ባህል የሰውን ልጅ ሰላም ለማስጠበቅ ራሱ የፈጠረው ትልቅ እሴቱ ነው። አካባቢው ወይም አዕምሮው የሚጠይቀውን ነገር መመለስ የሚያስችለው ሀብትም ነው። በየትኛውም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ውስጥ ባሉ ባህሎች ውስጥ ሰላም ይሰበካል። ባህል በመሰረቱ ባሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ የተፈጠረ በመሆኑ ሰላምን ለማስጠበቅ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነ በርከት ያሉ የጥናት ስራዎች አረጋግጠዋል።
በአገራችን ባህል ለሰላም ያለው ፋይዳ ትልቅ ቢሆንም በወጉ አልተጠቀምንበትም። ባህላችንን በአደባባይ ስንገልፅ፣ ስናስተዋውቅና ስናንፀባርቅ ያለውን የሰላም ትሩፋት በውል ተገንዝበን ሳይሆን ለታይታና ለተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ላይ ብቻ አነጣጥረን በመሆኑ አገሪቱ ከባህል መጠቀም የሚገባትን ያህል ሳትጠቀም ቀርታለች። በተለይ አሁን አሁን ባህልን ‹እኔ የበላይ ነኝ› በሚል አንዱ በሌላው ላይ ጫና በሚፈጥር መልኩ እየተተገበረ መሆኑ ሁኔታው ትኩረት እንዲቸረው አስገዳጅ ሆኗል።
ባህል ለሰላም ግንባታ ያለው ፋይዳ ትልቅ ለመሆኑ ግልፅ ማሳያው ከዚህ ቀደም በአገራችን በየትኛውም አካባቢ ግጭት ተፈጥሮ እርቅ ሲደረግ ጊዜ እና ጉልበት ሳይጠይቅ በቀላሉ ይተገበራል፤ ውጤታማም ነው። አሁን ግን በዚህ መልክ እርቅ በቀላሉ እየተፈጸመ አይደለም። በተለይ በአሁኑ ወቅት ደረጃው ይለያይ እንጂ ግጭት ሲፈጠር ለባህላዊ እርቅ የሚሠጠው ክብደት እየቀነሰ ነው። ውጤታማነቱና ዘላቂነቱም አጠያያቂ ነው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ባህልን በሚመለከት ተዘዋውረው ያከናወኑት ጥናት እንደሚያስረዳው ይህ ሁኔታ ሁለት መልክ መያዙን ነው። አንደኛው ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ለባህል ያለን አረዳድ አመጋገብ፣ አለባበስና ጭፈራ ላይ ብቻ የተገደበ መሆኑ ነው። ይህም ባህል ከሚሰጠን ጥቅሞች 10 በመቶ ብቻ ነው። ቀሪው 90 በመቶ ለአዕምሮ እና ሰብዕና ግንባታ ላይ የሚውለው ትልቁ ፋይዳ ተዘንግቶ ቆይቷል።
በሁለተኛነት የተነሳው ባህል ውስጥ የፖለቲካ ጥቅም ሰርጎ መግባቱ ነው። ይህም ባህል ለሰላም እሴት ግንባታ ያለውን ፋይዳ ክፉኛ ጎድቶታል፤ አሽመድምዶታልም። አንዳንድ የባህል ባለቤት ውስጥ ያሉ ትላልቅ አባቶች ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የቀረበ ግንኙነት ኖሯቸው ትርፍ በመፈለግ ባህላዊ እሴቶች የሚደበዝዙበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህም ከዚህ ቀደም ግጭት ሲፈጠር ‹እርቅ› ሲባል ፈጣን ምላሽ የሚገኝበት ይህ እሴት ዛሬ ደብዝዞ አሁን ላለንበት ቀውስ ሁሉ ለመዳረግ የራሱን ሚና ተጫውቷል።
በጥናቶቹ የባህል ባለቤት የሆኑ አባቶች እንደሚናገሩት የፖለቲካ አመራሩ በባህል ስራዎች ጭምር ጣልቃ ገብቷል። አመራሩ የተለያዩ ጥቅሞችን በማዘጋጀትና በመስጠት በተለይ የእርቅ እሴቶቻችን ላይ ዘምተዋል፤ ባህሎቹንም ከጥቅም ውጪ አድርገዋቸዋል። በዚህ ሂደት ከፖለቲካውም ከባህሉም ሆነው የሚያተራምሱ ሀይ ሊባሉ ይገባል። ይህ ማለት ግን በአንዳንድ ባህሎች እንደ የጋሞ አባቶች ያሉት ደግሞ ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው የከፋ ውድመት ሊያስከትል ከሚችል አገራዊ ቀውስ እየታደጉን ያሉ መሆኑን መዘንጋት የለባቸውም።
በዚህ ከቀጠልን አደጋው ቀላል አይደለም። በእጃችን ያሉትን የተለያዩ እሴት ያላቸው ባህሎቻችንን እናጣለን። ባህል አልባ ትውልድ ሆነን በመጤ ባህል ተገዝተን ወደከፋ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ እንዘፈቃለን። ማህበረሰባዊ መረጋጋት አይኖርም፤ ሰላማችንም አሁን ካለበት ደረጃ ተባብሶ የከፋ ይሆናል።
ባህል ሲጠፋ ተመሳሳይ አስተሳሰብ አይኖረንም፤ ተቀራራቢና ተመሳሳይ አስተሳሰብ ከሌለን ደግሞ የጋራ ፍልስፍና ርቆን ስነ ምግባራችን ከዚህ በታች ዘቅጦ እንደሰው አብሮ መኖር አንችልም። አሁን ‹‹የእኔ ነው›› የምንለው ወደ ከፋ ግለኝነት ይስፋፋል፤ አዎንታዊ የሆነው ይሉኝታም ይጠፋል።
በአሁኑ ወቅት አገር በቀል ባህሎቻችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በፖለቲካው ፍላጎት እና በእሴት ግንባታ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን እንረዳለን። ይህ ጉዳይ በተለይ አሁን ላለንበት የሰላም መደፍረስ ችግር የባህል እሴቶቹ በላቀ ሁኔታ እንዲጠቅሙን ዘርፉ ያሉበት ሳንካዎች ሊወገዱ ይገባል። በዋናነት ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎችም ትኩረት ሊነፈጉ አይገባም።
የመጀመሪያው ስራ ባህል ከታይታ ውጪ ባሉ በተለይ ከአልባሳት፣ አመጋገብ እና አለባበስ ባለፈ ያሉ አብዛኞቹ እሴቶች ላይ አረዳዳችንን ማስተካከል ነው። ሁለተኛው የፖለቲካ አመራሩ በተቻለ መጠን ነባሩን እሴቶች የማጎልበትና በአግባቡ በተመረጡ ጉዳዮች መጠቀም የሚያስችለው የፖሊሲ አስገዳጅነት ሊከበር ይገባል። ከዚህ ውጭ ግን ስልጣንን ተገን በማድረግ እጅን ባህሎች ውስጥ እንዳሻን በማስገባት ማበላሸት ለማንም የማይበጅ ተግባር በመሆኑ ሊገታ ይገባል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2011