የሰው ልጅ ልዩነትን ያለ አንድነት፣ አንድነትን ያለ ልዩነት ሊገልፀው አይችልም፡፡ አንድነት የሚለው ንድፈ ሃሳብ በልዩ ልዩ ማንነቶች ውስጥ የጋራ ማንነት እንዳለ የሚገልፅ ነው፡፡አንድነት የሚኖረውም ልዩነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡
ዛሬ በክፉ ከሚመለከቱዋቸው የራሳቸው ዜጎችና ከርስ በርስ ጦርነት ሸሽተው ኢትዮጵያ መሸሸጊያ እንድትሆናቸው አገራችንን የሙጢኝ ያሉት የቅርብም የሩቅም አገራት ጎረቤቶቻችን በየጎዳናው ላይ ሲለምኑና በስደተኛ ካምፖች ተኮልኩለው የሚሰፈርላቸውን ጥሬ እህል ሲቀራመቱ ማየት ምንኛ አሳዛኝ ትዕይንት ነው፡፡ ይህ የሆነውም የሰው ልጅ አንድ የሚያደርገውን እሴቱን አሽቀንጥሮ ጥሎ ለጊዜያዊ ጥቅም በመገዛቱ፣ የጋራ ማንነቱን ስለዘነጋና ራስ ወዳድነቱ ስላሸነፈው ብቻ ለመሆኑ ምንም ዋቢ መጥቀስ አያሻም፡፡
ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት በሱዳኑ የብሉ ናይል ግዛት በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት በየቀኑ ወደ 1ሺህ ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ጋምቤላ ክልል እየገቡ በመሆኑ ይህ ፍልሰት ቀደም ሲል ከነበረው ከአስር እጥፍ በላይ በመድረሱ ሁኔታው በኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠሩን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ማስታወቁ ይታወሳል።
በአገራቸው የተነሳውን ጦርነት ሸሽተው የተሰደዱ የየመንና እ.አ.አ. ከ2011 ጀምሮ በጦርነት ከምትታመሰው ሶሪያ ከ500 የሚበልጡ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በልመናና በመለስተኛ ስራ ላይ ተሰማርተው መገኘታቸው ሌላው አሳዛኝ ታሪክ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት “ከመጠለያ ጣቢያ ውጪ” ከሚለው ፖሊሲ በተጨማሪ ኤርትራውያን ስደተኞችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ 17ሺ345 ስደተኞች መኖራቸውና በሌሎች ከተሞች ራሳቸውን ማስተዳደር ከቻሉ መኖር የሚችሉበት መንገድ ተመቻችቶላቸው የተሻለ ኑሮአቸውን እየገፉ ሲሆን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ፅህፈት ቤት መረጃ መሰረት በአሁኑ ወቅት 905 ሺ831 የተመዘገቡ ስደተኞች በኢትዮጵያ ይገኛሉ።196ሺ350 የሚሆኑ ስደተኞች በኢትዮጵያ በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች ለመማር ተመዝግበዋል። ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ስድተኞች በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሲሆኑ፤ 3000 ስደተኞች ደግሞ በኮሌጅና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው። ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ስደተኞች ደግሞ በህፃናት መንከባከቢያ ወይም መዋዕለ ህፃናት የሚገኙ ናቸው።
ኢትዮጵያ ይህ ተግባሯ በርካታ ስደተኞችን ከተቀበሉ የአፍሪካ አገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ያስመድባታል።በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የጎረቤት አገራት ዜጎች ፍልሰት ታላቅ ትኩረት ስለተሰጠውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 9ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባ የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ አዋጅን በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁ ይታወሳል።ይህም ስደተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡
አዋጁ በተለያየ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ስደተኞች ልዩ ልዩ መብቶችን በማጎናፀፍ፤ኢትዮጵያ ለምታስተናግዳቸው ስደተኞች የምታደርገውን እንክብካቤ በማስቀጠል ዕውቅና ያገኙ ስደተኞች ከመንቀሳቀስ መብት በተጨማሪ ትምህርትና ሥራ የማግኘት መብት እንዲኖራቸው ያስችላል። በዚህ ዓለም አድናቆቱን ሰጥቶናል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን መሰሉንና ዓለም ያደነቀውን በጎ የማድረግ ተግባር ብታከናውንም ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን እድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነፃ ፍላጎታችን፣ የሕግ የበላይነትና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል» የሚለውን ሕገ መንግስት የተፃረሩ፣ አብሮ የመኖርን እሴት የዘነጉ፣ ሰብዓዊነት የራቃቸውና የግል ጥቅም ብቻ የናፈቃቸው አንዳንድ አካላት ተጋብቶና ተዛምዶ እንዲሁም የአገሩን ባላንጣ በጋራ የመከተውን ወገኑን የማፈናቀል ተግባር መፈፀማቸው ዓለም ከሚያደንቀን ተግባር የራቀ ሆኖ ታይቷል፡፡ይህ የሚወገዝ ድርጊት ነው፡፡ለእኛ ኢትዮጵያውያን አይመጥነንም፡፡
ለጎረቤት ሃገሮች ጥላና ከለላ የሆንን ህዝቦች የራሳችንን ዜጎች ማፈናቀል አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እሴቶቻችንን የሚሸረሽሩ ድርጊቶች እየተከሰቱ፣ የሕዝብን ፍላጎት የማይወክሉ ተግባራት እየተፈፀሙ፣ ለሥልጣን በሚደረግ ፍትጊያ የአገር ገፅታን የሚያበላሹ ተግባራት በመፈፀማቸው ኢትዮጵያውያን በመረጡት ሥፍራ የመኖር፣የመማር፣ የመሥራት፣ የመዘዋወርና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብታቸው አደጋ ላይ በመውደቁ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፤ ከትምህርት ገበታቸው ተገልለዋል፤ ንብረታቸው ወድሟል፤ ሕይወታቸው ጠፍቷል፡፡በአንጻሩ የጎረቤት ሃገራት ዜጎች መሰረታዊ ነገር ተሟልቶላቸው ማኖር እየቻልን የሃገር ውስጥ ተፈናቃይ ሊኖረን አይገባም ነበር፡፡ ስለሆነም አሁን ወደ ቀያቸው መመለስ የጀመሩት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት በማቋቋም ከዚህ በፊት የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት መፍታት ይገባናል፡፡
ከቀደመው ታሪካችን እንደምንረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታወቀው በዚህ ዓይነቱ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት ሳይሆን አብሮ በመኖር ጠንካራ ማህበራዊ ትስስሩ እና አገራዊ አንድነቱ ነው፡፡
ከነብዩ መሃመድ ተከታዮች ጀምሮ ባዕዳንን በስደተኛነት በማስተናገድ የሚታወቅ ነው፡፡ስለሆነም ዓለም በሚያውቀን የሩህሩህነት፣የአዛኝነትና አብሮ የመኖር ድንቅ ባህል ተጠቃሽ ወይም ምሳሌ በመሆን ገናናነታችንን ልናስመሰክር ይገባናል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2011