አንድ ነገር በተደጋጋሚ እየተሰራ ለውጥ ሳይመጣ ሲቀርና ተመልሶ በነበረት ሲሆን ውሀ ቢወቅጡት እምቦጭ ይላል ሀገርኛው አባባል፡፡በጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተው አረምም በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እምቦጭ የሚለውን ስያሜ ያገኘው አረሙን ለማጥፋት የተሰራው ስራ ውጤት ባለማስገኘቱና አረሙ ተመልሶ ወደነበረበት በመመለሱ ውሀ ቢወቅጡት እምቦጭ የሚለውን አባባል በመውሰድ እንደሆነ ይነገራል፡፡
አቶ በልስቲ ፈጠነ የአማራ ክልል አካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ባለስልጣን ም/ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡
አንድ የእንቦጭ ተክል እስከ 5 ሺህ ዘር የሚኖረው ሲሆን አንድ አበባ ደግሞ እስከ 500 ዘር ይኖራታል። ዘሩ ውሀ ሳያገኝ እስከ 30 አመት ድረስ በመሬት ውስጥ መቆየት ይችላል ይላሉ፡፡በዘሩም በአካሉም በቀላሉ መራባት የሚችለው እምቦጭ ያለው ስነህይወታዊ ባህርይ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑን የተናገሩት አቶ በልስቲ የጣና ሀይቅ በደለል ውሀ እየተሞላ መምጣቱ ደግሞ ለአረሙ መስፋፋት አስተዋፀኦ እደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
በሰው ጉልበትና በማሽን አረሙን ለመቆጣጠር ጥረት የተደረገ ሲሆን አረሙን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠርም ሌሎች ስነህይወታዊ አማራጮችን ለመጠቀም ጥናቶች እየተደረጉ ነው ያሉት አቶ በልስቲ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት ግን አልተቻለም ይላሉ።
ከዚህ ውስጥ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ ያስመጣቸው እምቦጭን ብቻ የሚመገቡ ጢንዚዛዎችን ለማራባት በሶስት ቦታዎች የማራቢያ ጣቢያ መረጣ የተደረገ ሲሆን ጢንዚዛዎቹ ባለፉት ሶስት አመታት ጥናት ተደርጎባቸው በ276 እፅዋት ላይ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያደርሱ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በጣና ሀይቅ የተከሰተው የእንቦጭ አረም አሁን በስድስት ወረዳዎች እና 21 ቀበሌዎች ከጎርጎራ እስከ ጣና ቂርቆስ 100 ኪ.ሜ ያህል የውሀ ዳርቻ ሸፍኖ ይገኛል፡፡
በአለም ላይ ከ100 አደገኛና መጥፎ አረሞች አንዱ የሆነው እምቦጭ ከ40 አመታት በፊት ወደ ኢትየጵያ እንደገባ ይነገራል፡፡ አረሙን ማጥፋት አይቻልም ይልቁንስ መቀነስና እንዳይዛመት ማድረግ ዋነኛ አማራጭ ነው የሚሉት አቶ በልስቲ በርካታ ሀገራት እምቦጭን ማጥፋት አለመቻላቸውን ይናገራሉ፡፡
አቶ በልስቲ ባለፉት ስድስትና ሰባት አመታት እምቦጭን ለመቆጣጠር በየአመቱ 200 ሺህ ያህል ሰዎችን ያሳተፈ ስራ በመስራት እስከ 95 በመቶ የሚሆነውን ሽፋን ከሀይቁ ላይ ማንሳት የተቻለ ቢሆንም እምቦጭ ካለው ስነህይወታዊ ባህርይ አንጻር በቀላሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ገነነ ተፈራ በኢትየጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት የደቂቅ አካላት ብዝሀ ህይወት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ አቶ ገነነ እምቦጭ ለከሰል፣ ለከብቶች መኖ፣ ለማዳበሪያ እና ወረቀት ምርቶች እንደሚውል በጥናት መረጋገጡን ይናገራሉ እናም እምቦጭን ለተለያዩ ግብዐቶች እንዲውል በማድረግ መቆጣጠር ይቻላል ይላሉ፡፡
አረሙ ጉዳት ያለው ቢሆንም ጥቅምም ስላለው ጥቅሙን መሰረት ያደረገ የመቆጣጠር ስራ በመስራት እንዳይዛመት ማድረግ ላይ በትኩረት መስራትም አማራጭ ነው የሚል ሀሳብ አላቸው፡፡
ሁሉም አካል የየራሱን ድርሻ በመውሰድና በጋራ በመስራት የተሻለ የመቆጣጠር ስራ መስራት ቻላል የሚሉት አቶ ገነነ አለምአቀፍ ተሞክሮዎችም የሚሳዩት ይህንን ቅንጅታዊ ስራ ነው ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ ትኩረት ያስፈልገዋል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ማን ምን ይሰራል የሚለውን በጋራ በመንደፍ ቅንጅታዊ አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ገነነ በዋናነት አረሙን ለማጥፋት ለሚከናወኑ እያንዳንዳቸው ተግባራት ባለቤት መስጠት ጥሩ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡
በድልነሳ ምንውየለት