”ልጅ ለእናቱ እንቁላል እየሰረቀ እናቴ ይሄን አገኘሁ እያለ ይሰጣታል፤ እናትም ልጇ እውነትም ወድቆ አግኝቶ ነው፣ ለእኔ አስቦ ሰጠኝ እያለች ልጇን አመስግና ትቀበላለች። ጎሽ ጎሽ የተባለው ልጅም በለመደ እጁ በሬ ሲጎትት እጅ ከፍንጅ ተያዘ እና ዘብጥያ ተወረወረ። ያን ጊዜ ታዲያ ያማረረው የሰረቀ እጁን ሳይሆን የተቀበለችውን እናቱን ነበር፤ ‹‹ምነው በእንቁላሉ በቀጣሽኝ አደባባይ ባለቆምሽኝ›› አለ ይባላል። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንደሚባለው ሆነና ዛሬ ለኑሮ ውድነቱ ምክንያት የሆነው በንግድ ስርዓቱ ላይ ያንዣበበው አደጋ በእንጭጩ ካልተቀጨ ነገ ለሀገር ትልቅ ስጋት ይሆናል።
የኑሮ ውድነቱ ከዕለት ወደ ዕለት ሽቅብ እንጂ ቁልቁል መውረድ አልሆነለትም። የእህል፣ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ ወተት እንዲሁም በሌሎች የዕለት ተዕለት ፍጆታዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ የህብረተሰቡ ትከሻ ከሚሸከመው በላይ እየወጣ ነው። ሀይ ባይ ያጣው የቤት ኪራይም በተመሳሳይ ነዋሪውን እያማረረ ይገኛል። ለእያንዳንዱ ነገር የዋጋ ጭማሪ ዋና ተዋናይ ህገወጥ ደላሎች መሆናቸው ጸሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። አሁን ጥያቄው እስከመቼ ነው የንግድ ስርዓቱ በደላሎች እየተመራ፣ ህዝብም እየተማረረና እያለቀሰ የሚቀጥለው የሚለው ነው።
ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌላው የዋጋ ጭማሪ በእያንዳንዱ ነገር ላይ ሲጨመር መነሻው ምንድነው? የሚለውን የንግድ ስርዓቱን በበላይነት የሚመራው አካል ቆም ብሎ ማስተዋልና የችግሩን ሰንኮፍ ፈልጎ መንቀል መቻል አለበት። በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱ ማቆሚያ ያለው አይመስልም፡፡ ለምሳሌ ያህል ሰሞኑን አንድ ኪሎ ጤፍ 37 ብር ፣ ምስር ክክ ከ75 እስከ 80 ብር፣ ሌሎች የጥራጥሬ እህሎችም ከ25 እስከ 40 ብር በኪሎ እየተሸጠ ነው።
እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል። የእያንዳንዱ የኑሮ ውድነት ጭማሪ መነሻ ምክንያት ግን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ በተሰገሰጉ ደላሎች ምክንያት የተፈጠረ እንጂ ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለውም፤ በምንም ምክንያት የእህል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር አይያያዝም።
የቤት ኪራይም በምንም መልኩ ከዶላር ጋር ግንኙነት የለውም። ስለዚህ ለእያንዳንዱ ነገር የዋጋ ጭማሪም ሆነ የኑሮ ውድነት በተጨባጭ የሚጠቀስ አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለም። ለዚህ ሁሉ ዋነኛው ችግር ፈጣሪ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ ያለው ህገወጥ ደላላ ነው። የንግዱ ማህበረሰብም በግልጽ እያለ ያለው “ደላላ ስራ ሊያሰራን አልቻለም” ነው ።
ደላላው ሰንሰለቱን እስከ አርሶ አደሩ ድረስ በመዘርጋት እህል በዚህ ዋጋ ሽጥ፣ ለእከሌ ሽጥ፣ ለገበያ አታቅርብ… የመሳሰሉ መረጃዎችን በመስጠት በገበያ ላይ እጥረት እንዲፈጠር እንዲሁም የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት ትልቁን ሚና እየተጫወተ ይገኛል። አንድ ምርት ከአምራቹ እስከ ሸማች ድረስ ከአምስት ያላነሰ የደላላ ሰንሰለትን አልፎ ነው የሚመጣው። ይሄ ደግሞ በአንድ በኩል አምራቹን አርሶ አደር የሀብቱና የጉልበቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን በሌላ በኩል ደግሞ የከተማው ሸማች በኑሮ ውድነት እንዲጠበስ እንዲሁም ህጋዊ ነጋዴ ከጨዋታው እንዲወጣ እያደረገው ነው። ይህም የዋጋ ግሽበት ባለ ሁለት አሀዝ እንዲሆን አድርጎታል።
ከዚህም ባሻገር ዛሬ ዛሬ ደላላ የሁሉም ነገር ባለቤት አድራጊ ፈላጭ ቆራጭ ጭምር ነው። በመንግስታዊ ተቋማት ጉዳይ አስፈፃሚ፣ የቤትና የመኪና ሽያጭና ኪራይ ዋጋ ተማኝ፣ ሌላው ቀርቶ የቤት ሰራተኛ ደመወዝ እና በስራ ላይ የመቆያ ጊዜ ሳይቀር ወሳኙ ደላላ ነው። ይሄ ሂደት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ጉዳቱ አሁን ከምናየውና ከምንሰማውም በላይ ይሆናል። የንግድ ስርዓት መዛባቱ ደግሞ የኑሮ ውድነቱን ከማባበሱም አልፎ የሀገር ህልውና የሚፈታተን ይሆናል። እንደ ተረቱ ሁሉ ዛሬ ‹‹በእንቁላሉ›› ያልተቀጣ ደላላ ነገ ወደ ‹‹በሬ›› መግባቱ አይቀርምና ይሄ ከመሆኑ በፊት የንግድ ስርዓቱ ላይ አስፈላጊው ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል። መንግስት የችግሩን ሰንኮፍ ፈልፈሎ በማውጣትም ህብረተሰቡን መታደግ አለበት።
አዲስ መን ሰኔ 9/2011