“በኢትዮጵያ የልብ ህክምና ማዕከል የማቋቋም ሃሳብ የተጠነሰሰው የዛሬ 41 ዓመት ገደማ በ1970 ዓ.ም በአሜሪካ ነው፡፡ በልብ ህክምና ሙያ ለመሰልጠን (ስፔሻላይዝድ ለማድረግ) በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቅኩበትን የትምህርት ማስረጃና የወደፊት ፍላጎቴን የሚገልጽ ሃሳብ ለኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ አቀረብኩ፡፡
ቃለ-መጠይቅ ያደረገችልኝ ፕሮፌሰር የምንቀበለው 10 ሰዎችን ነው፡፡ አንተ የተቀመጥከው 10ኛ ላይ ነው፡፡ ባቀረብከው ማመልከቻ ውስጥ ጥሩና ደስ የሚሉ ነገሮች አይቻለሁ፡ ፡ ስላቀድካቸው ነገሮች ከአንደበትህ መስማት እፈልጋለሁ፡፡ እውነት ትምህርትህን ስትጨርስ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰህ፣ በልብ ህክምና ትሠራለህ? በማለት ስትጠይቀኝ፡ ፡ “አዎ!” በማለት መለስኩላት፡፡
ፕሮፌሰሯም፣ “ኢትዮጵያ ተመልሰህ የልብ ሆስፒታል በሌለበት፣ መሳሪያ በሌለበት፣ ባለሙያ በሌለበት፣ እንዴት ነው የልብ ህክምና እሠራለሁ የምትለው?” ሲሉ ደግማ ስትጠይቀኝ፤ መላ እፈልጋለሁ አልኳት፡፡
“ቤት ስመለስ ፊቴ ላይ የመከፋትና የኀዘን ስሜት ያየችው ባለቤቴ፣ ‘ምነው ተከፋህ? አልተቀበሉህም እንዴ?’ በማለት ጠየቀችኝ፡፡ መቀበሉንስ ተቀብለውኛል፡፡ ነገር ግን አራት ነገሮች አርግዤ መጣሁ” አልኳት። የልብ ሆስፒታል መገንባት፣ ውድና ልዩ የሆኑትን የልብ ህክምና መሳሪያዎች ማሟላት፣ የሰው ኃይል (ካርዲዮሎጂስት) ማፍራትና ሆስፒታሉ በገንዘብ አቅም ዘላቂና ቀጣይነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል የሚሉት በዶ/ር በላይ አበጋዝ የተረገዙት ራዕዮች መሆናቸውን ዘርዝረው አስረዷቸው።
ለዚህ ራዕይ ሳይታክቱ የወጡና የወረዱት ዶ/ር በላይ አበጋዝ ሆስፒታሉን በኢትዮጵያ ህዝብና በሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አላሙዲ ትብብርና ድጋፍ አሠርተው በ2001 ዓ.ም አስመርቀዋል። ውድ የሆኑት ዘመናዊ የልብ ቀዶ ህክምና መሳሪያዎችንም በአጋር ድርጅቶች አሟልተዋል። የልብ ቀዶ ሀኪሞችንም (ካርዲዮሎጂስቶችን) የሚኒያፖሊስ የልብ ቀዶ ሀኪም በሆኑት በዶ/ር ቪብ ክሸንትና ታዋቂ በሆነው የህንድ ናርያና ሆስፒታል አሰለጠኑና ዛሬ ለተደረሰበት ደረጃ ማድረስ የቻሉ የአገር ባለውለታ ናቸው፡፡
እኝህ የአገር ባለውለታ ከሰሞኑ በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አማካኝነት የምስጋና እና የእውቅና የክብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የተሰበረ ልብ ጠጋኙ የአገር ባለውለታ ይህ እውቅናና ሽልማት ቢያንስባቸው እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም። ምንም በሌለበት በዚያ ዘመን “እኔ እና ራዕዬ አለሁ” ብለሁ ሳይታክቱና ሳይረቱ በዓለም ላይ በውድነቱና በአስቸጋሪነቱ የሚታወቀውን የልብ ህክምና በአገራቸው ላይ እውን ማድረግ ችለዋል። ስለሆነም አንድም ጊዜ ሳይሆን ብዙ ጊዜ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ኢትዮጵያዊ ናቸው።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ50ሺህ ሕፃናት ከልብ በሽታ ጋር ይወለዳሉ። በተጨማሪ ከ50 ሺህ እስከ 60 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ከተወለዱ በኋላ የልብ በሽተኛ ይሆናሉ። ሕክምናውን ስለማያገኙም ይሞታሉ። ይህንን ታሪክ ለመቀየር ላለፉት 41 ዓመታት የደከሙትን ኢትዮጵያዊ ሁሉም ወገን ሊያመሰግንና አርአያነታቸውን ሊከተል ይገባል። የዶ/ር በላይን መንገድ ልብ ብሎ ላስተዋለ ልባም ሁሉ የሚናገርው ሀቅ፤ ማንም ቢሆን በተሰማራበት መስክ ሊደክምለትና ሊያሳካው የሚገባው የአገር ውለታ እንዳለበት ነው።
አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ከማለት በፊት እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት የሚለው ዝነኛ ንግግርም የሚታወሰው እንዲህ ዓይነቱን ኢትዮጵያዊ ማየት ሲቻል ጭምር ነው። ዛሬ ሁሉም መብቱንና ጥቅሙን ብቻ ጠያቂ መሆን ጀምሯል። ግዴታን ወደ ጎን እያሉ መብትን ብቻ አምጡ ማለት አሊያም ምን አገባኝ በሚል ስሜት መነዳት ራስንም አገርንም የትም አያሻግርም። በህክምና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድና ሌሎች ዘርፎች ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደ ዶ/ር በላይ ባለራዕይና ለአገር ታማኝ ሆኖ ቢሠራ እንኳንስ ለአገር ለሌላም መትረፍ በተቻለ ነበር።
መንግሥት በዚህ ልክ የደከሙትን ወገኖች ፈልጎ ማመስገኑና እውቅና መስጠቱ ተገቢ ተግባር ነውና አሁንም በየዘርፉ ያሉ የአገር ባለውለታዎችን በንስር ዓይን ይፈለጉ፤ ይወደሱ፤ ይመስገኑ። ይህንን ማድረግ ፋይዳው እልፍ ነው።
አንድም የደከሙትን ለድካማቸው እውቅና መስጠት ነው፤ አንድም ደግሞ ሌሎችን ወደዚህ ዓይነቱ ተግባር ለማምጣት እርሾ ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም ለአገራቸውና ለወገኖቻቸው የደከሙና እየደከሙ ያሉ ባለውለታዎችንና ባለደጋግ ልቦችን ከልብ ማመስገን ልባምነት ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2011