የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ጥረት ቢደረግም ሊሳካ እንዳልቻለ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል። የዋጋ ንረቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ ለምን አልተቻለም? ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ በቀጣይ ምን መከናወን አለበት? መቆጣጠር ካልተቻለስ ምን መዘዝ ሊያስከትል ይችላል?
በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት ላይ ጥናት በመስራት የሚታወቁት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ሀዬሶ እንደሚገልፁት፤ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሄደበት መንገድ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ አላስቻለውም። መቆ ጣጠር ያልቻለው በቅድሚያ የችግሩን መንስኤ ለይቶ መንስኤውን መሰረት ያደረገ ተገቢ ሥራ ባለመሰራቱ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ዋጋ ግሽበት እንዲከሰቱ የሚያደርጉ ሁለት ነገሮች ናቸው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ኢኮኖሚው መሸከም ከሚችለው በላይ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚ መርጨት አንደኛው መንስኤ ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት ከባንኮች መበደር ያለበት የገንዘብ መጠን በህግ ያልተቀመጠ በመሆኑ መንግሥት ያለ ከልካይ ከግልና ከብሄራዊ ባንኮች በመበደር ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው ይረጫል። በየጊዜ ወደ ገበያው እንዲገባ የሚደረገው ገንዘብ ለዋጋ ግሽበቱና ለኑሮ ውድነቱ የራሱን ሚና እያበረከተ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።
የመንግሥት የበጀት ጉድለት ለዋጋ መናር ሁለተኛው መንስኤ ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ይህን ጉድለት ለማሟላት ከሚጠቀምባቸው ዘዴዎች አንዱ ግብር መጨመር ነው። ግብር ሲጨመር በተለይም ቀጥተኛ ያልሆነ ግብር ሲጨምር የአገልግሎትና ምርት ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል፤ ይህም የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት ምክንያት ሆኖ ብዙ ነገር ያዛባል።
ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ገበያው ከመርጨትና ከበጀት ጉድለት ጋር ተያያዢነት ያለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የመዋቅር ችግር ያለበት መሆኑ ለዋጋ ግሽበቱ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ኢኮኖሚው ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ- ከኢንዱስትሪ ወደ አገልግሎት መሸጋገር የነበረበት ቢሆንም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ አገልግሎት እየተሸጋገረ ነው ይላሉ። ኢንዱስትሪው ማደግ ባለበት ልክ አላደገም ያሉት መምህሩ ይህም መሆኑ ለዋጋ ግሽበት መንስኤ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በዋናነት ከውጪ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተመረኮዘ በመሆኑ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ምክንያት ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባ የዋጋ ግሽበት መኖሩንም ረዳት ፕሮፌሰሩ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከውጪ ሀገር የገባ የዋጋ ግሽበት አለ በሚለው የረዳት ፕሮፌሰር ዳዊትን ሀሳብም የሚቃወሙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ታደለ ፈረደ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ዋጋ ግሽበት ዋነኛው መንስኤ የሀገር ውስጥ ችግር ነው በማለት ይከራከራሉ። የዋጋ ግሽበቱ ከውጪ የመጣ ነው የሚለው ሀሳብ መንግሥት ዜጎችን ለማባበል የሚጠቀምበት ነው በማለት የፀና አቋም አላቸው።
“መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ጥረት አድርጓል” የሚለውን የረዳት ፕሮፌሰር ዳዊትን ሀሳብ ሲቃወሙ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሰራው ሥራ የለም በማለት ነው። “እንዲያውም እጁን አጣጥፎ የተቀመጠ ይመስላል” ሲሉ መንግሥት ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል። የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በቅድሚያ ምክንያቶችን ማወቅ አስፈላጊ ቢሆንም መንግሥት ምክንያቶቹን ባለማወቁ መፍትሄ ማምጣት አልቻለም ሲሉ ይወቅሳሉ።
መንግሥት ኢኮኖሚውን በቅጡ ማስተዳደር አለመቻሉ የብዙ ችግሮች መንስኤ ነው የሚሉት ዶክተር ታደለ በፊትም ኢኮኖሚው በአግባቡ እየተዳደረ አልነበረም፤ አሁንም እየተዳደረ አይደለም ብለዋል። በዚህም ምክንያት የዋጋ ግሽበቱ እያሻቀበ መሄዱን ያነሳሉ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው የፊሲካል እና ሌሎች የፖሊሲ አማራጮችን በመጠቀም የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲረጋጋ ማድረግ የመንግሥት ዋናው ኃላፊነት ነው። በመሆኑ መንግሥት ባለፉት አሥር ወራት የተረጋጋ የዋጋ እድገት እንዲኖር ጥብቅ የፊሲካል ፖሊሲ ተግባራዊ አድርጓል በማለት የዶክተር ታደለን ሀሳብ ይቃወማሉ።
‹‹የመንግሥት ወጪ በገቢው እንዲሸፈን፤ በእቅድ ከተያዘው በላይ እንዳይንር፣ የውጭ ብድር ጫናን የሚያረግቡ ተግባራትን አከናውኗል። የወጪ ጫና የሚፈጥሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዳይኖሩና የተጀመሩትም የሚጠናቀቁበት መንገድ በማመቻቸት የመንግሥት ወጪ በዋጋ ንረት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ ሰርቷል›› ሲሉ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ አህመድ ገለጻ አገራዊ አጠቃላይ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ 12.6 በመቶ ሆኗል። የዋጋ ንረቱን በአንድ አሃዝ እንዲገደብ ለማድረግ ያልተቻለ መሆኑን አስታውሰው በዝቅተኛው የሁለት አሀዝ እንዲረጋጋ ለማድረግ መቻሉን አመልክተዋል።
ለዋጋ ግሽበት ምክንያት የሚሆኑ ለረጅም ዓመታት የቆዩ ከኢኮኖሚው መዋቅራዊ ችግሮች እስከ ሰው ሰራሽ መንስኤዎች አሁንም ቀጥሏል የሚሉት ዶክተር ታደለ፤ የግብርና ምርትና ምርታማነት በሚፈለገው ልክ ባለማደጉ የግብርና ምርቶች አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ክፍተት እየሰፋ መምጣቱም በተለይም የግብርና ምርቶች ዋጋ እንዲንር አንዱ መንስኤ ነው ይላሉ።
እንደ ዶክተር ታደለ ማብራሪያ በሀገሪቱ ውስጥ ባለው የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥ ምክንያት ፋብሪካዎች ማምረት ካለባቸው በታች እያመረቱ ናቸው። አገልግሎት ሰጪዎችም አገልግሎት ለመስጠት ተቸግረዋል። በዚህም ምክንያት የሰራተኛውን ወጪ ለመሸፈን የዕቃና የአገልግሎት የመሸጫ ዋጋ ጨምረዋል። አንዳንድ ድርጅቶች የራሳቸውን ጄኔሬተር እየገዙ ለማምረትና አገልግሎት ለማቅረብ እየሞከሩ ናቸው። ይህ ደግሞ ተጨማሪ ወጪ እያስወጣቸው በመሆኑ የዋጋ ንረቱን እያባባሰው መጥቷል ብለዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት እንደሚሉት፤ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ገንዘብን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ መከተል መፍትሄ አይሆንም። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ሲከተል የቆየውን የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ መፈተሸ አለበት። ይህን ያረጀ የፖሊሲ ማዕቀፍ በመቀየር የዋጋ ግሽበትን መሰረት ያደረገ ሞኒተሪ ፖሊሲ መከተል ይገባል። ግሽበትን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ በመከተል በርካታ ሀገራት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ችለዋል። ኢትዮጵያም ይህንኑ ልምድ መቅሰም አለባት።
የዋጋ ግሽበቱን እንዲቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ብሄራዊ ባንክ በብቃት የገበያ ዋጋ መቆጣጠር እንዲችል ሁለት ነገሮች ሊኖሩት ይገባል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት፤ ገልተኛነቱን ማረጋገጥ አንዱ ሲሆን የአስተዳደራዊና የፖሊሲ ምርጫ ነጻነት እንዲኖረው ማድረግ ሁለተኛው መፍትሄ ነው ሲሉ አቅርበዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ የሀገሪቱን የንግድ ህግን ማስተካከልም አስፈላጊ ነው። የንግድ ስርዓቱ ውስጥ ፍትሃዊነትና ውድድር እንዲኖር በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል። ከሀገሪቱ የንግድ ዘርፍ 36 በመቶ የሚሆነው በኢ- መደበኛ ዘርፍ የተያዘ ነው። ይህ ኢ-መደበኛ ንግድ ወደ መደበኛ የሚመጣበትን ሁኔታ ማመቻቸትም የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የራሱ እገዛ ይኖረዋል።
ዶክተር ታደለ ፈረደ በበኩላቸው፤ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎች ላይ በእቅድ መስራት ያስፈልጋል ይላሉ። በአጭር ጊዜ ገበያውን ለማረጋጋት መንግሥት እንደለመደው ከውጪ ሀገራት ምርት እያስገበ ገበያውን ለማረጋጋት መስራት አለበት ይላሉ።
የግብርና ምርትን በዓይነትና በጥራት የማቅረብ ሥራ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ግብ አስቀምጦ መስራትም ትኩረት ሊደረግበት ይገባል የሚሉት ዶክተር ታደለ፤ ከውጪ የሚገቡ የፋብሪካም ሆነ የግብርና ምርቶች በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረት መደረግ አለበት። ገንዘብ ያለው ሁሉ አስመጪ ከሚሆን ይልቅ ሀገር ውስጥ አምራች እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ ይገባል ይላሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር ዳዊት ሀዬሶ በበኩላቸው፤ የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠር ካልተቻለ የውጪ የሚመጡ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይቀንሳል። ዜጎች እንዳይቆጥቡ ያደርጋል። ቁጠባ ከሌለ ደግሞ የወደፊት የሀገር ኢኮኖሚ እድገት እንዲገታ ያደርጋል። በሀገር ውስጥ ያሉ ባለሃብቶችና ኢንቨስተሮች መዋዕለ ንዋያቸውን በሀገር ውስጥ ከማፍሰስና ከመቆጠብ ይልቅ በውጪ ባንኮች መቆጠብን ይመርጣሉ። ባለሃብቶች ሀገር ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን የማያፈሱ ከሆነ ሥራ አጥነት ይበራከታል።
በአጠቃላይ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ካልተቻለ ኢኮኖሚውም እድገቱን በጣም ይቀንሳል። ያ ማለት ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት፤ ከፍተኛ ከሆነ የኑሮ ውድነት ጋር ሲመጣ ዜጎች ትናንትና በአነስተኛ ወጪ ይኖሩ የነበሩትን ኑሮ ዛሬ እንዳይኖሩ ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ ወደ ፖለቲካ ቀውስ የሚወስድበት ሁኔታም ሊፈጠር ስለሚችል በትኩረት መስራት እንደሚገባ ምሁራኖቹ አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2011
መላኩ ኤሮሴ