኔ እምነት ይቅርታ መጠየቅ ለሞቱትም፥ አካል ጉዳተኛ ለነበሩት፥ ለታሰሩት 40ሺ ሰዎችም፥ ከአገር ለኮበለሉትም እኔ ተጠያቂ ነኝ ማለት ነው። ተከራክሬ በነፃ ነው የተለቀቅሁት። በዚህም እነሱ ከተፈቱበት ጊዜ ሁለት ወር ነው የዘገየሁት። በእርግጥ መከላከያዬን በፅሑፍ በማስረጃም ያቀረብኩት ከእነሱ በፊት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በቀጣዩ ምርጫ የመሳተፍ ሃሳብ አለዎት?
አቶ በድሩ፡- እኔ ቦክሰኛ አይደለሁም፤ ቦክሰኛ ብቻ ነው አንዴ ከተዘረረ በኋላ እጁን የሚሰጠው። ምክንያቱም ፖለቲካ ማለት ለእኔ ዲን (እምነት) ነው። ከመጀመሪያውኑ ወደ ፖለቲካ የገባሁት እንጀራ ፍለጋ አይደለም፤ እምነቴ ስለሆነ እንጂ። ይህም ሲባል የተራበውን፥ የታረዘውን፥ መብቱ የተረገጠውን ሰው መብት መቆም ነው። ደግሞም ለምድሩ ብቻ ሳይሆን ለሰማዩም ያገለግለኛል ብዬ ቆርጬ የገባሁበት ነው። ስለዚህ ጓንት አላውልቅም የምልሽ አንደበቴ እስካለች ድረስ ለእውነትና ለፍትህ መከራከርን አልተውም። ነገር ግን ፍትህ ካለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በቅርቡ እንጠብቆ ዎታለን?
አቶ በድሩ፡- አላውቀውም፤ አየሩ ወዴት ነው የሚሄደው የሚለውን ነገር ገና አላየነውም። አሁን ያለው አየር አይጥመኝም። ወዴት እንደሚሄድም አላውቅውም። ምናልባት እንደ ሁሴን ጅብሪል መተንበይ የሚችል ሰው እስከሌለ ድረስ ምን እንደሚሆን ማወቅ አይቻልም። ለመሆኑ ምርጫስ ይካሄዳል? ምርጫ ቦርድስ አለ? እኔ ይህንን ለመናገር ይከብደኛል። የህዝብ ቆጠራው የቀረው የአማራ ክልላዊ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነው። አሁንም የክልሉ መንግሥት ወልቃይት፥ ጠገዴ፥ ራያ አላማጣ ካልተመለሱለት ምርጫ ይካሄዳል ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡- ካነሱት አይቀር አሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ያዩታል? ምን ምን ተስፋና ስጋቶች እንዳሎት ይጥቀሱልን?
አቶ በድሩ፡- እኔ መሰረታዊ ለውጥ የለም ባይ ነኝ፤ ኢህአዴግ ኢህአዴግ ነው። አንዳንድ ነገሮች ላይ ለውጥ እያየን ነው። ኢህአዴግ ኢህአዴግንቱን እስካልካደ ወይም ኢህአዴግ ካልተለወጠ ተለውጧል ማለት አልችልም። ፖሊሲውም መሰረቱም እንደተጠበቀ ነው። ወዴት ይሄዳል? ምን መወሰን ይቻላል? ይሄ ነው ለማለት አልችልም። አዎ አንዳንድ ጥሩ ነገሮች ተሠርተዋል፤ ግን ትልልቁ ነገሮች ገና አልተፈፀሙም።
አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ?
አቶ በድሩ፡- እንዴ የቀን ጅቦች ሲባል ነበር እኮ! የቀን ጅቦቹ የት አሉ? ማን ናቸው? የቀን ጅብ ከተባለ ጅቡ መታወቅ አለበት። አለዚያ በስተቀር ጅብ ያልሆነ ጅብ ነው ቢባልም እኔ አልቀበልም።
አዲስ ዘመን፡- የቀንጅ ጅብ የተባሉት ምን መደረግ አለባቸው ነው የሚሉት?
አቶ በድሩ፡- ዕርምጃ ነዋ! ወደ ህግ ማቅረብ ይገባል። ደግሞ ችግኙን ሳይሆን ግንዱን መምታት ነው የሚገባው። አሁን የሚያስፈልገው ከስር መመንጠር ነው። በእኔ እምነት ሜቴክ ምንም መነካት የለበትም ነበር። ምክንያቱም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሆኑ ነው። ያ ሁሉ ሲፈፀም ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ይሠራ ነበር? ምክትሉስ ምን ይሠራ ነበር? ለምን ዝም ተባሉ? ለመሆኑ ስለአቶ ጌታቸው አሰፋ ብዙ ይወራል፤ ይነገራል፤ ግን አቶ ጌታቸው አሰፋ ብቻቸውን ምን ይሠራሉ? ሌሎቹ ስልጣን ላይ የነበሩት ምን ይሠሩ ነበር? እንግዲህ መሰረታዊ ለውጥ መጣ የምንለው የቀን ጅቦቹ ተለይተው ለህግ ሲቀርቡ ነው። ቢያንስ ቢያንስ እንደ ደቡብ አፍሪካ ጥፋተኞቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋታቸውን አምነው ይቅርታ መጠየቅ ይገባቸዋል። አለበለዚያ እንዲያው በደምሳሳው ፍቅርና ይቅርታ ቢባል አሳማኝ አይሆንም።
እንዴትስ አድርጌ ነው ቁርሾ ሆዴ ውስጥ ተቀምጦ ይቅርታ የማደርገው? ሁለት ልጆች የሞቱባት እናት እንዴት አድርጋ ነው መታረቅ የምትችለው? ገዳዮቹ ቀርበው ይቅርታ አልጠየቋትም እኮ። ፈፅመዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎች እኛ የለንበትም እያሉ ፣የለም አላችሁበት ተከላከሉ ተብሎ ነው መቅረብ ያለበት እንጂ እዛና እዚህ ተቀምጦ መፈራረጁ ትርጉም የለውም። ስለዚህ በተግባር ያየነው የቀን ጅብ የለም፤ በቃላት ካልሆነ በስተቀር። ህዝቡን መሸወድ የለብንም፤ እውነቱን ልንናገር ይገባል።
በደል የፈፀመበትን ህዝብ በደሉ የሚቀረፍበትን መንገድ እንጂ ተለባብሰው ቢተኙ ገላልጦ የሚያይ ፈጣሪ አለ እንደሚባለው ሁሉ አለባብሰን ማለፍ አይገባንም። እውነቱን እናውጣ እውነቱን እንናገር። በጋዜጣችሁ ላይ የምታወጪው ከሆና ዕድሉን የምትሰጡኝ ከሆነ መናገር የምፈልገው ነገር አለ፤ ለእኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእምነት ተቋማት ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ቅሬታ ለመፍታት ጥረት ማድረጉ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ለእኔ ወንጀል ነው ይሄ።
አዲስ ዘመን፡- እንዴት?
አቶ በድሩ፡- አንደኛ ሁለት ፓትሪያርኮች በኢትዮጵያ ላይ እንዲቀመጡ መደረጉ፤ ምክንያቱም አፄ ኃይለስላሴ በ1936 ዓ.ም የኦርቶዶክስ ቀኖና አዋጅ ሲወፃ በፓትሪያርክ ላይ ፓርቲያርክ መሾም እንደማይችል ደንግገዋል። ስለዚህ ሌላ አዋጅ እስካልወጣ ድረስ ሁለት ፓትሪያርክ መሾም ህጋዊ አይደለም። ይቅርታ አድርጊልኝና ይሄ ለእኔ ትክክል አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ለሰላም ሲባል ስለሆነ ያ የተደረገው ህግ ተጣሰ ሊባል ይችላል?
አቶ በድሩ፡- በጭራሽ! ከህግ በላይ ሰላም ሊኖር አይችልም፤ ይቅርታ አድርጊልኝና ሰላም የሚፈጠረው በህግ ሲገዛ ነው፤ መቆጣጠር የሚቻልበት መሳሪያ ሲኖር ነው። ዝም ብለሽ ግባ ውጣ የምትይ ከሆነ ይህ ህግ አይደለም። የዕለት ሰላም እንጂ ነገን አናውቀውም። ደግሞ ይህ ህገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ የተቀመጠውን የሃይማኖትና የመንግሥት ቀይ መስመር መጣስ ነው።
ይህንን ቀይ መስመር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጣሰ ሌሎቹ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማሰብ ነው። ዛሬ እሰየው ለማስታረቅ ነው። ነገ ግን ለማጥፋት ቢመጣ ወንጀል ነው። ዛሬም ወንጀል ነው፤ ነገም ወንጀል ነው፤ ዛሬ ሁላችንም በህግ እንዳኝ። ህግ በሌለበት ሰላም የለም።
ለሙስሊሞቹ መከፋፈል ተጠያቂ ኢህአዴግ ነው። የአብደላ ሃበቢ «ሃበሽ» የተባለው አስተምህሮ ህዝብ ሳያውቅና ሳይፈልግ ወደ ሙስሊሙ ሊገባ የቻለው በአቶ አባይ ፀሐዬ ትዕዛዝ መሰረት ነው። ስለዚህ አሁንም ቢሆን መንግሥት ጣልቃ ገብነቱን ማቆም አለበት፤ ችግርም ካለ በህግና በህግ ነው ሊዳኙ የሚገባው። እኔ እንደ አንድ ግለሰብ አማኝ ልናገር እችል ይሆናል እንጂ ጣልቃ ልገባ አልችልም።
አዲስ ዘመን፡- ከአዲስ ዘመን ቅዳሜ ጋር ቆይታ በማድረግዎ ያለኝን የከበረ ምስጋና በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም አቀርባለሁ።
አቶ በድሩ፡- እኔም አስታውሳችሁ እንግዳ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2011
ማህሌት አብዱል