ባለፉት 27 ዓመታት አምስት አገራዊ ምርጫዎችን በማካሄድ የዴሞክራሲያዊ የምርጫ ተሳትፎን ለማሳደግ የተቻለው አሁን የምንመራበት ሕገ መንግሥት አርቅቀን ተግባራዊ በማድረጋችን ነው፡፡በአሁኑ ወቅት ይህንን በመስዋዕትነት የተገኘውን ህገ መንግሥትና ቱሩፋቶቹን ያልተረዱ አንዳንድ ወገኖች ልዩ ልዩ የመከፋፈያ ሃሳቦችን የተቃርኖ አጀንዳ በማድረግ ህዝብን ለማበጣበጥና የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ ለመጣል ሌት ተቀን ሲተጉ ይስተዋላል።
ከታሪክ መረዳት እንደሚቻለው በአንድ ወቅት የስልጣኔ ማማ ላይ የነበረች አገር ብዝሀነትን ማስተናገድ ባልቻሉ ገዥዎች በተፈጠረ የእርስ በርስ ግጭት ከነበረችበት የዕድገት ደረጃ አሽቆልቁላ ዜጎቿ ለረሀብ ፣ ለስደትና ለጦርነት እንዲዳረጉ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ዛሬ ይህ ታሪክ ተመልሶ መምጣት ሆነ መደገም አይገባውም፡፡
በአገራችን እንደታየውና እንደቀደመው አካሄዳችን ብዝሀነትን ማስተናገድ አቅቶን ለድህነትና ለኋላ ቀርነት የተዳረግንበትን፣ እንዲሁም ገናና ስልጣኔያችንን ያጣንበት መጥፎ ታሪክ እንዳይደገም ለሰላምና ልማት መትጋት ይገባናል፡፡የአሁኑ ትውልድም ልማትና ዕድገት በማፋጠን ከድህነት የምንወጣበትን ጊዜ ለማሳጠር መስራት ይጠበቅበታል፡፡
ባለፉት 27 ዓመታት የተሰራው ሥራ ውጤት የተገኘበት ቢሆንም ከሰራነው የሚቀረን ስለሚበልጥ በተጀመረው አዲስ የለውጥ ጉዞ የምንፈልገው ደረጃ ለመድረስ ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ መገምገም ያስፈልገናል፡፡ በአገራችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከሰተው አለመረጋጋት ለጀመርነው የዕድገት ጉዞ እንቅፋት መሆኑ ባይካድም በከባድ መስዋዕትነት የተገኘው ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ከእጃችን እንዲወጣና ተመልሰን ወደ ጦርነት አዘቅት እንድንገባ የሚፈልጉ ቢኖሩም የሚያጋጥመንን ተግዳሮት በፅናት አልፈን ለውጤት ለመብቃት ብርታታችን ወሳኝ ነው፡፡
በተለይም የህግ የበላይነትን ለማስፈን ሲባል እንደቀድሞው ሁለት ባላጋራዎች መንገድ ላይ ቢገናኙ ተበደልኩ ባዩ ምንም ኃይል ሳይጠቀም “በሕግ አምላክ ቁም!” በማለት ብቻ ባላጋራውን አስቁሞ የነጠላዎቻቸውን ጫፍ ቋጥረው (ተቆራኝተው) ያለ ፖሊስ አጃቢ ወደ መረጡት ዳኛ ዘንድ ሄደው ፍርዳቸውን ይቀበሉ እንደነበርው መልካም ባህላችን የዋህነታችን ባንመለስ እንኳ ካለፍርድ ከመታሰር፣ ተዘቅዝቆ ከመገረፍ፣ ጥፍር
ከመነቀል፣ ከመደፈር…የሚታደግ ነፃና ማንም የማይዘውረው የፍትህ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ በመሆኑ የፍትህ አካላቶቻችን እንዲጠናከሩና የለውጡ አካል ሆነው ነፃ ፍትህን እንዲያረጋግጡ የሚያሳይ ተግባር መከወን ይጠበቅባቸዋል፡፡
መንግሥት የሕግ የበላይነት ለማስፈን ቁርጠኝነት ሊያሳይ የሚችለው ዜጎች ከኖሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉና ንብረታቸው ሲወድም እንዲሁም የመንግሥት አስተዳደር በሕገ ወጦች ሲፈርስ በዝምታ ባለማስተዋል የድርጊቱን ፈፃሚዎች የሚያስተምርና ከስህተታቸው የሚያርም ርምጃ መውሰድ ሲችል ነው።
ባለፉት ዓመታት የአገሪቱን ሰላም መደፍረስና የሕዝቦቿን መበጣበጥ ለማየት የተመኙት ያሰቡት እንዳይሳካላቸው መንግሥት ያሳየው ታጋሽነት ወደር የሚገኝለት አይደለም። ከታጋሽነቱ ባለፈም ለበርካታ ዓመታት ከአገራቸውና ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው በስደት ይኖሩ የነበሩ ወገኖቻችን መንግሥት ባቀረበላቸው ጥሪ ወደ አገር ቤት መግባታቸው ፣ መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል አስበው በበረሀ የነበሩ ተቃዋሚዎች በተደረገው የሰላም ጥሪ ከወገኖቻቸው መቀላቀላቸው፣ በእስር ይማቅቁ የነበሩ ነፃ መውጣታቸው፣በጦርነት ይፈላለጉ የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም አስፍነው የሁለቱ አገራት ሕዝቦች በፍቅር ሲላቀሱ ማየታችን፣የዲፕሎማሲው ሥራ ሰፍቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ የአፍሪካና የአውሮፓ አገራት ወዳጅነት አጠናክረው በልዩ ልዩ ምክንያት በየአገራቱ በእሥር ላይ የነበሩ ዜጎቻችንን አስፈትተው ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ማድረጋቸው፣ እንዲሁም አገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የውጭ ዕዳ ለማቃለል የተደረገው ግዙፍ ድጋፍ ፣የአገር መከላከያን ጨምሮ የፀጥታ ኃይሉን ለማጠናከር የተካሄደው አደረጃጀት፣ ኢኮኖሚውን ለመገንባት የተወሰዱ ጠቃሚ እርምጃዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ይሁን እንጂ ለመልካም ሥራ የሚተጉ እንዳሉ ሁሉ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጩ አገርን የማበጣበጥ ተግባራት የሚፈፅሙ በመኖራቸው መስዋዕትነት ቢያስከፍሉም፤ በነቃ የሕዝብ ተሳትፎ መጥፎ ተግባራቸውን ባለመቀበል የሕዝቡን በጋራ የመኖር አንድነትና የጋራ እሴት መጠበቅ ተችሏል፡፡
መጪው ጊዜ የአገራችን ስም በበለጠ መልካምነትና በዕድገት የሚጠራበት እንዲሆን ዛሬ የምናከናውነው በጎ ተግባር መሰረት ስለሚሆን የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች በፅናት በማለፍ ለነገ የላቀ ዕድገታችን እያንዳንዷን የዛሬ ተግባራችንን በበጎ ጥረታችን ማለምለም ይኖርብናል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2011