ተወልዳ ያደገችው የካቲት 12 ትምህርት ቤት አካባቢ ነው።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በፀሃይ ጮራ ትምህርት ቤት የተማረች ሲሆን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም በየካቲት 12 ትምህርት ቤት ተከታትላለች። ከዚያ ደግሞ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብታ ክላርኔት ለአንድ ዓመት ከተማራች በኋላ አቋርጣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ጋዜጠኝነት ማጥናት ጀመረች።
ግና መክሊቷ ሌላ ነበርና ይህንንም ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ አቋርጣ በቲያትርና ጥበባት ትምህርት ክፍል የነፍሷ ጥሪ የሆነውን ቲያትር ከዲፕሎማ እስከ ማስተርስ ድረስ ተማረች። በበርካታ የህፃናት ቲያትሮችና መጻህፍቶች፥ በአጫጭር የሬዲዮና ቴሌቪዥን ድራማዎች፥ በፊልሞችና የግጥም መፃህፍቶቿ ስሟ ጎቶ ይነሳል።
በተለይም ፎንተሊና በተባለ የሬዲዮ ፕሮግራሟ አማተር የኪነጥበብ ሰዎች በር በመክፈት ረገድ ትጠቀሳለች። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የባለስልጣናት ህፀፆች ደፍራ በመናገር ትታወቃለች። ከዛሬዋ የዘመን እንግዳ አርቲስት አስቴር በዳኔ ጋር ስለስራዎቹና ስለወቅታዊ አገራዊ ፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- እናትነት ለአንቺ ምንድን ነው?
አርቲስት አስቴር፡- እናትነት ማለት የተፈጥሮ ፀጋና ስጦታ ነው። እናትነት ማለት ለራስ አለመኖር ማለት ነው። እናትነት ማለት ለሀገር ትውልድ ማፍራት ትውልድን ማቆየት ማበርከት ማለት ነው። እናም እግዚአብሔር ምን ያህል ቢያምነና ቢወደን ነው ሰው ያህል ፍጡር በእኛ ውስጥ አድሮና ተወልዶ እንዲያድግ የፈቀደው ብዬ አስባለሁ።
በተለይ እንደእኔ አይነት የኪነጥበብ ሰውና ሌላ ልወለድ እያለ ሁልጊዜ የሚታገል ሃሳብ ያላት ሴት እናትነት ሌላ ፈተና ነው። ስለዚህ ሁለቱንም ልጆች በእኩልነት ማሳደግ ይጠበቅበታል። ምክንያቱም አንዱን ስታሳድጊ ሌላው ስለሚበደል ማለት ነው። ግን ለእኔ ሁለቱንም በደስታ እየተወጣሁት ነው ብዬ አምናለሁ።
በተለይ ደግሞ የቤት ሰራተኛ ልጆቼን በማይሆን መንገድ ከሚቀርፅብኝ ብዬ ራሴ ነኝ የምሰራው። ብዙውን ግዜ ግን ሁለቱንም ማካሄድ ከባድና አስጨናቂ ነው የሚሆነው። ልጆቼን በምትይበት ጊዜ ውጭ ያለው ስራ ያመልጥሻል። እናም አንድ ቆንጆ ወጥ ሰርቼ ልጆቼ በልተው ሲጨርሱ እሰይ አንድ ፊልም አስመረቅሁ እላለሁ።
አርቲስት አስቴር፡- እናትነት ማለት የተፈጥሮ ፀጋና ስጦታ ነው። እናትነት ማለት ለራስ አለመኖር ማለት ነው። እናትነት ማለት ለሀገር ትውልድ ማፍራት ትውልድን ማቆየት ማበርከት ማለት ነው። እናም እግዚአብሔር ምን ያህል ቢያምነና ቢወደን ነው ሰው ያህል ፍጡር በእኛ ውስጥ አድሮና ተወልዶ እንዲያድግ የፈቀደው ብዬ አስባለሁ። በተለይ እንደእኔ አይነት የኪነጥበብ ሰውና ሌላ ልወለድ እያለ ሁልጊዜ የሚታገል ሃሳብ ያላት ሴት እናትነት ሌላ ፈተና ነው።
ስለዚህ ሁለቱንም ልጆች በእኩልነት ማሳደግ ይጠበቅበታል። ምክንያቱም አንዱን ስታሳድጊ ሌላው ስለሚበደል ማለት ነው። ግን ለእኔ ሁለቱንም በደስታ እየተወጣሁት ነው ብዬ አምናለሁ። በተለይ ደግሞ የቤት ሰራተኛ ልጆቼን በማይሆን መንገድ ከሚቀርፅብኝ ብዬ ራሴ ነኝ የምሰራው። ብዙውን ግዜ ግን ሁለቱንም ማካሄድ ከባድና አስጨናቂ ነው የሚሆነው። ልጆቼን በምትይበት ጊዜ ውጭ ያለው ስራ ያመልጥሻል። እናም አንድ ቆንጆ ወጥ ሰርቼ ልጆቼ በልተው ሲጨርሱ እሰይ አንድ ፊልም አስመረቅሁ እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የቤቱንም ስራ ሆነ ኪነጥበቡን እኩል ማስኬዱ ከባድ አልነበረም? በተለይ የቤት ስራውንና ልጅ የማሳደጉን ኃላፊነት ለብቻ መወጣት?
አርቲስት አስቴር፡- በተለይ ለባለሙያ ሴት በጣም ከባድ ነው። የውጭ ብቻ ሳይሆን የቤቱም ኃላፊነት አይቀርልሽም። የማርፍበት ጊዜ ስለሚናፍቀኝ በድሮ እናቶች እቀናለሁ። ሰራተኛ ባይኖራቸውም እንኳ የቤት ውስጥ ስራቸውን ከጨረሱ በኋላ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በሚገባ የሚወጡበትና ከጎረቤቶቻቸው ጋር ቡና እየተጠራሩ የሚጫዋወቱበት ጊዜ ነበራቸው። አሁን ላይ ያለን ሴቶች ግን ለዚህ አልታደልንም። የአብዛኞቹ ሰራተኞቹ ባህሪ ደግሞ ገንዘብ ብቻ ነው ፈልገው የሚመጡት።
ስራ ለመልመድም ፍላጎት የላቸውም። አሰልጥነሽ አሰልጥነሽ ልክ ጥሩ ልምድ እንዳገኙ ጥለውሽ ነው የሚሄዱት። እና ከእነሱ ጋር መግባባት በጣም ከባድ ሆነብኝ። ስትናደጂ መጥፎ ቃላቶች ሊወጡ ስለሚችሉ ሃጥያት ውስጥ ነው የሚያስገቡሽ። የሚገርምሽ ሌቦች አጋጥመውኝ ያውቃሉ፥ ከጎረቤት ጋር ተሻርከው ጥለውኝ የሄዱበት አጋጣሚም አለ። የቤቴ እቃ ይወጣል፤ ይሰጣል፤ አንቺ ስትወጪ ሌላ ሰው ይመጣል። እናም ምንም አስተማማኝ ስላልሆነ አንድ ቀን ከራሴ ጋር ተማከርኩና ራሴን ችዬ መስራት ጀመርኩ።
መጀመሪያ አካበቢ በጣም ተሞላቅቄ ስላደግሁኝና ለቤተሰቦቼ የመጨረሻ ልጅ ስለነበርኩ ጓዳ ማለት ዳገት ነበር የሆነብኝ። አንዳንድ ጊዜ ሽንኩርት ስልጥ አይኔን ሲያስለቅሰኝ በዚያው የምሬን አለቅስ ነበር። ለምን ማስተርስ ይዤ እንዴት እዚህ ሽንኩርት እከትፋለሁ እያልኩ እበሳጫለሁ። ግን መጨረሻ ላይ እንደ ግዴታ ሳይሆን ደስ የሚል ኃላፊነት መሆኑን አእምሮዬን አሳመንኩ።
ከዚያ በኋላ ሁሉንም በፕሮግራም አጣጥሜ ነበር የማስኬደው፤ ልጆቼንም ስራዬን ሳልጎዳ ማለት ነው። በእርግጥ የሚመረጥ አማራጭ አይደለም ግን በተለያዩ አገራት በዞርኩባቸው ወቅቶች መታዘብ የቻልኩት ብዙዎቹ ሰዎች የቤት ሰራተኛ ሳይኖራቸው ነው የሚኖሩት ስለዚህ እንደሚቻል አመንኩ። ወስኖ ከገቡበት በኋላ ደግሞ ኢኮኖሚዬን አዳንኩ፤ ነፃነቴንም አገኘሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከኑሮ ጫና የተነሳ እንዳው ባላገባ ኖሮ ብለሽ የተቆጨሽበት ቀን አለ?
አርቲስት አስቴር፡- አይ ብዬ አላውቅም! እኔ እንዳውም እግዚአብሔር ረድቶኝ ዩኒቨርስቲ ሳልገባ ነው ልጅ የወለድኩት። ለነገሩ በልጅነቴ መውለድ ነበር የምፈልገው። የመጀመሪያ ልጄ አሁን የ15 ዓመት ልጅ ሲሆን ዘንድሮ የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተፈታኝ ነው። ሴቷም ልጄ 12 ዓመት ሆኗታል። እናም እነሱን ለማሳደግ የከፈልኩትን ዋጋ ደስ የሚል ስቃይ አድርጌ ነው የምገልፀው። በእርግጥ በእርግዝናዬ ወቅት በተለይ እስከ ሶስት ወር ድረስ የነበረው ተፈጥሯዊ ህመም ባላገባሁ አይደለም ባልተፈጠርኩ ብለሽ ልታማርሪ ትቺያለሽ።
እንዳውም አንድ ጊዜ ጥርሴን አመመኝና ሃኪም ቤት ስሄድ እርጉዝ ስለሆንሽ ጥርሽን መነቀል አትቺዬም ተባልኩ። እስከ ሰባት ወር መጠበቅ ነበረብኝን ያንን ጊዜ አልረሳውም። ቢያምሽ እንኳ መድሃኒት አትወስጅም። በጣም ህመም ነበረው። በዛ ላይ ቀን ቀን ሬዲዮ እስራለሁ፤ ድርሰቶች እፅፋለሁ ። ፎንተሊና ኢንተርቴመንት አማካኝነት ብዙ ስራዎች እስራ ነበር። ማታ እማራለሁ።
የመጀመሪያ መንፈቀ ዓመት ላይ እወልዳለሁ ብዬ ባስብም ጊዜው ተንጓተተና ወልጄ በ10ኛው ቀን ነው ፈተና የተቀመጥኩት። ሁለተኛዋን ልጄንም ስወልድ ከትምህርት ጋር ነው። የሚያስጨንቀው ነገር እንዳለ ሆኖ ደስ እያለኝ የምከፍለው ዋጋ ነበር። ፈጣሪ ትልቅ አቅም እንደሰጠኝ ትልቅ ደረጃ እደረስላሁ የሚል ህልም ነበረኝ።
አዲስ ዘመን፡- የውጭ አገር ፎቢያ (ፍርሃት) አለብሽ ይባላል፤ ምን ያህል እውነት ነው?
አርቲስት አስቴር፡- አገሬን ከመውደድ የሚነጭ እንጂ ፎቢያ አይደለም፤ እኔ በሰው አገር መኖር አልፈልግም፤ በውጭ አገር ረጅም ጊዜ ቆየሁ የሚባለው ለሁለት ወር ለፊልም ትምህርት ቡርኪናፋሶ ዋጋድጉነው።
በወቅቱ እስከመለስ በጣም ነው የሚጨንቀኝ። አየሩ ራሱ ሊስማማኝ አልቻለም ነበር። የጎዳና ልጆች እኮ በቲሸርት የሚያድሩበት አገር ነው። በእርግጥ በስልጣኔ ሊበልጡን ይችላሉ፤ እኛ እነሱ የደረሱበት ለመድረስ በጣም ሩቅ ያለን ይመስለኛል፤ ስለዚህ ወደእነሱ ከምናድግ ወደ ኋላ ብናድግ ይሻላል ብዬ አምናለሁ። ወደ ባህላችን ፤ወደራሳችን ማንነት፤ ያላየናቸውና ስልጣኔ መስሎን የጣልናቸው ሃብቶቻችን ጠቃሚ ቱፊቶች ብንመለስ ይሻላል ባይ ነኝ። እናም ወደዚያ ብንመለስ ምንአልባት ለጎብኚዎቻችን የተሻለ ነገር እንፈጥራለን ብዬ አስባለሁ። ደግሞም እኮ በቀላሉ እነሱ ወደደረሱበት ስልጣኔ እንደርሳለን ብዬ አላምንም።
አዲስ ዘመን፡- ተስፋ ቆርጠሻል ማለት ነው?
አርቲስት አስቴር፡- ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን እነሱ ጋር ለመድረስ የሚያስችል ሁኔታ ላይ ባለመሆናችን ነው። አንዳንድ ጊዜ ስታስቢው የህዝቡ ባህል ራሱ ጎተቶ የሚይዘው ይመስለኛል፤ ለምሳሌ ታስታውሽ እንደሆነ ቀለበት መንገድ ሲሰራ አንዳንድ ነዋሪዎች የግንባታ ግብዓቶችን ሲሰርቁ፤ የተሰራውን እያፈረሱ ይዘርፉ ነበር። ይህም ሌላ አገር አላቸው ወይ እስኪባል ድረስ አድርሶን ነበር። እናም የህዝቡ ንቃተ ህሊና እስኪያድግ ድረስ ያለንንና የቀደመውን የስልጣኔ መንገድ ብንከተል የተሻለ ነው የሚል አቋም አለኝ። ምንአልባት ይሄ ለዓለም የምናስተዋውቀው አዲስ ነገር ሊኖረን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን በሰራሽው ስራዎች ምንያህል ውጤታማ ነበርኩ ብለሽ ታምኛለሽ?
አርቲስት አስቴር፡- ያው እኔ የኪነጥበብ ባለሙያ እንደመሆኔ ኑሬዬ የተመሰረተው በኪነጥበብ ዙሪያ ነው። ፈጣሪ የሰጠኝ የመፃፍ ተሰጥቶ አለኝ፤ ከዚያ ደግሞ መተወን ማዘጋጀት የሚባለውን ነገር በትምህርት እየደገፍኩት ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ደርሽያለሁ። በነገራችን ላይ ህፃናት ቲያትር ሆነ ብዬ ነበር የገባሁት።
መጀመሪያ ላይ «የወፍ አፍ» የሚባል ቲያትር ነበር የሰራሁት። ከነሽዋፈራው፥ ከእነቴዎድሮስ ለገሰና ግሩም ዘነበ ጋር ያንን ቲያትር ስንሰራ ህፃናት የሚያደርጉት ድርጊት ፍቅር አስያዘኝ። አንዳንዶቹ ቲያትሩ እየተሰራ መጥተው ቺብስ ያጎርሱሻል፤ የዋህነታቸው፤ ቅንነታቸው እና የእውነት ተመልካች ናቸው። ደስ ቢላቸውም ቢያስጠላቸውም አይዋሹም። ከዚያ አንድ ዓመት ሜጋ አንፊ ቲያትር ሰርቼ ስወጣ በቀጥታ ህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት ነው ሄጄ የተቀጠርኩት። እዛ ስሄድ ደግሞ ተመልካች አልነበረም። በዚህ ምክንያት ገቢውም አነስተኛ የሚባል ነበር።
ስለዚህ ይህንን ችግር ለመፍታት ብዬ በየትምህርት ቤቱ እየሄድኩ እየቀሰቀስኩኝ አዳራሹን መሙላት ጀመርኩ። የሚገርምሽ እኔ እስከምመጣ ድረስ ቅዳሜና እሁድ ብቻ ነበር ተመልካች የሚጠብቁት። ተመልካቹም ከ30 ሰው አይበልጥም ነበር። ግን ባደረኩት ቅስቀሳ ከሰኞ እስከ አርብ ድረስ ማሳየት ጀመርን። እናም ገበያው በጣም ማደግ ጀመረ። እዛም በሄድኩበት ጊዜ ያጋጠመኝ ነገር ልጆች የእውነተኛ ተመልካች መሆናቸውን አረጋግጫለሁ። ደግሞም እኔ የሰማናቸው ተረቶች ውጤቶች ነን ብዬ ስለማምን በቲያትር ቤቱ በነበረኝ ቆይታ ትውልድ ቀረፃ ላይ የራሴን አሻራ እንዳሳረፍኩ ነው የምቆጥረው።
አዲስ ዘመን፡- ከህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት ታዲያ ለምን ለቀቅሽ?
አርቲስት አስቴር፡- ከቲያትር ቤቶቹ የለቀቅ ኩበት ምክንያት ልጅ በመውለዴ ነው። በወቅቱ የኮንትራት ሰራተኛ ነበርኩና በወለድኩ በ14 ቀኔ አለቃዬ ስራ እንድገባ አዘዘችኝ። እኔም አሻፈረኝ ብዬ መንግስት የሰጠኝ ሶስት ወር ጨርሼ ስገባ የማይመቸኝ ሁኔታዎች መፈጠር ጀመሩ። በዚህ ምክንያት ጥዬ ወጣሁና የራሴን የማስታወቂያ ድርጅት ከፈትኩ። በወቅቱ ልጄን እያጠባሁ፥ ዩኒቨርስቲ እየተማርኩ ልሰራ የምችለው ስራ ምንድን ነው? ብዬ ሳስብ የመጣልኝ ድርሰት መፃፍ ነው።
እናም «የሰዓሊው ልጅና ልዑሉ» የሚለውን ተረት ፃፍኩኝ፤ ስፖንሰር አገኘሁናም ታተመ። ቀጥሎም ይህንኑ መፃሃፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋም ለማሳተም ችያለሁ። ከዚያ ወዲህ ህፃናቱ ይጠብቁ ጀመር። «በሚቀጥለው ዓመትስ መጽሐፍ የለንም ወይ?» ብለው ሲጠይቁኝ ለካ አንዴ የመሮጫ ትራኩ ላይ ከወጣሁ መቆም የለብኝም ብዬ አሰብኩ። እናም በተከታታይ መፃፍ ጀመርኩ። እስከ አምስት ስድስት እትም የደረሱ አሉ። አሁን አሁን ሌሎች ጉዳዮች ሃሳቤን ወሰዱትና ስፖንሰር መፈለጉን ተውኩት እንጂ ህፃናት ላይ በጣም ይሰራል። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ቦታዎች ላይ የማነቃቂያ ትምህርቶችን በነፃ እሰጣለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት አለቃሽ የደረሰብሽ ነገር ክፉ ጎረቤት እቃ ያስገዛል እንደሚባለው ሆነልሽ ማለት ነው?
አርቲስት አስቴር፡- እውነት ነው! በነገራችን ላይ እኔ እዚህ የደረስኩት ስለተደነቅሁኝና ስለተበረታተሁ ሳይሆን ስለተገፋሁ ነው። እድሌ ሆኖ በየሄድኩበት እገፋለሁ። ምክንያቱም እኔ እንደሌሎቹ ሰዎች ማስመሰል አልችልም። እውነቱን ነው የምናገረው። ዋናው መነሻዬ ግን ፍቅር ነው። ሁልጊዜም ቢሆን ሰዎችን ለመጉዳት ብዬ አልነሳም። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ደግሞ ኪነጥበቡ አካባቢ ፉክክር አለ። በስህተት መንገድ ሮጠሽ ለማሸነፍ ስትይ ጥሎ ማለፍ አለ። እኔ ቲያትር እንኳ ብዙ ያልሰራሁት በዚህ ክፉ ፉክክር ምክንያት ነው። ደብል ካስቷ የእኔን መቅረት በተስፋ የምትጠብቅ መሆኑን በማየቴ ሶስት ቲያትር ጥዬ ሄጂያለሁ። ግፊያ ስለምጠላና ሌላ እንጀራ እንዳለኝ ስለማምን ብቻ ራሴን አገላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ይሄ ባህሪሽ ከስንፍና ወይም ከፍርሃት አያስቆጥርብሽም?
አርቲስት አስቴር፡- ስንፍና ሳይሆን ሰላምን ፍለጋ ነው። ምክንያቱም ሌላ እንጀራ እንዳለኝ አምናለሁ። እርግጥ ነው ተናጥቄና ተፋትጌ መብላት እችላለሁ። በተመሳሳይ ማስታወቂያ ስራ ላይም ግልፅ የወጣ ክፉ ፉክክር አለ። ሙስና አለ፤ ስራው የሚመጣበትም መንገድ ጤናማ አይደለም። እናም እኔ እየኖርኩ መኖር እንጂ እየሞትኩ መኖር አልፈልግም። የእውነት ኖሬ የእውነት መሞት ነው የምፈልገው። እንዳውም አንድ ጊዜ ባጃጅ ላይ «ሀበሻ የውሸት እየኖረ፤ የእውነት ይሞታል» የሚል ፅሁፍ አነበብኩ።
እኔ በዚህ ሃሳብ አልስማም። እንዲያውም የእውነት ኖሬ የውሸት መሞት አለብኝ ብዬ ነው የማምነው። የእውነት ከሆነ የኖርኩት ታሪክ አለኝ። ስለዚህ ሞቴን ውሸት አደርገዋለሁ። ሞተው የማንረሳቸው ብዙዎቹ ሰዎች በታሪካቸው ውስጥ አሻራ ማሳረፍ የቻሉ ናቸው። እኔ ከሁሉ የሚያስጨንቀኝ በፈጣሪ አይን ምን አይነት ሰው መሆኔ ነው። ምክንያቱም ሰውን መሸወድ ይቻላል፤ እግዜርን ግን አይሸወድም። በእርግጥ ጥሩ መሆንሽ ሁሉንም ላያሳድስት ይችላል። አንዳንዶች ሁሌ በመንገድሽ እንቅፋት በመጣል ሊያደናቅፉሽ ይሞክራሉ። እኔ ግን ይህንን ወደ መልካም ነው የምቀይረው፤ ሲገፉኝ የበለጠ አቅም አጎልብቼ እነሳለሁ።
እንዳውም ልንገርሽና የግጥም መጽሃፌን በአወጣሁበት ወቅት የግጥም መጽሃፍ ብዙ ተነባቢ ስላልነበር በእናቴ ግፊት ከስዕል ጋር አወጣሁት ብዙ ተቀባይነት አገኘ። የእኔን አርዓያነት ተከትለው በርካቶች ግጥምና ስዕልን አብረው ማውጣት ጀመሩ። በሌላ በኩል በአገራችን የፊልም ታሪክ ሴት ዳይሬክተርና ፕሮዲዩሰር ከሄለን ታደሰ ቀጥሎ እኔ ነበርኩ። በመጀመሪያ እንዴት ራሷ ደራሲ ዳይሬክተር ትሆናለች ተብሎ ተሰደብኩበት። ግን ማንም ችግርሽን አይረዳም። ከዚያ ግን ብዙ ሴቶች እየመጡ ያማክሩኝ ነበር። እኔም በቻልኩት መጠን መንገዱን አሳያቸዋለሁ። በዚህ ምክንያት በርካታ ሴቶች ፕሮዲውሰርና ዳይሬክተር መሆን ችለዋል። ስለዚህ ሁልጊዜ ትግል ውስጥ ነኝ፣ ሁልጊዜ እሰራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በፎንተሊና በተባለው ፕሮግራ ምሽ አማካኝነት በርካታ አማተሮችን ወደፊት በማምጣት ረገድ ውጤታማ ነበርኩ ብለሽ ታምኛለሽ?
አርቲስት አስቴር፡- እንዳልሽው ፎንተሌና ፕሮግራም እንድሰራ መነሻ የሆነኝ የራሴ ገጠመኝ ነው። እኔ በ17 ዓመቴ ሬዲዮ ላይ አንድ ግጥም ለማንበብ አንድ ወር ሙሉ የምጠብቅበት ጊዜ ነበር። ተቀርፆ ራሱ ላይተላለፍ ይችላል። እናም ያንን ነገር በመልካም ልበቀለው ነበር ያሰብኩት።
እናም 98 ነጥብ 1 የመጀመሪያ ፕሮግራም ሲጀምር የመጀመሪያ ተባባሪ አዘጋጅ ሆንኩና ተሰጥዖው ኖሯቸው ግን መድረክ ያጡ ልጆችን እያመጣው ግጥም ያነቡ ነበር። ከእነዚያም መካከል እነ በላይ በቀለ፥ ሰለሞን ሳህለ፥ ትዕግስት ማሞ፥ ቴዎድሮስ ፀጋዬ፥ እነ አንዷለምና በረከትም እዛ ላይ እድሉን አግኝተው ጋዜጠኞች ገጣሚዎች ሆነዋል። በወቅቱ ግን ልክ እንደበቃ ሰው ነው ቃለመጠይቅ አድርጌ ይዤያቸው የምቀርበው።
ተደጋጋሚ እድልም እሰጣቸው ነበር። አዲስ አበባ ቴሌቪዥን ላይም አጫጭር ድራማዎች እሰራ ነበር፤ በዚያም ላይ ተገኝ፥ ማክዳ ሃይሌን የመሳሰሉ አርቲስቶች እንዲሳተፉ በማድረግ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት እድል ተፈጥሮላቸዋል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን አሁን ፊልም ላይ አናይሽም፤ አግልለዋታል የሚባል ወሬም አለ?
አርቲስት አስቴር፡- አዎ እውነት ነው ያልሽው ነገር። አንድ ፊልም ቤት እንዳውም አስቴር ካለችበት ፊልሙ አይታይም ብሎ አቋም ይዟል። በዚህ ምክንያት ከፊልም ተገልያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለምንድን ነው አንቺ ያለሽበት ፊልም እንዲታይ ያልተፈለገው?
አርቲስት አስቴር፡- አንድ ወቅት ላይ የፊልም ዳኛ ነበርኩ። ያ የእኔ ፊልም እንዳይታይ ያደረገው ግለሰብ በተሳሳተ መንገድ የሱ ፊልሞች እንዲያሸንፉ እንዳደርግ ጠየቀኝ። እኔ ደግሞ በግል ባለኝ ቅርበት አላውቅህም፤ የማውቀው ፊልሙን ነው የሚል ምላሽ ሰጠሁት። ግለሰቡ ግን ራሱ ተሸላሚ መሆን ነበር የፈለገው።
በዚህ ምክንያት በሬዲዮ ሁሉ ስሜን ማጥፋት ጀምሮ ነበር። በቅርቡም ያው በተለያየ መገናኛ ብዙሃን ትሰሚዋለሽ ብዬ አስባለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባዘጋጁት ፕሮግራም ላይ ለቀረፃ ትፈለጊያለሽ ተብዬ ተጠርቼ እንድወጣ ተደርጌያለሁ። ያ አልበቃ ብሎ የውሸት ወሬዎች ተፈብርከው ስሜን የማጥፋት ዘመቻ ተካሄደብኝ። ከእነዚያም መካከል «ራሷ ጥላ ወጣች፥ ፊት ካልተቀመጥኩ አለች» የሚሉ ይገኙበታል።
እሱ ብቻ እንዳይመስልሽ! ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ በማደርጋቸው ጥረቶች እኔ ላይ መጥፎ ነገር በማውራት የተጠመዱ ሰዎች አሉ። የሚገርምሽ እንቅስቃሴዎቼን ሁሉ ፊልም ቀርፀው አሳይተውት ስለእኔ መጥፎ አስተሳሰብ እንዲኖረው ጥረት አድርገዋል። እኔ ግን ያ ሁሉ ተደርጐብኝ ምንም አልሆንኩም፤ ለመበቀልም አልሞክርም። አሁንም ግድ ስለሆነብኝ ነው የምነግርሽ።
ፈጣሪ ራሱ ተበቅሏቸው እነሱ ማን እንደሆነ ህዝቡ ያወቀበት ሁኔታ ተፈጥሯል። እኔ አሁንም እየሰራሁ ነው። ለምን እንደሆነ ባላውቅም አካሄዴን ስለሚፈሩት ሊያስቆሙኝ ይሞክራሉ። እኔ ደግሞ አልቆምም። ይህንን ስል ሁሉንም ማለቴ አይደለም። አንዳንዶቹ ሁልጊዜ የገጠር ገፀባህሪ ተላብሰሽ እንድትሰሪ ይፈልጋሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ መጥተው ሳያናግሩሽ ዋጋ ውድ ትጠይቃለች ይሉሻል።
አንዳንዶቹ ቢዚ ናት ይሉሻል። እኔ የራሴ ስቲዲዮና ካሜራ ስላለኝ በፈለጉበት ጊዜ ተነስቼ ፊልም መስራት እችላለሁ። ድርሰቶች እፅፋለሁ መጽሃፍ አሳትማለሁ። የማነቃቂያ ትምህርቶችንም እሰጣለሁ። ከቀረፃና ከኤዲቲንግ ጋር የተያያዙ ስራዎችንም እሰራለሁ። እናም ሁልጊዜ ስራ ውስጥ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ካነሳሽው አይቀር በቤተመ ንግስቱ ፕሮግራም ጋር ተያይዞ የተለያዩ ወሬዎችን በተመለከተ ለአድናቂዎች እውነታውን ለማጥራት እድሉን ልስጥሽ?
አርቲስት አስቴር፡- እኔ ልክ እንደማንኛውም አርቲስት ባህል ሚኒስቴር ነው በደብዳቤ የተጠራሁት። ያንን ጥሪ ወረቀት ነው ይዤ የሄድኩት። እንደደረስኩም በር ላይ ስለእኔ መጥፎ ነገር እንደተነገራቸው ያስታውቃል። ከእዛ በፊትን ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደጋጋሚ አውርተናል፤ ትውውቃችንም እስከ ሶስት ዓመት ይዘልቃል። በሳልቪና መጽሃፌ ላይ ኤዲቲንግ አግዞኛል።
የዚያን ለታ ግን ሁኔታቸው ለየት አለብኝ። በመጀመሪያ ስም ዝርዝር ውስጥ የላችሁም አሉንና ግርግሩ ይለፍ ብዬ መኪናዬ ውስጥ ተቀመጥኩ። በኋላም ተምልሼ ስመጣ ስም ዝርዝር ውስጥ እንዳለሁ ተነግሮኝ ገባሁ። ግን 30 ደቂቃ ከተቀመጥኩ በኋላ ለቪዲዮ ቀረፃ ትፈለጊያለሽ ተብዬ ወጣሁ። ለምን እንደወጣሁ ስላላወቅሁ ደብዳቤ ፅፌ አስገባሁ፤ በወቅቱ ታዲያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የነገሩት ራሷ ጥላ ወጥታለች የሚል ነበር።
ሌላው የሚያስጠላው ተያያዥ የሆኑ ጉዳቶች ጥፋት እንዳጠፋ ሰው ደርሰውብኛል። ለምሳሌ 50 አርቲስቶች ቻይና ሄደዋል፤ ከእዛ ውስጥ እኔ የለሁም። እኔ በፊት ዶክተር ዐብይን ስደግፍ በጣም የሚሳደቡና የሚቃወሙ ሁሉ ሄደዋል። በእርግጥ እናንተ ያያችሁትን እሱ ውስጥ ያለውን ጥንካሬ ቀድሜ ስላየሁት እድሉን ቢያገኝ ላገሩ ጥሩ ይሰራል ብዬ ስለማምን ነበር እደግፈው የነበረው። እና አንዳንድ ጊዜ ሴት ስትሆኚ ብዙ ነገር ይተረጉምብሻል። ብዙውን ጊዜ የሴቶች የበታችነት ሲባል ውሸት ይመስለኝ ነበር። ሌላው ይቅርና ስለመደመር እየተወራ ነው እኔ የተቀነስኩት።
ይሁንና ብዙ የእኔን ሃሳቦች እየተጠቀሙባቸው ናቸው። ሃሳብሽ ይፈለጋል አንቺ ግን አትፈለጊም። አሁንም ቢሆን ለግል ጥቅሜ አይደለም የምናገረው፤አሁንም ሃሳቤ ከጠቀመ ሃሳቤን አዋጣለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እንደነገርሽኝ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የቀደመ እውቅና አለሽ፤ ከዚያ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንቺ በጠበቅሽው መንገድ ነው አገሪቱን እየመሩ ያሉት ብለሽ ታምኛለሽ?
አርቲስት አስቴር፡- ለእኔ እንደጠበቅሁት ነው እየሰራ ያለው። እንዳውም እሱ ካቀዳቸው ትልልቅ ስራዎች አንፃር ጊዜ የሚያንሰው ነው የሚመስለኝ። ደግሞም አይናችን ትናንሽ ነገሮችን ማየት ስለማይችል ነው እንጂ ከተማ ውስጥ ብዙ ለውጦች አሉ። በተለይም ከፅዳት አንፃር። በየቦታው እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በጣም ትላልቅ ናቸው።
ሳንሸማቀቅ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ማውራት መቻላችን በራሱ ትልቅ ነገር ነው ብዬ ነው የማምነው። ይህንን ነፃነት በስንት ብር ትገዢዋለሽ? አሁን ችግር ያለ የሚመስለው ነፃነት ስላገኘ ሰው መንግስት ስደበኝ፤ አንጓጠኝ፤ እንደፈለግህ ሁን፤ ስላለነው ይሄ ሁሉ ገፈት እየተቀበለ ያለው። ግን ዲሞክራሲን ካልተለማመድን ከነፃ ንግግር የበለጠ እንደገና ወደ ሃይል እርምጃ የሚኬድበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ህዝቡ ስልጣንም ያለው እስኪመስል ድረስ የተሰጠውን ነፃነት በአግባቡ እየተጠቀመ አይደለም።
በተጨማሪም ስልጣናቸውን ያጡና ኢትዮጵያ ትልቅ ሱቃቸው የነበረች የኢኮኖሚ ጥቅማቸው የግል የበላይነታቸው የተነካ ሰዎች ህዝብ ሲያፈናቅሉ የነበሩት በመንግስት ሃላፊነት ላይ ተቀምጠው ነው። ምክንያቱም የተቀየረው አንድ ግለሰብ ነው። አንድ አስተሳሰብ ነው የተቀየረው፤ አመጣጡ ራሱ የተለመደ አይነት ስላልሆነ ባለው ህዝብ ላይ ነው ለውጥ ለማካሄድ እየሞከረ ያለው።
ያ ደግሞ በጣም ከባድ ነው። የሰውን ልብ እንዴት አድርገሽ መቀየር ትቺያለሽ? ሁሉንም ንቅል አድርጎ በአዲስ ሰው ቢተካ ምንአልባት እንደዚህ ላይቸገር ይችላል። ባለው ህዝብ ላይ ስለሆነ ሪፎርም እያደረገ የመጣው መንገጫገጮች ይታያሉ። ይሄ እንግዲህ ሰዎች የእሱ ችግር ሊመስላቸው ይችላል። ለእኔ ግን አይደለም! ምንአልባት የሱ ችግር ብዬ የማምነው ሁሉንም ለማስደሰት ጥረት ማድረጉ ነው።
ለእኔ በአንድ ዓመት የሰራው ስራ ብቻ በ10 ዓመት የማይሰራ ነው። በጣም የሚያሳዝነኝ ቆሻሻን ስለሚጠርግ ይሰደባል። ችግኝ ስለሚተክል ይሰደባል። ሰው ስለማያስር ይሰደባል። ሰው ስለማይገድል ይሰደባል። አንዳንድ ጊዜ ህዝቡ ምን እንደሚፈልግ ራሱ ግራ ይገባኛል። ፍቅር ሊያሸንፈን ያልቻልን ህዝቦች ነን። እስከዛሬ የህዝቡን ክፋት መንግስት ነበር የሸፈነው። በቃ መንግስት ክፉ ነው አሳሪ ነው።
ጨቋኝ ነው ስለሚባል ሁላችንም አይናችን መንግስት ላይ ነበር። አሁን ደግሞ መንግስት መልካም ሲሆን እርስበርስ የማንተማመን የማንግባባ፤ በዘር በብሄር ተናቁረን አገራችንን ጠላት ሆነንባት ስሟን እንኳ መጥራት አስጠልቶን እንደክፉ ባለጋራ በጣጥሰን ልንጨርሳት ተዘጋጅተናል። እኔ በአጠቃላይ የዚህ ህዝብ እና አገር መሪ በመሆኑ በራሱ በጣም ልናደንቀው ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ያልተለወጠ ህብረተሰብ ባለበት በዚህ ወቅት መፈጠር የለበትም ብለሽ ነው የምታምኚው?
አርቲስት አስቴር፡- በየዘመናቱ የተለየ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ትውልዳቸው አይቀበላቸውም። እየሱስ ክርስቶስም ነብይ በአገሩ አይከበርም ብሏል። ግን ዐብይ አሁን ከኖረበት ዘመን ይልቅ ሲያልፍ የሚወደስ መሪ ይመስለኛል። ምንአልባት አንድ ቀን ኢትዮጵያ የምትባል አገር ውስጥ ሰዎችን የሚወድ ቆሻሻን ሳይጠየፍ የሚያፀዳ፥ በሄደበት አገር እስረኛ እያስፈታ የሚመጣ መሪ ተብሎ ይወደሳል። አሁን ግን የሚወደው ሰው ቢኖርም የሚያከብረው ሰው ግን የለም። ብዙውን ጊዜ ሰዎች መጥፎ የሚሆኑብሽ አንቺ ጥሩ ስትሆኚ ነው። በጣም የፍቅር ሰው ከሆንሽ ትሰለቺያለሽ። ክፉ ከሆንሽ ግን ሰው ሁሉ ይሽቆጠቁጥልሻል።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በእጅ የያዙት ወርቅ ሆኖብናል እያልሽ ነው?
አርቲስት አስቴር፡- ልክ ነሽ እንደዛ ነው የሆነብን። እኛ የማናከብረውን መሪያችንን የታላላቅ አገር መሪዎች እንዴት እንደተቀበሉትና እንደሚያከብሩት አይተናል። እኔ እንደማምነው ይህ መሪ የመጣበት ጊዜ ወርቃማ ነው፤ ግን እድላችንን መጠቀም አልቻልንም። የዓለምን ትኩረት የሳበ ሰው ነው። ከ100 የዓለም ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎች አንዱ ሆኗል። ለእኔ የሚሰራው ስራ ፍጥነቱ ከአይምሮ በላይ ነው። ስለኢትዮጵያና ኤርትራ የሰራው ስራ በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በአንድ ወቅት ላይ በሰጠሽው ቃለመጠይቅ መንግስት ህዝብን መምራት እንጂ በህዝብ መመራት የለበትም ብለሻል። ምን ማለትሽ እንደሆነ እስቲ አብራሪልን?
አርቲስት አስቴር፡- እንደመሪ ትንሽ ኮስተር ማለት ይገባዋል ብዬ አስባለሁ። በየቤታችን እንደምናይው አባት ኮስተር ስለሚል ይፈራል ይከበራል፤ እናት ግን ልጆቿን ለማሳደግ ስንት ደፋ ቀና ብላ ሳለ አትፈራም አትከበርም። ሁለተኛ ነገር መሪ ለህዝቡ መመሪያ አውጥቶ ቀድሞ ሄዶ መምራት ነው ያለበት። የህዝብን ፍላጎት እየተከተልሽ ለማስፈፀም የምትሄጂ ከሆነ ግን ማንም አያመሰግንሽም፤ ለምሳሌ በጣም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ሲፈናቀል ዜና ነበር።
አሁን ግን አንድ ነጥብ 3 ሚሊዮን ህዝብ ወደ ቦታው ተመልሶ ዜና አልሆነም። እዚህ አገር መጥፎ ዜና ነው የሚጎላው። ይህን ለማለት ያስቻለኝ ቅንጅቶች አዲስ አበባ አሸንፈው ተረከቡ ሲባሉ ህዝቡን ነው «እንግባ፤ አንግባ» ብለው የጠየቁት። ህዝብ ይመራል እንጂ አይመራም። ምንአልባት ቅንጅቶች አዲስ አበባን ተረክበው ቢሆን ኖሮ የአዲስ አበባ ፖለቲካ እንደዚህ የታመመ አይሆንም ነበር።
አዲስ ዘመን፡- አንቺ በደፋር ተናጋሪነትሽ ትታወቂያለሽ፤ ይህ ድፍረት ከየት የመነጨ ነው ትያለሽ?
አርቲስት አስቴር፡- ድፍረቱ የመጣው ከፍርሃት ሊሆን ይችላል። እኔ መኖር የምፈልገው በአገሬ ነው፤ ልጆቼም አገር እንዲኖራቸው እፈለጋለሁ። ግን አገራችን ስትበላሽ ሳይ የት አገር ነው የሚኖሩት የሚል ነገር ያስጨንቀኛል። ብዙውን ጊዜ ፖለቲከኞች ሃሳባቸው በግልፅ ባለመናገራቸው ምክንያት ብዙ ችግሮች ሲደርሱ እናያለን።
እኔም ያ ነገር ያስቆጨኝ ስለነበር የህወሓት 40ኛ ዓመት ለማክበር ደደቢት በሄድንበት ወቅት ይህንን እድል ላላገኝ እችላለሁ ብዬ በድፍረት ለመናገር ፀልያለሁ፥ ንስሃ ገብቻለሁ። ግን የሚገርምሽ ባለስልጣናቱ ስላልጠበቁ ሴትም ስለሆንኩኝ በወቅቱ አድንቀውኛል።
ለምሳሌ ተቃዋሚ ፓርቲ አትበሉ ተፎካካሪ በሉ ያልኩት ሃሳብ አሁን ላይ ነግሷል። በአዲስ አስተሳሰብና ፍልስፍና አገሪቱን የሚመራ ወጣት መሪ ይፈጠራል ብላችሁ አታስቡም ወይ? እውነት እናንተ በምርጫ ስልጣን ትለቃላችሁ? ብዬ የተጠየኳቸው ጥያቄዎች አሁን ላይ ሳስበው ዶክተር ዐብይን እያሰብኩ የተናገርኩ ነው የሚመስለው።
በተጨማሪም ከደርግ ጋር በነበረው ነገር ሁለት ወንድማማቾች በሃሳብ ልዩነት ነው የተጋደሉት ጠላት እያልን ለምንድነው ግንቦት 20 በተከበረ ቁጥር የደርግ ወታደር እያልን የምናነሳው? ስል በድፍረት መጠየቄ ብዙ አነጋገሪ ሆኖ ነበር። በወቅቱ ጀነራል ሳሞራ ሃሳቤን ተቀብለውት ነበር።
ከእዛ ስመጣ እንዳውም እንዳትፈሪ ብለው ስልካቸውን ሁሉ ሰጥተውኛል። እዚህ ስመጣ ግን ብዙ ነገር መንገጫገጭ ጀመረ ፤ ከሚዲያ ላይ መገፋት ፥ ሰዎች ዝም ብለው መፍራት ግን ጎርፉ ወይም እሳቱ በርሽ ድረስ እስኪደርስ መጠበቅ የለብኝም ብዬ በወሰድኩት እርምጃ ለውጥ ያመጣ ይመስለኛል። አሁን አሁን ሳስበው እንዳውም የትኩረት አዝማሚዬ ወደ ፖለቲካ ያደላ ይመስለኛል። ለግል ጥቅሜ ሳይሆን ተጎድተሽ አገር ለመጥቀም ስል ፊቴን ሙሉ ለሙሉ ወደ ፖለቲካው ለመግባት አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በቀጣዩ ምርጫ እንጠብቅሽ?
አርቲስት አስቴር፡- እንዳልኩሽ አንድ እግሬ ገብቷል፤ በተለያዩ የፖለቲካ መድረኮች ላይ እየተሳተፍኩ አስተያየት እሰጣለሁ፤ በራሴም ብዙ ጥናቶች አድርጊያለሁ። ስለዚህ አንድ የተለየ ድምፅ ለመሆን አስባለሁ። በግሌ ካስገቡኝ አይቀርም። ምርጫውስ የሚካሄድበት ጊዜ መቼ ታወቀ?። እነዚህ ሁኔታዎች ከተመቻቹ ግን ከገባሁበት አይቀር አንደኛዬን ፊቴን ወደዛ ማዞር ሳይሻል አይቀርም።
አዲስ ዘመን፡- አስቴር አወዛጋቢ ማንነት ያላት ናት ትባያለሽ፤ ነሽ እንዴ?
አርቲስት አስቴር፡- አወዛጋቢ ነኝ። ለምን መሰለሽ እውነትን ስትከተይ የማንም ወገን አይደለሽማ። ማንንም ለማስደሰት አልሄድም። እኔ እንዳልኩሽ በእግዚአብሔር ሃይል ትክክል መሆንን ነው የምፈልገው። የሆነ አጥር ውስጥ መግባት አልፈልግም። የሴት ክለብ፣ ወጣት ክለብና የሆነ የዘር ክለብ ውስጥ መታቀፍ አልፈልግም። ሰፊውን ዓለም ያጠብብኛል። ሃይማኖትም ጋር ስሄድ ኦርቶዶክስ ጋር በጣም የምወዳቸው ነገሮች አሉ። ፕሮቴስታንት ጋር በጣም የምወዳቸው ነገሮች አሉ። እናም ከሁለቱ የምፈልገውን መርጬ መጠቀም ነው የእኔ ምርጫ። በተረፈ መጽሐፍ ቅዱስ አነባለሁ። ስለዚህ በዚህ የተለየ ምርጫዬ ምክንያት አወዛጋቢ ብባል አይገርመኝም።
አዲስ ዘመን፡- አርቲስቶች በየዘመኑ ለዘመኖኞቹ በማዜምና በማጨብጨብ ትተቻ ላችሁ፤ አንቺ የኪነጥበብ ሰው በየዘመኑ የሚቀያየር የራሱ አቋምና አስተሳሰብ የሌለው ነው ብለሽ ታምኛለሽ?
አርቲስት አስቴር፡- እንግዲህ ጫማ የምትገዥው በልክሽ እንደሆነ ሁሉ አስተሳሰብም የሚገመተው በልክሽ ነው። በዚህ ረገድ እኔ ራሴን የቀረፅኩበት መንገድ አለ፤ ሌላውም እንዲሁ። በተለይ ቤተሰብ ከሚያሳድግሽ ውጪ ራስሽን የማስተዳደር ሃላፊነት ሲወድቅብሽ መንገድሽን ማስተካከልና መቃኘት ይጠበቅብሻል። ምንአልባት እኔ ያነበብኳቸውን መፃሐፍቶች ሌሎች አላነበቡ ይሆናል። ሁሉም ናቸው ማለት ግን አይደለም። ለእውነት የሚታገሉ አሉ።
ምንአልባት ድምፃቸው አይሰማ ይሆናል። ግን እንዛ የሚፈሩትንም አልፈርድባቸውም። ከቤተሰብ ጀምሮ እኔ ራሴ ደፋር ተናጋሪ በመሆኔ በየቀኑ የተለያየ ጫና ነው የሚደርስብኝ። በተለይ ሴት ስትሆኚ ጫናው ይበረታብሻል። እንድትሸማቀቂና እንድትቆሚ የማይደረግ ነገር የለም። አውቃለሁ የሚሰድበኝ የኢትዮጵያን አንድነት ሰላም የማይፈልግ ሰው ነው። ለነገሩ ሰይጣን መንግስቱን እያፈረስኩበት እንዴት ሊወደኝ ይችላል። ምክንያቱም እሱ የሚፈልገው ሰው እንዲለያይ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲጨራረስ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ ስለአገር አንድነትና ስለሰንደቅ አላማው ልዩ ፍቅር እንዳለሽ ስትናገሪ ትደመጫለሽ፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው ትያለሽ?
አርቲስት አስቴር፡- በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ፌስ ቡክ ላይ ነው የፈራረሰችው፤ እንዳውም በማይናወጥ መሰረት ላይ እየተገነባች ነው ያለችው። አሁን የምናያቸው መፈናቀሎች የተፈጠሩት ጥቅማቸው በተነካባቸው ሰዎች አማካኝነት ነው። ከዚህ ቀደምም የሃይማኖት ጦርነት ለማስነሳት ያልማሱት ጉድጓድ እንደሌለ እናውቃለን፤ በቅርቡም የክርስቲያን ልብስ ለብሰው መስጊድ አቃጥለዋል።
ቤተክርስቲያንንም የሙስሊም ልብስ ለብሰው አቃጥለዋል። ይህንን ሁሉ አድርገውም ቢሆን ግን የሃይማኖት ጦርነት አልተነሳም። ህዝቡን በቋንቋ፥ በብሄር እያሉ በተቻላቸው መጠን ሊከፋፍሉት ሞክረዋል። ህዝቡ ግን አሁንም ተጋብቶ ተዋልዶ እየኖረ ነው ያለው። እንዳልኩሽ ግን መጥፎው ዜና ብቻ ስለሚጎላ 10 በመቶ ብቻ ልትሆን የምትችለውን ክፉ ተግባር በማጮህ ነው የአገር አንድነት የሌለ የሚመስለን። ሌላው ይቅርና ኤርትራ እንኳን መጥታለች።
እናም ዋናው መሰረት ተገንብቷል ባይ ነኝ። ኢትዮጵያ የፈራረሰች የምትመስለው ፌስ ቡክ ላይ ነው፤ አንድ ሰው እኮ 15 የሐሰት አድራሻ ከፍቶ ሲሰድብሽ ሰው ሁሉ የጠላሽ ይመስልሻል። ግን መሬት ላይ ያለው ሃቅ ይሄ አይደለም። እኔ የኦሮሞና አማራ ቤተሰብ መሃል ብፈጥርም ስለሆነ ብሄር ሳወራ አገሬ ትጠብኛለች። ግን የሁሉንም ህዝብ ጉዳትን ወክዬ ብናገር የበለጠ አንድነቱን አመጣለሁ ብዬ አስባለሁ። በምናገራቸው ነገሮች ልክ የኦሮሞ ህዝብ እንደጠላኝ ተደርጎ ይገለፃል።
አለፍ ሲልም «አስቴር በዳኔ ሳትሆን አስቴር ኪዳኔ ነሽ» እየተባልኩ እዘለፋለሁ። ኢትዮጵያን መወደድ ኦሮሞን መጥላት እንደሆነ የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ድሮችንን እወዳለሁ ስል «የድሮ ስርዓት ናፋቂ» አሉኝ። ድሮን የምናፍቅበት ምክንያት እኔ የድሮ ህዝብ እንግዳ ሲመጣበት እንኳ አልጋውን ለቆ፥ እግር አጥቦ፥ አብልቶ የሚያስተኛ መሆኑን፤ አሁን ግን ያ መልካም እሴት በመጥፋቱ መቆጨቴን ለመግለፅ ነው። ከየት ነህ ከየት ነሽ ሳይባባል ተከባብሮና ተጋብቶ ይኖር ስለነበረ ነው። እናም ያንን መሰረት ብናመጣው ይሻላል ከሚል እሳቤ ነው። ብዙዎቻችን የሰለጠንን መሰሎን የተውናቸውን እሴቶቻችንን እንመልስ የሚል አቋም ነው ያለኝ።
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራችንን ደግሞ ማንም ይፍጠረው ግን የማንነታችን መገለጫ ነው። አፄ ምኒሊክ የኦሮሞ ህዝብን በድለው ሊሆን ይችላል፤ ግን ምኒሊክ ደግሞ ለአገር የጠቀሙት ብዙ ተግባራት አሉ። እሳቸው ባመጡት ስልክ እየተጠቀምን ነው፤ እሳቸው ባመጡት መኪና እየተጠቀምን ነው። እሳቸው ከሆነ ያመጡት ባንዲራውን የአሁን አይነት ቅርፅ ያላትን አገር ያወረሱን ምን ችግር አለው ባንዲራውን ብንጠቀም?። ያ ባንዲራ ግን እኔ የኢትዮጽያ ባንዲራ ተብሎ ነው የደረሰኝ።
እዛ ባንዲራ ጋር አንድነት፥ ሃይልና የተሰበሰበ ህዝብ ነበር። እነ አበበ ቢቂላ እኮ ኦሮሞ ሆነው ነበር የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሰው በዓለም አደባባይ የአገራቸውን ስም ሲያስጠሩ የነበሩት። ስለዚህ መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር ከትናንቱ እኔ የተሻልኩ ነኝ ለማለት የሚያስቡትን ነገር ሁሉ ባንዲራው ላይ መጨመር የለባቸውም። ከእዛ አንፃር በጣም ነው ያንን የድሮ አንድነትና የህዝብ ፍቅር የምናፍቀው።
ለኦሮሞ ወንድሞችና እህቶች የተነገረው መጥፎ ታሪክ እኮ ለእኔም ተነግሮኛል። ግን አልተቀበልኩትም እንጂ። ምክንያቱም የበታችነት እንዲሰማሽ፣ እድሜ ልክ ተበዳይ፣ ተጠራጣሪና ሌላውን ህዝብ እንድትጠይ የሚያደርግሽ እንጂ የሚጠቅም አይደለም። ይሁን እንዲህ ተበድዬ ነበር በቃ ይቅር ብያለሁ ማለት ነው የሚገባው።
ወደፊት መቀጠል ነው የሚያዋጣው። ከሞተ መሪ ጋር ለምን እታገላለሁ? የሞተን መሪ ለመበቀል መሞከር፣ የሞተ መሪን ራዕዮን ለማስፈጸም እያሉ ማምለክ በሽተኝነት ነው። አንቺ በህይወት በመኖርሽ ከሁለቱም ትሻያለሽ። ምክንያቱም ስህተትሽን ለማረም ዕድል አለሽ።
ዐብይ አህመድ ከኦሮሞ የወጣ መሪ ነው። ተበድለን ነበረ ካሉ ለምን አያከብሩትም? ለምን አይገዙለትም ? አሁን ስልጣን ላይ ያለው እኮ በኦሮሞ ስም የሚጠራ መሪ ነው። እርስ በእርሱ የሚባላና የሚፋተግ ትውልድ ማፈሪያ ትውልድ ነው። እና ደግሞ ስንት ዝም ያለ አገር የሚወድ ትውልድ ዜጋ አለ። ያ ድምጹ ታፍኗል። በጣም ብዙ የኦሮሞ ህዝብ አቃፊና ደጋፊ ነው። ከህዝቡ ጋር ተዋድዶ የሚኖር ነው። ግን በጥቂቶች ምክንያት ጸረ ኢትዮጵያ እስኪመስል ድረስ የደረሰበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ ያንን ለመታደግ እንደገና ሌላ ስራ ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የማህበራዊ ሚዲያ በብዛት ተጠቃሚ እንደመሆንሽ አሁን ላይ ያለው የህዝቡ አጠቃቀም ጤናማ ነው ብለሽ ታምኛለሽ?
አርቲስት አስቴር፡- የሰው አእምሮ የተሰጠውን ነው የሚያበቅለው። የሰው አእምሮ እኮ ማሳ ነው። እንደውም አንድ ግጥም አለኝ። ‹‹ሰው ነው የእኔ ማሳ ሃሳብን ዘርቼ ሃሳብ የማጭድበት… ››የሚል። የሰው አእምሮ ላይ ሀሳብ ትዘሪያለሽ ከእዛ እንደ መሬቱ አይነት ይሆናል። ወይ በደንብ የሚያበቅል ይሆናል ወይ ደግሞ የማያበቅል ይሆናል። ሚዲያው በየቀኑ ፖለቲካ ባወራ ቁጥር ህጻናት ሁሉ ስለፖለቲካ ነው የሚያወሩት። ፖለቲካ ደግሞ በተፈጥሮው ከባድ ነው።
ያስጨንቃል። ሰው ሲሾም ሲነሳ ብቻውን አይደለም። ደጋፊና ተቃዋሚ የሚባል ነገር ይኖራል፣ የሚሞት ሰውም ይኖራል። የአንድን ሰው ሃሳብ በመቀበልና ባለመቀበል ብቻ የሚያልቅ አይደለም፣ የሕይወት ዋጋ የሚያከፍል ነው። ስለዚህ ይህንን ጠንካራና አስጨናቂ ነገር በየቀኑ መስማትና ማየት ለአእምሮ ጤንነትም ችግር ነው። ምንም ሌላ ነገር እኮ ማሰብ አልቻልንም።
እኔ አንድ ዓመት ሌላ ነገር ማሰብ እስከማልችል ድረስ ሂደቱ አእምሮዬን ተቆጣጥሮታል። ምናልባት እኔ የትኩረት አቅጣጫዬን ወደ እዛ ስላተኮርኩ ሊሆን ይችላል። ግን ሌሎችም ሰዎች እንደዛ ናቸው። ህጻናት ያወራሉ በየጸጉር ቤቱና የተለያዩ ቦታዎችም ይወራል። ጤነኛ አይደለም። ህይወት ፖለቲካ ብቻ አይደለም። ከዚህ ተላቅቆ ሌሎች መንፈሳዊ ነገሮችን ማከናወንም ይጠቅማል። በፖለቲካ እየተራኮትን ህዝብ እየተራበ ነው። ኑሮም እየተወደደ ነው፣ ስርዓት የለም። ካዛንቺስ ብቻ ለመብራት ክፍያ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ተሰልፎ ይታያል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
አርቲስት አስቴር፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
ማህሌት አብዱል