ኢትዮጵያ የበርካታ ቱሪስት መስህቦች ባለቤት ናት፡፡ በተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅትም በዓለም ቅርስነት ከመዘገባቸው ቅርሶች ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሃገር መሆኗን መስክሯል፡፡
እነዚህ የኢትዮጵያ ቅርሶች የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔም ጭምር የሚዘክሩ ናቸው። ለምሳሌ 1700 ዓመት እድሜ እንዳላቸው የሚገመቱት የአክሱም ሃውልቶች ዛሬም ቢሆን የጥበብ ደረጃቸው ብዙዎችን የሚያስደምም ነው፡፡ የሮሃ ወይም የአሁኗ ላሊበላም በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት መቀመጫ ከመሆኗም በዘለለ ትልቅ የስልጣኔ እምብርት እንደነበረች ይነገራል፡፡ በከተማዋ ከአንድ አለት ተፈልፍለው የተገነቡት 11 የሚሆኑ የንጉስ ላሊበላ አብያተክርስቲያናት ትልቅ የቱሪዝም መስህቦች ናቸው፡፡ በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ መንግስት መቀመጫ የነበረችው የጎንደር ከተማም ያበረከተችው የጎንደር ቤተመንግስት ለጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ትልቅ ሃብት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ መገለጫዎች ቁጥር በርካታ ከመሆናቸውም ባሻገር ድንቅ ስራዎቻቸውም ዘመን ተሻጋሪዎች ናቸው፡፡ የሃረር ከተማና የጀጎል ግንብ፣ የጅማ አባጅፋር ቤተመንግስት፣ የድሬ ሼህ ሁሴን መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች፣ የሶፍመር ዋሻ፣የሼህ ሆጀሌ መኖሪያ፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ ወዘተ የአገራችን የቱሪዝም ሁነኛ መሰረቶች ናቸው። ከማይዳሰሱ ሃብቶቻንም ውስጥ በዩኒስኮ ጭምር የተመዘገቡት የመስቀል በዓል፣ የፊቼ ጨምበላላ እና የገዳ ስርዓት ይገኛሉ፡፡
የተለያዩ ብርቅዬ አእዋፋትና እንስሳት እንዲሁም እፅዋትን አቅፈው የያዙትና በተፈጥሮ አቀማመጣቸውም የቱሪስትን ቀልብ የመግዛት አቅም ያላቸው ብሄራዊ ፓርኮቻችንን እና ጥብቅ ደኖችም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው እድገት የላቀ ሚና አላቸው፡፡
ከ80 በላይ የሚሆኑት ብሄር ብሄረሰቦቿ ያላቸው ድንቅ ባህልም ለቱሪዝም መስህብ በመሆን የላቀ አስተዋፅኦ አለው፡፡ በአገራችን በሁሉም አቅጣጫዎች ስንጓዝ የምናገኘው የአኗኗር ዘይቤ የተለያየ ከመሆኑም ባሻገር ለሰለጠነው ዓለም ጭምር ቀልብን የሚገዙ ባህላዊ ክንውኖችንም የሚያካትት ነው፡፡ የአለባበስ፣ የአመጋገብ፣ የጭፈራ፣ የሰርግ፣ የለቅሶና ሌሎች ክዋኔዎችም የየራሳቸው ገጽታ ያላቸው ናቸው፡፡
ያም ሆኖ ግን አገራችን በዘርፉ ያላትን ሃብት ያክል በአግባቡ አለመጠቀሟን ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በአንድ በኩል የቱሪዝም ዘርፉን በአግባቡ አለማስተዋወቃችን በሌላ በኩል ደግሞ ዘርፉን ለማሳደግ ተገቢው ትኩረት አለመስጠቱ እንደምክንያት ይነሳል፡፡
በመሆኑም ከዘርፉ የሚገባንን ጥቅም ለማግኘትና ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር የቱሪስት መስህብ በሆኑ አካባቢዎች ያለውን መሰረተ ልማት አገልግሎት ይበልጥ ማሳደግ፣ አገራችን ያላትን የቱሪዝም ሃብት በስፋት ማስተዋወቅና የሌሎችን አገራት ልምድ በመውሰድ ዘርፉ የሚያድግበትን መንገድ መቀየስ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምንጭ ሊታይ ይገባል፡፡
ከዚህም ጎን ለጎን በቅድሚያ የአገራችን ህዝብም ስለራሱ አገር የቱሪዝም ሃብት በአግባቡ ሊረዳ ይገባል፡፡ በተለይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ዜጎች ስለአገራቸው የቱሪዝም ሃብት በአግባቡ የሚረዱበትን መንገድ መፍጠርና በሚሄዱበት ቦታ ስለአገራችው የሚያስተዋውቁበትን መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡
የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች እንደሚሉት የኮሙኒኬሽን ስራ ውጤታማ የሚሆነው በተለያዩ መንገዶች መረጃዎችን ማዳረስ ሲቻል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከኢትዮጵያ ውጭ ለስራም ሆነ ለሌሎች ጉዳዮች የሚጓዙ ዜጎች ለአገራቸው አምባሳደር ሊሆኑ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅድሚያ ስለአገራቸው ጠንቅቀው መረዳትና በሚሄዱበት ቦታ ምን እና እንዴት መረጃ መስጠት እንዳለባቸው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግን በአብዛኛው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ወደ ውጭ የሚሄዱ ዜጎች አንድም ስለአገራቸው በቂ መረጃ ሳይኖራቸው በሌላም በኩል ስለሚያውቁትም ነገር ለሌሎች እንዴት ማካፈል እንዳለባቸው በቂ እውቀትና ግንዛቤ ሳይይዙ ስለሚሄዱ አንዳንድ ጊዜ የአገራቸውን ገጽታ ከመገንባት ይልቅ አበላሽተው የሚመለሱበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ከዚህም ባሻገር በስራ ምክንያት በውጭ አገራት በአምባሳደርነትም ሆነ በአታሼነት የሚሄዱ ዲፕሎማቶች ስለአገራቸው በቂ ግንዛቤና ስለቱሪዝም ሃብታችን በቂ እውቀት ይዘው ሊሄዱ ይገባል፡፡ አምባሳደርነት አገርን መወከል በመሆኑ በሚመደቡበት ስፍራ ሁሉ ስለአገራቸው የቱሪዝም ሃብት በማስተዋወቅ ቱሪስቶች አገራችንን እንዲጎበኙ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም አንድን ቱሪስት ወደ አገር ቤት መላክ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት በመሆኑ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የላቀ ነው፡፡
በሌላ በኩል በአገራችን አሁን አልፎ አልፎ የሚታየው አለመረጋጋትና የሰላም መደፍረስ ችግሮች የአገራችንን ገጽታ የሚያበላሹና ቱሪስቶችንም የሚያሸሹ በመሆኑ ሰላምን ለማምጣትም መረባረብ ተገቢ ነው፡፡ እኛ ስንዋደድና ስንከባበር ሌሎቹም ያከብሩናል፤ ወደእኛም ለመምጣት ፍላጎት ያድርባቸዋል፡፡ በመሆኑም ስለሰላማችን ደጋግመን ልናስብበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011