የአዲስ አበባ ወንዞች መበከል ከአዲስ አበቤዎች ባለፈ በታችኛው የወንዞቹ ተፋሰስ አካባቢዎች በሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ። ችግሩም በጊዜ መፍትሄ ካልተሰጠው ጉዳቱን ሊያከፋው፤ ለጭቅጭቅም መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ። የሸገር ፕሮጀክትም ይሄን ችግር ለማቃለል ሁነኛ መፍትሄ እንደሚሆን ምሑራን ይገልፃሉ። ፕሮፌሰር ተሾመ ሶረምሳ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢያዊ ሳይንስ ማዕከል የድህረ ምረቃ ፕሮግራም መምህርና ተመራማሪ ናቸው።
የአዲስ አበባ ወንዞችን በተመለከተ የተከናወኑ በርካታ ጥናቶችንም መርተዋል። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የአዲስ አበባ ወንዞች ሁኔታ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ደረጃ መሰረት ከተበከለ ወንዝነት በጣም ወደተበከለ ወንዝነት ተሸጋግረዋል። ይህ ማለት ወንዞቹ ለምንም ጥቅም መዋል የሌለባቸው ሆነዋል ማለት ነው። ይሁን እንጂ በተለይ በወንዞቹ የታችኛው አካባቢዎች ላይ የተለያዩ የመስኖ ስራዎች እየተከናወኑባቸው፤ አትክልቶችም እየለሙባቸው ነው። ይህ ብቻም ሳይሆን በአንዳንድ ቦታዎች ልጆች በውሃው ውስጥ ሲዋኙና ሰዎችም ሲታጠቡባቸው ይስተዋላል።
እነዚህ ወንዞች ደግሞ በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ደረጃ በሚከለክለውና ለምንም ዓይነት ጥቅም መዋል የሌለባቸው ሆነው ሳሉ በዚህ መልኩ በጥቅም ላይ መዋላቸው በሰውም ሆነ እንስሳት ጤና ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍ ያለ እንዲሆን ያደርገዋል። ፕሮፌሰር ተሾመ እንደሚሉት፤ ምንም እንኳን ተጨማሪ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ወንዞቹ በታችኛው መዳረሻቸው አካባቢዎችና መንደሮች ላይ ያላቸው ጉልህ ተጽዕኖ ወደ አዋሽ ወንዝ ጭምር የሚገባ ከመሆኑ ጋር የሚገለጽ ነው።
ይህ ችግር ደግሞ ተገቢ መፍትሄ የሚፈልግ እንደመሆኑ፤ የሸገር ፕሮጀክት እውን ሲሆን ከከተማዋ ባለፈ በእነዚህ አካባቢዎች የሚደርስን ጉዳት ለማቃለል ያስችላል።ከአዲስ አበባ ወንዞች ውስጥ በዋናነት የአቃቂ ወንዝን የብክለት ደረጃ የሚያነሳውና በኢትዮጵያና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አጋር አካላት አማካይነት እአአ በ2005 የቀረበ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ ከከተማዋ በየቀኑ ከሚወጣው 1ሺ335 ኪዩቢክ ሜትር(468 ቶን) ደረቅ ቆሻሻ ከ48 በመቶው በላይ በተለያየ መልኩ ወደ ወንዞች ይገባል።
ከከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች ከሚወጡ ከፍተኛ ፍሳሽ ቆሻሻዎች ውስጥም ከ60 በመቶው በላይ በቀጥታ ወንዞቿን (በተለይም ሁለቱ አቃቂ ወንዞችን) ይቀላቀላሉ። በዚህ መልኩ የሚፈጠር የወንዞች መበከል ደግሞ በሰዎች ጤና፣ በአካባቢና ብዝሃ ሕይወት የጎላ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።ሪፖርቱ እንዳመለከተው፤ ወንዙ ከከተማዋ ውጪ ላሉ አካባቢዎች ለመጠጥ፣ ለምግብ ማብሰያና ንጽሕና መጠበቂያ፣ ለመስኖና መሰል ግልጋሎትን ይሰጣል።
ሆኖም ከከተማዋ የሚወጣው ደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ በተለያየ መልኩ ከወንዙ ጋር ስለሚገናኝ ወንዙ እንዲበከልና ለህብረተሰቡ የሚሰጠው ግልጋሎት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንዲያመዝን አድርጓል። ለምሳሌ፣ የአካባቢ ብክለትን ከማስከተሉ ባለፈ፤ ውሃው የኦክስጅን እጥረት እንዲኖርበት በማድረግ በውሃ ውስጥ ያሉ ዓሳን ጨምሮ የተለያዩ ዝርያዎች ጠፍተዋል። በታችኛው የውሃው ክፍል በወንዞቹ በሚገለገሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የጤና ችግርን በመፍጠር ለከፍተኛ የሕክምና ወጪ በመዳረግ ላይ ይገኛል።
በመሆኑም ችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ሊደረግለት ይገባል።በተመሳሳይ እአአ በ2015 የአቃቂ ወንዝ መበከል በተለይ በገጠሩ ማህበረሰብ ላይ እያሳደረ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ የዳሰሰ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ወንዙ በከባድ ብረትና ጎጂ ኬሚካሎች ለከፍተኛ ብክለት ተጋልጧል። በታችኛው አካባቢ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚገለገሉበት እንደመሆኑም ለከፋ ጉዳት ዳርጓቸዋል። በህብረተሰቡ ላይ እያሳደረ ካለው የጤና ችግር ባለፈም፤ በእንስሳት፣ በእጸዋት፣ በውሃ ውስጥ ባሉ ህብቶችና አካባቢ ላይ ጉልህ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።
ይህ ችግር ተገቢው መፍትሄ እስካልተበጀለት ድረስም በዚህ መልኩ ችግር ላይ የወደቁት የህብረተሰብ ክፍሎች ጤናና የእንስሳቶችም ሕልውና አደጋ ላይ ይወድቃል።በወንዞች ዙሪያ የሚስተዋለውን ችግር ከማቃለል አኳያ የተቀናጀ የወንዞች አስተዳደር ስርዓትና አሰራር ያለውን ፋይዳ ማመላከት ላይ ትኩረቱን በማድረግ እአአ በ2018 የተከናወነ ሌላ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ፤ ለአቃቂ ወንዝ መበከል ከቤት የሚወጡ ቆሻሻዎችን ጨምሮ ኢንዱስትሪዎች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎችም ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን ወደወንዝ በመልቀቅ ጉልህ ሚና አበርክተዋል።
በዚህም ወንዙ በባክቴሪያና ሌሎች ኬሚካሎች እንዲጎዳ፤ በአካባቢው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም ሊገለገሉበት በማይገባ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሆኗል። ይሄም በበርካታ አጥኚዎችና ጥናቶች የተመላከተ ቢሆንም፤ ጉዳዩ ችግሩን ከመናገር ያለፈ የመፍትሄ እርምጃን ይፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ተገቢው የወንዞች አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት ይኖርበታል።የእነዚህን ጥናቶች ሀሳብ የሚጋሩት ፕሮፌሰር ተሾመ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ወንዞቹ የአዲስ አበባን ቆሻሻ ተሸክመው ነው ወደሌላ የሚሄዱት። ይህ ደግሞ በአዲስ አበባ ተመርተው በወንዞቹ አማካኝነት ወደሌላ የሚሄዱ ቆሻሻዎችን የማስቀረት ስራን ይጠይቃል። ከዚህ አኳያ የሸገር ፕሮጀክት እውን ከሆነ ቆሻሻውን አጣርቶ ንጹህ ውሃ እንዲሄድ ማድረግና በቆሻሻው ምክንያት ይደርስ የነበረውን ችግር ማቃለል ያስችላል።
ይህ ፕሮጀክት ምንም እንኳን አካባቢን ማስዋብ የሚለው ሀሳቡ ጎልቶ የሚነገርለት ቢሆንም፤ ከዚህ የዘለለ በርካታ ፋይዳዎች አሉት። ምክንያቱም፣ አካባቢን በማስዋብ ሂደት ውስጥ ደረቅ ቆሻሻን ማስወገድ አለ፤ ፍሳሽ ቆሻሻዎችንም በአግባቡ የማከም/የማጣራት ሥራ ይከናወናል፤ አዲስ አበባም እንደ አፍሪካ መዲናነቷ ደረጃውን የጠበቀ ውበት እንዲኖራት ይደረጋል፤ በሂደት ውስጥም አረንጓዴ ሳንባ ይፈጠራል። ከዚህ ባለፈም ፕሮጀክቱ አረጋውያን በወንዝ ዳርቻዎች አረፍ ብለው የሚጨዋወቱበት፤ ወጣቶች እየተዝናኑ የሚያውቁበት፤ ህዝቡ ወግና ባህሉን የሚለዋወጥበት ብሎም ማህበራዊ ትስስሩን የሚያጠናክርበት የተለያዩ ግንባታዎችና ሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ልማቶች የሚከናወኑበት ነው።
እናም የሸገር ፕሮጀክት አንደኛ፣ እንደማንኛውም ያደጉ አገራት ከተሞች ከተማው ጽዱና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን፤ ህብረተሰቡም ንጹሕ አየር እንዲያገኝ ያደርጋል። ሁለተኛ፣ የአዲስ አበባ ወንዞች ከከተማዋ ይዘው የሚወጡትንና በታችኛው አካባቢ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩበትን ቆሻሻና ኬሚካል በንጹህ ውሃ እንዲተኩት ያደርጋል።እንደ ፕሮፌሰር ተሾመ ገለጻ፤ የአዲስ አበባ ወንዞች በአፈጣጠራቸው ከተራራ አካባቢ ተበታትነው የሚነሱና በሂደት እየተሰባሰቡ በአንድነት አባ ሳሙኤል የሚገቡ ናቸው። እነዚህ ወንዞች ቀድሞ እንደማንኛውም ወንዝ ንጹህ ነበሩ።
ሆኖም ከጊዜ ወደጊዜ ንጽሕናቸው እየጎደለ፤ የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር ሲጨምርና ኢንዱስትሪውም ሲበዛ ብክለቱም በዛው ልክ እየበዛ መጥቶ አሁን ላይ ለሰውም፤ ለእንስሳትም አገልግሎት የማይሰጡበት ይልቁንም ለጉዳት የሚዳርጉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።እናም አዲስ አበባ በዚህ መልኩ የሚገለጹ ወንዞቿን ማጽዳትና በታችኞቹ አካባቢዎች ላይ የሚያደርሱትን ተጽዕኖ ማስቀረት ካልቻለች ወንዞቹ በታችኛው አካባቢ ላይ የሚያደርሱት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ይበረታል። በተለይም ከጤና ጋር ተያይዞ ያለው ጉዳት ስር እየሰደደ ይሄዳል። በዚህ መልኩ አካባቢው እየተጎዳ የሚሄድ ከሆነ ደግሞ በህዝቦች መካከል ሰላማዊ ግንኙነት እንዳይኖር፤ ለጭቅጭቅና ለግጭት መነሻ ሊሆንም ይችላል።
ይህ ከመሆኑ በፊት ግን ከተማዋ ጽዱና ቆሻሻን ወደወንዞች የማትለቅቅ እንድትሆን ማድረግ ይገባል።ለዚህ ደግሞ መንግሥት በቁርጠኝነት በመስራት፤ ሚዲያውም የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር በማከናወን፤ ህብረተሰቡም ቆሻሻን ከማስወገድ ጀምሮ የሚጠበቅበትና ሃላፊነት በመወጣት የመተጋገዝና በትውልድ ቅብብሎሽ የሚጓዝ ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። የአዲስ አበባ ወንዞችም ባልታከመ ፍሳሽና ቆሻሻ ምክንያት የተበከለ ውሃን ይዘው መሄዳቸው እንዲያበቃ የሚያደርግ የአካባቢ ጥበቃ ሕግን መሰረት ያደረገ ተግባር መከናወን ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2011
ወንድወሰን ሽመልስ